Wednesday, 06 April 2022 00:00

በህወኃት ሀይል ከፍተኛ ውድመት የደረሰበት የወሎ ዩኒቨርስቲ

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

   “ዩኒቨርስቲውን ወደ ቀደመ አቋሙ ለመመለስ ገና ብዙ በጀትና ልፋት ይጠይቃል”
          “ወራሪው ሀይል ዩኒቨርስቲው ዳግም ወደ ስራ እንዳይመለስ ነበር እቅዱ”

            የህወኃት ሀይል ወሎን በወረራ ከመቆጣጠሩ በፊትም ሆነ በኋላ ዩኒቨርስቲዎችንና የጤና ተቋማትን ኢላማ አድርጎ ባደረሰው ጥቃት ወሎ ዩኒቨርስቲ 12 ቢሊዮን ብር የሚገመት ሀብቱን አጥቷል፡፡ ወራሪው ሀይል ከአካባቢው ከተወገደ በኋላ ባሉት ሶስት ወራት ዩኒቨርስቲው ሌት ተቀን ባደረገው እንቅስቃሴና ጥረት መሰረታዊ የሚባሉ ነገሮችን አሟልቶ መጋቢት 15 ቀን 2014 ዓ.ም ከ95 በመቶ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ የመማር ማስተማር ሂደቱን ጀምሯል፡፡
ይሁን እንጂ ዩኒቨርስቲውን ወደ ቀደመ አቋሙ ለመመለስ እጅግ ከፍተኛ በጀትና ትግል እንደሚጠቅ የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ይናገራሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ደሴ ተገኝታ ከዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት መንገሻ አየነ (ዶ/ር) ጋር ባደረገችው ቆይታ ዩኒቨርስቲው ስለደረሰበት ከፍተኛ ውድመትና በአጠቃላይ ጉዳች ዙሪያ ሰፊ ማበራሪያ ሰጥተዋታል እንደታነቡ እንጋብዛለን
 
            ራስዎን ለአንባቢያን በማስተዋወቅ ብንጀምርስ?
የወሎ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ነኝ። ከዚህ ቀደም በዚሁ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ከኮሌጅ ዲንነት ጀምሮ የዩኒቨርስቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት ሆኜም አገልግያለሁ። በትምህርት ዝግጅት፣ በተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የፊዚክስ መምህርም ነኝ። በትምህርት ደረጃም ተባባሪ ፕሮፌሰር ነኝ። በፊዚክስ ትምህርት ክፍል በተባባሪ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ አስተምራለሁ። ከዚህ በተጨማሪም በባህርዳር ዩኒቨርስቲ የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎችን አስተምራለሁ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎችን አማክራለሁ። ስለዚህ ከአስተዳደራዊ ስራዬ ጎን ለጎን፣ የማስተማርና የምርምር ሥራ ሃላፊነቴንም እየተወጣሁ እገኛለሁ። የምርምር ዘርፌ ፊዚክስ ቢሆንም፣ በብዛት የኔ የምርምር ፍላጎት በፊዚክስ መምህራን ስልጠና ላይ ያተኮረ ነው። በፊዚክስ ብቻም ሳይሆን በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግ፣  ማቲማቲክስ የትምህርት ዘርፎችም ላይ ትኩረት አድርጌ ምርምር እሰራለሁ። በዚህ ዘርፍ ላይ በጣም የታወቁ ከሚባሉት ጆርናሎች ውስጥ   እንደ ፊዚካል  ሪቪው ባሉ ህትመቶች ላይ የጥናት ወረቀቶቼ ወጥተውልኛል።
እስቲ በጦርነቱ ውድመት የደረሰበት የወሎ ዩኒቨርስቲ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ በዝርዝር  ይንገሩን?
ጥሩ! ወሎ ዩኒቨርስቲ የተቋቋመው በ1999 ዓ.ም መንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ለማስፋፋት በወሰደው አቋም 13 ዩኒቨርስቲዎችን ባቋቋመበት ወቅት ነው። በትውልድም ሁለተኛ ትውልድ ከሚባሉት ውስጥ ይመደባል። በቅርቡ መንግስት በዩኒቨርስቲዎች የትኩረት ዘርፍ ባደረገው ልየታ፤ “ኒቨርስቲ ኦፍ አፕላይድ ሳይንስ” ከሚባሉት ዩኒቨርስቲዎች አንዱ ነው። እንደሚታወቀው፤ መንግስት የሪሰርች ዩኒቨርስቲ፣ አፕላይድ ዩኒቨርሲቲ፣ ኮምፕረኼንሲቭ ዩኒቨርሲቲ፣ ቴክኒካል ዩኒቨርስቲና ቲቺንግ ዩኒቨርስቲ በሚል ዩኒቨርስቲዎችን ለይቷል። ስለዚህ ወሎ ዩኒቨርስቲ “ዩኒቨርስቲ ኦፍ አፕላይድ ሳይንስ” ከሚባሉት ጎራ የምንሰለፍ ተቋም ነን።
በሌላ በኩል፣ የዛሬ 10 ዓመት መንግስት ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ቅድሚያ ሰጥቶ በተለይ የቴክኖሎጂ ዘርፉን በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ በወሰደው ቁርጠኛ አቋም 10 የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶችን አቋቁሟል። ከነዚህ ኢንስቲትዩቶች አንዱ የኛ የኮንቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አንዱ ነው። በሰሜን ምስራቅ ኢትየጵያ ኮምቦልቻ የኢንዱስትሪ መንደር መሆኗን ተከትሎ፣ ምናልባትም ከሁለተኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲ እኛ እና ድሬደዋ ዩኒቨርስቲ ይመስለኛል በቴክኖሎጂ የልህቀት ማዕከልነት እንድናስተምር የተፈቀደልን። ሁለታችን ብቻ። ስለዚህ ሁለተኛው ግቢያችን በኮምቦልቻ ከተማ  የኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስትቲዩት  ተብሎ ይጠራል። በውስጡ ሁለት ኮሌጆች ይዟል “ኮሌጅ ኦፍ ኢንጅነሪንግ እና ኮሌጅ ኦፍ ኢንፎርማቲክስ” የተሰኙትን ኮሌጆች ማለት ነው
ከዚህ በተጨማሪ ዩኒቨርስቲያችን ጠንካራ የውጪ ግንኙነት ጀምሮ ነበርና አሜሪካን አገር ከሚገኘው የቱሊን ዩኒቨርስቲና ከማይክሮሶፍት ጋር በመተባበር ብቸኛው የ”አፕ ፋክተሪ” (አፕልኬሽንን ወይም ሶፍትዌርን) በልዩነት የሚያለማ ተቋም መስርተን፣ በዚህ ዘርፍም የላቀ አስተዋጽኦ ማድረግ የጀመረ ተቋም ነው። በአጠቃላይ ዩኒቨርስቲያችን የሁለተኛ ትውልድ ዩኒቨርስቲ ይባል እንጂ በፕሮግራም ስፋትና በልህቀቱ ምናልባትም ከመጀመሪያ ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የሚስተካከል ዩኒቨርስቲ ነው ብለን በልበ ሙሉነት መናገር የሚያስችለን ዩኒቨርስቲ ነው። በአጠቃላይ አስር ት/ቤትና ተቋም ብለን የለየናቸው አሉን። ገሚሶቹ በኮሌጅ ስም ይጠራሉ። ሌሎቹ እንደ ህግና የእንስሳት ህክምና ት/ቤቶች ራሳቸውን የቻሉ ናቸው።
ሰባት ኮሌጆች ሲኖሩ አንድ የመምህራን ትምህርት ስልጠናና ብሄቪየራል ሳይንስ ተቋምም አለን። በአጠቃላይ በ10 ኮሌጆች ተዋቅሮ ነው ዩኒቨርስቲው የመማር ማስተማር ሂደቱን እያከናወነ ያለው። ወደ 100 የሚጠጉ የድህረ ምረቃ ፕሮግራሞች አሉን። እንደዚሁም በህክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ፣ በህክምና ት/ቤት ስር፣ የህክምና የመጀመሪያ ዲግሪና በሁለት ዘርፎች ማለትም በካይናኮሎና በሰርጀሪ የስፔሻሊቲ ፕሮግራሞችን ያስተምራል።  የተወሰኑ የፒኤችዲ ፕሮግራሞች አሉን አዳዲስም እየከፈትን እንገኛለን።
በአጠቃላይ በመደበኛ፣ በክረምትና በተከታታይ ትምህርት ፕሮግራም ከ26 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ የሚገኝ ተቋም ነው።
ዩኒቨርስቲያችሁ ይህንን ሁሉ ዘርፈ ብዙ ስራዎች ሲሰራ የነበረው በሰላሙ ጊዜ ነበር- ከወረራው በፊት። አሁን ግን ህንፃዎችን ጨምሮ ብዙ ሃብቱ በህወኃት ሃይሎች ወድሟል፡፡ ለመሆኑ  ምኑን ከምኑ አድርጋችሁ ነው ትምህርት የጀመራችሁት?
