Print this page
Saturday, 02 April 2022 12:19

ኦፌኮ በብሔራዊ ምክክሩ ይሳተፍ ይሆን?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

             • አገራዊ ምክክሩ ከሁሉም አቅጣጫ ፍኖተ ካርታ ሊኖረው ይገባል
             • የምክክር ሂደቱ ላይ የሁሉም መተማመንና ቅቡልነት ያስፈልጋል
             • የተቋቋመው የምክክር ኮሚሽን ፈፅሞ ገለልተኛ አይደለም

             ከጸጥታ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ጠቅላላ ጉባኤውን ለማካሄድ ፈጽሞ እንደማይችል ሲገልጽ የቆየው ኦፌኮ፤በመጨረሻ ተሳክቶለት ባለፈው መጋቢት 17 እና 18 ጠቅላላ ጉባኤውን ያካሄደ ሲሆን  በዚህ ጉባኤም ፕ/ር መረራ ጉዲናን በሊቀ መንበርነት፣ አቶ በቀላ ገርባን በተቀዳሚ ም/ሊቀ መንበርነት እንዲሁም አቶ ጃዋር መሃመድን በም/ሊቀ መንበርነት መርጧል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ ከፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ አባል አቶ ሙላቱ ገመቹ ጋር  በጠቅላላ ጉባኤውና በቅርቡ ይጀመራል ተብሎ በሚጠበቀው አገራዊ ምክክሩ ዙሪያ ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡ እነሆ፡-

              ከዚህ ቀደም የፓርቲያችሁን ጠቅላላ ጉባኤ በወቅቱ ማካሄድ እንደምትቸገሩ አስታውቃችሁ ነበር፡፡ ከሰሞኑ ግን ጉባኤውን ማድረግ ችላችኋል፡፡ እስቲ በጉባኤው ያከናወናችሁትን ዋና ዋና ጉዳዮች ይንገሩን?
እኛ ጉባኤውን ያካሄድነው ችግሮች ተቃለውልን፣ ተመችቶን አይደለም። ነገር ግን ምርጫ ቦርድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተነሳ በ1 ወር ጊዜ ውስጥ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርጉ የሚያስገድድ መመሪያ አወጣ። ይሄ ለኛ በጣም አስቸጋሪ ነበር። ከ10 ሺህ መስራች አባላት ውስጥ ቢያንስ 5 በመቶ ጉባኤተኛ በጠቅላላ ጉባኤው መገኘት እንዳለበት የፓርቲዎች መተዳደሪያ ደንብ  ይደነግጋል፡፡ ይሄን ሁሉ ተሳታፊ ከየዞኑ ለማሰባሰብ ካለብን የገንዘብ እጥረት  ባሻገር፣ የፀጥታ ጉዳይም በጣም አሳሳቢ ነበር። በአንድ በኩል፣ የምርጫ ቦርድ አስገዳጅ መመሪያ አለ፣ በሌላ በኩል የፀጥታ ችግሩ አለ፤ በዚህ ውጥረት መሃል ነው ከሚቀር ብለን፣ አባሎቻችንን ሰብስበን ጠቅላላ ጉባኤውን ያደረግነው።
በዚህ ጠቅላላ ጉባኤያችሁ ምን የተለዩ ውሳኔዎች ተላለፉ?
የደንብ ማሻሻያ አድርገናል። የአመራሮች ምርጫ እንደ አዲስ ተካሂዷል፡፡ ትልቁ በጉባኤያችን የተወሰነው ጉዳይ ደግሞ ለሃገራችን ይበጃል ያልነውን ፍኖተ ካርታ ነው፡፡ ጉባኤው ስለ ፍኖተ ካርታው በጥልቀት መርምሮ እንዲዘጋጅ አቅጣጫ አስቀምጧል። በሌላ በኩል፤ መንግስት በሁሉም ቦታዎች ያሉ ግጭቶችንና ጦርነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ በምክክር መፍታት አለበት የሚለውን የቀደመ አቋማችንን በድጋሚ አፅንተናል። አሁንም ለሃገሪቱ ችግሮች በምንም መልኩ ሃይልና ጉልበት መፍትሔ አይሆንም። ብቸኛው መፍትሔ መሳሪያ አስቀምጦ መነጋገር፣ መወያየት፣ መደራደር ብቻ ነው፤ በዚህም ነው ሃገር ሠላምና መረጋጋትን እንዲሁም ዘላቂ ብልፅግናን  የሚያመጣው የሚለው፣ በጉባኤው በሰፊው የተንፀባረቀ ሃሳብና አቋም የተያዘበት ጉዳይ ነው።
ፓርቲያችሁ ብቸኛው የፖለቲካ ችግሮች መፍትሔ ውይይት ነው እያለ ነው፡፡ በቅርቡ እንደሚደረግ በሚጠበቀው አገራዊ ምክክር ላይ ለመሳተፍ ተዘጋጅታችኋል ?
እኛ ከዚህ ቀደምም በተደጋጋሚ ስንጠይቅ ስንወተውት ነበር። በመሬት ጉዳይ፤ በፍትሃዊ የኢኮኖሚ ክፍፍል ጉዳይ፣ በህገ መንግስት ጉዳይ፣በታሪክ ጉዳይ፣ በስርዓተ መንግስት ጉዳይና በመሳሰሉት ላይ ምርጫ ከመደረጉ በፊት ውይይት እንዲካሄድ ደጋግመን ጠይቀናል። እኛ አሁንም አገር አቀፍ ምክከር መካሄዱን እንፈልጋለን። ነገር ግን ይሄ አገር አቀፍ ምክክር፣ በሁሉም አቅጣጫ ፍኖተ ካርታ ሊኖረው ይገባል፤ ሂደቱ ላይ የሁሉም መተማመንና ቅቡልነት ሊኖር ይገባል። ከመሃል  አንዱ እንኳ የማይስማማ ከሆነ፣ ግቡን የመምታት ዕድሉ ዝቅተኛ ይሆናል። በእኩልነት ላይ  የተመሰረተ ሃገር ለመገንባት የሚደረግ ጥረት እንደመሆኑ፣ ማንም ከዚህ  ሂደት ሊገለል አይገባውም። ነገር ግን መንግስት ሂደቱን አጠራጣሪና ሁሉን አሳታፊ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡  
በማስረጃ ሊያስደግፉልን ይችላሉ?
ሁላችንም በተሳተፍንበት ሁኔታ የምክክሩ ፍኖተ ካርታ ሊዘጋጅ ሲገባው፣ በህዳር 2014 ላይ መንግስት ስብስባ ጠራን። እኛም በተወካዮች ተገኘን። በእለቱም ሃገራዊ የምክክር  ሂደት እንደሚጀመር፣ ሃገራዊ የምክክር ሂደቱ ምን ሊመስል እንደሚችል የሚተነትን ሠነድ አዘጋጅቶ ነው የጠበቀን፤ ይሄ  ሊሆን አይገባውም ነበር። ቢያንስ በራሱ በብልጽግና በኩል ሃሳብ ቢቀርብ፣ ሌላውም ቢያቀርብና የተውጣጣ ፍኖተ ካርታ ቢዘጋጅ ነበር የሚጠቅመው፡፡ ነገር ግን መንግስት  ከፓርቲዎች ጋር  ምንም ውይይት ሳያካሂድ ነው የምክክር ኮሚሽኑን ማቋቋሚያ አዋጅ በፓርላማ ያፀደቀው። ይሄ አዋጅ ከመፅደቁ በፊት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣በተደጋጋሚ ያሰማው #ሃሳባችንን ተቀበሉ; የሚል ተማፅኖ እንኳ ሰሚ አላገኘም።  በኮሚሽንና ኮሚሽነሮች አሰያየም ላይ እንኳ ሳይቀር ቢያንስ ከመንግስት ውጪ ይሁን፣ ካልሆነም ፕሬዚዳንቱ ሂደቱን ይምሩት (የኮሚሽኑን ማቋቋሚያ) ተብለው ተጠይቀው ነበር። ግን ማንም ትኩረት አልሰጠውም፡፡ ወዲያው እነሱ የሚፈልጓቸውን ሰዎች ግልፅ ባልሆነ መስፈርትና መንገድ መርጠው ይፋ አደረጉ። በኋላ እኛ እንደ ኦፌኮ የገባን፣ የእነሱ አቋም #ግመሉ ይጓዛል ውሾቹ ይጮሃሉ” አይነት እንደሆነ ነው። ይሄ አካሄድ እንግዲህ በኋላ ላይ ምን ውጤት እንደሚያመጣ የምናየው  ይሆናል። ለኛ በዚህ መልክ የተቋቋመው የምክክር ኮሚሽን ፈፅሞ ገለልተኛ አይደለም። በአንድ ፓርቲ  የተቋቋመ ኮሚሽን ነው፡፡
