Wednesday, 06 April 2022 00:00

ተስፋ የተጣለበት የሩስያና ዩክሬን ውይይት ያለ ፍሬ ተቋጭቷል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

     ከዩክሬን ህዝብ 10 በመቶው ወይም ከ4 ሚ. በላይ ሰው ተሰድዷል

            ከ4 ሚሊዮን በላይ ዩክሬናውያንን ለስደት የዳረገውን ጦርነት በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት በሩስያና በዩክሬን ተደራዳሪዎች መካከል ባለፈው ማክሰኞ በቱርክ የተካሄደው ውይይት፣ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ተስፋ ሰጪ ነበር ተብሎ ቢዘገብም፣ ሩስያ ግን ምንም አይነት ውጤት ሳያስገኝ መቋጨቱን አስታውቃለች፡፡
የሩስያ መንግስት ቃል አቀባይ ዲምትሪ ፔስኮቭን ጠቅሶ ዘ ጋርዲያን እንደዘገበው፣ የማክሰኞ ዕለቱ ውይይት እንደ ከዚህ ቀደሞቹ ሁሉ ይህ ነው የሚባል ተጨባጭም ሆነ ተስፋ ሰጪ ውጤት ሳይገኝበት ተጠናቋል፡፡
የሩስያ ጦር ከዩክሬን በገጠመው ያልጠበቀው ከባድ መከላከልና መልሶ ማጥቃት ከፍተኛ ውድመት እየደረሰበት እንደሚገኝና በቁጥጥር ስር ያዋላቸውን አንዳንድ የዩክሬን አካባቢዎች ለመልቀቅና ወታደሮቹን ወደ ቤላሩስና ወደራሱ ግዛቶች በመመለስ መልሶ ለማደራጀት እንደተገደደ አንድ የብሪታኒያ የወታደራዊ ስለላ ተቋም አስታውቋል፡፡
የሩስያ መንግስት የመዲናዋን ኪየቭ ዙሪያ ጨምሮ በሰሜናዊ ዩክሬን የሚያካሂደውን ጦርነት ገታ እንደሚያደርግ ማክሰኞ ዕለት ቢያስታውቅም፣ መዲናዋን ኪዬቭ እና ቼርኔቭን ጨምሮ በአንዳንድ ከተሞች የአየር ድብደባውን አጠናክሮ መቀጠሉ የተነገረ ሲሆን፣ በተለይ በማሪዮፖል እጅግ የከፋ ዘግናኝ ጥፋት መፈጸሙ ተዘግቧል፡፡
ፎክስ ኒውስ በበኩሉ፤ የዩክሬን ጦር ለመጀመሪያ ጊዜ በሩስያ ሉአላዊ ግዛት ላይ ጥቃት መፈጸም መጀመሩን የሚያሳዩ መረጃዎች መገኘታቸውን የዘገበ ሲሆን፣ የሩስያ መንግስት ጥቃት በደረሰባቸው ሁለት የገጠር መንደሮች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መጣሉንና የተወሰኑ ነዋሪዎችን ማስወጣቱንም አክሎ ገልጧል፡፡
የቀድሞው የሩስያ ጠቅላይ ሚኒስትርና ፕሬዚዳንት ዲምትሪ ሜድቬዴቭ በበኩላቸው፤ አገራቸው በጦርነቱ የኒውክሌር ጦር መሳሪያን የምትጠቀመው በሩስያ ላይ የኒውክሌር ሚሳኤል ድብደባ ከተፈጸመ፣ በሩስያ ወይም በአጋሮቿ ላይ ሌሎች የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች ጥቃት ከተፈጸመ፣ የሩስያን የኒውክሌር ተቋማት የሚጎዳ ወሳኝ ጥቃት የሚፈጸም ከሆነና በሩስያና በአጋሮቿ ላይ የህልውና ስጋት የሚፈጥር ወረራ ከተፈጸመ መሆኑን እንዳስታወቁ ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
የሩስያ መንግስት በጦርነቱ የሚያሰልፋቸውን ቅጥር ወታደሮች በሶርያ እየመለመለ እንደሚገኝ የዘገበው ቢቢሲ በበኩሉ፤ በዩክሬን ጦርነት ከጎኑ ተሰልፈው ለሚዋጉ ፈቃደኛ ሶርያውያን በወር ከ5 ሺህ ዶላር በላይ ደመወዝ ለመክፈል፣ በጦርነቱ ለሚሞቱ ሶርያውያን ቅጥር ወታደሮች ቤተሰቦች ደግሞ ተጨማሪ 50 ሺህ ዶላር በካሳ መልክ ለመክፈል ተስማምቶ በጀመረው ምልመላ እስካሁን 200 ያህል የሚሆኑ ሰዎችን መመዝገቡንም አመልክቷል፡፡
ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያንና ስፔንን ጨምሮ 7 የአውሮፓ አገራት ዜጎቻቸው በጦርነቱ ከዩክሬን ጎን ተሰልፈው እንዳይዋጉ ጥሪ በማስተላለፍ ላይ እንደሚገኙና፣ የዩክሬኑ መሪ ለውጭ አገራት በጎ ፈቃደኞች ጥሪ ካቀረቡበት ጊዜ አንስቶ በጦርነቱ ከ20 ሺህ በላይ የተለያዩ የአውሮፓ አገራት ፈቃደኛ ዜጎች ከዩክሬን ጎን ተሰልፈው በመዋጋት ላይ እንደሚገኙ አል አይን ኒውስ ዘግቧል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከሰሞኑ ባወጣው መረጃ፤ ሩስያ ጦርነቱን ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ከዩክሬን የተሰደዱ ሰዎች ብዛት ባለፈው ረቡዕ ከ4 ሚሊዮን ያለፈ ሲሆን ይህም ከአገሪቱ ህዝብ 10 በመቶ ያህል እንደሚሆን ተዘግቧል፡፡
የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ እንዳለው፤ ጦርነቱ እስካሁን ድረስ 1ሺህ 179 ንጹሃን ዩክሬናውያንን ለሞት እንደዳረገ የተረጋገጠ ሲሆን፣ 1ሺህ 860 የሚሆኑ ደግሞ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ባለፈው ቅዳሜ በፖላንድ ያደረጉትን ጉብኝት ሲያጠናቅቁ ባደረጉት ንግግር፣ ነገሩን ከማቀዛቀዝ ይልቅ በእሳት ላይ ነዳጅ ማርከፍከፋቸው  የተነገረ ሲሆን፣ በዲሞክራሲ የሚያምነው አለም ራሱን ለተራዘመ ጦርነት እንዲያዘጋጅ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የሩስያው ፕሬዚዳንት በስልጣን ላይ መቆየት የለባቸውም ሲሉ የተናገሩት ባይደን፤ ይህ አባባላቸውም ያላሰቡት ውዝግብ ውስጥ እንደከተታቸው ተነግሯል። ባይደን ይህን ማለታቸውን ተከትሎ፣ በርካታ ሩስያውያንና ባለስልጣናት በነገሩ ክፉኛ መቆጣታቸውንና የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭም፣ የፕሬዚዳንት ፑቲን ስልጣን የሚወሰነው በመረጧቸው ሩስያውያን እንጂ በአሜሪካው መሪ አይደለም ሲሉ ምላሽ መስጠታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በርካታ አለማቀፍ መገናኛ ብዙሃንም የባይደን ንግግር አሜሪካ በሩስያ የመንግስት ለውጥ እንዲኖር እንደምትፈልግ የሚያሳይ ነው ሲሉ ነገሩን እንዳራገቡትና ዋይት ሃውስም በአስቸኳይ ማስተባበያ መስጠቱን አመልክቷል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ኔዘርላንድ 17 የሩስያ ዲፕሎማቶችን በአፋጣኝ ከግዛቷ እንደምታስወጣ ካስታወቀችበት ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ፣ በሩስያ ዲፕሎማቶች ላይ ሲሰልሉ አግኝተናቸዋል በሚል ተመሳሳይ እርምጃ የሚወስዱ የምዕራባውያን አገራት መንግስታት እየተበራከቱ ሲሆን፣ እስካሁንም ቤልጂየም፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ አየርላንድ በድምሩ 43 የሩስያ ዲፕሎማቶችን ለማባረር መወሰናቸውን ኤአርቲ ኒውስ ዘግቧል፡፡
ፖላንድ ባለፈው ሳምንት በስለላ ስራ ላይ ተሰማርተው አግኝቻቸዋለሁ ያለቻቸውን 45 የሩሲያ ዲፕሎማቶች ማባረሯን ያስታወሰው ዘገባው፤ አሜሪካ፣ ስሎቫኪያ፣ ቡልጋሪያ፣ ኢስቶኒያ፣ ላቲቪያ፣ ሊዩቴኒያና ሞንቴኔግሮም በሩስያ ዲፕሎማቶች ላይ መሰል እርምጃ ከወሰዱ አገራት ተርታ እንደሚሰለፉ አክሎ ገልጧል፡፡


Read 15387 times