ወራሪው ሀይል እንደሚታወቀው ጥቃቱ ግልፅ ነው፡፡ የትምህርትና የጤና ተቋማትን በከፍተኛ ሁኔታ ኢላማ አድርጎ ነው ጥቃት የፈፀመው፡፡ እነዚህን ተቋማት በመድፍና በከባድ መሳሪያዎች እያወደመ ነው የወጣው፡፡ የእኛ ዩኒቨርስቲ በወራሪው ሀይል መመታት የጀመረው፣ ይህ አጥፊ ቡድን ገና አካባቢውን ሳይቆጣጠር፣በ20 እና 30 ኪ.ሜ  እርቀት ላይ እያለ ነበር ኢላማውን ዩኒቨርስቲና  ጤና ተቋማትን አድርጎ፣ መድፍ እየተኮሰ ተቋማችንን ሲያወድም ነበር። ግቢውን ተዘዋውራችሁ እንዳያችሁት፤ መለስተኛ ጉዳት  ከገጠማቸው የተቋሙ አንዳንድ ህንፃዎች ባለፈ ላይመለሱ የሞቱ በምህንድስና ቋንቋ (structural damage) የደረሰባቸው ሁለት ትልልቅ ህንፃዎች አሉ። እነዚህ ህንፃዎች፤ የህክምናና ጤና ሳይንስ እንዲሁም የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ የነበሩ ናቸው፡፡
ሌላው የዩኒቨርስቲው ዋና ቤተ መፃሐፍት በከፍተኛ መድፍ ተመትቶ፣ አብዛኛው ክፍል ወድሟል፡፡ ይህ የምነግርሽ ውድመት የደረሰው ትህነግ አካባቢውን ከመቆጣጠሩ በፊት ሆን ብሎ አስቦና አልሞ፣ የትምህርት ተቋማትን ለማውደም ባደረገው የከባድ መሳሪያ ጥቃት ነው። ዋናው ጉዳይ ይሄ አይደለም። ወራሪው ሀይል አካባቢውን በወረረና በተቆጣጠረ ማግስት በጣም ከፍተኛ ሙያተኞችን በማሰለፍ፣ ተሳቢ መኪናዎችን አቅርቦ በዩኒቨርስቲያችን የሳይንስ፣ የህክምናና የጤና ሳይንስ፣የግብርና ሳይንስ እንዲሁም የእንስሳት ህክምና ት/ቤት ውስጥ የነበሩ ትልልቅ የላብራቶሪ ማሽኖችን ነቅሎ ወስዷል፡፡ በተለይ የዩኒቨርስቲያችን ላብራቶሪዎችን በዘመናዊ መሳሪያ የተደራጀ አድርጎ አቋቁሞ ነበር፡፡ ለምሳሌ፡- ለምርምር ከገዛናቸው ላብራቶሪዎች ውስጥ ኮቪድ በተከሰተ ጊዜ ለኮቪድ ምርመራ ማዕከልነት ያቋቋምናቸው ሁለት የኮቪድ ምርመራ ማዕከላት ነበሩ፡፡ እነዚህ ማዕከላት እጅግ ከፍተኛ በሆነ ወጪ የተገነቡና በሰሜን ምስራቅ ቀደም ብሎ ኮቪድን በመመርመር ትልቅ ሚና ሲጫወት የነበረው ዩኒቨርስቲ ነው፡፡ በእነዚህ ማዕከላት የነበሩት ትልልቅ የሳይንስ ቁሳቁሶችን በአግባቡ በሙያተኛ አስነቅሎ ወስዷል፡፡
ከዚህ ባለፈ በታችኛውም በቴክኖሎጂውም ሆነ በዋናው ግቢ አካዳሚክ ዘርፉ ላይ የነበሩ በመንግስት በጀት የተገዙ ትልልቅ ሀብቶችን እንዲሁም ዩኒቨርስቲያችን ከአለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር ያገኛቸውን ትልልቅ ሀብቶች በሙሉ፣ የሚችለውን አስነቅሎ ወስዶ፣ የተረፉት ደግሞ አገልግሎት እንዳይሰጡ አድርጎ አውድሞ ነው የወጣው፡፡
በአጠቃላይ ዩኒቨርስቲያችን ያጋጠመውን የውድመት መጠንና አይነት በአራት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው የአካዳሚክ ሴክተሩ ጉዳት ነው፡፡ በተለይ በዚህ ዘርፍ ከፍተኛ ጉዳት ነው የገጠመን። ወርክሾፖቻችን፣ ላብራቶሪዎቻችን፣ የኮምፒውተር ላብራቶሪዎቻችን፣ ቨርቹዋል ላብራቶሪዎች እንዲሁም በሁሉም ቤተ መፃሀፍት የነበሩ ኢ-ላብረሪዎች ጭምር ዘርፎም አውድሞም ትልቅ ጉዳት ላይ ጥሎ ነው የሄደው፡፡ በተለይ ከፍተኛ ውድመት የገጠመን በህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የስኬል ላብራቶሪ፣ የፋርማኮሎጂ የኢንቫይሮመንታል፤ የፐብሊክ ኸልዝ ላብራቶሪዎች፣ የሜዲካል ላብራቶሪዎች እንዲሁም በፋርማሲ ደግሞ የፋርማስዩቲካል (የድራግ እንፎርሜሽን ሴንተር) የምንለውን በከፍተኛ ሁኔታ ዘርፎና አውድሞ ነው የወጣው፡፡ በዚህ ዘርፍ እኛም ሆነ ትምህርት ሚኒስቴር ሙያተኛ ልኮ ባስጠናው መሰረት፣ ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ሀብት ወድሟል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ከፍተኛ ውድመት የገጠመው የዩኒቨርስቲው ህንፃዎች ናቸው። ቅድም እንዳልኩት፤ ሁለት ህንፃዎች መቶ በመቶ ወድመዋል፡፡ አሁን ያለንበት የአስተዳደር ህንፃ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ገና አንድ ዓመቱ ብቻ ነው፡፡ አዲስ ነበር፡፡ እንደምታየው ስብርብሩ ወጥቷል። አሁንም ያለንበት የኔ ቢሮ አልነበረም። የተሻለ ነው ተብሎ ነው እዚህ የገባሁት እንጂ የፕሬዝዳንት ቢሮ ሌላ ህንፃ ላይ ነበር። በከፋ ሁኔታ በመጎዳቱ እዚህ ተዛውረን ነው ያለነው። ይህም ቢሆን ድንገት በዘነበ ዝናብ ውሃ ገብቶ ውሃ እየተቀዳ ሲወጣ ተመክልተሻል፡፡ አሁንም አስተካክለን መጠነኛ ጥገና አድርገን ስለመጣችሁ እንጂ ህንጻው ስትራክቸራል ችግር ባይገጥመውም አብዛኛው የህንፃው አካላት ተሰባብሮ ተጎድቷል፡፡ በዚህ ዘርፍም (በህንጻ ውድመት) ከ3 ቢ ብር በላይ የሚገመት ሀብት ወድሞብናል፡፡ ሶስተኛው ትልቅ ውድመት ያጋጠመው የአይሲቲ መሰረተ ልማታችን ነው፡፡ ዩኒቨርስቲያችን በሶስቱም ግቢ ማለትም የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጢጣ የሚባለው ቦታ ነው ያለው፡፡ የኢንጂነሪንግና የቴክኖሎጂ ግቢ ኮምቦልቻ ነው የሚገኘው፡፡ በእነዚህ ግቢዎች ጠንካራ የሚባል የአይሲቲ መሰረተ ልማት ገንብተን ነበር፡፡ በተለይ በዋናው ግቢ ደሴ ካምፓስ ላይ የአይሲቲ መሰረተ ልማቶችን በአንድ ላይ የያዘ ራሱን የቻለ አንድ ህንፃ ነበር፡፡ በዚህ  ህንፃ የቪዲዮ ኮንፈረንስ፣የስማርት ክላስ ሩምና አጠቃላይ የዳታ ማዕላትን በጠንካራ ሁኔታ ገንብተን ነበር፡፡ እነዚህን ጠንካራ የአይሲቲ መሰረተ ልማቶች ወራሪው ሀይል የቻለውን ዘርፎ ያልቻለውን አውድሟል፡፡ በዚህ ዘርፍም 1 ቢሊዮን ሀብት ወድሞብናል።
በሌላ በኩል፤ ዩኒቨርስቲዎች የራሳቸውን ወጪ በራሳቸው ለመሸፈን እንደ ሃገር ኢንተርፕራይዝ እንዲያቋቋሙ በተፈቀደላቸው መሰረተ ዩኒቨርስቲያችን የኢንተርፕራይዝ ዘርፍ ነበረው፡፡ በዚህ ዘርፍ ከ180 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ሀብት ወድሞብናል፡፡ በአጠቃላይ በጦርነቱ ዩኒቨርስቲው 11.9 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ የሀብት ውድመት ደርሶበታል፡፡ ይሄ እንግዲህ በእኛም ሆነ በትምህርት ሚኒስቴር ባለሙያዎች ተጠንቶ የተገኘ የውድመት መጠን ነው፡፡
አሁን ይሄ ሁሉ ውድመት ደርሶ ያውም በአጭር ጊዜ እንዴት ወደ መማር ማስተማር ስራው ሊመለስ ቻለ ብለሽ ወዳነሳሽው ከባድ ጥያቄ ልመልስ፡፡ እውነት ነው ከባድ ነው፡፡ ምክንያቱም ከነበረን ሀብት አንጻር የወደመብን ሃብት እንዳናንሰራራ የሚያደርግ ነው፡፡ ይሄ ሃቅ ነው፡፡ ነገር ግን ይህንኑ ተቋም መልሶ ወደ ስራ ማስገባቱ ከወራሪው ጋር ያለንን ትግል አስቀጣይ ነው።  ምክንያቱም በህንፃው ግድግዳ ፅፈው ከሄዱት ነገር የተገነዘብነውና የተማርነው ነገር፣ እርምጃው ይሄ ተቋም ደግሞ እንዳያንሰራራና የመማር ማስተማር ስራው እዚህ ግቢ ዳግም እንዳይካሄድ አድርገናል ብለው ነው የወጡት፡፡
ይህ ወራሪ ሀይል ከጦርነቱ ባለፈ የትምህርት ተቋማቱን ዒላማ አድርጎ ጉዳት ለማድረስ የተነሳው በተለይ የአማራ ህዝብ፣ በአጠቃላይ ኢትዮጵያዊያን በትምህርት የሚያገኙትን ጥቅም እንዳያገኙ፣ የትምህርትና የምርምር አገልግሎቱ ዳግም እንዳይሰራ የሚል ህልም ይዞ ያደረሰው ጥፋት ስለሆነ፣ በየትኛውም አጋጣሚና አኳኋን ተቋሙን መልሶ ወደ ስራ ማስገባት፣ ይሀን ሀይል ከማሳፈር ያለፈ ትርጉም ያለው በመሆኑ ይህንን እውን አድርገናል፡፡
