Saturday, 02 April 2022 12:06

ኦስካርን ያደበዘዘው ያልተጠበቀ ክስተት!

Written by  ትግስቱ በለጠ
Rate this item
(0 votes)

 ባለፈው እሁድ ምሽት በካሊፎርኒያ፣ ቤቨርሊሂልስ የተካሄደው 94ኛው የኦስካር ሽልማት ሥነሥርዓት፣ እንደ ወትሮው የደመቀና ያሸበረቀ ነበር ማለት ይቻላል። "ሁሉም ዝግጁ፤ ሁሉም ስንዱ" ነበር፡፡ ዓመታዊውን የኦስካር ሽልማት የሚያደበዝዝ ነገር የተከሰተው ሥነሥርዓቱ ከተጀመረ በኋላ ነው፡፡ ድንገት በአዳራሹ የታደሙትን ዝነኞች ብቻ ሳይሆን መላውን ዓለም ያስደነገጠ ክስተት ተፈጸመ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡-
በዶክመንታሪ ፊልም ዘርፍ የኦስካር አሸናፊን ሊያስተዋውቅ ወደ መድረክ ብቅ ያለው ኮሜዲያን ክሪስ ሮክ፤ እንደ ወትሮው ሁሉ በአዳራሹ ውስጥ በታደሙ የሆሊውድ ዝነኞች ላይ መቀለድ ጀመረ፡፡ አዳራሽ ሙሉ ታዳሚ መሳቅና መዝናናት ላይ ነበር፡፡
ክሪስ ሮክ፣ ቀልዱን የዝነኛው ተዋናይ ዊል ስሚዝ ሚስት የሆነችው ጄዳ ፒንኬት ስሚዝ ላይ ሰነዘረ፡፡ ቀልዱ በበሽታ ሳቢያ ካጣችው የራስ ጸጉሯ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ መጀመሪያ ላይ ዊል ስሚዝ  በሚስቱ ላይ በተቀለደው ቀልድ ከሌላው ታዳሚ ጋር ከልቡ ሲስቅ ይታያል - ያውም እያጨበጨበ፡፡ ለጄዳ ፒንኬት ስሚዝ ግን ቀልዱ የሚያስቅ አልነበረም፤ ፊት  የሚያስጨፈግግ እንጂ፡፡
ዊል ስሚዝ በዚያው ቅጽበት የሚስቱን ስሜት ያጤነ ይመስላል፡፡ በመሳቁም ጭምር ሳይጸጸት  አልቀረም፡፡ ከአፍታ በኋላ እንደ አራስ ነብር ተቆጥቶ፣ እየተንደረደረ መድረኩን አቋርጦ፣ ወደ ኮሜዲያኑ አመራ። አጠገቡ ሲደርስም  ከቡጢ የሚስተካከል  ከባድ ጥፊ አቀመሰው። ወደ መቀመጫው ከተመለሰም በኋላ ዝም አላለም፤ እያምባረቀ ነውር በሆነ ቋንቋ ተሳደበ፡፡ ("ከዚህ በኋላ ስለ ሚስቴ ትንፍሽ ብትል" በሚል ዓይነት!)
