Saturday, 09 April 2022 15:04

ፊፋ ከ22ኛው የዓለም ዋንጫ 7 ቢ.ዶ ገቢ ይጠብቃል

Written by  ግሪም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 ኳታር ለምታስተናግደው 22ኛው ዓለም ዋንጫ 226 ቀናት ቀርተዋል፡፡ ወደ ዓለም ዋንጫው ለማለፍ በስድስቱ የፊፋ ዞኖች በተካሄዱ ማጣርያዎች 29 ብሄራዊ ቡድኖች ማለፋቸውን አረጋግጠዋል፡፡ በቀሩት የ3 ብሄራዊ ቡድን ኮታዎች 6 አገራት በሰኔ ወር ላይ በሚካሄዱ የጥሎ ማለፍ ማጣርያዎች የሚፋለሙ ሲሆን ስኮትላንድ ፣ ዩክሬንና ዌልስ ከአውሮፓ፤ ዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ ከኤሽያ፤ ፔሩ ከደቡብ አሜሪካ፤ ኮስታሪካ ከሰሜንና መካከለኛው አሜሪካ፤ ኒውዝላንድና አውስትራሊያ ከኦሺኒያ ዞን ናቸው፡፡ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ከዓለም ዋንጫው እስከ 7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ይጠብቃል፡፡ የሚሳካለት ከሆነ በውድድሩ ታሪክ አዲስ የገቢ ሪከርድ ሆኖ ሊመዘገብ የሚችል ነው፡፡
በ22ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ ከበቁት 29 አገራት ኳታር ብቻ በአዘጋጅነቷ በቀጥታ እንዳለፈች ይታወቃል፡፡ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ይህን አይነቱን እድል ለመጨረሻ ግዜ የሚሰጥ ይመስላል፡፡  በቀጣይ የዓለም ዋንጫዎች በአዘጋጅነት ቀጥታ ተሳትፎ የማግኘቱ እድል   ከአንድ አገር በላይ ይሆናል፡፡ በ2026 እኤአ ላይ ካናዳ፤ ሜክሲኮና አሜሪካ  23ኛውን የዓለም ዋንጫ  በጋራ እንደሚያስተናግዱ የሚታወቅ ሲሆን በቀጥታ የማለፍ እድሉ ለሶስቱም በመሆኑ በሰሜንና መካከለኛው አሜሪካ ዞን የሚካሄደው ማጣርያ በጣም ጥቂት ብሄራዊ ቡድኖችን ቢያሳትፍ ነው፡፡ በ2030 እኤአ ላይ 24ኛውን የዓለም ዋንጫ ለማዘጋጀት ከአንድ በላይ አገራት ማመልከታቸው ስለማይቀር  በአዘጋጅነት የማለፍ እድሉን ከአንድ አገር በላይ ሆኖ ይቀጥላል፡፡
በ22ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ተሳትፏቸውን ያረጋገጡት 29 አገራት በታሪካዊው ውድድር አንዴና ከዚያም በላይ መካፈል የቻሉ ናቸው። በዓለም ዋንጫው ላይ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የምትሳተፈው አዘጋጇ ኳታር ብቻ ናት። የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበርን የሚወክሉት 12 አገራት ጀርመን፣ ዴንማርክ፣ ፈረንሳይ፣ ቤልጅዬም፣ ክሮሽያ፣ ስፔን፣ ሰርቢያ፣ እንግሊዝ፣ ስዊዘርላንድ፣ ሆላንድ፣ ፖላንድና ፖርቱጋል ናቸው፡፡ ሜክሲኮ፣ ካናዳና አሜሪካ ከሰሜን እና መካለኛው አሜሪካ ያለፉት፤ ደቡብ ኮርያ፣ ጃፓን፣ ኢራንና ሳውዲ አረቢያ ከኤሽያ፤  ከአፍሪካ ሴኔጋል፣ ካሜሮን፣ ጋና፣ ሞሮኮና ቱኒዚያ ከአፍሪካ እንዲሁም  ብራዚል፣ አረንጀንቲና፣ ኢኳዶር እና ኡራጋይ ከደቡብ አሜሪካ ተሳታፊ ናቸው፡፡
22ኛው የዓለም ዋንጫ ካመለጣቸው አገራት ዋናዋ ተጠቃሽ የአውሮፓ ሻምፒዮኗ ጣሊያን ናት። በ2018 እኤአ ላይ ራሽያ ባዘጋጀችው 21ኛው የዓለም ዋንጫ ያልተሳተፈች ሲሆን  ሁለት ተከታታይ የዓለም ዋንጫዎች አምልጠዋታል፡፡ ከአውሮፓ የዓለም ዋንጫው ያመለጣት አገር ስዊድን ናት፡፡ ከአፍሪካ ናይጄርያ፤ አልጄርያና ግብፅ እንዲሁም ከደቡብ አሜሪካ ኮሎምቢያ እና ቺሊ ሳይሳካላቸው ቀርተዋል፡፡
ከታላላቅ ተጨዋቾች መካከል በዓለም ዋንጫው ለመጨረሻ ግዜ የመሳተፍ እድልን ማግኘታቸው ተጠቅሶ ብዙ የተወሳላቸው የአርጀንቲናው ሊዮኔል ሜሲ እና የፖርቱጋሉ ክርስትያኖ ሮናልዶ ናቸው፡፡ በርካታ ምርጥ ተጨዋቾች ደግሞ በየብሄራዊ ቡድኖቻቸው ማጣርያውን ማለፍ ሳይሆንላቸው ቀርቶ የዓለም ዋንጫው ያመልጣቸዋል፡፡
ከጣሊያን ፍሬደሪኮ ኪዬዛ፣ ጂያንሉጂ ዲናሮማ፣ ጂዮርጂዮ ቼለኒ ማርኮ ቬራቲ፤ አርቪንግ ሃላንድና ማርቲን ኤድጋርድ ከኖርዌይ፤ ዝላታን ኢብራሞቪች ከስዊድን፤ ዴቪድ አልባ ከኦስትሪያ፤ ዊልፍሬድ ኒዲዲ ከናይጄርያ፤ ሪያሃድ ማህሬዝ ከአልጄርያ፤ መሃመድ ሳላህ ከግብፅ፤ ሊውስ ዲያዝና ጄምስ ሮድሪጌዝ ከኮሎምቢያ፤ አሌክሲ ሳንቼዝና አርቱሮ ቪዳል ከቺሊ በ22ኛው የዓለም ዋንጫ የማናያቸው ምርጥ ተጨዋቾች ናቸው፡፡


ለ22ኛው ዓለም ዋንጫው
በዶሃ የወጣው የምድብ ድልድል   
ምድብ 1
ኳታር፣ ኢኳዶር፣ ኔዘርላንድስ፣ ሴኔጋል
ምድብ 2
እንግሊዝ፡ ኢራን፡ አሜሪካ፡ ስኮትላንድ/ዌልስ/ዩክሬን
ምድብ 3
አርጀንቲና፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ሜክሲኮ፣ ፖላንድ
ምድብ 4
ፈረንሳይ፣ ዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ /አውስትራሊያ/ፔሩ፣ ዴንማርክ፣ ቱኒዚያ
ምድብ 5
ስፔን፣ ኮስታሪካ/ኒውዚላንድ፣ ጀርመን፣ ጃፓን
ምድብ 6
ቤልጂየም፣ ካናዳ፣ ሞሮኮ፣ ክሮኤሺያ
ምድብ 7
ብራዚል፣ ሰርቢያ፣ ስዊዘርላንድ፣ ካሜሩን
ምድብ 8
ፖርቱጋል፡ ጋና፡ ኡራጓይ፡ ደቡብ ኮሪያ

Read 1109 times