Print this page
Saturday, 02 April 2022 11:47

አምባገነኑ ዴሞክራሲ

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ
Rate this item
(0 votes)

   (ያልተስተዋሉት የዴሞክራሲ ክፍተቶች)

            "--ዴሞክራሲ በተለይ በሶስተኛው ዓለም የሚሰጠው ግምትና መሬት ላይ የሚታየው እውነታ ልዩነቱ የትየለሌ ነው፡፡ ዴሞክራሲ ገና እንጭጭ ነው፤ ጮርቃ… የዴሞክራሲ ሥርዓት መገለጫ አድርጋ እራሷን ያቀረበችው አሜሪካ እንኳን የጥቁሮቹንና የነጮቹን እኩልነት ከተቀበለች ገና ሀምሳ ዓመት መሆኑ ነው፡፡--"
           
           በየካቲት ወር 2006 ዓ.ም በኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ ላይ “ያልተስተዋሉት የዴሞክራሲ ክፍተቶች” በሚል ርዕስ ለረጅም ጊዜ ሳንሰላስለው የቆየሁትን ጥያቄ አንስቼ እንደ አቅሚቲ እይታዬን አጋርቼ ነበር፡፡ ይህ ከሆነ ከአንድ ወር በኋላ ዘ ኢኮኖሚስት (the Economist) መጽሔት ላይ “What is gone wrong with democracy” በሚል ርዕስ ከእኔ አተያይ ጋር ተመሳሳይ ባይሆንም ትንተና መደረጉን አይቼና ጥያቄዬ አለማቀፋዊ ይዘት እንዳለው ተገንዝቤ ተገረምኩ፡፡ ሆኖም ከዚያም ጊዜ በኋላም ቢሆን ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር፣ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን ትውልዶች ያለውን ተገቢነት በተመለከተ መጠየቄን ቀጥያለሁ፡፡
እውን ዴሞክራሲ ለዚህ ዘመን ትውልድ የሚገባውና የመጨረሻው ወይም ብቸኛው የአስተዳደር ዘይቤ ነውን? ሀገራት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት ታግለው፣ ይህን የህልም ያህል ሊጨብጡት የራቃቸውን ጽንሰ ሀሳብ እውን ማድረግ ተስኗቸው፣ ሲተረማመሱ የምናየው ለምንድን ነው? የዘመኑ ትውልድ ከዴሞክራሲያዊ አስተዳደር የተሻለ ስርዓት ሊሻ፣ ሊገነባ አይገባምን? መጠየቃችንን እንቀጥላለን፡፡ ሆኖም  በጥያቄዎች ተጀምሮ በጥያቄዎች በሚጠናቀቅ የፍለጋ ጉዞአችን ውስጥ ኢትዮጵያ ማነጻጸሪያችን ልትሆን እንደማትችል እንድትረዱልኝ እፈልጋለሁ፡፡ ላም ባልዋበት ኩበት ለቀማ እንዳይሆንብን።
ዘመናዊ የዴሞክራሲ ስርዓት የዕድገት ሂደቶች
አንባቢዬ ይህንን አስቀድሞውኑ እንደሚረዳ በማሰብ የዴሞክራሲን ጥንተ አመጣጥና ትርጓሜን በመተንተን አልባዝንም፡፡ ከዚያ ይልቅ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ከአቴናዊያን ቀደምት ስልጣኔ መንኮታኮት በኋላ ከተቀበረበት የድንቁርና የመቃብር ጉድጓድ ወጥቶ፣ እንዴት የዘመናዊ ዓለም በተለይም የ20ኛውና 21ኛው ክፍለ ዘመን ትውልዶች ተመራጭ አስተዳደር ዘይቤ ሊሆን እንደበቃ እንድንጠይቅ ፈቃዴ ነው፡፡
