Print this page
Saturday, 09 April 2022 00:00

“እኛም እንዴት እንደቻልነው ግራ ገብቶናል!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)


             እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እባክሽ ፍቅሬ ሆይ ተመከሪ
እባክሽ ፍቅሬ ሆይ ተመከሪ
ከይሉኝታ ጋራ ጡርን ፍሪ
የምትል አሪፍ ዜማ ነበረች፡፡ አለ አይደል... ሴትዮዋ የመጀመሪያውን ደረጃ ለስለስ ያለ ምክር አልቀበል ብላ ነው “እባክሽ...” ወደማለት የገባው...ወደ ልመና በሉት፡፡ ዘንድሮ እንዲህ አይነት ነገር ላይ ከደረስን የከረምን አይመስላችሁም! ፖለቲካ የማያውቅ ቦተሊከኛ፣ ራሱ ቢቀሰቅሱት፣ ቀዝቃዛ ውሀ ቢቸልሱበት ራሱ አልነቃ ያለ አንቂ፣ ትንታኔ መስጠት ማለት ይህንንም፣ ያንንም መውቀጥና ክፉ ቀለም መቀባባት የሚመስለው ተንታኝ በበዛበት በዚህ ዘመን፣ ምክር መቀበል ይቅርና ለመምከር የሚሞክር ማግኘቱ አስቸጋሪ ነው... የምር! ይሉኝታ የሚሉትን ነገርማ እርሱት፡፡ በባሌም ይሁን በቦሌ በየት በኩል እንደወጣ ግራ ገብቶናል፡፡ አይደለም እኛ ተራ ህዝቦች ዘንድ እንደልብ ሊገኝ  ወደ ፈጣሪ መሄጃ መንገዱን ያመቻችሉናል ባልናቸው ዘንድ እንኳን ብርቅ እየሆነ ነው፡፡
አሀ...ልክ ነዋ! ወይ ለይቶልን ዓለም አቀፍ የአፋልጉኝ ማስታወቂያ እንዳናወጣ፣ ዓለማችን እንደ ዘንድሮ የይሉኝታ ድርቅ መትቷት አያውቅም!  የዩክሬይኑን ጦርነት እዩልኝማ፡፡ ይህን ያህል ውድመት ደረሰ፣ ይህን ያህል አውሮፕላን ተመትቶ ወደቀ  ከሚሉት የዕለት ተዕለት ዜናዎች ባለፈ አጋጣሚውን ተጠቅሞ አንዲትን ታሪካዊ ሀገር ለማጥፋት የአውሮፓውያኑ ርብርብ የሚገርምና አሳፋሪ ነው፡፡ የምር...ሩስያ ምክንያቷ ምንም ይሁን ምን ወረራውን ህጋዊ አያደርገውም፡፡ ግን ደግሞ አውሮፓውያኑ በኢራቅ በሉት፣ በአፍጋኒስታን በሉት ከአሜሪካ ጋር በአንድ እንትን፣ እንትን ሲሉ አይደለም እንዴ የከረሙት፡፡ በሺዎችና በአስር ሺዎች ሲያልቁ ቅም ብሏቸው ያውቃል እንዴ! የትኛው የሞራል ከፍታቸው ነው እነሱን ቀጪ፣ ሌላውን ተቀጪ ለማድረግ የሚያበቃቸው! የይሉኝታ ነገር ሲነሳ ለነገሩ አነሳነው እንጂ፣ እኛ ራሳችን ስንት በየቀኑ እየጨመረና እየተባዛ ያለ ጉዳይ አለብን!  
