Monday, 11 April 2022 00:00

“መማሪያ አታድርገኝ፤ መማሪያ አላባክንም” እንበል።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

    • የዩክሬን ፍርስራሽና ራሺያ የገባችበት ማጥ! ለነሱ መከራ ነው፡፡ ለሌሎች መማሪያ።
         • ለአመታት የማይድን ጥፋት፣ በቀላሉ የማይሽር በሽታ ነው - የጦርነቱ ትርፍ።
         • አንዱ ጥፋተኛ ሌላው ተጎጂ ቢሆኑም፣ ሁለቱም ከሳሪ ናቸው - መጠኑ ቢለያይም።
            
           ዩክሬን፣ ከእለት እለት ስትፈርስ እያየን ነው። ነገር ግን፣ ራሺያም ከጉዳት አላመለጠችም። 10 ሺ የራሺያ ወታደሮች ወይም ከዚያ በላይ መሞታቸው ተዘግቧል። ከ2000 በላይ የጦር ተሽከርካሪዎችም ከጥቅም ውጭ ሆነውባታል። እንዲያም ሆኖ፣ የዩክሬን መከራ ይብሳል።
ተጠቂ ከመሆኗም በተጨማሪ፣ የጦርነቱ ጉዳት በዩክሬን ላይ ይከፋል። ብዙ ሺ ሰዎች፣ ወታደሮችና ሲቪሎች ሞተዋል። አካላቸው ጎድሏል። ከዩክሬን ጠቅላላ ሕዝብ፣ 10% ያህሉ፣ በአንድ ወር ውስጥ፣ ከኑሮው ተነቅሎ፤ ቤተሰብ ተነጣጥሎ፣ ንብረቱን ጥሎ፣ ወደ ጎረቤት አገራት ለስደት ተበታትኗል።
“የአውሮፓ የዳቦ ቅርጫት” የሚል ስያሜዋ፣ ዛሬ ለዩክሬን የባዶ ቃላት ጩኸት እየሆነ ነው። በርካታ አገራትን የሚቀልብ የስንዴና የበቆሎ አዝመራ የበዛላት፣ ለደርዘን አገራት የሚተርፍ ሱፍና ዘይት የሚመረትባት ዩክሬን፣ ዛሬ ተመፅዋች ሆናለች።
ገሚሶቹ፣ መጠለያና እርዳታ ፍለጋ፣ ወደ ውጭ አገራት ተሰድደዋል። ከስደት የቀሩት፣ የቀድሞ ኑሯቸውን መቀጠል አይችሉም። ከአገር ባይወጡም፣ ብዙዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል። እናም፣ የምግብ እርዳታ የሚጠብቁ ሚሊዮን ተፈናቃዮች፣ ከጦርነት ሽሽት ከከተማ ከተማ የሚንከራተቱባት አገር ሆናለች - ዩክሬን።
የቢሮ ህንፃዎችና መኖሪያ ሰፈሮች፣ ፋብሪካዎችና ወደቦች፣ የገበያ መደብሮችና መጋዘኖች፣… በየእለቱ ይፈርሳሉ። የውሃና የኤሌክትሪክ፣ የስልክና የነዳጅ ተቋማት ይቃጠላሉ። ግን፤ የዩክሬን አበሳ፣ በዚህ አያበቃም። የዛሬ ጦርነት ሲያልቅ፤ ለሌላ የነገ ጦርነት ክፉ መርዝ ይዘራል። አንድ ዙር እልቂትና ውድመት ሲጠናቀቅ፤ ለሌላ ዙር ጥፋት ብዙ ሰበቦችን ይፈጥራል።
