Monday, 04 April 2022 00:00

ከሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ጀርባ ያሉ እውነታዎች

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(0 votes)

 ወቅታዊው ድባብ
የሰሜን ጦር ቃልኪዳን (ኔቶ)፣ ግዛቱን ከጊዜ ወደ ጊዜ በማስፋፋት፤ ዩክሬንን በአባልነት ለማካተት  የጀመረው ሂደት፣ ሩሲያን ስላሳሰባት ወደ መጠነ ሰፊ ዘመቻ ልትገባ ችላለች፡፡ይህም በአካባቢው ከፍተኛ ውጥረት አንግሷል፡፡ በተለይ፤ በአሜሪካ የሚመራው የምዕራቡ ዓለም፣ በቀጥታ በጉዳዩ ላይ እያንጸባረቀ ባለው ከመስመር የወጣ አቋም፣ አለማችን እጅግ አስፈሪ ወደሆነ የእልቂት አውድ ውስጥ እየተንደረደረች ነው፡፡
ሩሲያ በዩክሬን የተነሳ ከምዕራባውያን ጋር በገባችው እሰጣ ገባ ምክንያት፤ አለማችን የምትገዛበት ኢ-ፍትሃዊ የግንኙነት ማእቀፍን ወይም ሉላዊነትን (Globalization) እርቃን አስቀርቶታል የሚሉ ታዛቢዎች በርካቶች ናቸው፡፡ ለወትሮው ስፖርትና ፖለቲካ እሳትና ውሃ ናቸው በሚል ሰበብ በመካከላቸው የበርሊን ግንብ ተተክሎ ነበር፡፡ ይህ ግንብ አሁን ፈርሷል፡፡ ሩሲያን ያልቀጣ የአለም አቀፍ የስፖርት ፌዴሬሽን ማግኘት ፈጽሞ አይታሰብም፡፡ ምነው እነዚህ ፌዴሬሽኖች፣ አሜሪካ ከራሷ ግዛት በብዙ ሺህ ኪሎ ሜትሮች ርቃ በሊቢያ፣ኢራቅና ሶሪያ ላይ የቦንብ በላ ስታወርድ ጆሮ ዳባ ልበስ አሉ፤ ብለው የሚሞግቱ ገለልተኛ ታዛቢዎች አልጠፉም፡፡  
የግጭቱ መላምታዊ  ምክንያት
ሩሲያ ለምን በዚህ ሰዓት ጦርነት ውስጥ መግባት ፈለገች? የሚለው  ጥያቄ፣ ከሀገራት የኃይል አሰላለፍ ወይም ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ቁመና አንጻር መገምገም አለበት፡፡ ሩሲያ ከምዕራባዊያን ጋር ባላት የኃይል እሽቅድምድም ምክንያት ምናልባትም፣ ወርቃማ የሚባሉትን የሃሳባዊያን ዓለም አቀፍ መርህዎች ብትጥስ የሚደንቅ አይሆንም፡፡
እንደ ሩሲያ ያለ ታላቅ ሀገር፣ ከምእራባዊያን ወታደራዊ ተጽእኖ ራሱን የሚጠብቅበት አስተማማኝ ቀጠና ወይም በፈር ዞን ይፈልጋል፡፡  ሀገሪቱ ምእራባዊያን በኔቶ አማካኝነት ያጠመዱትን ቦንብ ለማክሸፍ፤ ዩክሬን ላይ ወረራ ብትፈጽም ሊያስደነደቅ አይችልም፡፡ ከዚህ ቀደም ከናዚ ጀርመን ወረራ የታደገቻቸው የባልቲክ ሀገራት፡-  ሉቲኒያ፣ኢስቶኒያ እና ላቲቪያ የጦር ቃልኪዳኑ አባል ሆነዋል። በዚህም የተነሳ፤ በአሜሪካ የሚመራው የምዕራቡ ዓለም ቀጣናዊ ተጽእኖ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ ሄዷል፡፡ ለዚህ ተጽዕኖ ልጓም ለማበጀት ደግሞ፤ ዩክሬንን መውረር አንደኛው መላ ሆኖ ተገኝቷል፤ ለሩስያ፡፡ ስለዚህ ወቅታዊውን የባልቲክ የጂኦፖለቲካ ቀውስ፣ በደረቁ መገምገም፣ ከስህተት ላይ ይጥላል፡፡ ከሌሎች ኃያላን ሀገራት ጋር ያለውን ንጽጽራዊ ተዛምዶ በቅጡ መመርመር ሙሉ ስእል ለማግኘት ያስችላል።