እናላችሁ... “ከይሉኝታ ጋራ ጡርን ፍሪ...” እንደተባለው ጡርን የሚፈራ እንኳን ይጥፋ!  ሌላ ወሬ ካወራን እኮ ከመሰንበት አልፈን እየከረምን፣ እየከራረምን ነው፡፡ ስሙኝማ...እንግዲህ  ጨዋታም አይደል... አሁን ጉዳዩ በቀጥታ ባይመለከተንም፣ ዊል ስሚዝ፣ ክሪስ ሮክን ያላሰውን ጥፊ ሳንተነትን ዝም ብለን እናልፍ ነበር! ልክ ነዋ...ለምሳሌ ስለዩክሬይኑ ጦርነት እንደ እኛ በየዩቲዩቡ፣ በየምናምኑም ጉደኛ፣ ጉደኛ ትንታኔ የሚሰጥ ይገኛል? (“ኔቶ የተባለች ሀገር...” ያልከው ዩቲዩበር፣ ከአክብሮት ጋር፣ ያሳሳተህን የፌስቡክ ገጽ ለዙከርበርግ ሹክ በልና አሳግደውማ! አሳስተውህ ነው፣ አይደል? “አሳሳቱኝ...” እንጂ “ተሳሳትኩ...” የሚል ሰው የማይሰማባት ሀገር እየሆነችብን ስለሆነ ነው!) እናላችሁ...የዊል ስሚዝን ጥፊ እንደ ግጭት መፍቻ ፍቱን መፍትሄ ልንወስደው የምንሞክር ስለማንጠፋ ነው፡፡
“እባክህ ሴትየዋ አስቸገረችኝ፡፡”
“የትኛዋ ሴትዮ?”
“ሚስቴ ነቻ! ማንን ልልህ ነው?”
“እንዴት ነው ያስቸገረችህ?”
“ብቻ ስገባ ስወጣ እኔን የምትለክፍበት ሰበብ አታጣም፡፡ ስልችት ነው ያለኝ፡፡”
“እና ዝም እያልካት ነው?”
“ምን እንዳደርጋት ነው የምትፈልገው?”
“አንድ ቀን በሩን ከውስጥ በኩል ግጥም አድርገህ ዘግተህ እንደ ዊል ስሚዝ በቃሪያ ጥፊ ጆሮዋን አታበርረውም!”
እንዲህ አይነት ምክር የሚሰጥ ሰው የለም ብላችሁ የምታስቡ ከሆነ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ አይደላችሁም ማለት ነው! አይደለም ለእሱና ለእሷ፣ ለአንዳንድ የቦተሊካ ቡድኖች ነን ለሚሉት የስትራቴጂ ሰነድ ምዕራፍ አንድ ቁጥር አንድ ድንጋጌ ሊሆንም ይችላል፡፡ (ልክ ነህ ወዳጄ...በቦተሊካውም ውስጥ እንደዚህ አንገታችን  ላይ የደረሱ ብዙ ነገሮች አሉ ብሎ ʻለማሳበቅʼ ያህል ነው፡፡)
እናላችሁ... ዳያስፖራዎቻችን እንደገረማቸው... አለ አይደል... የዕውነትም ሳናውቀው ስፔሻል ሰዎች ሳንሆን አይቀርም፡፡ ደግሞላችሁ... የኑሮ መወደድ ችግሩ ዝቅተኛው ኤኮኖሚ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ህዝብ ተሻግሮ መካከለኛ መደብ የሚባለውንም እያስማጠ ያለ ችግር ሆኖም፣ እንደበፊቱ በባዶ መሶብና በተራገፈ ጆንያ...አለ አይደል... “ለማን ይድላው ብዬ ነው የቸገረኝ የምመስለው!” ብሎ ቲራቲር አልለቀቀንም፡፡ ኮሚክ እኮ ነው... ለመግለጽ እንኳ የሚያስቸግር የኑሮ ጫና ተከምሮብን  የደላን ማስመሰል አሪፍ አይደለም፡፡ እንደውም ባያስጠረጥረን ነው!  “ሰውየዋ እኮ አብራ ተለጥፋ በየወሩ ይሰፈርላታል አሉ!” መባል ይመጣል፡፡
የምር አስቸጋሪ ነገር እኮ ነው፡፡ ሰው የዜግነት መብቱ የሆነውን የነዋሪነት መታወቂያ ለማሳደስ ከሌሊቱ አስር ሰዓት ሄዶ የሚሰለፍበት በምን እዳው ነው! ተቋማቱ ደግሞ የታደሰ መታወቂያ ካልሆነ እያሉ ጉዳይ ማስፈጸም አስቸጋሪ ነው፡፡ ኮሚክ ነገር እኮ ነው...ሰዉ እኮ ሳያሳድስ የቆየው በዋናነት በስንፍናው ወይም በመሳሰለው ሳይሆን በአዋጁ የተነሳ ነው፡፡ እናማ...ራሱ የፈጠረው ባልሆነ መጓተት፣ ሌላው የኑሮ ጣጣ ሳያንስ ለምን እንደሚጉላላ ግራ የሚገባ ነው፡፡  ሁኔታው በሚገባ በስነ ስርአትና ኑሮ አቅሙን እየተፈታተነው ያለ ህዝብ ሳይጉላላ እስኪፈታ፣ ያልታደሰው መታወቂያ በሁሉም ስፍራ  ጥቅም ላይ የሚቆይበት ለሁሉ የሚሠራ መመሪያ ቢጤ መኖር ነበረበት፡፡ አንዱ ባንክ ሲሰጣችሁ፣ ሌላው ባንክ በገዛ አንጡራ ፍራንካችሁ እየከለከላችሁ ምን የሚሉት አሠራር ነው! (“ብለው፣ ብለው በአደራ እንዲያስቀምጡልን በሰጠናቸው በገዛ ገንዘባችን መታወቂያ ምናምን እያሉ ያስፈራሩናል እንዴ!” ያልከው ወዳጃችን... “አልገድልህምን ምን አመጣው?” የምትለዋን ነገር ልታስታውሰን ምንም አልቀረህ!)  