ጦርነት፣ ነባር እንከኖችን ያራባል፤ ለነገ አዳዲስ ችግሮችን ይዘራል፤ ያዛምታል። ነባር የጥላቻ ቅኝትን አክርሮ፣ የመጠፋፋት ፖለቲካን አስፋፍቶ፣ ለሌላ ቀውስና ትርምስ፣ ለሌላ ዙር ጦርነትና ለፍጅት ያዘጋጃል። ለነገ፣ የጥፋት እርሾዎችን ይነሰንሳል፤ የዛሬ ጦርነት።
ዩክሬንም፤ ከእነዚህ የጦርነት ክፉ መዘዞች አታመልጥም።
የምስራቅና የደቡብ ዩክሬን አካባቢዎችን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። ለበርካታ ዓመታት ሲንተከተክ የነበረ ጭፍን የሃይማኖትና የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ፤ በጦርነቱ ሳቢያ ብሶበት ተቀጣጥሏል። ቤንዚን እንደ ተርከፈከፈበት እሳት፤ የጥላቻ ፖለቲካው፣ በየእለቱ የጥፋት መፈብረኪያና የጥቁር ጠባሳ መፈልፈያ ሆኗል።
ሲብላላ የቆየ ነባር በሽታ ይፈላል፤ ሲብሰለሰል የነበረም ይገነፍላል -  በጦርነት ሳቢያ።
በአጭሩ ዩክሬን፤ ከዘንድሮው ጦርነት በብዙ ጉዳት ብትተርፍ እንኳ፣ ወደፊት በደህና ትቀጥላለች ማለት አይደለም። በጦርነቱ ሰበብ የተባባሰው የአገር ውስጥ ችግርና ነባር የፖለቲካ በሽታ፣ በቀላሉ አይሽርም። ከጥላቻ ፖለቲካና ከጭፍንነት በሽታ፣ ሙሉ ለሙሉ የመዳን እድል ሊኖራት ይቅርና፣ ወደ አምና ወደ ካቻምና ታሪኳ ተመልሳ ማገገሟም ያጠራጥራል።
የራሺያ ጦር፣ ሳይውል ሳያድር፣ ዛሬውኑ ለቅቆ ቢወጣ እንኳ፤ ዩክሬን በቀላሉ ጤና አታገኝም። መጥፎነቱ ደግሞ፣ የራሺያ ጦር፣ ከዩክሬን ጠቅልሎ የመውጣት አቅድ የለውም።
አዎ፤ የጦርነቱ መከራ፤ ለዛሬና ለዘንድሮ እጅግ መራራ ነው። ነገር ግን፣ ለነገና ለወደፊትም፣ የጦርነቱ መዘዝ፣ የበርካታ ዓመታትን ታሪክ ይመርዛል። እዚህ ላይ ነው፣ የአርቆ አሳቢዎች ጥቅም!
መጪውን ዘመን ለማስተዋል፣ የጦርነት ክፉ መዘዞችን ከወዲሁ ለመገንዘብ፣ ከወዲሁም ለመጠንቀቅ የሚችሉ አዋቂዎችንና ጥበበኞችን ማግኘት፣ መታደል ነው። ክፋቱ ግን፣ ጥበበኞች እንደልብ አይገኙም። ቢገኙ እንኳ፤ ሁልጊዜ ይሳካላቸዋል ማለት አይደለም። እንዲያውም፣ ብዙ ጊዜ፣ ሳይሳካላቸው አገርን ሳይፈውሱ ይቀራሉ። ለምን? አስተዋዮች፣ ብዙ ጊዜ፣ በተለይ በቀውጢ ሰዓት፣ ሰሚ ያጣሉ። ሲብስም፤ ይወገዛሉ።