ከጨለማው ዘመን (6-13 ክፍለ ዘመናት) ጀምሮ በህንድ የታሚልናዱና የቤንጋል ግዛቶች፣ የመካከለኛው ዘመን የጣሊያን የከተማ መንግሥታትና በሌሎችም አካባቢዎች ከፊል ዴሞክራሲያዊ ምርጫዎችና አንዳንድ እንቅስቃሴዎች፣ ለዘመናዊው የዴሞክራሲ አስተዳደር መሰረት የጣሉ ቢሆንም፣ ላቅ ያለ እመርታ የታየው ግን ዛሬም ድረስ በሚያገለግለውና በእንግሊዝ ፓርላማ በ1689 እ.ኤ.አ የፀደቀው ቢል ኦፍ ራይትስ (Bill of rights) አማካኝነት ነበር፡፡
ይህ ቢል ኦፍ ራይትስ ለዜጎች መጠነኛ መብትና ነጻነት ከማጎናፀፉ በተጨማሪ በተወሰነ የጊዜ ገደብ ውስጥ የሚካሄድ ምርጫ እንዲኖር፣ የነገስታቱ ስልጣን እንዲገደብ፣ በፓርላማ ውስጥ ብቻም ቢሆን የመናገር ነጻነት እንዲከበር ፈቅዷል፡፡ ዴሞክራሲ ዘመናዊው ዓለም የያዘውን መልክ ከማግኘቱ በፊት በአሜሪካና በፈረንሳይ አብዮቶች ጎልምሶ፣ ዳብሮና በልጽጎ፣ እንደየሀገራቱ ነባራዊ ሁኔታ፣ ተቀያይጦ፣ ተሸራርፎ፣ ብዙ የለውጥ ቅርጽ ደረጃዎችን አልፎ፣ ዛሬ የምናይለትን ዥጉርጉር መልኮች አግኝቷል፡፡
ነገር ግን ከጨለማው ዘመን ማግስት በኋላ በጥልቅ ሀይማኖተኝነት የተተበተቡ ትውልዶች የተሻለ የአስተዳደር ስርዓትን እንዲናፍቁ ምክንያቱ ምን ነበር? ለዚህ ጥያቄ የሚሆን ይህ ነው የሚባል መልስ ማግኘት ያስቸግራል፡፡ ሆኖም ጉዳዩን በጥልቀት ያጠኑት ምሁራን እንደሚሉት፤ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የተካሄደው የፕሮቴስታንቲዝም እንቅስቃሴ፣ በዘመኑ ለነበሩ ትውልዶች ከመንፈሳዊ አስተውሎት ውጭ ያለውን ዓለም የሚመለከቱበት አዲስ የአመለካከት ነጻነት መፍጠሩ፣ ከተሀድሶ ዘመን መበሰር በኋላ የሰው ልጆች የሀይማኖት ነጻነት መጎልበት፣ የባህል እንቅስቃሴና የንግድ ዝውውር መጠናከር፣ በዚህም የሰው ልጆች የአኗኗር ሁኔታ መሻሻል፣ በዘመኑ ሰዎች በአንድነት ለጋራ ጉዳይ እንዲመክሩ፣ ውሳኔዎቻቸውንም በድምጽ ብልጫ እንዲያሳርጉ ዕድሎችን ፈጥሯል፡፡
ይህም አዝጋሚ በሆነ ሂደት ሲሻሻል ሲወራረስ ቆይቶ ዘመናዊውን ቅይጥ ዴሞክራሲያዊ የአስተዳደር ስርዓት አስገኝቷል፡፡ በ1787 እ.ኤ.አ የተረቀቀው የአሜሪካ ሕገመንግሥት፣ እሱንም ተከትሎ በ1791 የፀደቀው ቢል ኦፍ ራይትስ፣ በ1833 እንግሊዝ የወሰደችው የባሪያ ንግድን የማስቆም እርምጃን የመሳሰሉት ሁሉ በመጎልበቱና በመዳበሩ፣ ቀርፋፋ ጉዞ ያለፈባቸው ሂደቶች ናቸው፡፡
የሆነስ ሆነና ዴሞክራሲ ዛሬ በ21ኛው ክፍለዘመን ለምንገኝ ትውልዶች ሁሉ የሚበጅና የሚገባ ብቸኛው የአስተዳደር ዘይቤ ነውን?