እስኪ በዚህ በ3 ወር ጊዜ ውስጥ ትምህርት ለማስጀመር ያከናወናችኋቸውን ተግባራት ያብራሩልኝ፡፡
ምንም እንኳን ለማህበረሰብ የሚያስፈልጉን የላብራቶሪ ወርክሾፕ ተቋማትን በአጭር ጊዜ መልሰን ማምጣት ባንችልም፣ በውጭና በአገር ውስጥ ካሉ አጋሮቻችን ጋር በመተባበር በመሰረታዊ ደረጃ የመማር ማስተማሩን ሂደት ለማስቀጠል፣ ባለፉት 3 ወራት ሌት ተቀን ሰርተን ተሳክቶልናል፡፡ ተሳክቶልናል ስንል ተቋሙ አገግሟል ማለት እንዳልሆነ ግን በደንብ መታወቅ አለበት፡፡ ይህን ያህል ሀብት የወደመበት ተቋም በ3 ወር ጊዜ ውስጥ መልሶ ያንን ሀብት ማግኘት አይችልም፡፡ እዚህ ላይ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዳይወሰድ በአንፅኦት መግለፅ ስላለብኝ ነው፡፡ ነገር ግን ለምሳሌ የኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎች እንደሚታወቀው ቦርዲንግ ዩኒቨርስቲዎች ናቸው፡፡ መኝታ፣ህክምና እና ምግብ እያቀረብን ነው ልጆቹን የምናስተምራቸው፡፡ ስለዚህ የመማር ማስተማሩን ሂደት ለማስቀጠል የመጀመሪያ ተግባራችን የነበረው የተማሪዎችን መኖሪያ፣ካፍቴሪያና ክሊኒኩን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ስራ ማስገባት ነው፡፡ ለዚህም አንድ ትልቅ ማርሺያል ፕላን አዘጋጅተናል። ይህ ማርሺያል ፕላን ሶስት ትልልቅና መሰረታዊ አካላቶች አሉት፡፡ የመጀመሪያው አካል ተቋሙን መልሶ ስራ ማስጀመር ነው- “ሪከቨሪ” የምንለው ማለቴ ነው፡፡ በትልቁ ማርሺያል ፕላን ውስጥ ሪከቨሪ ፕላን የምንለው አካል ማለት ነው፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የተቋሙን አካላት መልሶ መጠገንና መገንባት ወይም “ሪኮንስትራክሽን ፕላን” የምንለው አለ፡፡ በሶስተኛ ደረጃ ምናልባትም ይህንን ወራሪ ሀይል ለማሳፈር እንደገና የመጣውን መከራ ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር የ”Re innovation” እቅድ አለን። ተቋሙን ዘመኑን በሚዋጅ መልኩ መልሶ የማቋቋም እቅድ አለን ማለት ነው። ከዚህ አንጻር አሁን እየሰራን ያለነው የመጀመሪያውን ክፍል Recovery የምንለውን ነው። በተለይ የእናንተን ጋዜጣ የሚከታተል ህዝብ እንዲገነዘበውና በአፅንኦት እንዲያየው የምንፈልገው ጉዳይ፣ ተቋሙ ስራ ጀምሯል ማለት፣ በማርሻል እቅዳችን ገና እያገገምን ነው እንጂ መልሶ ግንባታው (Reconstruction) እና የ Reinnovation ሥራው ገና አለመጀመሩን ነው። የውድመቱ መጠን የሚታየውና ገና ብዙና ከፍተኛ አቅም የሚጠይቀው የመልሶ ግንባታውና የሪኢኖቬሽኑ ስራ ይሆናል ማለት ነው። ይህንን ደጋግሜ ህዝቡ እንዲያጤነው የምፈልገው፣ መንግስትም ትኩረት እዲሰጠው የምንሻው ተቋሙ ሀብቱ ሁሉ ወድሞበት በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ማስተማር ገባ ሲባል፣ ጉዳቱን ቀለል አድርጎ የማየት ነገር እንዳይመጣና የተሳሳተ ግንዛቤ እንዳይወሰድ ግልጽ ለማድረግ  ነው።
በአጠቃላይ ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ ከዚህ ሰቆቃና መከራ ለመውጣት ከፍተኛ እንቅስቃሴ አድርገናል። በተለይ የዩኒቨርስቲያችን ማህበረሰብ፣ አመራር፣ ቦርዱና ትምህርት ሚኒስቴር በመነጋገር፣ ሀብት ወደ ዩኒቨርስቲያችን አንቀሳቅሰን፣ የመማር ማስተማር ሂደቱን በፍጥነት ጀምረናል። እናንተም በተገኛችሁበት የተማሪዎችን የእንኳን ደህና መጣችሁ መርሃ ግብር አካሂደናል።