አዎ፣ ጥበበኞችን ያገኘ አገር እድለኛ ነው። ነገር ግን፤ ጥበበኞችን የሚሰማና ሃሳባቸውን የሚያገናዝብ አድማጭ ዜጋ፤ በብዛት ያስፈልጋል። አብዛኛው ፖለቲከኛና ዜጋ ግን፣ ከዛሬው የጦርነት መከራ ባሻገር፤ ስለወደፊቱ የማሰብ ፋታ ለራሱ አይሰጥም። ስለ ዘለቄታውና ስለ አገር ጤንነትም፣ ጉዳዬ ብሎ አይሰማም፤ አያገናዝብም። ይሄ አይገርምም።
የጦርነት እሳት አገሬውን እያቃጠለ፤ የማሰቢያ ፋታና በስክነት የማሰከላሰል ብስለት፣ በቀላሉ አይገኝም። ዩክሬን የገጠማት የጦርነት እሳት ደግሞ ከባድ ነው።
በአውሮፓ ምድር፣ አንድ ሃያል አገር፤ ጎረቤት ላይ፣ ሁለት መቶ ሺ ወታደሮችን ሲያዘምትና ጠቅላላ ጦርነት ሲያካሂድ፣… ለሩቅ ለተመልካችም ያስደነግጣል። ደግሞም፣ ዓለምን አናውጧል። በተለይ ለአውሮፓ አገራት፣ የቁም ቅዠት ሆኖባቸዋል። ይሄ መዓት ነው፤ ዩክሬን የወረደባት።
የባሰም ሊሆን ይችል ነበር እንጂ። ደግነቱ፤ ጦርነቱ እንደ አጀማመሩ አይደለም። በጥቂት ቀናት ውስጥ፣ የሚፍረከረክና የሚፈርስ የመሰለው የዬክሬን መንግስትና ጦር፤ በተፈራለት፣ በተተነበየለት ወይም በተፎከረበት ፍጥነት፣ በቀላሉ አልተገነደሰም፤ አልተናደም። ስድስት ሳምንታትን የተሻገረው የጦርነት መከራ፣ ለዩክሬን ቀላል ነበር ማለት አይደለም። ቢሆንም፣ የተፈራው ወይም የተፎከረው ያህል አይደለም - በጦርነቱ መባቻና ማግስት ከነበረው ግምት ጋር ሲነፃፀር ማለት ነው።
እልቂቱና ስቃዩ፣ ባይቋረጥም፤ እሳቱና ውድመቱ ባይቀንስም፤ የዩክሬን መንግስት በቀላሉ የማይፍረከረክ፣ በሳምንት ውስጥ የማይበታተን እንደሆነ፣ ሁሉም አይቷል፤ አውቋል። ይሄ፣ ለዩክሬን፣ እንደ ትንሽ የመፅናኛ ድል ሊቆጠር ይችላል።
ነገር ግን፣ ‹አለመፍረስ፣ አለመሸነፍ፣ እጅ አለመስጠት› ማለት፤ ከጥፋትና ከውድመት ማምለጥ ማለት አይደለም። የእስካሁኑን መከራ፤ ወደ ኋላ ተመልሶ፣ መሰረዝና ማስቀረት አይቻልም። የጠፋ ህይወትና ንብረት፣ ጠፍቷል፤ አይመለስም። በቃ ጦርነትን ማስቀረት አለመቻል፣ ትልቅ ውድቀት ነው። ይህም ብቻ አይደለም።
