Saturday, 02 April 2022 11:37

ግራ ገብቶት ግራ የሚያጋባ ዘመን!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(0 votes)              እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ!
አንድዬ፡- እ....ምስኪን ሀበሻ እ...እንደምን ነህ?
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድ...አንድዬ!
አንድዬ፡- ዛሬ ምን ሆነሃል፣ እንዴት ብለህ ነው የምታየኝ!
ምስኪን ሀበሻ፡- እንዴት አየሁህ፣ አንድዬ?
አንድዬ፡- አንተ ንገረኝ እንጂ! ነው ወይስ እላይ ውጣና በአስቸኳይ ከስልጣኑ አውርደው ተብለህ ልታወረድኝ ነው የመጣኸው? ወይ ፍረድ ወይ ውረድ ስትሉኝ አይደል የከረማችሁት!
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ እባክህ እንደሱ...
አንድዬ፡- እሺ፣ እሺ፡፡ ግን አስተያየትህ ከዚህ በፊት አይተኸኝ የማታውቅ ነው የሚመስለው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- እውነቱን ልንገርህና አንድዬ፣ እኔ ራሴ አንተን ምን ሆነሀል ብዬ ልጠይቅህ ነበር፡፡ ሳይህ በሆነ ነገር የተከፋህ መስሎኝ ነው...
አንድዬ፡- ስማኝ፣ ምስኪኑ ሀበሻ፣ እኔም እውነቱን ልንገርህ አይደል... አዎ፣ የእናንተ ነገር ግራ ገብቶኛልም፣ ከፍቶኛልም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ዛሬም አንተ ዘንድ መምጣቴ እኛም የመጨረሻ እንደከፋን ልነግርህ ነበር፡፡
አንድዬ፡- የእናንተ እንኳን ምንም አዲስ ነገር የለውም፡፡ ሁልጊዜም የምትከፉበት ሰበብ አጥታችሁ አታውቁም፡፡ ግን ንገረኝ እስቲ ምስኪኑ ሀበሻ፣ አሁን አሁን ምን እየሆናችሁ ነው?
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፤ ዛሬ የሆዴን ዘርግፌው ብናገር አትዘንብኝና፣ ምን እየሆንን እንደሆነ አንተ ንገረኝ እንጂ፡፡
አንድዬ፡- ጭራሽ ወደ እኔ አዙራችሁ አረፋችሁት!
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፤ ወደ አንተ ለማዞር ሳይሆን እኛ ራሳችን ምን እየሆንን እንደሆነ በራሳችንና እርስ በእርሳችን ግራ ስለገባን፣ ስለተጋባን አንተ እንቆቅልሹን ፍታልን ለማለት ነው፡፡
አንድዬ፡- እንቆቅልሽ አልከው፡፡ እውነትም እንቆቅልሽ! እስከዛሬ ስፈልገው አጥቼው የነበረውን ግሩም ቃል ነው ያመጣህልኝ፡፡ አየህ እኔም ልልህ የፈለግሁት ይህንን ነው፡፡ ከባድ እንቆቅልሽ ሆናችሁብኛል፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ የልቤን ብናገር... ማለት የእኔን ብቻ ሳይሆን ሁሉም ልብ ውስጥ ያለውን ብናገር አትተታዘበኝም፣ አይደል!
አንድዬ፡- ምነው ምስኪን ሀበሻ፣ ምነው! እሱንማ አንዴ አልክ እኮ... መደጋገም አያስፈልግም፡፡  ደግሞስ እኔ ዘንድ መጥተህ የልብህን ያልተናገርክ፣ የት ሄደህ ልትናገር ነው!
ምስኪን ሀበሻ፡- ትንሽ መረር እንዳልልብህ ብዬ ነው፣ አንድዬ፡፡
አንድዬ፡- ግዴለም አንተን ካልመረረህ እኔን አይመረኝም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ... ምን፣ ምን አደረግንህ? ይህን ያህል ምን ብንበድለህ ነው!
አንድዬ፡- ቆይ፣ ምስኪኑ ሀበሻ ተረጋጋ እንጂ!
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ለም... ለምን ይህን ያህል...