ያልተስተዋሉት የዴሞክራሲ ክፍተቶች
ስለ ዴሞክራሲ ክፍተቶች ስናወራ ትኩረታችን በዓለም ፖለቲካ፣ በዴሞክራሲ ስም ስለሚፈጸሙ አሻጥሮች አይደለም። ይህን ለማድረግ ሺ ገጾች አይበቁም፡፡ ነገር ግን ዴሞክራሲ ቴክኖሎጂ አይደለም። ወይም ማንም መንዳት ስለቻለ ብቻ የሚጋልበው ሞተር ብስክሌት አይደለም፡፡ ዴሞክራሲ ሂደት ነው፡፡ የመቶ ምናልባት የሺ ዓመታት ሂደት… ዛሬ የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት አላቸው የሚባሉ አገራት በሙሉ ከሁለትና ሶስት መቶ ዓመታት በፊት ጀምሮ ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚያጎለብቱ፣ የሚያዳብሩ፣ የሚስተምሩ የሲቪል ማህበራትና ተቋማት ነበሯቸው፡፡
ዶ/ር ሃራልድ ዊድራ የተሰኘ አንድ ሊቅ.፤ ‹‹Communism and the emergence of democracy›› በሚል መጽሐፉ ላይ ስለዴሞክራሲ ስርዓት በአዝጋሚ ሂደት የሚገነባ ስርዓትነት እንዲህ ይላል፤ “Power emanate from the people, but the power of nobody, the essence of democratic system is an empty place void of real people. Which can be temporarily filled but never be appointed, the seat of power is there, but remains open to a constant change››
‹‹የስልጣኑ ምንጭ ህዝብ ቢሆንም ስልጣኑ የማንም አይደለም፡፡ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት መሰረቱ ለማንም ያልተገባ፣ በጊዜያዊነት ብቻ የሚሞላ እንጂ ማንም የማይሰየምበት ባዶ ቦታ መያዙ ነው፡፡ የስልጣኑ መቀመጫ በዚህ ባዶ ቦታ ላይ ሲሆን ለመደበኛ ለውጥ ክፍት እንደሆነ ይቆያል፡፡››
የሥልጣኑ ምንጭ ህዝብ በሆነበት አግባብ መሪዎች ወደስልጣን የሚመጡት በብዙሃኑ ድምጽ ተመርጠው ይሆናል፡፡ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገለጫዎች ነጻ ምርጫ፣ የመናገርና የመደራጀት፣ የመሰብሰብ የመሰለፍ ነጻነት፣ የፕሬስ ነጻነት ወዘተ… ሁሉ ቢሆኑም፣ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ተግባራዊ ማጠንጠኛ ግን የብዙሃኑ ድምጽ (majority rule ) መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ የድምጽ ብልጫ ስርዓት
የብዙሃኑ መንግስት በአናሳዎቹ ላይ እንዲገነባ ያስችላል፡፡ የብዙሃኑ ፍላጎት እስከሆነ ድረስ አናሳዎቹን የሚጎዳ ማንኛውም እንቅስቃሴ ሕጋዊ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
በዚህ መደዴ የብዙኀን የድምጽ ብልጫ አማካኝነት፣ 49% የሀገሪቱ ህዝብ የማይፈልገው፣ የማይቀበለው ያላመነበት፣ ጥቅሙን፣ ክብሩ፣ ህልውናውን፣ ማንነቱን የሚጎዳ ድርጊት፣ 51% ለሚሆኑት ብዙሃን ፍላጎት ሲባል ብቻ ተግባራዊ እንዲሆን ያስችላል፡፡ በእንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት የመውጣት ሂደት የተፈጠረውን ሁነት ተመልከቱ፡፡ ከአውሮፓ ህብረት መውጣትን በተቃወሙትና በደገፉት መካከል ያለው ልዩነት 2 ሚሊዮን ሲሆን፤ ለእነዚህ ጥቂት ግለሰቦች የሀሳብ ብልጫ ሲባል 15 ሚሊዮን ዜጎች የማይፈልጉት ሃሳብ እንዲጫንባቸው ሆኗል፡፡