‹አለመሸነፍ፣ ሙሉ ለሙሉ አለመፍረስ› ማለት፤… ጥፋትን ማስቆም፤ ውድመትን መግታት እንደመቻል አይደለም። በተወሰኑ አካባቢዎች ውጊያው ቢበርድም፤ በአንዳንድን ከተሞች ቢረግብም፤ ጦርነቱ አልቆመም። እንዲያውም፤ በሌሎች ክልሎች፣ የጦርነቱ እሳት እየሰፋ እየፋመ ነው።
በዚያ ላይ፣ የደቡብና የምስራቅ ዩክሬን ክልሎች፤ እስከ ወዲያኛው ተገንጥለው፣ በራሺያ ስር የሚወድቁ፤ ወይም ሙሉ በመሉ በራሺያ ግዛት የሚጠቃለሉ ይመስላል።
ከዚህ ትልቅ ታሪካዊ ጉዳት ጋር አብረው የሚመጡ አደጋዎችን፣ በዝርዝር ቆጥሮ መጨረስ አይቻልም። የሚሊዮኖችን ኑሮ እስከ ወዲያኛው ይበጣጥሳል። የመውጫ የመግቢያ በሮችን፣ የንግድ መስመሮችን ይዘጋባቸዋል። የከበባው አጥር እየጠበበ፣ ገመዱ እየከረረ፤ አገሪቱን በየአቅጣጫው እየቦጫጨቀ፤ ዙሪያዋን ለተጨማሪ አደጋ ያጋልጣታል። ለሌላ ዙር የወረራ ዘመቻ ያመቻቻታል።
ታዲያ፤ ስለነገ ማሰብ አስፈላጊ የሚሆነው፤ የዛሬውን መከራ ለማሳነስ አይደለም።
የጦርነት ክፋት፤ በጥቂት ቀናት ውስጥ፣ በመላው ዓለም በገሃድ የሚታይበት ነው - ዘመኑ። በየመንገዱ የወደቁ አስክሬኖች፣… “ጦርነት በዚህ አካባቢ አልፏል” ብለው፣ የጥፋትን ጉዞ በአካል የሚመሰክሩ አሳዛኝ እውነታዎች ናቸው። ድሮም ዛሬም፤ በየትም አገር፤ እንዲህ አይነት አሳዛኝ ትዕይንቶች፣ ጦርነት በፈጠረበት አጋጣሚ ሁሉ ይኖራሉ። ዛሬ ግን፤ የአካባቢው ነዋሪዎች ብቻ አይደሉም፤ የጦርነትን ዘግናኝነት የሚያዩት። በየቦታው በካሜራ ተቀርፆ፣ ለዓለም ይሰራጫል።
እናቶች፣ ሰፈር ውስጥ፣ “ልጄ የሞተው፣ እዚህች ቦታ ላይ ነው” እያሉ ሲለቅሱ፣ ዓለም ሁሉ ይመለከታል። በመድፍ የተቆፈረውን አስፋልት፣ በዙሪያው የፈሰሰውና የደረቀውን ደም እያዩ፣ ያነባሉ። በመድፍ የፈረሰ ቤታቸውን እየተመለከቱ፤ “ባለቤቴመ በፍንዳታው የሞተችው እዚህ ቦታ ነው” ብለው በድንዛዜ ይናገራሉ - አዛውንቱ።
በየከተማው፣ በየጎዳናው፣ በየቤቱ ሃዘን ነው። ከሁለት ወር በፊት፤ ከሞላ ጎደል፣ ሰላም የነበረ ሰፊ አገር ውስጥ፣ …ከዛፍ እንደሚረግፍ ቅጠል፣ የሰው ህይወት በየቦታው ወዳድቆ ማየት፣ …ይዘገንናል። ወድመቱም እንደዚያው ነው።


በመጀመሪያው እለት፤ አንድ የመኖሪያ ህንጻ ሲቃጠል ይታያል። በሳምንቱ ግን ሰፈሩ ሁሉ ፈራርሷል፤ በእሳት ከስሏል። እና ግሞ፣ የተፈናቃዩ ብዛት፣ የስደቱ ግፊያ!