አንድዬ፡- ኸረ ግዴለህም፣ እንድንደማመጥ ረጋ ብለህ ብትነግረኝ እኮ...
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ! አንድዬ! አንተ...አን...
አንድዬ፡- እኔም ላቋርጥህና ሌላ ጊዜ ስታቋርጠኝ ይቅርታ ትጠይቀኝ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ትዝም አላለህ፡፡ ይህን ያህል የእውነትም ጥርስ ነክሳችሁብኛል ማለት ነው!
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ እንደሱ አትበል! ለምን እንደሱ አይነት ነገር ትለኛለህ!
አንድዬ፡- እሺ በቃ አልልህም፤ ረጋ በል፡፡ ልብህን ልታፈርሳት ነው እኮ! እሺ፣ እንደማመጥ... ምን ልትለኝ ነበር?
ምስኪን ሀበሻ፡-  አንድዬ፣ አትቆጣኝና...አንተ እኮ እኛን  ማዳመጥ ከተውክ ቆየህ!
አንድዬ፡- ምስኪን ሀበሻ ተው ግዴለህም! ምን ነበር የምትሉት...ጡር ይሆንብሀል። አሁን ማን ይሙት እኔ አድምጫችሁ አላውቅም?
ምስኪን ሀበሻ፡- አ..አንድዬ፣ ይቅርታ። በቃ ሁላችንም አሁን የምንለውም፣ የምንባለውም፣ የምናደርገውም እየጠፋብን ስለሆነ ነው የዘባረቅሁብህ፡፡
አንድዬ፡- አልዘባረቅህብኝም፤ ይልቁንም እንዲህ በግልጽ በመናገርህ ደስ ይለኛል፡፡ ለምንድነው እኔ የተውኳችሁ የመሰላችሁ ብዬ አልጠይቅህም፡፡ ስሜታችሁ ይገባኛል፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- ተቀበልከኝ ማለት ነው፣ አንድዬ?
አንድዬ፡- ምንድነው የምቀበልህ! የመቀበልና ያለመቀበል ጉዳይ አይደለም። ይልቅ እኔ ደግሞ የሚሰማኝን ብነግርህ ትፈቅድልኛለህ?
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ!...እንደ..
አንድዬ፡- እሺ እንደሱ አልልም። ግን ይኸውልህ እኔም እንደ እናንተ ግራ ገብቶኝ የምጠይቀው አጥቼ ነው፡፡ ቆ...ቆይ አታቋርጠኝ፡፡ እዚህ በመጣህ ቁጥር እንደምነግርህ፣ አንዳንዴ ችላ ያልኩ ቢመስላችሁም፣ ሁሉም ነገራችሁን መከታተሌ አልቀረም፡፡ የአሁኑ ሁኔታችሁ ግን ግራ ነው የገባኝ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- ይኸውልሀ አንድዬ፣ ይኸውልሃ! አንተ ግራ የገባህ ነገር፣ እኛን ምን እንደሚያደርገን አስበው፡፡
አንድዬ፡- ንጽጽሩን ተወውና ግራ የሚገባኝ ዋናው ነገር ምን መሰለህ...ምድነው በለኛ!
ምስኪን ሀበሻ፡- እሺ አንድዬ፣ ግራ የገባህ ዋና ነገር ምንድነው?
አንድዬ፡- እንደሱ ጥሩ ነው፡፡ አየህ እኔ ብቻ ስናገር ውዬ ደግሞ ታች ስትወርድ ሲለፈልፍብኝ ዋለ እንዳትል ብዬ ነው። ቆይ... አልጨረስኩም፡፡ ግራ የገባኝ ነገር ምን መሰለህ፣ እንደው በአጭር ጊዜ ነገራችሁ ሁሉ ለትርጉም የሚያስቸግረው ለምንድነው እላለሁ፡፡ ምንም አንኳን ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ የማይለቋችሁ ባህሪያት እንዳሉ ባውቅም፣ የዘንድሮውን ግን ቀንድና ጭራውን ለመያዝ አስቸግሮኛል፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ እኛ ራሳችን እኮ  ግራ ግብት ብሎን ነው፡፡
አንድዬ፡- ስማኝ ምስኪኑ ሀበሻ፣ ልንገርህ አይደል...እናንተ አሁን ግራ የገባችሁ ሳትሆኑ ዋናዎቹ ግራ አጋቢዎች ሆናችኋል፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ይቅርታ አድርግልኝና አንተ እንደው መስሎህ ነው እንጂ ግራ ያጋባንህ እኮ በቃ፣ ምን ልበልህ እከሌ ከእከሌ ሳንባባል ሁላችንም ግራ ስለተጋባን ነው፡፡
አንድዬ፡- እሺ ይሁንልህና እስቲ ግራ አጋቡን የምትሏቸውን ነገሮች አንድ፣ ሁለት እያልክ አስረዳኝ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ምኑን ላስረዳህ! የት ጀምሬ የትስ ልጨርስ!