ምንም እንኳን ኢ-ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴዎችን ለማስቆም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተሩን በ1945 እ.ኤ.አ እንዲሁም የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎቹን ደግሞ በ1948 እ.ኤ.አ ያፀደቀ ቢሆንም፣ ሀገራት ለእነዚህ ሕጎች ተገዥነታቸው ምንም በመሆኑ ከድንጋጌዎቹ ወዲህ በርካታ የዘር ማጥፋ ሙከራዎች፣ አናሳዎቹን የማፈናቀል፤ የማዋከብ እርምጃዎችን እዚህም እዚያም ለመታዘብ ችለናል፡፡ በብሔር ተዋጽኦ በተሞሉና በተፈጥሮ ሀብት በበለፀጉ ሀገራት መካከል የብዙሃኑ ሕግና የአናሳዎቹ መብት ፍጥጫ በእጅጉ የከረረ ነው፡፡ ከወዲሁ ትውልዱ ከዚህ የተሻለ የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት የማይገነባ ከሆነ፣ ወደፊት ብዙ ጥፋቶችን ልንመለከት እንችላለን፡፡
ሌላው የዴሞክራሲ ስርዓት ትልቁ ክፍተት አምባገነኖችን የሚያሰርጉ በርካታ ሽንቁሮችን አቅፎ መያዙ ነው፡፡ በቅርቡ በግብጽ ታሪክ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ወደ ስልጣን የመጡትና አሁን ያንቀላፉትን መሐመድ ሙርሲን ወደ ስልጣን ያመጣቸው ንቅናቄ ስሙ ዴሞክራሲ ነበር፡፡ በጦር ኃይሉ ጣልቃ ገብነት እስከተገፈተሩበት ቅጽበት ድረስ ሙርሲ የብዙሃኑን ድምጽ በመጠቀም ሁሉንም ስልጣን ለእሳቸውና ለፓርቲያቸው ጠቅልለው፣ አናሳዎቹን ለመጨቆን ማቆብቆባቸው ታይቷል፡፡
ዛሬም ግብጽ ወደ ሌላኛው ወታደራዊ አምባገነን መንግስት እየተንደረደረች ይመስላል፡፡ ዴሞክራሲ አስመሳይ አምባገነን መንግሥታትን አብዝቶ ይታገሳል፡፡ እነሱ እስከተመረጡ ድረስ ብዙ ሚሊዮን ገንዘቦች ፈሰው አስመሳይ ምርጫዎችን በማካሄድ፣ የህዝቡን የመምረጥ መብት ያስከበሩ፣ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ያከበሩ እያስመሰሉ፣ ለሚያወናብዱ ሸፍጠኞች የመጫወቻ ሜዳ ይለቃል፡፡ የብዙዎቹ አፍሪካ ሃገራትና የኢትዮጵያም አብነት ይሄ ነው፡፡ ዘ ኢኮኖሚስት፤ የሩሲያውን ጠ/ሚኒስትር ቭላድሚር ፑቲንንም #አስመሳይ ምርጫ ያካሄዳሉ; ሲል ኮንኗቸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ወደ ስልጣን የሚመጡ ቡድኖችም ይሁኑ ግለሰቦች አምባገነኖች ለመሆን የሚያስችል መደላድል እንዲያገኙም ዴሞክራሲ ይፈቅዳል፡፡ መሪዎቹ በእነሱ እዝ ስር የሆኑትን የፖሊስና የመከላከያ ሠራዊትን በማግባባትና በመጠቀም፣ ህዝብን እየጨቆኑ ላልተወሰኑ በርካታ ዓመታት በስልጣን ላይ የመቆየት ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡ በሌላ በኩል፤ በአብላጫው ህዝብ ይሁንታ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ወደ ስልጣን የሚመጡ ግለሰቦችና ቡድኖች፣ ለህዝብ ቃል የገቧቸውን ፖሊሲዎች ተግባራዊነት ወደ ጎን ትተው፣ ራሳቸውን እንዲያገለግሉ ይፈቅዱላቸዋል፡፡ ይህን ድርጊት ለማስቀረት የሚቋቋሙት ተቋማትም እንደ ጸረ ሙስና፣ ሲቪክ ማህበራት የመሳሰሉት በእነርሱ የእጅ አዙር ቁጥጥር ስር ስለሆኑ፣ ተጽዕኖዎአቸው እዚህ ግባ የሚባል አይሆንም፡፡ በተለይ ዴሞክራሲያዊ ባህልና ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ባልዳበሩባቸው ታዳጊ ሀገራት፣ ይኸው ችግር ጎልቶ የሚስተዋል ይመስላል፡፡
ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የቱንም ያህል የሰለጠነ የአስተዳደር ዘይቤ ቢሆንም፣ ቀላልና ጥቃቅን የውሳኔ ሀሳቦችን ለመበየን ሳይቀር ረጅም ንትርክና አምባጓሮን ሲያስነሳ ይስተዋላል፡፡ የአሜሪካን የበጀት አብነት ማን ይረሳል? ነገሩ በብዙሃኑ ድምጽ በድምጽ ብልጫ የሚተገበር በመሆኑ፣ የብዙሃኑን ድምጽ ለማግኘትና የራስን ፍላጎት በሌሎቹ ላይ ለመተግበር የሚደረገው ትንቅንቅ፣ በትንቅንቁ ሂደት የሚጣሉ ቀይ መስመሮች፣ ብዙ የብዙ ብዙ ናቸው፡፡ ይህ ሁሉ ቢቀር እንኳን ዴሞክራሲ ከሀገር ወዳዶችና ሀቀኞች ይልቅ አጭበርባሪዎችና ጮሌዎች ወደ ስልጣን እንዲመጡ የሚፈቅድ ስርዓት እንደሆነ ይታያል፡፡
ዴሞክራሲ የተማሩትና የሰለጠኑት የህዝቡ አባላት ብቻ በእውቀትና ብልጠት የሚነጥቁት የአስተዳደር ስርዓት ነው፡፡ አሜሪካዊው ፖለቲከኛ፣ ዲፕሎማት ጀምስ ማዲሰን እንዲህ ይላል... ‹‹Democracies have ever been spectacles of turbulence and contention. Have ever been found incompatible with personal security the right of property, and have in general been as short in their lives as they have been violent in there death››
‹‹የዴሞክራሲ ሂደቶች የጠብ የብብጥና ሁካታ ድምቀቶችና ሞገሶች ሆነው አሳልፈዋል። ከግለሰቦች የደህንነትና የሀብት መብት ጋር አብረው እንደማይሄዱም ታይቷል። በአጠቃላይ ህልውናቸው የማጠሩን ያህልም በውድቀታቸው አውዳሚ ሆነዋል፡፡››
በተለያዩ የዓለም ማዕዘናት የተሻለ የዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት ሲባል ብቻ ብዙ ሺ ህዝቦች እልፍ መስዋዕትነቶችን ይከፍላሉ፡፡ ሆኖም በከፍተኛ ጥረትና ውድመት ሊገነቡት የታገሉለት የዴሞክራሲ ስርዓት በክሽፈቱም ሌሎች ዘግናኝ ጥፋቶች ይፈጸሙበታል፡፡ ዴሞክራሲ የጠብ የክርክር፣ የመነቋቆር ግርማ የመሆኑን ያህል፣ የሃሳብ ልዩነትን የማስተናገድ ህብር ያው ስርዓት መሆኑ የማይካድ ሃቅ ነው፡፡ በአቴናዊያን የስልጣኔ ዘመናት የስፓርታ ሰዎች በሚከራከሩበት ጉዳይ ላይ የመጨረሻውን እልባት የሚያገኙለት በድጋፍና በተቃውሞ ጎራ ያሉት ሁሉ እንዲጮሁ በማድረግ ሲሆን የበለጠ መጮህ የቻለው ወይም ድምፁ ጎልቶ የተሰማው አካል ተቀባይነት እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡
አርስቶትል ይህን የስፓርታ ሰዎች አድራጎት ከአቴናዊያኑ ጋር በማነጻጸር ‹‹የልጆች ጨዋታ›› ሲል ተሳልቆባቸዋል፡፡ ግን ዛሬስ በስፓርታ ሰዎች የልጅ ተግባር ላይ ለመሳለቅ የሚያስችል የሞራል ልዕልና ላይ ደርሰናል እንዴ?
