Monday, 11 April 2022 00:00

ለ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

      የቀሩት ቀናት ከ100 ያነሱ ናቸው 52 ሚሊዮን ዶላር ወጭ ሆኖበት እስከ 138 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ይጠበቃል በብሮድካስት እና በሶሺያል ሚዲያ 6500 ሰዓታት በቀጥታ ይሰራጫል ሄይዋርድ ስታድዬም በ200 ሚሊዮን ዶላር የተገነባ ነው

              በአሜሪካዋ ዩጂን ከተማ ለሚካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የቀሩት ቀናት ከ100 ያነሱ ናቸው፡፡ የዩጂን ከተማ አስተዳደር ለሻምፒዮናው ባደረገው አጠቃላይ ዝግጅት ከ52 ሚሊዮን ዶላር በላይ በጀት ያወጣ ሲሆን ከመስተንግዶው ለአሜሪካ ኢኮኖሚ ከ138 ሚሊዮን ዶላር በላይ ያልተጣራ ገቢ እንደሚገኝ ተገምቷል፡፡
የዩጂን ከተማ  ባለስልጣኖች እና የቱሪዝም ባለሙያዎች የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ወደ አሜሪካ መምጣት ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖ ከፍተኛ በመሆኑ በዓለም አትሌቲክስ ያለውን እድል ለመጠቀም እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የዩጂን ከተማ ሻምፒዮናው በሚካሄዱባቸው ቀናት ከመላው ዓለም ከ30ሺ በላይ እንግዶችን ትጠብቃለች። ሻምፒዮናው በዓለም አቀፍ የብሮድካስት ኩባንያዎችና በማህበራዊ ሚዲያ ከ6,500 ሰአታት በላይ ቀጥታ ስርጭት እንደሚኖረው የሚጠበቅ  ሲሆን በዓለም ዙርያ ወደ 1 ቢሊዮን ለሚጠጉ አትሌቲክስ ተመልካቾች እንደሚደርስ ተገምቷል፡፡ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው  በ49 የውድድር መደቦች በሚካሄዱ ውድድሮች 200 አገራትን የወከሉ ከ2000 በላይ አትሌቶች ይሳተፋሉ፡
ዩጂን የአሜሪካ አትሌቲክስ መናሐርያ ከተማ መባሏ ያለምክንያት አይደለም፡፡ በመጀመርያ ሁለቱ የዓለማችን የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያዎች ናይኪ እና ሬይቡክም ዋና መቀመጫቸውን በከተማዋ  አድርገዋል። የአሜሪካ ኦሎምፒክ ቡድን ላለፉት 4 ኦሎምፒያዶች የማጣርያ ውድድሩን  በከተማዋ ያካሄደ ሲሆን ታላቁ የሄይዋርድ ስታድዬም ከ12 በላይ የአሜሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎችን ያስተናገደ፤ የፕሮፎንታይኔ ክላሲክ እና የዳይመንድ ሊድ ውድድሮችን በየውድድር ዘመኑ የሚዘጋጅበት ዘመናዊ የስፖርት መድረክ ነው፡፡ ሻምፒዮናውን የሚያስተናግደው በዩኒቨርስቲ ኦፍ ኦሬጎን የሚገኘው ሄይዋርድ ፊልድ በሰንሰለታማ ተራራዎች፤ ጥቅጥቅ ባሉ ደኖች እና በአስደናቂ መልክዓምድሮች የተከበበ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮችን ለማስተናገድ ሙሉ ለሙሉ በተደረገለት እድሳት ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጭ ሆኖበታል፡፡ ስታድዬሙ አትሌቶች ባፈለቁት ሃሳብ ለአትሌቶች ምቹ ሆኖ የተገነባ ፤ የላቀ ምህንድስና የሚታይበት፤ ዘመናዊ ስነህንፃን የሚያንፀባርቅ እና አጠቃላይ ቅርፁ የከተማዋን መልክዓምድር የሚገልፅ ነው፡፡
የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከዓለም ዋንጫ እና ከኦሎምፒክ ቀጥሎ የሚታይ የዓለማችን ግዙፍ የስፖርት መድረክ ሲሆን የ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አዘጋጅ አሜሪካ ዓለምን በስኬታማ መስተንግዶ ለማስደሰት በጉጉት እየጠበቀች ነው፡፡ አሜሪካ በዓለም አትሌቲክስ ላይ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ የምትታወቅ ሲሆን በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በምታስተናግደው ሻምፒዮናው ለአትሌቲክስ ስፖርት በሚዲያ ሽፋን፤ በገቢ እና በውድድር የጥራት ደረጃ ከፍተኛውን ስኬት እንደሚገኝ ተጠብቋል፡፡ በሻምፒዮናው መስተንግዶ የሚገኙ ስኬቶችና የሚመዘገቡ ውጤቶች በቀጣይ በቡዳፔስት ለሚዘጋጀው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እንዲሁም በ2024 ላይ የፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ ለምታካሂደው 33ኛው ኦሎምፒያድ ልዩ ነፀብራቅ እንደሚፈጥርም ተወስቷል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በኦሬጎን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው አዘጋጅ ኮሚቴ ያዘጋጀው ሎጎ በጥንቃቄ መዘጋጀቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሎጎው የዓለም አትሌቲክስ ማህበርን ኦፊሴላዊ ሎጎ፤ ከሄይዋርድ ስታድዬም አንድ ጎን ጋር በማዋሃድ የተሰራ ሲሆን የያዛቸው ቀላማትም በጥንቃቄ ተመርጠው ተዘጋጅቷል። በሎጎው ላይ የሚገኘው የወይንጠጅ ቀለም የውድድሩን ዓለም አቀፋዊነትን የሚገልፅና የዓለም አትሌቲክስ አፍቃሪዎችን የሚወክል ነው፡፡
ሰማያዊው በዓለም አትሌቲክስ ውድድሮች ላይ ከፍተኛ ውጤት የምታስመዘግበውን አሜሪካን ሲመስል፤ አረንጓዴው ቀለም ደግሞ የሻምፒዮናውን አዘጋጅ ከተማ ኦሬጎን የሚያንፀባርቅ እንደሆነ ደማቁ ቀይ ቀለም ደግሞ የሻምፒዮናውን አስተናጋጅ ስታድዬም ሄይዋርድ ፊልድን እንደሚያመለክት ተገልጿል፡፡

Read 7878 times