Saturday, 02 April 2022 12:21

ከጊዜና ከቦታ ጋር፣ ፀብና ፍቅራችን

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

ሁሉም ነገር፣ እዚያው በዚያው፣ ከቅርባችን ቢሆንልን! “ቅርበት”፣ የሁልጊዜ ምኞታችን ነው - ያንተም፣ የሷም።  “ቅርብ ነው?” ትላለች በተስፋ። “ይርቃል እንዴ?” ይላል - እየሰጋ።
ሁሉም ነገር፣ ወዲያው ወዲያው በፍጥነት ቢሟላልንስ! ይሄም፣ በሁሉም ቦታ የምንፈልገው ምኞታችን ነው። “ዛሬ ይከፈታል? ቶሎ ይበስላል? አሁን ይቀርባል?” እንላለን - በጉጉት። “አሁን ትመጣለች? አሁን ይደርሳል?” ይላሉ - ፍቅረኞች።
ግንባታውና ምረቃው፤ ድግሱና መዝናኛው፤ … ሁሉም ነገር፣ አሁኑና ወዲያውኑ! ከጥያቄ ጋር ወዲያውኑ መልሱ ሲመጣ፣ ስራው ሀ ተብሎ በተጀመረ፣ ወዲያውኑ ሆ አስብሎ የሚያስጨፍር ውጤት ሲገኝ አስቡት።
ችግኙ ገና ከመተከሉ፣ አድጎና በዝቶ፣ አረንጓዴ የለበሰ ደን፣ በአበቦች የደመቀ፣ በፍራፍሬ የተሞላ የተትረፈረፈ ለምለም ገነት ማየት ቢቻል!  ለአፍታ መቆየትና መጠበቅ ባይኖር! “ቆይታን”፣ እንደ ጠላት መቁጠራችን ይቀራል? ጠላት ባይሆን እንኳ፣ ቆይታን አንታገስም ነበር። “ይዘገያል እንዴ? አይቆይም አይደል?” እያልን በፈጣን የጥያቄ እሩምታ ሰውን እናጣድፋለን፤ ሰማይ ምድሩን እናጨናንቃለን።
ምኞታቸው ሁሉ፣ በሕይወት ፍጥነት ከተፍ፣ ከምኞትም ቀድሞ ከች ገጭ የሚልላቸው ሰዎች በዓለማችን ካሉ፤ ምንኛ ታድለዋል!ወይም እድለኛ ይመስላሉ።
ሁሉም ነገር፣ በቅርበትና በቅጽበት፣ ስንዝር ሳይርቅ፣ ከትርታ ፍጥነት ቀድሞ እንደልብ የሚገኝ ቢሆን ይታያችሁ። ከጊዜና ከቦታ ጋር ያለን ፍቅር፣ የዚህን ያህል በጣም ሃያል ነው።
ግን ምን ዋጋ አለው? ብዙም ሳንርቅ፣ ብዙም ሳንዘገይ፣ ሃሳባችንና ምኞታችን ተቀይሮ፣ ከቅርበትና ከፍጥነት ጋር፣ እጅግ የመረረ ፀብ እንጀምራለን። ርቀትንና ቆይታን በፍቅር እንመኛለን። ቅርበትንና ፍጥነትን፣ ዋና ጠላት እናደርጋቸዋለን።
“ለስንት ጊዜ ይዘልቅልናል?” ብለን እናሰላስላለን። “እስከ መቼ ይቆይልናል?” ብለን እንወተውታለን። “እስከ የት ይደርሳል? ምን ያህል ርቀት ይጓዛል? የት ድረስ ይሰፋል? የቱን ያህል ይስፋፋል?” እያልን፣ እንመኛለን - የቅርቡን ሳይሆን የሩቁን፣ የአጠገባችንን ሳይሆን የማዶ የማዶውን፣ ከአድማስ ባሻገርን እንናፍቃለን።
በእርግጥም፣ “ባህርን የሚያሻግር ሃሳብ”፣ “አድማሳችንን የሚያሰፋ ራዕይ”፤… እያልን እናደንቃለን፤ እናዳንቃለን፤ርቀትን በማወደስ።
“የሚያዛልቅ አላማ”፣ “ዘመን ተሻጋሪ ተግባር”፣ “ዘላለማዊ እውነት” እያለን፣ የጊዜ ቆይታን፣ የዘመን ርዝመትን እናሞግሳለን።
ምንም እንኳ፣ “ፈጣን፣ ቀልጣፋ፣ ስሉጥ” ብለን የጊዜ ቅጽበትን ብናዳንቅም፣… “ችኩል፣ ከውካዋ፣ ቀዥቃዣ” የሚሉ የማጣጣያ ቃላትም አሉልን። ነገርን ማጣደፍ፤ በጊዜ ለመጥፋት ሆኖ ይታየናል።