ሀብት የማሰባሰቡን ስራ ገና ቀደም ብለን ጠንከር ባለ ሁኔታ ነበር የጀመርነው። ለዚህም አራት ኮሚቴዎችን አቋቁመን፣ አራት የተለያየ ስራ እንዲሰሩ ነበር ያደረግነው። የመጀመሪያው ኮሚቴ፣ የጥናትና ምርምር ተቋማትንና የሙያ ማህበራትን ትኩረት አድርገው፣ ከዩኒቨርስያችን ጋር እንዲሰሩና ካላቸው ሀብት የተወሰነውን ወደ እኛ ፈሰስ እንዲደርጉ ማድረግ ነበር።
ይሄ ኮሚቴ በጣም ብዙ እርቀት ተጉዟል። የግልንም ሆነ የመንግስትን፣ አገር አቀፍም ሆነ ዓለም አቀፍ ተቋማትን በማነጋገር ብዙ ስራ ተሰርቷል።  በዚህም ወደ 70 ያህል ተቋማትን ደርሰናል። ከነዚህ መሃል የተወሰኑት ሀብት ወደኛ ማምጣት ጀምረዋል።
ሁለተኛው ኮሚቴ፣ የትምህርት ተቋማትን  ብቻ ትኩረት አድርጎ ሀብት የሚያሰባስብ ነው። ይህ በትምህርት ሚኒስቴርም 13 ያህል ዩኒቨርስቲዎች፤ ከዩኒቨርስቲያችን ጋር እንዲሰሩ በቀጥታ ሪኮመንዴሽን ተሰጥቷቸው፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ ጅማ ዩኒቨርስቲ፣ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ፣ አምቦ ዩኒቨርስቲ እና ሌሎችም 13 ዩኒቨርስቲዎች፣ ዩኒቨርስቲያችንን  መልሶ በማቋቋም ሂደት ውስጥ ካላቸው ሀብት ላይ ድጋፍ እንዲያደርጉ፣ አቅጣጫ ተቀምጦ የተወሰኑት ሀብት ማምጣት ጀምረዋል።
በሶስተኛ ደረጃ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩልሽ፣ ኮምቦልቻ ቴክሎጂ ኢኒስቲትዩት፣ ቴክሎጂን እንደ ልህቀት ማዕከል አድርጎ የሚሰራ ተቋም በመሆኑ፣ ለዚያ የሚሆን ሀብት ማግኘት የምንችለው በሀገሪቱ ከሚገኙ የተክኖሎጂ ተቋማት፣ ኢንዱስትሪዎችና የአገልግሎት ዘርፉን ከሚመሩት ተቋማት ነው በሚል ይህንን ዘርፍ ብቻ ትኩረት አድርጎ ሀብት የሚያመጣ ራሱን የቻለ ኮሚቴ አለን። ይህም ኮሚቴ ጥረት እያደረገ ሲሆን  በምንፈልገው ደረጃም ባይሆን፣ መጠነኛ ሀብት እየመጣ ነው። ለምሳሌ ኮምፒዩተሮች፣ ሰርቨሮችና መሰል ሀብቶች እየመጡ ነው።
ሌላው የወሎና የኢትዮጵያውያንን በአጠቃላይ በውጭ አገር በማንቀሳቀስ ውጪ ሀገር ሀብት ወደኛ የሚያመጣ የወሎ ዩኒቨርስቲ አድቫይዘሪ ካውንስል፣ በአሜሪካ ቀደም ብለን አቋቁመን ስለነበር እነሱ ደግሞ ይሄኛውን ስራ ትኩረት አድርገው ይሰራሉ ማለት ነው። ከዚያ ባለፈ ግለሰብ ቢሆኑም እንደ ተቋም የምንቆጥራቸውና ከዚህ ቀደም ከዩኒቨርስያችን ጋር ይሰሩ የነበሩትን ግለሰቦች በመፈለግ ፕሮፖዛል እያቀረብን፣ ብዙ ቃል ተገብቶልናል። በእርግጥ እስካሁን ይህ ተደርጎልናል ባንልም፣ በሂደት ቃል የተገቡልን ነገሮች እንደሚፈጽሙልን እምነት አለን።
በዚህ እንቅስቃሴያችን ወሎ በጠቅላላው ያሉት የትምህርትና የህክምና ተቋማት አብረው ስለወደሙ ስለ ዩኒቨርስቲያችን ፕሮፖዛል ስንጽፍ፣ እግረ መንገዳችንን ስለህክምና ተቋሞቻችንና፣ ስለ ት/ቤቶቻችን አብረን እየጻፍን በተለይ ከደሴና ከቦሩ ሆስፒታሎች ጋር አብረን የምንሰራ እንደመሆኑ፣ እነዚህንም ሆስፒታሎች ለማቋቋም በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉ ግለሰቦች ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ለደሴና ለቦሩ ሆስፒታሎች የሚሆኑ የቁሳቁስ ግብአቶችን፣ የሆስፒታል አልጋዎችን፣ በቅርቡ ከውጪ ለማስቀመጣት ከፍተኛ ጥረት እያደረግን ነው ያለነው።  ይህም እንደሚሳካ እምነት አለን። ያን ጊዜም በደንብ ይፋ የምናደርገው ይሆናል። አሁን ባለን ጠንካራ እንቅስቃሴ ሀገራችን ሰላም ከሆነችና መረጋጋቱ በዚሁ ከቀጠለ በእርግጠኝነት ሆስፒታሎቻችንም ሆነ ዩኒቨርስቲያችንን  ከትላንቱ የተሻለ የምናደርግበት  ዕድል ጭምር አድርገን ነው የያዝነው። ይህም እንደሚሳካ እናምናለን።