የምትወረርን፣ የምትገነጠልን፣ የምትፈናቀልን አንዲት ግዛትና የግዛቷን ነዋሪዎች የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ለመምከር የእሳቱ ወላፈን ጫፋቸውን የማይነካቸው፣ ብዙ ሰዓታቸውን ወንበር ላይ ተቀምጠው በእንቅልፍ በሚያሳልፉ የፓርላማ አባላት ግዴለሽ የእጅ ብልጫ እንዲወሰን ማድረግ ከእስፓርታ ዘመን ብዙም እንዳልራቅን የሚያመለክተን ነው፡፡ ለዚያውም የጉዳዩ አካላት ቀጥተኛ ተሳትፎ ባላደረጉበትና ድምጽ የመስጠት ስልጣን ያላቸውን ግለሰቦች ለሚፈልጉት አጀንዳ ድምጽ እንዲሰጡ የሚያግባቡ፣ የሚያባብሉ (lobbiests) ባሉበት አግባብ፣ ስፓርታን መናቅ፣ ነገሩን “ቂ” በ “ቃ” ይስቃል ያደርግብናል፡፡
እዚህ ላይ የዓለማቀፉን እግር ኳስ ማህበር ፊፋ አብነት ማንሳት እንችላለን፡፡ የአዘጋጅ ሀገርን ለመምረጥ በሚደረግ ሂደት ለውድድር የቀረቡ ሀገራት ድምጽ የመስጠት ስልጣን ያላቸውን ግለሰቦች እየተናጠቁ፣ በጥቅም ሲያግባቡ፣ ሲሽቆጠቆጡ ይታያል፡፡ የቱንም ያህል የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ባህል ያላቸው ሀገሮች፣ ከዚህ በጠለቀና በረቀቀ ቴክኒክ፣ በፖለቲካው መድረክ ብዙ መልኮች ያሏቸው ማግባባቶችና ሽፍጦች ይደረጋሉ፡፡ ዴሞክራሲ እነዚህንም ይታገሳል፡፡
ዴሞክራሲ በልቅ የግለሰብ ነጻነት አማካኝነት ትውልድን የሚያቆሽሹ ብዙ ጋጠወጥ ልማዶችና ባህሎች እንዲስፋፉ እንዲዳብሩ፣ በመርሆዎቹ አማካኝነት ቀና ፍላጎት አለው፡፡ ዴሞክራሲ ብዙ በዚህ ጽሁፍ ተዘርዝረው የማያልቁ የባህል ብረዛ መንገዶች አሉት፡፡ ዴሞክራሲ የቱንም ያህል የ21ኛው ክፍለዘመን አሸናፊና ምጡቅ የአስተዳደር ዘይቤ ቢሆንም፣ የምዕራባውያንና የአሜሪካ የእጅ አዙር የቅኝ ግዛት ዘዴ እንደሆነ መጠርጠርስ ስህተት ይሆን እንዴ?
በሌላ በኩል፤ ዴሞክራሲ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች የሚያስተናግድበት መንገድ የቱንም ያህል ቀርፋፋ ቢሆንም እንኳን ለሰብዓዊ ልማት (በነጻነት የማሰብ፣ የመናገር፣ የመጻፍ፣ የመደራጀት ወዘተ… ) የሚሰጠው ግምት ከፍ ያለ በመሆኑ አጥብቀን እንድንፈልገው ያደርገናል፡፡ የሰው ልጅ ትልቁ ክብሩ በነጻነት መናገሩ፣ ማሰቡ፣ መመራመሩ ነው፡፡ ከገነትስ የተባረረው በዚህ ሰብብ አይደለምን?
ነገር ግን ብዙዎች ዴሞክራሲ ለዘመናዊው ዓለም ሲባል በሚገባና በልኩ የተሰፋና ያለቀ የአስተዳደር ዘይቤ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ፡፡ ዴሞክራሲ በተለይ በሶስተኛው ዓለም የሚሰጠው ግምትና መሬት ላይ የሚታየው እውነታ ልዩነቱ የትየለሌ ነው፡፡ ዴሞክራሲ ገና እንጭጭ ነው፤ ጮርቃ… የዴሞክራሲ ሥርዓት መገለጫ አድርጋ እራሷን ያቀረበችው አሜሪካ እንኳን የጥቁሮቹንና የነጮቹን እኩልነት ከተቀበለች ገና ሀምሳ ዓመት መሆኑ ነው፡፡ ሆኖም ዛሬም ሙሉ በሙሉ የቆዳ ቀለም ልዩነት አለመቆሙ በገሀድ የሚታይ ዕውነት ነው፡፡ ዴሞክራሲ ከዚህም በላይ ብዙ እንዲሻሻል እንዲጎለብት ሊሰራበት የውሳኔ አሰጣጥ መንገዶቹ ሊቀየሩ ያስፈልጋል፡፡ ዴሞክራሲ ዛሬ ዓለም ከጫፍ እስከ ጫፍ የሚታመስባቸውን የውስጥ ችግሮችና ጦርነቶቹን እንድትቀርፍ እንዲያግዛት፣ ሊያድግ ሊበለጽግ ግድ ይላል፡፡



Read 1306 times