ከዚያም በላይ ያስፈራል እንጂ። እንደ አዲስ ከች ድቅን እያሉ፣ ያለ ቆይታ የሚፈራረቁ እልፍ ቅፅበቶች ማለት፣… እልፍ የድንጋጤ ቅፅበቶች እንደማለት ነው። ፋታ የሌለው እልፍ የድንጋጤ ክውታ፣ አያስፈራም? ታዲያ፣ ከውካዋ የቅዠት ዓለምን ጠልተን፣ መንቀዥቀዥንና መንከውከውን ብናጣጥል ይገርማል? እውነትም፣ “የዘመን ርዝመት፣ መልካም ነው” ያሰኛል። ፋታ የሚሰጥ ቆይታን ያስመኛል።
ግን፣ ከፍጥነት ጋር ተቆራርጠን እንቀራለን ማለት አይደለም። ፍጥነት፣ የሁልጊዜ ምኞታችን ነው። ነገር ግን፣…
ማሳለጥን፣ ማፋጠንንና ማቀላጠፍን ከመመኘት ጎን ለጎን፣ ማቻኮልን፣ ማዋከብን፣ ማጣደፍን እንጠላለን። “ጠደፈ” ማለት፣ ገደል ገባ ማለት እንደሆነ ይገልፃል - የደስታ ተክለወልድ መዝገበ ቃላት። “ጥድፍ” ማለት ደግሞ፣… ገደል ማለት እንደሆነ ሲያብራሩ፤ “መያዣ መጨበጫ፣… መቆንጠጫ መቆሚያ የሌለው፣… የገባበትን የሚያንከባልል” ማለት እንደሆነ ገልፀዋል። ታዲያ ፍጥነትንና ቅፅበትን ከመውደዳችን ጎን ለጎን፣ ክውታን ብንጠላ፣ ጥድፊያን ብንፈራ ይፈረድብናል?
ከቅርበት ጋር የምንጣላውም፣ ያለምክንያት አይደለም። አዎ፣ ቅርበትን እንመኛለን። ነገር ግን፣ “ቅርብ አዳሪ፣… ሃሳበ ጠባብ፣ ስንዝር የማያነቃንቅ ድንዛዜ፣ ዙሪያው የታጠረ እስር ቤት” ብለን ቅርበትን ከማጥላላት አንቦዝንም።
የዛሬ እንጀራችንን፣ የእለት ጉርሳችንን፣ አረፍ ምንልበት ማደሪያ መጠለያችንን፤… በሰላም ወጥቶ መግባትን፣ በጤና ውሎ ደህና ማደርን፣… የቅርብ የቅርቡን፣ የቀኑ የሌሊቱን፣ እያስበለጥን፣ እናስባለን፤ እንናገራለን። “ደህና አደራችሁ?” ብለን እንጠይቃለን። “ወቅታዊ ጥያቄ ነው” ልንለው እንችላለን - በፖለቲካ ልሳን። ጥያቄችን፣ የእለት የእለቱን ብቻ ነው። ምኞታችንም፣ ከቀን ከሌሊቱ አይሻገርም። “ሰላም ዋሉ፤ ደህና እደሩ” እንባባላለን።
ግን ደግሞ፤ የቅጽበት የቅጽበቱ ባጭር ባጭሩ የሆኑ ነገሮችን ማናናቅ ወይም ማጥላላትም እናውቃለን። “ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ”፣ አስከፊ ኑሮ ነው እንላለን።
ረዥም እድሜን ብቻ ሳይሆን፣ ከብዙ አመታት የበለጠና የዘለለ፣ ዘላለማዊ ሕይወትን ጭምር እንመኛለን። መኖሪያ ቤትና መኝታ ክፍል፣ የስራ ቦታና ትንሽ ማሳ፣ የማሽን መትከያ ወይም የመሸጫ ሱቅ፣… የቅርብ የቅርባችን እዚያው በዚያው፣ መዋያና ማደሪያ ቦታን፣ የሃሳባችንና የኑሮአችን ማጠንጠኛ ናቸው፡፡ነገር ግን፤የቅርባችንን ብቻ ሳይሆን፤ የሩቅ መንገድንና ረዥም ጉዞውን፤ በስደት ውቅያኖስ መሻገርን፣ አሜሪካና ካናዳ ውስጥ ኑሮ መመስረትን ሁሉ እናወራለን።
