Monday, 04 April 2022 00:00

ሌሎች ጥንታዊ ሥልጣኔዎች ፍልስፍናን ማፍለቅ ያልቻሉት ለምንድን ነው?

Written by  ብሩህ ዓለምነህ
Rate this item
(1 Vote)


            "--በዚህም የተነሳ፣ ለግሪኮቹ ይሄ ዓለም ‹‹ሊታወቅ የሚችል›› እና ‹‹ለመኖር መልካም የሆነ ሥፍራ ነው››፡፡ ይሄም ማለት፣ ሌላ የተስፋ ዓለም ሳትናፍቅ በዚህ ዓለም ላይ ስኬታማና ደስተኛ ሆነህ መኖር ትችላለህ፡፡ ይሄም አመለካከታቸው በትምህርት ሥርዓታቸው፣ በኪነ ጥበብ ሥራዎቻቸውና
በፍልስፍናቸው በግልፅ ተንፀባርቆ ይታያል፡፡--"
         
            በታሪክ ውስጥ የተነሱ የተለያዩ ጥንታዊ ሥልጣኔዎች ታይተዋል፡፡ ለምሳሌ፡- ቻይና፣ ህንድ፣ አክሱም፣ ፐርሺያ፣ ባቢሎን፣ ኢንካ፣ ግብፅ… ወዘተ፡፡ ሆኖም ግን ከእነዚህ ጥንታዊ ሥልጣኔዎች ውስጥ አንዳቸውም ፍልስፍናን ማፍለቅ አልቻሉም፡፡ ለምን ይሆን?
‹‹Thales of Miletus and the Birth of Greek Philosophy›› በሚለው የቪዲዮ ሌክቸሩ Leonard Peikoff ‹‹ሌሎች ጥንታዊ ሥልጣኔዎች ፍልስፍናን እንዳያመነጩ የከለከላቸው ሁለት ምክንያቶች አሉ›› ይላል፤
የመጀመሪያው፣ ከእውነት ምልከታ (View of Reality) ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሌሎች ጥንታዊ ሥልጣኔዎች ‹‹በዚህ ዓለም ላይ ምንም የሚታወቅ ነገር የለም፤ በዚህ ዓለም ላይ ያሉ ክስተቶች በሙሉ በሌላ በማይታይ ኃይል የሚዘወሩ ናቸው›› ብለው ማመናቸው ነው፡፡ ይሄም አመለካከታቸው ማህበረሰባቸው አእምሮ ውስጥ የተአምራዊነት እሳቤ በጥልቀት እንዲሰርፅና የነገሮችን መንስኤ ለማወቅ ጭራሽ ፍላጎቱ እንዳይኖራቸው አድርጓቸዋል፤ መንስኤን ሳይታወቅ ደግሞ ፍልስፍናም ሆነ ሳይንሳዊ ዕውቀትን ማመንጨት አይቻልም፡፡
ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ፣ ከግሪኮቹ በተቃራኒ ሌሎች ጥንታዊ ሥልጣኔዎች ‹‹ይህ ህይወትና መኖሪያዋ ምድር የማይታወቁ ብቻ ሳይሆን ‹‹እርኩስ ናቸው›››› ብለው ማሰባቸው ነው፡፡
እነዚህ ሁለት እሳቤዎች ግን በግሪክ አልነበሩም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፣ እንደ ፔኮፍ አመለካከት፣ ሁለት ተያያዥ ነገሮች (ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ምክንያቶች) ከሌሎች ሥልጣኔዎች በተለየ ግሪኮች ሳይንስንና ፍልስፍናን እንዲያፈልቁ አስችሏቸዋል፤
የመጀመሪያው፣ ፖለቲካዊ ምክንያት ነው። እንደሚታወቀው ሄለናውያን (ግሪካውያን) ከሌሎች አጎራባች ህዝቦች በተለየ የፖለቲካ ነፃነት ነበራቸው፤ ሲተዳደሩበት የነበረው የዲሞክራሲ ሥርዓት ለዚህ አባባላችን ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ይሄም በነፃነት ለማሰብ ምቹ ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል፡፡ የፖለቲካ ነፃነት ያልነበራቸው የአቴንስ ጎረቤቶች (ለምሳሌ ስፓርታ) ፍልስፍናን ማፍለቅ አልቻሉም፡፡
ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ሃይማኖታዊ ነው፡፡ እንደ ሌሎች ህዝቦች ሁሉ ግሪኮችም ሃይማኖት የነበራቸው ቢሆንም፣ ሃይማኖታቸው ግን የተለየ ነበር፡፡ ግሪኮቹ ብዙ አማልክት የነበራቸው ቢሆንም፣ እነዚህ አማልክት ግን የዩኒቨርሱ ፈጣሪም ሆነ አስተዳዳሪ ወይም ገዥ አይደሉም፡፡ ግሪኮቹ፣ ‹‹ዩኒቨርስ ከጥንት ጀምሮ የነበረ ተፈጥሯዊ ክስተት ነው›› በማለት የሚያምኑ ሲሆን፤ ‹‹አማልክቱም ልክ እንደ ሰዎችና ሌሎች ፍጡራን የዚህ ተፈጥሯዊ ክስተት ውጤት ናቸው እንጂ ፈጣሪ አይደሉም›› በማለት ያምናሉ፡፡ ለዚህም ነው የግሪክ አማልክቶች ለሰዎች በጣም ቅርብና ወዳጅ የሆኑት፡፡ ስለዚህ፣ አማልክቱ በዩኒቨርሱ ሥራ ውስጥ ጣልቃ አይገቡም፤ ደግሞም አይችሉም፡፡ ይሄም ማለት የግሪኮቹ አማልክቶች ‹‹ሁሉን ቻይ›› እና ‹‹ሁሉን አዋቂ›› አይደሉም፡፡
በዚህም የተነሳ፣ ለግሪኮቹ ይሄ ዓለም ‹‹ሊታወቅ የሚችል›› እና ‹‹ለመኖር መልካም የሆነ ሥፍራ ነው››፡፡ ይሄም ማለት፣ ሌላ የተስፋ ዓለም ሳትናፍቅ በዚህ ዓለም ላይ ስኬታማና ደስተኛ ሆነህ መኖር ትችላለህ። ይሄም አመለካከታቸው በትምህርት ሥርዓታቸው፣ በኪነ ጥበብ ሥራዎቻቸውና በፍልስፍናቸው በግልፅ ተንፀባርቆ ይታያል።
ግሪኮቹ ‹‹ይሄ ዓለም ሊታወቅ የሚችልና ለመኖርም መልካም የሆነ ሥፍራ ነው›› ብለው በማመናቸው የተነሳ ለሰው ልጅ አእምሮና አካል እኩል ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ ለምሳሌ፣ የትምህርት ዓላማቸው ‹‹ጤናማ መንፈስ በጤናማ አካል ማስገኘት›› የሚል ሲሆን (እጓለ 2003፡ 87)፤ የግሪክ ቀራፂያን ሲሰሯቸው የነበሩ የሰው ኪነ-ቅርፆች (Sculptures) ደግሞ ለተማፅኖ ወደ ሰማይ የማያንጋጥጡ፣ በሐዘን ወደ ምድር የማያቀረቅሩ፣ ይልቅስ ከፈረጠመ አካል ጋር የደስተኛነትና የበራ መልክ የሚታይባቸው ነበሩ፡፡
ፔኮፍ፣ ከሌሎች ሥልጣኔዎች በተለየ ግሪኮች ሳይንስንና ፍልስፍናን እንዲያፈልቁ ያስቻላቸው በማለት ከጠቀሳቸው ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ምክንያቶች በተጨማሪ፣ እጓለ ገብረዮሐንስ ደግሞ ውድድርንና ሥነልቦናዊ ምክንያትን ይጨምርበታል (እጓለ 2003፡ 54)፡፡ እንደ እጓለ አመለካከት፤ የጥንት ግሪካውያን ከሌሎች ዘመንኛ ህዝቦች በተለየ አዲስ ነገርን ለማወቅ ከፍተኛ ጉጉት ነበራቸው። ይሄም ማህበራዊ ሥነ ልቦናቸው ቅዱስ ጳውሎስ ሳይቀር ‹‹የአቴና ሰዎች አዲስ ነገርን ከመናገርና ከመስማት በስተቀር ሌላ ምኞት አልነበራቸውም›› (ሐዋ 17፡ 21) በማለት መስክሮላቸዋል፡፡ ለዚህ ምኞታቸው ማሳኪያ ደግሞ ‹‹አሪዮስፋጎስ›› የተባለ የንግግር መድረክ አዘጋጅተው ነበር፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በግሪክ አሳቢያን መካከል ሲደረግ የነበረው የሐሳብ ክርክርና ውድድር በግሪክ አሳቢዎች የተከማቸበትን ሥልጣኔ እንዲያፈልቁ አድርጓቸዋል፡፡