"አፍቃሪ ናዚ ዩክሬናዊያን፣ በሩሳዊያን ማንነት  ላይ  የደቀኑት አደጋና የዩክሬን ወታደራዊ አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ መፈርጠም፣ ለጦርነቱ መነሻ ነው" ይላሉ ቭላድሚር ፑቲን፡፡ የጦርነት ግቡም ከናዚ የማጽዳት (ዲናዚፊኬሽን) እና ወታደራዊ ትጥቅን ማስፈታት  (ዲሚሊተራይዜሽን) እንደሆነ፤ የክሬምሊን አፈቀላጤዎች ይናገራሉ።  ፈርጣማ ወታደራዊ አቅም፣ የሀገራትን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር፤ የማይተካ ሚና አለው፤ የሚለውን ሃሳብ በሙሉ ልብ ለመቀበል፤ ሩሲያን እማኝ ማድረግ ይበቃል።
አህጉራዊም ሆነ አለም አቀፋዊ ተቋማት ያሰፈሯቸው ድንጋጌዎች፣ ደካማ ሀገርን ሰለባ እንደሚያደርጉ እውናዊያን (ሪያሊስቶች) ይናገራሉ፡፡ እውናዊያን እንደሚሉት ከሆነ፣ አለማችን የምትገዛው በወታደራዊና ምጣኔ ሀብታዊ አቅም እንጂ፤ ዓለም አቀፍ ተቋማት በሚያመቻቹት የሰጥቶ መቀበል መርህ፣ ለስላሳ ግንኙነት አይደለም፡፡ ጠንካራ ወታደራዊ አቅም  ያለው ሀገር፣ ብሔራዊ ጥቅሙን የበለጠ ያስከብራል እንደማለት ነው፡፡
የብዙዎች ጥያቄ የሚሆነው፤ ሩሲያ በዩክሬን አማካኝነት ኔቶ የደቀነባትን አደጋ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቀልብሳ በአሸናፊነት ትወጣለች ወይስ ለምዕራባዊያን ሴራ እጅ ትሰጣለች፤ የሚለው ይሆናል፡፡
የኃያሉ ፍጥጫ፣ አውሮፓን ልክ እንደ ሁለተኛ አለም ጦርነት፣ የትርምስ ማእከል እንዳያደርጋት የሚሰጉ በርካቶች ናቸው፡፡ የዚህ ዳፋ ደግሞ፤ በሁሉም የአለም ጥግ ላለ የሰው ዘር የሚተርፍ ነው፡፡ ዓለማችን ከዚህ ቀደም ያስተናገዳቻቸው የመጀመሪያውና የሁለተኛው ዓለም ጦርነቶች፣ ግዙፍ ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ ማድረሳቸው  ይታወቃል፡፡
በጦርነቶቹ ማግሥትም፤ መሰል ውድመት ዳግም እንዳይከሰት በሚል እሳቤ፣ የመንግሥታቱ ማኅበርና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሊመሠረቱ በቅተዋል። ምናልባትም አሁን ሩሲያ ከምዕራባዊያን ጋር የጀመረችው ቁርቋሶ፣ ወደለየለት ጦርነት ቢያመራ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በሌላ ፍትሃዊ ተቋም የሚተካበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ተብሎ ይገመታል፡፡
የኃያላኑ ተጽእኖ ሚዛናዊ ሆነ መቀጠሉ ለቀሪው ዓለም ፋይዳው የበዛ ይሆናል፡፡ በተለይ፤ እንደ አፍሪቃ  ላሉ በእድገት ወደ ኋላ የቀሩ ሀገራት፣ በተለያዩ ጎራ የተሰለፉ ኃያላን መኖራቸው ከልክ ያለፈ ተጽእኖን በተወሰነ ደረጀ ለመቋቋም ይረዳል፡፡ በመሆኑም፤ የሩሲያ አሸናፊነት ልክ እንደ ቀዝቃዛው ጦርነት አለማችን በሁለት ኃያላን ዋልታ (በባይፖላር ሥርዓት) እንድትመራ ያደርጋታል፤ ሲሉ ተንታኞች ይጠቁማሉ፡፡
የአለም አቀፍ ግንኙነት ተንታኞች ለጦርነቱ መቋጫ አራት የቢሆናል መላምት አስቀምጠዋል። የመጀመሪያው፤ ሩሲያ ዩክሬንን ማሸነፍ ተስኗት፣ ወደ ውስጥ የምትሰበሰብበት ኹነት ሊፈጠር ይችላል። በውጤቱም፤ በፖለቲካዊ ቀውስ የምትታመስ ደካማ ሩስያ ለአይነ ሥጋ  ትበቃለች። ሌላው ሩስያ ጦርነቱን ብታሸንፍም፣ ወደ ሽምቅ ኃይል የተቀየረው የዩክሬን መደበኛ ጦር፣ አካባቢውን የትርምስ ቀጠና በማድረግ፣ ራስ ምታት ሆኖ ሊቀጥል ይችላል። ቀውሱ እንዲባባስ የኔቶ አባል ሀገራት እጃቸውን ያስገባሉ።
ሶስተኛው ቢሆናል፣ ሩሲያ እንደወጠነችው ጦርነቱን በማያዳግም ሁኔታ ማሸነፍና ተጽዕኖዋን ወደ ባልቲክ ሀገራት ማስፋፋት ነው። የመጨረሻው ቢሆናል፣ ከሁሉም የከፋ ነው። ሩሲያ እና ኔቶ ቀጥታ ጦርነት ውስጥ ይገባሉ።