አንድዬ፡- የፈለግኸው ላይ ጀምረህ የፈለግኸው ላይ ጨርሰው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ዋናው ችግራችን እኮ እሱ ነው፡፡
አንድዬ፡- ምነው ምስኪኑ ሀበሻ፣ ምነው! ታች ሁናችሁ ግራ ያጋባችሁኝ አንሶ ጭራሽ እዚህ ድረስ መጥተህ ልትጨምርልኝ ነው! ለምን ማለት የፈለግኸውን በቀጥታ አትለኝም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- ይቅርታ አንድዬ፣ ይቅርታ። ግራ ላጋባህ ብዬ አይደለም፡፡ ግን ማለት የፈለግሁት ነገሩ ሁሉ ድብልቅልቅ ከማለቱ የተነሳ የት እንደምጀምርና የት እንደምጨርስ አላውቀውም ልልህ ፈልጌ ነው፡፡ አንድዬ፣ መጀመሪያና መጨረሻ የሚባል ነገር ለመኖሩም እርግጠኛ አይደለንም እኮ! በበኩሌ እኔ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡
አንድዬ፡- ወይ ጣጣ! እንደ እናንተ ወጉ ይድርሰኝና ወይ ጣጣ ልበል እንጂ። ችግራችሁን በግልጽ መናገር ሳትችሉ እኔ ላይ ጣት ለመቀሰር ግን ማንም አይቀድማችሁም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ ጣት መቀሰር እኮ አይደለም፡፡ እኛስ ወዴት እንሂድ! አቤት የምንልበት ማን አለንና! አንተ ችላ ካልከን ማን አለንና ነው!
አንድዬ፡- ይቺን ይቺንማ ማን ብሏችሁ! ብቻ እኔ ከእናንተ ግራ ከሚያጋቡኝ ነገሮች ምን አለ መሰለህ...አሁን፣ አሁን የምትናገሩት፣ ወይም የተናገራችሁ የመሰላችሁ ነገር ሁሉ ግራ ይገባል፡፡ ሰው ሁሉ እንዲህ ተመሳሳይ ይሆናል! እዚህ አንድ ነገር ትላላችሁ፣ እዛ ደግሞ ተቃራኒውን ነገር ትላላችሁ፡፡ እዚህ “ተባረክ!” ያላችሁትን እዛ “እርጉም ከመአርዮስ!” ትሉታላችሁ፡፡ እዚህ ሳያነጥስ መሀረብ የምታቀርቡለትን፣ እዛ በሳል ሲንፈራፈር “ሲያንሰው ነው!” ትላላችሁ። እዚህ የሳማችሁትን እዛ ትነክሱታላችሁ። እዚህ የልብ ወዳጅ ያደረጋችሁትን፣ እዛ ደመኛ ጠላት ታደርጉታለችሁ፡፡ ታዲያ ይህ ነገራችሁ ግራ ያልገባኝ ምን ግራ ሊገባኝ ነው!
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ...
አንድዬ፡- ቆይ ቆይማ ምስኪን ሀበሻ። ምን መሰለህ...ሌላ ጊዜ ስትመጣ ደግሞ የተቀሩትን ግራ የሚገቡኝን ነገሮች እነግርሀለሁ፡፡ ሰላም ግባ!
ምስኪን ሀበሻ፡- አሜን አንድዬ፤ አሜን!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 494 times