እንደ እጓለ አመለካከት፣ እነዚህ ሁለት ምክንያቶች (ሁልጊዜ ለአዲስ ነገር መጓጓት እና የሐሳብ ክርክሩ) ግሪካውያን በተለያዩ የዕውቀትና የሙያ ዘርፎች ላይ አዳዲስ ሐሳቦችንና ፍልስፍናዎችን እንዲያፈልቁ አድርጓቸዋል፡፡ ‹‹የዘመናዊ አውሮፓ የሥልጣኔ መንፈስ ከእነዚህ ጥንታዊ የሐሳብ ክርክሮችና ፍጭቶች ከተገኘው የዕውቀት ብርሀን የሰረፀ ነው፡፡››
ምንም እንኳ ግሪኮቹ በነፍስ ዘላለማዊነት የሚያምኑ ቢሆንም፣ ምድርን የደስታ ቦታ ማድረጋቸው ግን ‹‹ከሞት በኋላ ህይወት›› የሚል ናፍቆት እንዳይጠናወታቸው አድርጓቸዋል፡፡ ይሄንንም ጭብጥ ‹‹The Ghost of Achilles›› በተባለው የሆሜር ሥራ ውስጥ የትሮጃን ጦርነት ጀግናው አኪለስ፣ ለንጉስ ኦዲሲየስ እንዲህ ሲለው እናገኘዋለን፣
“No winning words about death to me, shining Odysseus!
By god, I would rather slave on earth for another
man2some dirt-poor tenant farmer who scrapes to keep
alive2than rule down here over all the breathless dead.”
The Odyssey, Book II, 555–558
(እንደ ብርሃን የምታንፀባርቀው ኦዲሲየስ! እኔ ስለ ሞት በኩራት የምናገረው ነገር የለኝም፤ ምንም ትንፋሽ በሌለው ሌላ የሙታን ዓለም ንጉስና ገዥ ሆኜ ከምኖር ይልቅ በምድር ላይ የምስኪን ሰው ባሪያ ሆኜ መኖርን እመርጣለሁ፡፡)
በችሎታቸውና በአካላቸው ጥንካሬ ዓለምን ለሚያሸንፉት ግሪኮቹ፣ ከሞት በኋላ ካለው ህይወት ይልቅ በዚህ ምድር ላይ ያለው ክብርና ዝና ይበልጥባቸዋል። እንደዚህ ዓይነት መፍቀሬ-ምድር ግሪኮቹ ላይ ብቻ ሲታይ የነበረ ዓይነተኛ ሥነ ልቦናቸው ነው፡፡
‹‹በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች…›› ይላል Peikoff ‹‹በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ግሪኮቹ፤ ‹‹ዕውቀትን የሚቻል ብቻ ሳይሆን የሚወደድና ልናገኘውም የሚገባ (the Love of Wisdom)›› በማድረጋቸው የተነሳ ምድራችን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ አሳቢያን የተከማቹባትን ሥልጣኔ (a Civilization of Thinkers) ከወደ ግሪክ ማግኘት ችላለች፡፡
ከዚህ አኳያ ጥንታዊት ግሪክ በድቅድቅ የጨለማ ዘመን ላይ የተለኮሰች አስገራሚ የብርሃን ፍንጣቂ ተደርጋ ትወሰዳለች። የዚህ አስደናቂ የብርሃን ፍንጣቂ ጮራም፣ 2500 ዓመታትን ተሻግሮ አሁንም ድረስ ኑሯችንን ያደምቅልናል።
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 6183 times