ዩኒቨርስቲው በፍጥነት እንዲያገግምና በሙሉ አቅሙ ስራ እንዲጀምር የገንዘብ ሚኒስቴርም ሆነ ትምህርት ሚኒስቴር  ያደረጉላችሁ ድጋፍ የለም?
እስካሁን በውጪና በሀገር ውስጥ በምናደርገው እንቅስቃሴ የምናገኘው ሀብት የውስጥ ፋሲሊቲዎቻችንን ለማሟላት የሚውል እንጂ ከዚያ ያለፈ አይሆንም። መስረታዊው የተቋማችን መልሶ የመገንባት ስራ፣ በመንግስት ሀብትና በጀት የሚመራ ነው። ስለዚህ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነው በገንዘብ ሚኒስትር የሚመራው የሚኒስቴሮች ምክር ቤት አባላት ዩኒቨርስቲውን መጥተው ጎብኝተው፣ የጉዳት መጠኑንም ተመልክተዋል። ከዚህ በኋላ እኛ በምናቀርበው ዕቅድ መሰረት፤  12 ቢሊዮን ብሩን በአንድ ጊዜ ይሰጡናል ብለን ባንጠብቅም፣ ነገር ግን በየዓመቱ የሚገባውን ያህል የበጀት ድጎማ ያደርጋሉ ብለን እናስባለን። አሁን ያለንን በጀት በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ተጠቅመን ስለማንጨርስ እያዘዋወርን እንድንጠቀም ይሁንታ ሰጥተውን፣ የጥገናው ስራ በፍጥነት የተካሄደልን በእነሱ ትልቅ ድጋፍም ጭምር ነው። የተጨማሪ በጀት ጥያቄዎችንም ከወዲሁ እያስያዝን ነው ያለነው። ፕሮጀክቶችንም ለምሳሌ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መንታ ህንጻዎች ሙሉ በሙሉ ስለወደሙ በነዚህ ህንጻዎች ፋንታ የሚገነቡትን በአማካሪዎቻችን አስጠንተን እያቀረብን ነው። ስለዚህ እነሱ ኮድ ወጥቶላቸውና ተመዝግበው ፕሮጀክት ይሆናሉ የሚል እምነት አለኝ።
ሌላው የመንግስት ግዢና ንብረት ባለስልጣን ከሁሉም  የፌደራል ተቋማት ቀደም ብሎ በተለይ ተቋማችን መልሶ እንዲያገግም፣ የግዢ ስርዓቱ ላይ የተለዩ መንገዶችን በማበጀት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተርም ተቋሙን በአካል መጥተው በመጎብኘት ካላቸው ሀብት ላይ በሁለት መኪና ፈርኒቸሮችን ጭነው በመምጣት ጭምር አይዟችሁ ብለውናል። የግዢ ስርዓቱም ቀላል እንዲሆንልን በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተውልናል። በዚህ አጋጣሚ ባስልጣኑንና አመራሮቹን ማመስገን እፈልጋለሁ። አየሽ የግዢ ሂደቱን ከመደበኛው አካሄድ በልዩነት እድል ሰጥተውን ገዛዝተን ነው ወደስራ የገባነው። ይህ ቀላል ድጋፍ አይደለም። ሌሎች ሚኒስትር መስሪያ ቤቶችም ድጋፎቻቸውን በቅርቡ ያመጣሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ያመጡም አሉ።
 ከነዚህም ማዕድን ሚኒስቴር፣ ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ልከውልናል። አጠቃላይ የተደረገልንን ድጋፍ ወደፊት በአደባባይ የምናመሰግን ይሆናል። ይሄ ሁሉ እንዳለ ሆኖ ግንባር ቀደም ሚናው ግን የመንግስት በጀት መሆኑን ማስገንዘብ እንፈልጋለን።
አካባቢው ላይ ተከስቶ ከነበረው ጦርነትና ከተቋሙ መውደም ጋር ተያይዞ ለተማሪዎች ጥሪ ስታደርጉ፣ በተማሪዎችም ሆነ በወላጆቻቸው በኩል “አይ እንፈራን፣ ልጆቻችንን አንልክም፣ ተመልሶ ችግር ቢፈጠርስ” የሚል ፍርሃትና ስጋት አልገጠማችሁም? ጥሪ ከተደረገላቸው ተማዎሪችስ ምን ያህሉ ጥሪውን ተቀብለው ገብተዋል?
