Saturday, 09 April 2022 15:14

የአትሌት ሚሊዮን ደምሴ ቅሬታ

Written by  ግሪም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 በ24ኛው መስማት የተሳናቸው ኦሎምፒክ  ላይ ኢትዮጰያን ለመወከል ያደረግኩት  ጥረት ትኩረት አላገኘም ሲል አትሌት ሚሊዮን  ደምሴ  ለስፖርት አድማስ ቅሬታውን ገለፀ፡፡
ከመጋቢት 10 እስከ 17 ሐዋሳ ላይ በተዘጋጀ አገር አቀፍ ሻምፒዮና ላይ የአዲስ አበባ መስማት የተሳናቸው ፌደሬሽን በበጀት እጥረት አልተሳተፈም ነበር፡፡ በ100 ሜትርና 200 ሜትር  ውድድሮች  ጥሩ ውጤት ለማምጣት በቂ ዝግጅት ማድረጉን የሚናገረው አትሌት ሚሊዮን ደምሴ ግን ሙሉ ወጭውን በግሉ በመሸፈን የሚወዳደርበትን እድል ፈጥሯል፡፡  በ100 ሜትር   የምድብ  ማጣርያ ላይ   ርቀቱን በ11.40 ሰከንዶች ሲያሸንፍ  በ200 ሜትር ማጣርያ  ደግሞ  ሁለተኛ መውጣት ችሏል፡፡  ከእነዚህ ውጤቶቹ በኋላ ግን ባልጠበቀው መንገድ በፍፃሜ ውድድሮች እንዲሳተፍ ያልተፈቀደለት ሲሆን ከእሱ የዘገየ ሰዓት ያላቸውና ክልላቸውን የወከሉ አትሌቶች በፍፃሜው እንዲወዳደሩ አዘጋጆቹ ወስነዋል፡፡ ከፍፃሜው በኋላ አትሌት ሚሊዮን በሚሳተፍበት የውድድር መደብ በመስማት የተሳናቸው ኦሎምፒክ ለኢትዮጲያ በተካሄደው ምርጫ 11.45 ያስመዘገበ   አትሌት ተመርጧል፡፡ አትሌት ሚሊየን ደምሴ በጉዳዩ ላይ በፃፈው የቅሬታ ደብዳቤ ውሳኔው እንዳሳዘነው ገልጿል፡፡ለኢትዮጲያ ቡድን በተካሄደው ምርጫ ያለው ሰዓትና ውጤቱ ከግምት ውስጥ አለመግባቱ በፍፃሜው ውድድርም እንዳይሳለፍ መወሰኑም እድሉን እንዳበላሸበትም አብራርቷል፡፡ ለአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር እና ለአዲስ አበባ መስማት የተሳናቸው የስፖርት ፅህፈት ቤት ለፃፈው የቅሬታ ደብዳቤም በቂ ምላሽና የሚያስተናግደው አካል አላገኘም፡፡  በመስማት የተሳናቸው ኦሎምፒክ ላይ በ100 ሜትር ለመሳተፍ  የሚጠየቀው ሚኒማ 11.75 ሰከንድ እንደሆነ ታውቋል፡፡
አትሌት ሚሊዮን ደምሴ በኢትዮጲያ መስማት የተሰናቸው ስፖርት የላቀ ውጤትና ሪከርዶችን ማስመዝገቡን ለስፖርት አድማስ በላከው መረጃ አመልክቷል፡፡ በአጭር ርቀት ውድድሮች ብቻ ሳይሆን በርዝመት ዝላይም ስኬታማ ሆኖ በአገር አቀፍ ውድድሮች ምርጥ ሰዓቶችና የሜዳልያ ክብሮችም አስመዝግቧል፡፡ በ2007 በባህርዳር ላይ በርዝመት ዝላይ የወርቅ፤ በ2008 ሐዋሳ  ላይ በርዝመት ዝላይ  የነሐስ፤  በ100 ሜትር የነሐስ ሜዳልያ፤ በተመሳሳይ በ2008 በርዝመት ዝላይ የብር ሜዳልያ፤ በ2010 ሐዋሳ ላይ  በ100 ሜትር የወርቅ፤ በ200 ሜትር የወርቅ እንዲሁም በርዝመት ዝላይም የወርቅ ሜዳልያዎችን ተጎናፅፏል፡፡ በ2011  በኬንያ በተካሄደው የዞን ሻምፒዮን በርዝመት ዝላይ የብር እንዲሁም በ4 X 100 ሜትር ዱላ ቅብብል የብር ሜዳልያም አግኝቷል፡፡
በመስማት ለተሳናቸው ዓለም አቀፍ የስፖርት ኮሚቴ የሚዘጋጀው  የመስማት የተሰናቸው ኦሎምፒክ በየ4 ዓመቱ የሚካሄድ ነው፡፡ ዘንድሮ በብራዚሏ ከተማ ካክስያስ ዶ ሱል የሚካሄደው ለ24ኛው ጊዜ ሲሆን ከ100 በላይ ሀገራት የተውጣጡ 4,500 መስማት የተሳናቸው አትሌቶች ይሳተፉበታል፡፡

Read 1568 times