Saturday, 02 April 2022 11:55

የቻይናው ወጣት ቢሊዬነር

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 “መቼም ቢሆን ህልሜን እንጂ ሌላ ነገር ሰርቼ አላውቅም”

             በወጣትነቱ ምርጥ መካኒካል ኢንጂነሪንግ የመሆን ህልም ነበረው - ቻይናዊው ዲንግ ሊ። በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ የተከሰቱትን ታላላቅ ሳይንቲስቶች፣ እነ ቶማስ ኤዲሰንና አልበርት አንስታይንን ሲያደንቃቸው ለጉድ ነው። ገና የአስራ ሶስት ዓመት ልጅ ሳለ ለኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ልዩ ፍቅርና ዝንባሌ ነበረው። በአስራ ስድስት ዓመቱ የሬዲዮ የተለያዩ ክፍሎችን የመገጣጠም ችሎታ አዳብሯል።
በኮሌጅ ያሳለፋቸው አራት ዓመታት የዲንግ ወርቃማ ጊዜያት ሲሆኑ፤የቀለም ትምህርቱን ከማጥናት ይልቅ በኤሌክትሮኒክስ ዙሪያ የተፃፉ 300ሺ መፃሕፍት ከነበራቸው የት/ቤቱ ቤተ-መጻሕፍት የሚያገኛቸው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (IT) መፃሕፍትን ማንበብ ያስደስተው ነበር። በሁሉም ጉዳዮች ላይ የራሱ ሃሳብ እንደነበረው የሚያስታውሱት የመመረቂያ ፅሁፍ  አማካሪው ፌንግ ሊን፤ ዲንግ ከሌሎች ተማሪዎች የተለየ እንደነበር ይናገራሉ - ብዙ ጊዜ እንግዳ የሆኑ ጥያቄዎችን እንደሚያነሳ በመጥቀስ። ዲንግ ከኮሌጅ የተማረው ነገር ቢኖር ከልብ ማጥናትን ሲሆን አሁንም ድረስ እስከ እኩለ ሌሊት ከማጥናት አላረፈም። ከኮሌጅ ገና ሳይመረቅ ሶፍትዌር በመስራት ከዘመነኞቹ እንደሚልቅ ያስመሰከረ ተማሪም ነበር። ህልሙን እውን ለማድረግ ከቻይና ቴሌኮም ሥራው ብቻ ሳይሆን የውጭ አገር ድጋፍ ከሚደረግለትና ጥሩ ደሞዝ ከሚከፍለው አንድ ተቋምም በገዛ ፈቃዱ ለቋል።
ዲንግ ሊ Net Ease የተሰኘውን የኢንተርትኔት ቢዝነስ በጁን 1997 ዓ.ም ሲጀምር ከአስራ ሁለት የማይበልጡ ሠራተኞች ነበሩት፤ ይሁንና ሥራውን በማስፋፋት በአጭር ጊዜ ውስጥ የሠራተኞቹን ቁጥር 300 ማድረስ ችሏል።
በመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት ገንዘቡንና ጉልበቱን የኢንተርኔት ሶፍትዌር ፈጠራ ላይ በማዋል ሲሰራ የቆየው ዲንግ; በቻይና በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን ባለሁለት ቋንቋ የኢ-ሜይል ሲስተም ሥራ ላይ ለማዋል የቻለ ትጉህ ሰው ነው። የዚህ ኢ-ሜይል ሲስተም መተዋወቅ በቻይና ኢንተርኔት እንዲለመድና እንዲስፋፋ ምክንያት እንደሆነ ብዙዎች ያወሳሉ። በእርግጥ ዲንግ የቢዝነሱን ማደግና መውደቅ በወረቀት ላይ ማስላት አይወድም። ሆኖም የቢዝነሱ ስኬት በብርሀን ፍጥነት የሚለካ እስኪባል ድረስ እጅግ አስደናቂ ነው።
በአንድ ዓመት ከግማሽ ብቻ የኩባንያው የአንድ አረቦን መሸጫ ዋጋ ከዘጠና ሳንቲም ወደ ሠባ ዶላር ተተኩሷል። 2001 ዓ.ም ለዲንግ ኩባንያ ክፉ ጊዜ ነበር። በ2000 ዓ.ም የተሳሳተ የገቢ ሪፖርት አቅርቧል የሚል ወሬ ስለተሰራጨበት በሩ ለደንበኞች ክፍት አልነበረም። በዚህም ሳቢያ የአንድ አረቦን መሸጫ ዋጋ ሲጀምር እንደነበረው ወደ ዘጠና ሳንቲም ለመውረድ ተገደደ።