ትክክል ነው። የጉዳት መጠናችንን በሀገር ውስጥም በውጪም ሚዲያዎች ስናስተላልፍ ጉዳዩ ሁለት ስለት ሊይዝ እንደሚችል ይገባን ነበር። በመጀመሪያ የጉዳት መጠኑን ባሳየንና ባስገነዘብን ቁጥር መልሶ የመከፈቱና ስራ የመጀመሩ ጉዳይ ተስፋ አስቆራጭ እንዳይመስል ጎን ለጎን በተለይ ሚዲያ ላይ የተጠቀምነው ነገር፣ ተማሪዎቻችንን ከመጥራታችን በፊት የተለያዩ የሀገር ውስጥ ሚዲዎችን በመጋበዝ ካፌያችን ምግብ አብስሎ ማቅረብ እንደሚችል ሰርተን፣ የዩኒቨርስቲው መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ካፌ ውስጥ ቁጭ ብለው እየተመገቡ ለሚዲያ አሳይተናል። በዚህም አብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል ወሎ ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ምግብ ቤት ተማሪን ለመመገብ በሚችልበት አቅም ላይ ነው የሚል ግንዛቤ ተወሰደ። አሁንም ምግብ ቤቱ ዘመናዊ ዳቦ መጋገሪያ፣ የሻይ ማፍያ ማሽኖችንና ሌሎችም አሉን ማለት አንችልም፡፡ ነገር ግን ባለን ሃብት ተማሪዎቻችንን መመገብ በምንችልበት ደረጃ ላይ እንገኛለን። ሌላው የተማሪዎች መኖሪያ ጉዳይ ነው። አብዛኞቹ በጦርነቱ በር፣ መስኮትና ጣሪያቸው ወድሞ ስለነበር፣ እነዛን በሮች ጣሪያዎችና የኮሪደር በሮች በተሻለ ሁኔታ ሰርተን አጠናቀን በሚዲያ  በማሳየት ተማሪዎቻችንና ወላጆቻቸው በእኛ ላይ እምነት እንዲኖራቸው በሰራነው ስራ አብዛኞቹ ተማሪዎቻችን መጥተውልናል። የትራንስፖርት ችግር እንዳለና በተለያየ አካባቢ ያሉት ተማሪዎችም ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ አለ ባሉት ችግር መሰረት ሊዘገዩ እንደሚችሉ፣ የነገሩን ተማሪዎች በመኖራቸው የቅጣት ጊዜውን በሁለት ቀን አራዝመን እስከ መጋቢት 16 ለመቀበል ባደረግነው ዝግጅት፣ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ እየገቡ ይገኛሉ። ወደ ስብሰባና ስልጠናው የገባውን የተማሪ ብዛት አይተሻል። ስብሰባውም የሳይኮሶሻል ጉዳቱ ከቁሳዊ ጉዳቱ ባስ ያለ ሊሆን ስለሚችል የስነ-ልቦና ባለሙያዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የዩኒቨርስቲው አመራሮች የምክር፣ የስልጠና የስነልቦና ግንባታና የመመሪያ ደንቦችን ትግበራ በተመለከተ አስፈላጊው አገልግሎት ተሰጥቷቸው መጋቢት 15 ቀን 2014 ዓ.ም በተሳካ ሁኔታ የማስተማርር ስራችንን ጀምረናል። ይህ እንዲሆን ሌት ተቀን የሰሩ የዩኒቨርስቲውን ማህረሰብ፣ የአስተዳደር ሰራተኞች፣ የመንግስት አካላት፣ ተማሪዎቹንም ጭምር ማመስገን እንፈልጋለን። ቀጣይ የተቋሙን ሂደቶችም እንዲሁ ለሚዲያ የምንገልጽ ይሆናል። ጉዳዩ ይመለከተናል ብላችሁ እዚህ ድረስ መጥታሁ ከጎናችን ስለቆማችሁ፣ እናንተንም ማመስገን እፈለጋለሁ።

Read 5824 times