የጦርነትን ክፋት ማየት፤ …ያሳዝናል፤ ያሳምማል።
ማየት ብቻ ሳይሆን፣ ማሳያ መሆን ደግሞ፤ የምድር ሲዖል ውስጥ እንደመግባት ነው። ማሳያና ምሳሌ ከመሆን ያድነን። ያድናቸው። ይዳኑ።
በእርግጥ፤ የጦርነት ክፋት ማሳያ ከመሆን መዳን፤ እንደ ንግግር ቀላል አይደለም።
ከትልቅና ከሃያል አገር አጠገብ በመሆናቸው ብቻ፣ የጦርነት ሰላባ የሚሆኑ አገሮች አሉ። ድሮም ነበሩ። ከጃፓን ወይም ከጀርመን አጠገብ፤ ከቱርክ ወይም ከራሺያ አቅራቢያ ሆነው የተፈጠሩ አገራት፤ መከራቸውን አይተዋል - በአንደኛውና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት፤ ከዚያም በፊት።
ዛሬና ለወደፊትም፣ አስፈሪ አገራት አሉ፣ ይኖራሉ። ህንድ፣ ቻይና፣ ራሺያ እና ሌሎችም ያስፈራሉ። ታዲያ፣ ከአስፈሪ አገር አጠገብ መሆን፣ ምን መፍትሔ አለው? ቦታ መቀየር አይቻል ነገር! ችግር ነው።
ኢትዮጵያ፣ በዚህ በዚህ፣ በኩል እድለኛ ናት። ነገር ግን፣…
ነገር ግን፣ በአገር ውስጥ፣ እዚሁ በዚሁ፤ ራሳችን የጦርነት ማሳያና ምሳሌ ከመሆን አላመለጥንም። ለምን? የጦርነት ክፋቱን፣ በአይን እስክናየው ድረስ፣ ማሳያ እስክንሆን ድረስ፣ ጦርነትን አቅልለን እናስበዋለን። ጦርነትን እየጠራን፣ ጦርነት የማይፈጠር ይመስለናል። እሳቱ የማይነካን፣ ፍንጥርጣሪው የማይደርስብን፣ መዘዝም የማያመጣብን እናስመስላለን። በዚህም ምክንያት፣ ጦርነትን በሩቁ ማስቀረት ያቅተናል። ገና ሳይጠነሰስና ሳይለኮስ፤ ነገሮችን የማስተካከል፤ ችግሮችን የማፍታትና የማቀዘቅዝ እድል ያመልጠናል።
ጦርነት፣ አንዴ ከተጋጋለ በኋላ፣ ስለ መፍትሔ የሚያስቡ ሰዎች፣ ድምፃቸው ይጠፋል።
ጦርነት አንዴ ከተቀጣጣለ በኋላ ደግሞ፣ ስለጦርነት ክፋት ወይም ስለሰላም በጎነት መናገር፣ እንደ ከባድ ጥፋት፣ ወይም እንደ ድክመትና ሞኝነት ይቆጠራል። እሳት የሚያራግብና የሚያቀጣጥል፤ የሚያባዛና የሚያዛምት ሰው፣ ያለ ከልካይ ይገንናል።
በሌላ አነጋገር፣ ‹የጦርነት ክፋትን ከማየትና ማሳያ ከመሆን መዳን› ማለት፤ አስቀድሞ ጦርነትን በሩቁ የሚያስቀርር ጥበብን ይዞ መትጋት ማለት ነው። ይህን ማድረግ ይቻላል፣ እንችላለን። ከባድና የረዥም ጊዜ ጥረት ቢሆንም፣ ይቻላል። ማለቴ፣ በአብዛኛው ይቻላል። አንዳንዴ ግን፣ አስቸጋሪ ነው።
ከ80 ዓመት በፊት፣ የፋሺስት ጣሊያን ወረራና ጦርነት፣ ኢትዮጵያ በሩቁ ማስቀረት ትችል ነበር ለማለት ያስቸግራል።
ዩክሬንም፣ ዛሬ ከጦርነት የማምለጥ እድል የነበራት አይመስልም።