በኢትዮጵያ ጉዳይ ምክንያት፤ የአሜሪካ መንግስት መዲና ላይ በተቃውሞና በድጋፍ ጎዳና መውጣት፤ በአሜሪካ ቤተመንግስት ደጃፍ፣ የኢትዮጳያ ባንዲራ ማውለብለብ፣ ስለ ባዲራው ቀለማት እየተወዛገቡ መጣላት፣ … ይሄ ሁሉ፤ውቅያኖስ ተሻጋሪ፣ አገር አቋራጭ ወሬያችን ነው።
በኢትዮጵያ የተመረተ ምርጥ ቡና፣ ዓለማችንን ዞሮ፣ የምድራችን የምስራቅ ጫፍ በሆነችው በአገረ ጃፓን ውስጥ፣ጥሩ ገበያ ማግኘት አለማግመኘቱም ጉዳያችን ነው። የማራቶን ጀግናው አበበ ቢቂላ፣ በጃፓን አገር፣ ታሪኩ በክብር ሲታወስና ሲወሳ፣… “የሩቅ አገር ወሬ ነው” ብለን ነገሩን እናናንቀውም።
እንዲያውም፤ በኔዘርላንድና በእግሊዝ፣ ሃይሌ ገብረስላሴ ዝነኛ መሆኑን ስንሰማ፤ በጣሊያንና በጃፓን አበበ ቢቂላ ታሪክ ሰርቶ ሲወደስ፣… የአገራቱ ርቀት ያህል፣ ነገሩ በክብር ገዝፎ ይታየናል።
የአበባ ምርት፣ ከኢትዮጵያ ኔዘርላንድ ድረስ ሄዶ ገበያ ማግኘቱ፤ ጃፓንና አሜሪካ ድረስ የቡና ገበያ መጨመሩና መቀነሱ፤… የሆነ ጊዜ ላይ፣ በዓለም ዙሪያ የአንድ ኪሎ ቡና ዋጋ ከሶስት ዶላር በታች መውረዱ፣ አሁን እንደምናየው፤ ዋጋው ከ5 ዶላር በላይ ማሻቀቡ፤ የኢትዮጵውያን ጉዳይ ነው።
በእርግጥ፣ ከገበሬው ጎጆ አጠገብ የተለቀመ የቡና ፍሬ፣ ከሰፈር ሱቅ የምንሸምትበት የቡና ዋጋ፣ የቅርባችንና የእለት ኑሯችን ናቸው - ለገጠሩ የቡና ገበሬና ለከተማው ቡና ጠጪ።
ነገር ግን፣ የአውሮፓ የአበባ ገበያና የአሜሪካ የቡና ዋጋስ? እጅግ የምናስብበትና የምንብሰለሰልበት፤ የሩቅ በመሆኑ ነው። ወንዝ የማይሻገር አበባና ቡና፣ ቢሊዮን ዶላር አያስገኝም። መንቀሳቀሻ ነዳጅ መግዛት፣ ስንዴና ዘይት ማስመጣት የሚቻለው፤ ከሩቅ አገር በዶላር ነው።
እዚሁ የምናያት የስንዴ የሰሊጥ ማሳ፣ እንጀራችን ናት። ነገር ግን፣ ዩክሬን ወይም ፓኪስታን… ከባህር ማዶ፣ ከዓለማችን ሰሜን ጫፍ የሚገኝ የስንዴ ወይም የሱፍ ማሳም፤ ቀላል ጉዳይ አይደለም። የዘይት ዋጋ ለ1 ሊትር ከ80 ብር ወደ 200 ብርና ከዚያ በላይ ሲያሻቅብ አይተን የለ! ከሩቅ የሚገኝ ነገር፣ ለህይወት ለኑሯችን ቅርብ ነው።
ለነገሩ፣ የመኖሪያ ቤት እጥረት፣ የዚህች ክፍል ኪራይ፣ የዚያች ሱቅ መጥበብን ብቻ ሳይሆን፤ በአጠቃላይ፣ ስለመላው ዓለም ድንቅ ተፈጥሮ ወይም ስለ ዓለም ፍጻሜ ምፅአት እናወራለን።
ስለ ጸሐይና ጨረቃ፣ ስለከዋክብት አቅጣጫና ዑደት፤ ብርሃናቸውን በሚመለከት ወይም የውድቀት የጽልመት ዘመናቸውን የሚዘረዝር ትረካ ወይም የተፃፈ ትንበያም፣ ከሰው ልጆች ኑሮና ታሪክ ጋር የተቆራኘ ነው።
የመኖሪያ ክፍል ወይም የጓሮ አትክልት ማሳዎችን በካሬ ሜትር እየለካን እየገመትን እንነጋገራለን። ግን፣ ምድርና ሰማያት እያልን ምልዓተ ተፈጥሮን፤ እውን ነገሮችን በሙሉ “ሁሉን እውነታ”፤ “ሁለንታን” በአንድ ማዕቀፍ ጠቅልለን፤ ለማሰብና ለመናገር እንመኛለን፤ በሃይማኖትም ሆነ በሳይንስ ቅኝት።


Read 11487 times