በእርግጥ ዲንግ የቻይና ባለጸጋ እሆናለሁ ብሎ አስቦ አያውቅም። የNet Ease ኩባንያ ስኬትም ሆነ ውጣ ውረዱን ሲናገር አንዳችም በስሜት መዋጥም ሆነ መጥለቅለቅ አይስተዋልበትም። አንዳንዶች ዕድል ለስኬት እንዳበቃው ቢናገሩም፣ እሱ በዚህ ረገድ ከሌሎች የተለየ አቋም አለው።
በኢንጅነሪንግ የባችለር ዲግሪውን ባገኘበትና በቼንግዱ ግዛት በሚገኘው በቻይና የኤሌክትሮኒክ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ለተማሪዎች ንግግር ሲያደርግ፤ “ጠንካራ መሆን የሚፈልጉ ሰዎች ሁልጊዜም መልካም  አጋጣሚዎችን ይፈጥራሉ፤ ብልሆቹ መልካም አጋጣሚዎች እንዳያመልጧቸው በጥንቃቄ ሲጠቀሙባቸው፣ ራሳቸውን ደካማ አድርገው የሚያስቡ ደግሞ መልካም አጋጣሚዎች እስኪፈጠሩላቸው ይጠብቃሉ” ብሏል።
የቢዝነስ ጨዋታው አዝናኝም አስተማሪም እንደሚሆን ተስፋ የሚያደርገው ዲንግ፤ በመጪዎቹ አስርት ዓመታት በቻይና አስደናቂ የኢንተርኔት ዕድገት እንደሚታይ ፅኑ ዕምነት አለው፤ በተለይ በኤሌክትሮኒክስ ቢዝነስ።
ገንዘብ የማይሰሩ ቢዝነሶች በየቦታው እንዳሉ የሚናገረው ዲንግ፤ በተጨባጭ ግን ገንዘብ የማይሰራ ቢዝነስ የሚባል ነገር እንደሌለ የራሱን ኩባንያ አሰራር በመጥቀስ ያስረዳል፡- “የኔ ግብ ቀላልና ግልፅ ነው….”ይላል፤ “Net Ease …. የላቀ አገልግሎት እንዲሰጥ የምችለውን ሁሉ መስራት”።
ለውጭ ተመልካች ኩባንያው ፈፅሞ የስኬት ተምሳሌት ለመሰኘት የሚበቃ አይደለም። ለምን ቢባል ብዙ በዓይን የሚታይ ነገር ስለሌለው። በዲንግ ልብ ውስጥ ያሉትን ትላልቅ ህልሞች የሚያውቀው ግን ፈጣሪና ራሱ  ባለቤቱ ብቻ ነው። ይኼ የቻይና ቢሊኒየር ስላቋቋመው ኩባንያ ሲናገር፤ ሥራችን ሃላፊነትን መወጣት ነው፤ ይላል። “ለኢንቨስተሮች፤ ለደንበኞች፣ ለተጠቃሚዎች፣ ለሰራተኞችና ለኢንተርኔት… ያለብንን ሃላፊነት መወጣት።”
ዲንግ በዕድሜው ወጣት ቢሆንም ከህይወት አንድ ነገር ተምሯል - መልካምነትን። የአንድ ቢሊዮን ዶላር ሃብት ለዚህ ባለፀጋ ምንም ማለት አይደለም። የቻይና ባለፀጋ መሰኘቱም ከባልንጀሮቹ ጋር የታሸገ ምግብ  ከመካፈል አላገደውም።
“ሃብት ማለት፡- ለእኔ ሁለት ነገሮች ማለት ነው፤ ገንዘብና ተሰጥኦ። ዛሬ በእጄ ላይ ያለው የትናንት ውጤት ነው፤አዕምሮዬ ውስጥ ያለው ግን የወደፊቱን ዓለም ይፈጥራል” ይላል።
ለዚህም ይመስላል ዲንግ የሰራተኞቹን ዕውቀትና ሙያ ለማሻሻል በየጊዜው ሥልጠናዎች የሚሰጠው። ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች አዳዲስ ምሩቆችን እየለመለመ የሚቀጥረው ወጣቱ ቢሊኒየር፤ የኩባንያውን ብቃት ለማሳደግ ከሁለት ሺህ እስከ ሶስት ሺህ የሚደርሱ ሰራተኞችን የመቅጠር ዕቅድ አለው።
የዛሬው ባለፀጋ ዲንግ የዩኒቨርስቲ የተማሪነት ዘመኑ ሁሌም እንደሚናፍቀው ይናገራል - በተለይ ደግሞ ቤተ-መፃሕፍቱና በጥያቄዎች የታጨቀው ጭንቅላቱ።
“አንዳንዴ ድክም ሲለኝ ደጉ ጊዜ ይለኛል፤ እናም ኢንተርኔት አካባቢ አንዣብባለሁ” የሚለው ዲንግ፤ “መቼም ቢሆን ግን ህልሜን እንጂ ሌላ ነገር ሰርቼ አላውቅም” ይላል፡፡
የዚህን ቻይናዊ ሥራ ፈጣሪ የስኬት ታሪክ አስመልክቶ የቅርብ ወዳጁ በሰጠው አስተያየት፡- “ባህሪውን እወድለታለሁ፤ እንደ ንግድ ሰው የላቀና ብልጣብልጥ ነው፤ ግን ደግሞ የህጻን ልጅ የዋህ ልብ አለው።” ብሏል።
("ታላላቅ ህልሞች፤ የሚሊዬነሮች የስኬት ጉዞ" ከተሰኘው መጽሐፍ የተወሰደ)

Read 1510 times