ጦርነቱን የማስቀረት፣ አሁንም የመግታት እድል የነበረውና ያለው፣ በራሺያ መንግስት እጅ ነው። ደግሞም ለዩክሬን ብቻ ሳይሆን ለራሺያም ይጠቅማል።
የጦርነት ክፋት፤ ለአሸናፊም ጭምር ነው። ማሸነፍም በኪሳራ ነውና።
በስድስት ሳምንት ጦርነት፤ 10 ሺ ገደማ ወይም ከዚያ በላይ የራሺያ ወታደሮች ህይወታቸውን አጥተዋል። የዚያኑ ያህል ቆስለዋል። ሁለት ሺ፣ የራሺያ ወታደራዊ መኪኖች ከጥቅም ውጭ ሆነዋል። ሶስት መቶ ያህሉ፣ ታንኮች ናቸው።
በእርግጥ፤ እልቂትና ውድመቱ ሁሉ፤ የድክመት ውጤት አይደለም። ጦርነት በተፈጥሮው፤ የሞት፣ የስቃይና የውድመት ጉዞ ነው።
ሌላ ሌላውን ሁሉ ትተን፤ የመኪና ብልሽትን ብቻ ብናይ እንኳ፤ እንደ ሰላም ጊዜ አይደለም። የብልሽት ትርጉም፣ በጦርነት ጊዜ ይለወጣል። ጥቂቶት ብልሽቶችን፣ እዚያው በቦታው መጠገን ይቻል ይሆናል። አብዛኞቹን ግን፤ እዚያው በተበላሹበትና በቆሙበት ቦታ ጥሎ ወይም አቃጥሎ መሄድ የግድ ነው። የተበላሹ ቦቴዎችን፣ ሮኬት ተሸጋሚ መኪኖችን  ማን ይጎትታል? ስንቱን አንስቶ፣ ስንቱን ጭኖ ማጓጓዝ ይቻላል? በጦርነት እሳት ውስጥ ሆኖ፣ ውድመትን ማስቀረት አይቻልም። በቃ፣ የጦርነት ዱካ ሁሉ፣ በውድመት ዱካ የተሞላ ነው።
ራሺያ የገባችበት ማጥ ደግሞ፣ ተራ ጦርነት አይደለም፤ ከባድ ነው። ስጋት የገባቸው የአውሮፓና የአሜሪካ መንግስታት፤ እንደ ጉድ የጦር መሳሪያ ለዩክሬን እያጎረፉላት ነው። አለበለዚያ፣ ነገስ፣ የማን ተራ ይሆናል? ቢያሰጋቸው አይፈረድባቸውም።
አዎከ የራሺያ ጦር፤ የዩክሬንን ከተሞች የማቃጠልና ወደ ፍርስራሽ ክምር የመቀየር አቅም አለው። ደግሞም ብዙ አፍርሷል። በእርግጥ፣ የተፈራው ያህል አይደለም። የራሺያ ጦር፣ እስካሁን፣ ከመራራ ጭካኔ፣ ትንሽ ተቆጥቧል። ተመስጌን ነው።
ነገር ግን፣ አቅም ስላለው፣ ዩክሬንን ሙሉ ለሙሉ ቢያፈርሳትም እንኳ፤ የዩክሬን ኪሳራ፤ ለራሺያ ትርፍ አያስገኝላትም። ጦርነት፣ ምርትና ትርፍ የለውም። ኖሮት አያውቅም። ወደፊትም አይኖረውም።
ጥፋትና ኪሳራ ነው፣ የጦርነት ተፈጥሮ። ለራሺያም እንዲሁ።
በእርግጥ፤ ሕልውናውን ከወራሪ ለማትረፍ፤ እጅግ የከፋ ጥፋትን ለመቀነስ፤ ለዚያውም፣ ሌላ አማራጭ ሲጠፋ፣ ወደ ጦርነት መግባት የግድ የሚሆንበት ጊዜ አለ። ያም ቢሆን፣ ያለ ኪሳራ አይደለም። ከተሳካ፣ ኪሳራን መቀነስ እንጂ፤ ከኪሳራ ማምለጥ አይችልም። የጦርነት ተፈጥሮ አይቀየርም። ጥፋትና ኪሳራ ነው፣ ተፈጥሮው።
ይህን አሳዛኝ መማሪያ እናባክነው። እንማርበት። ወደፊት፣ መማሪያ ከመሆን እንድንድን ይጠቅመን ይሆናል።

Read 9298 times