ምጣኔ ሀብታዊ ተጽእኖ
የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት፣ ከፖለቲካዊው ውጥረት በዘለለ ምጣኔ ሃብታዊ ተጽእኖው በእጅጉ የጎላ እንደሆነ በገሀድ እየተመለከተን ነው፡፡ የነዳጅና ጋዝ ግብይትን በዶላር ፋንታ ሩብል  እንዲተካ ሩስያ ወስናለች፡፡ ይህ እርምጃ፤ ምጣኔ ሀብታዊ ትርጉሙ የላቀ መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ፡፡
የዓለማችን ግዙፍ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት ተርታ የምትመደበው ጀርመን፣ እስከ 45 በመቶ የሚጠጋ የተፈጥሮ ጋዝ የምታስገባው ከሩሲያ ነው፡፡ የጀርመን መንግሥት ለዩክሬን ያለውን አጋርነት የሚያሳየው፣ ይህንን የኢኮኖሚ ትስስር በማይጎዳ መልኩ እንደሆነ፤ የሀገሪቱ ቱባ ባለሥልጣናት በመግለጽ ላይ ናቸው። የዩክሬን  ባለሥልጣናት፣ የሰሜን ጦር ቃልኪዳን ኔቶ፣ ከበራራ ቀጠና ነጻ እንዲያወጅላቸው ጠዋትና ማታ ቢማጸኑም፣ ይህንን ተግባራዊ ማድረግ ፈጽሞ እንደማይሞከር የጦር ቃል ኪዳኑ አፈቀላጤ ገልጸዋል፡፡
በሀገራት ላይ የሚኖረው
የጎንዮሽ ተጽእኖ
ዓለም ትኩረቱን በሩሲያና ዩኩሬን ላይ ሲያደርግ፤ ሀገራት የየግላቸውን የቤት ሥራ ለመሥራት ደፋ ቀና ማለት ጀምረዋል፡፡ ቻይና "ታይዋን እንደ ዩክሬን አይደለችም" የሚል፤ ማስፈራሪያ አዘል መልዕክት ማሰማት ጀምራለች፡፡
እኛም እንደ ሀገር፤ ሉአላዊነታችንን የሚፈታተን ሽብርተኛ ድርጅትን ለመደምሰስ በይደር ያቆየነው የቤት ሥራ ይጠብቀናል፡፡ የሽብር ኃይሉን ማጥፋት ለድርድር የሚቀርብ እንዳልሆነ፣ በቅርቡ ምክትል ኢታማጆር ሹም አበባው ታደሰ መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡  
ለሽብር ቡድኑ ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ ምእራባዊያን፤ በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት የመጠመዳቸውን መልካም አጋጣሚ መጠቀም ብልህነት ነው፤ ይላሉ አንዳንድ የጦር አዋቂዎች፡፡ ይህ አመክንዮ ውሃ አያነሳም የሚሉ በዚያው ልክ በርካቶች ናቸው፡፡ ምዕራባዊያን በሁሉም ሀገራት ያለውን ብሔራዊ ጥቅማቸውን የሚቃኙበት፤ራሱን የቻለ የተደራጀ የውጭ ጉዳይ መምሪያ  አላቸው፡፡
 ለዚህም ማሳያ የሚሆነን፣ ሰሞኑን የሥጋት ደመና የፈጠሩት ኤስ 3199 እና ኤችአር 6600 የተባሉት አዲስ ሸምቀቆዎች ናቸው፡፡ እንደ ሩሲያ የዳበረ ወታደራዊና ምጣኔ ሀብታዊ አቅምን አዳብረን ቢሆን ኖሮ፤ በራሳችን የግዛት ወሰን ውስጥ ያለውን ፈተና ይቅርና ቀጠናውን ለመቆጣጠር ማማተር እንችል ነበር፡፡ ለማንኛውም፣ የሩሲያ ቀና ማለት ለእኛም የሚተርፍ በረከትን ይዞ መምጣቱ አይቀርም፡፡
ህዳግ
በአጠቃላይ፤ ምእራባዊያንን የበለጠ ባለጠጋ፣ ታዳጊ ሀገራትን በአንጻሩ ደግሞ በማደህየት ላይ ለተመሰረተው የአለም አቀፍ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሐብታዊ ትስስርን (ሉላዊነትን) የሚተካ፣ ሌላ አማራጭ የግንኙነት ማእቀፍን አውን ለማድረግ ፖለቲካዊ ትኩሳቱ ወሳኝ ኩርባ ሊሆን ይችላል፡፡

Read 1286 times