ኮሚሽነሮቹ በቀጥታ በህዝብ አይደለም እንዴ የተጠቆሙት?
ስለ መጠቆማቸው ምንድን ነው ማረጋገጫው? በህዝብ የተጠቆሙት በኮሚሽኑ ስለመካተታቸው ማነው የሚያውቀው? ይሄ ባልታወቀበትና ማን እንዴት በማን ተጠቁሞ፣ ስንት ድምጽ አግኝቶ፣ የኮሚሽኑ አባል እንደሆነ በግልፅ ባልታወቀበት ሁኔታ ሂደቱ አሳታፊና ገለልተኛ ኮሚሽን የተቋቋመበት ነው ማለት አይቻልም። እኛ አሁን ከተመረጡት ሰዎች ጋር የግል ችግር  የለብንም፤ ዋናው የሂደቱ ግልፅነትና አሳታፊነት ላይ ነው። ይሄ እንደሌላው  ኮሚሽን መታየት የለበትም። ትልቅ ሃገር የሚያድን ፕሮጀክት ተደርጎ ነው መታሰብ የነበረበት። ሁሉንም ሃሳቦችና አመለካከቶች ማስተናገድ የሚችል መሆን አለበት።  ከዚህ አንፃር አሁን የተቋቋመው ኮሚሽን፣ በሃገሪቱ እንዲመጣ የሚፈለገውን ውጤት  ለማምጣት ያግዛል ብለን አናምንም፡፡
በምክከር ሂደቱ ላለመሳተፍ ወስናችኋል ማለት ነው?
እኛ ሂደቱ ላይ ቅሬታ ስላለን አሁን ያለው አካሄድ ካልተሻሻለ ለምን እንሳተፋለን? በማናምንበት ጉዳይ ውስጥ ለምን እንሳተፋለን? እኛ ብቻ አይደለንም፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱ  ጭምር እኮ ነው ሂደቱ እንዲሻሻል አቋም  የያዘው። እኛም የምክር ቤቱን አቋም ነው የምናንፀባርቀው። ያለውን አማራጭ ተጠቅሞ መነጋገር ካልተቻለና ሁሉም ራሱ በሚፈልገው መንገድ ብቻ ሌሎች እንዲጓዙ የሚፈልግ ከሆነ፣ ታዲያ እንዴት ነው ተቀራርቦ የዚህን ሃገር የፖለቲካ ችግር  ማቃለል የሚቻለው? ቀላል ጥያቄ እኮ ነው የተጠየቀው፤ ሂደቱን ግልፅ አድርጉ ነው የተባለው። ይሄን ማድረግ ለምን ከበዳቸው? እኛ እኮ ሂደቱን በጋራ እናስተካክል ነው ያልነው እንጂ ይቅር አይደለም ያልነው። እኛ ምክክሩ እንዲቀር በፍፁም ፍላጎት የለንም። በጣም የምንፈልገው ጉዳይ ነው። ግን ደግሞ ብልፅግና ፓርቲ ለራሱ ብቻ እንዲስማማ  አድርጎ ባዘጋጀው  ሂደት ላይ መሳተፍ አስቸጋሪ ይሆንብናል።
ምንድን ነው አስቸጋሪ የሚያደርገው?
አሁንም በሂደቱ ላይ እንኳ እኔ ያልኩት ካልሆነ ያለው ብልፅግና፣ በኋላ በሂደቱ መጨረሻ ላይ በሚመጡ ውጤቶች ምን ያህል  ይስማማል? የሂደቱ ውጤት ያስማማናል ወይ? ሂደቱ ላይ እምነት ሳይኖር ውጤቱ ላይ  እንዴት ነው መስማማት የሚቻለው? ይሄ እኮ ማንም ሰው በቀላሉ የሚገነዘበው ነው።
ኦፌኮ በሃገሪቱ ግጭትና ጦርነት ቆሞ ህዝብ ማህበራዊ እረፍት ሊያገኝ የሚችለው እንዴት ባለ መንገድ ነው ብሎ ያምናል?
ፈረንጆች ግጭትን ለመፍታት በመጀመሪያ በተጋጪዎች መካከል መተመማን የሚፈጥሩ እርምጃዎች መቅደም አለባቸው ይላሉ። እነዚህን መተማመንን የሚገነቡ እርምጃዎችን ደግሞ መጀመሪያ  የሚያመቻቸው፣ ባንኩንም ታንኩንም የያዘው መንግስት ነው መሆን ያለበት። ለሰላም እጁን መዘርጋት አለበት። ስልጣንና ጥቅምን ወደ ጎን አድርጎ፣ ለሠላም እጅን መዘርጋት ወሳኝ ነው። ጠመንጃ ያነሱ ሰዎች ጠመንጃቸውን አስቀምጠው ቆም ብለው እንዲያስቡ የሚያደርጋቸው ይሄ መተማመን ነው። ይሄ ሲሆን ነው ግጭትን ማስቆም የሚችል እርምጃ እየተወሰደ ነው  የሚባለው።
አሁን መንግስት ግጭት አቁሜአለሁ ማለቱና ማንኛውንም ችግር በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ተዘጋጅቻለሁ ማለቱንስ እንዴት ያዩታል?
መንግስት ይሄን ያለው የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነትን ታሳቢ በማድረግ ነው እንጂ በዘላቂነት ግጭትን ለማቆም ከማሰብ በመነጨ አይመስለንም። ለተራቡ ለተቸገሩ ወገኖች ግጭቱ መቆሙ ጠቃሚ ነው፤ነገር ግን ዘላቂነት ያለው ውጤት  የሚመጣው ሌሎች ተጨማሪ የሰላም  አማራጮችም ሲታከሉበት ነው።

Read 1113 times
Administrator

Latest from Administrator