ይኼ ሁሉ ሲሆን ግን ከዝነኛው ኮሜዲያን ክሪስ ሮክ የአጸፋ ምላሽ አልተሰጠም። ሁኔታውን በትዕግስትና በእርጋታ ነው ለማሳለፍ የሞከረው፡፡ "ከበሰለ አዋቂ ሰው የሚጠበቅ ምላሽ!" በማለት ብዙዎች አድናቆታቸውን ቸረውታል፡፡ ድንገተኛ ጥፊ ባሳረፈበት ዊል ስሚዝ ላይ ክስ መመስረት ይፈልግ እንደሆነ በፖሊስ የተጠየቀው ኮሜዲያኑ፤ እንደማይፈልግ ነው የተናገረው፡፡
አካዳሚ አዋርድ በበኩሉ፤ በእሁድ ምሽቱ ክስተት ላይ መደበኛ ምርመራ መጀመሩን  አስታውቋል፡፡ "ከአስደንጋጩ ክስተት በኋላ ዊል ስሚዝ ከአዳራሹ  እንዲወጣ ቢጠየቅም ፈቃደኛ አልሆነም፡፡" ብሏል፤ አካዳሚው በመግለጫው፡፡
የሆሊውዱ ልዕለ ኮከብ ዊል ስሚዝ፣ የአካዳሚውን የሥነምግባር ደንብ በመጣሱ የዲሲፕሊን እርምጃ እንደሚጠብቀው ያመለከተው አካዳሚው፤ አፕሪል 18 በሚካሄደው ቀጣዩ የአካዳሚው የቦርድ ስብስባ ላይ የሚወሰደው እርምጃ ሊወሰን እንደሚችል ጠቁሟል፡፡ የዲስፕሊን እርምጃው ከአካዳሚ አዋርድ  መታገድ፣ መባረር ወይም ሌሎች ቅጣቶችን እንደሚያካትት ታውቋል፡፡   
ዊል ስሚዝ ኮሜዲያኑን በጥፊ ከመታው ከአንድ ሰዓት በኋላ "ኪንግ ሪቻርድ" በተሰኘው ፊልም ላይ ባሳየው የትወና ብቃት "የዓመቱ ምርጥ ተዋናይ" ተብሎ የመጀመሪያውን ኦስካር ተሸልሟል፡፡ ፊልሙ የቴኒስ ክዋክብቱ የሰሪ እና ቬነስ ዊሊያምስ አባት፣ ሪቻርድ ዊሊያምስን ታሪክ የሚዘክር ነው ተብሏል፡፡
ዊል ስሚዝ የኦስካር ሽልማቱን ከተቀበለ በኋላ ባደረገው ከተለመደው ረዘም ያለ በለቅሶ የታጀበ ንግግር፤ አካዳሚውን፣ እጩ ተሸላሚዎችንና የሥነሥርዓቱን ታዳሚዎች በሙሉ ይቅርታ ጠይቋል፡፡ በዚህች ቅጽበት ይቅርታ የተነፈገው በጥፊ የተመታው ክሪስ ሮክ ብቻ ነበር፡፡ በርግጥ በነጋታው ሰኞ ዕለት፣ ስሚዝ በኢንስታግራም ገጹ ክሪስ ሮክን በይፋ ይቅርታ ጠይቋል፡፡
በሌላ በኩል፤ ከእሁዱ ክስተት በኋላ የክሪስ ሮክን የኮሜዲ ሥራ ለማየት ትኬት የሚቆርጡ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ መጨመሩ ታውቋል። ኮሜዲያኑ ባለፈው ወር ከሸጠው በእጅጉ የሚልቅ ትኬት በአንድ ሌሊት ሸጧል ተብሏል፡፡ 46 ዶላር የነበረው የአንድ ትኬት ዋጋም፣ ወደ 411 ዶላር ማሻቀቡ ተጠቁሟል።
በኦስካር ሽልማት ሥነሥርዓት ላይ የተፈጠረውን አስደንጋጭ ክስተት ተከትሎ፣ የሆሊውድ ዝነኞችና ታዋቂ ግለሰቦች በማህበራዊ ድረ-ገጻቸው ላይ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል - የዊል ስሚዝን ድርጊት በመደገፍና በማውገዝ፡፡ ጥቂቶቹን ተርጉመን እንዲህ አቅርበነዋል፡፡
***
“ክሪስ ሮክ ቀልዱን ሰነዘረ። ዊል ስሚዝ ከቡጢ የማይተናነስ ጥፊ አቀመሰው። እዚህ ጋ መፈተሽ ያለበት አካላዊ ድርጊት ብቻ አይደለም፡፡ ዓለም  ፀጉሯ በረገፈ ሴት በትህትና መሳቁ፣ በዓለም መድረክም ማሾፊያ መሆኗ ጭምር ነው። የዛሬው ምሽት ሰዎች በቀለዱት ቀልድ መመታት የሚጀምሩበት መሆን የለበትም፤ ይልቁንም በሰዎች የጤና ችግር ማሾፍ የሚቆምበት ሊሆን ይገባዋል።”
(`The Good Place` ፊልም ተዋናይ ጀሚላ ጃሚል)
"የድርጊቱን ዝርዝር ባናውቅም ራስን ለመከላከል ካልሆነ በስተቀር መማታትን አንደግፍም፡፡"
(ሪቻርድ ዊሊያምስ፤ የቴኒስ ኮከቧ ሰሪና ዊሊያምስ አባት)
“አንድ ነገር ልንገራችሁ፤ መድረክ ላይ ወጥቶ ኮሜዲያን ላይ የአካል ጥቃት ማድረስ ሲበዛ መጥፎ ልምምድ ነው። አሁንም ሁላችንም ሊያስፈራን የሚገባው በኮሜዲ ክለቦችና ቴአትር ቤቶች ቀጣዩ ዊል ስሚዝ ለመሆን የሚሻው ማነው የሚለው  ነው፡፡”
(ኮሜዲያን ኬቲ ግሪፊን)
“እኔ ብሆን ዛሬ ጠዋት በዊል ስሚዝ ላይ የ200 ሚ. ዶላር ክስ መመሥረቴን አስታውቅ ነበር፡፡ ያ ቪዲዮ እኮ ለዝንተ ዓለም ይኖራል፤ በሁሉም ሥፍራ ይገኛል፡፡ ያ የማዋረድ ተግባር ለረዥም ጊዜ ሳይረሳ የሚዘልቅ ነው፡፡”
(ኮሜዲያን ጄም ኬሪ)
"በትላንትናው ምሽት የአካዳሚ ሽልማት ላይ ያሳየሁት ባህርይ ተቀባይነት የሌለውና ይቅር የማይባል  ነው፡፡"
(ዊል ስሚዝ፤ ተዋናይና የኦስካር አሸናፊ)
“አንተን - ክሪስን በይፋ ይቅርታ ልጠይቅህ እወዳለሁ፤ ከመስመር ወጥቼ ነበር፤ ተሳስቼአለሁም። በሰራሁት አፍሬአለሁ፤ ድርጊቴ መሆን የምፈልገውን ሰው አመላካች አይደለም፡፡ በፍቅርና በደግነት ዓለም ውስጥ ግጭት  ቦታ የለውም።”
(ዊል ስሚዝ፤ተዋናይና የኦስካር አሸናፊ)
“ምናልባት ዓለም ነገርዬው የተከሰተበት መንገድ ላያስደስተው ይችላል፤ ለእኔ ግን እስከዛሬ ያላየሁት ድንቅ ነገር ነው፤ ምክንያቱም አሁንም ለሚስቶቻቸው ፍቅር  ያላቸውና የሚጨነቁ ወንዶች እንዳሉ እንዳምን አድርጎኛል፡፡”
(ቲፋኒ ሃዲሽ፤ Girls Trip ፊልም ላይ ከፒንኬት ስሚዝ ጋር በመሪ ተዋናይነት የተጫወተች)
"ስሚዝ በጣም የተረጋጋና ከሁሉም ጋር ተግባቢ ሰው ነው፤ ቤተሰቡን የሚወድና ለቤተሰቡ ቅድሚያ የሚሰጥ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው እንደዚያ ሲሆን ያየሁት፡፡ በዕድሜ ዘመኑ ለመጀመሪያ ጊዜ!"
 (ካሮሊን ስሚዝ፤ የዊል ስሚዝ እናት)


Read 2243 times