ብቻ...አለ አይደል... ሀገሪቷ  የዘንድሮዋ ጦቢያ ነችና በመገረማችን ትዝብት ላይ የምንወድቀው እኛው ራሳችን ነን፡፡ ግን እንደው ለጨዋታው ያህል እንኳን ጡር የሚባል ነገር መፍራት በቃ ሙሉ ለሙሉ ቀረ ማለት ነው!
ዳያስፖራ ያሉ ወዳጆቻችን ግራ ግብት ነው ያላቸው፡፡ የእኛን ሀገር ኑሮ በዚህ አይነት ፍጥነትና ክብደት መወደድ በኤኮኖሚውም ሆነ በሌሎች የእውቀት ዘርፎችም ምክንያት ቢፈልጉለት መልስ ሊያገኙለት ቸግሯቸዋል። እናላችሁ... ይጠይቁናል “እንዴት ነው የቻላችሁት?” እያሉ ይጠይቁናል፡፡ እኛም እንመልሳለን... “ይድረስ በሰሜንም፣ በደቡብም፣ በምዕራብም በምስራቅም ለምትገኙ ውድ ዳያስፖራዎች...እኛም እንዴት እንደቻልነው ግራ ገብቶናል!” ስሙኝማ...አሁን በዚህ ዘመን እንዲህ እጥር፣ ምጥን፣ ቅልብጭ ያለች መልስ ማግኘት ይቻላል? አሁን ሁሉ ነገር ውስጥ ድንቅር እያሉ የሚያስቸግሩን ቦተሊካ፣ “የእኛ ቡድን፣ የእነሱ ቡድን...” ቅብጥርስዮ ጣጣዎች የሌሉበት መልስ... “እኛም እንዴት እንደቻልነው ግራ ገብቶናል!” እናም ዳያስፖራዎች ሆይ... የቻልንበትን ተአምር ምንነት ስንደርስበት እንነግራችኋለን...ታገሱንማ!
“ስማ በህልሜ ምን እንዳየሁ ብነግርህ አታምነኝም፡፡”
“ብቻ ጂ ፕላስ ፎር ህንጻ ውስጥ ስንፈላሰስ እንዳትለኝ!”
“አላወቅኸውም፡፡”
“አሁን ገባኝ...አንተም ለቪ ኤይት በቃህ እንዴ?”
“አይደለም...”
“እና ንገረኛ!”
“እግሬን ዘርግቼ ተንሰራፍቼ ጥሬ ሥጋ በቆጭቆጫ ስቀጨቅጨው አላይ መሰለህ!”
“አትለኝም! አንተ እኮ ድሮም እድለኛ ነህ!” (ቂ...ቂ...ቂ...)
እናላችሁ... እንዲህ የምንባባልበት ዘመን አይመጣም ብሎ ማለት አይቻልም። ቂ...ቂ...ቂ... እናም “እኛም እንዴት እንደቻልነው ግራ ገብቶናል!” ለማለት ያህል ነው፡፡
እባክሽ ፍቅሬ ሆይ ተመከሪ
እባክሽ ፍቅሬ ሆይ ተመከሪ
ከይሉኝታ ጋራ ጡርን ፍሪ
እናም ሥራዎቻችሁና ውሳኔዎቻችሁ ህይወታችን ላይ በተለያዩ ደረጃዎች ተጽእኖ የምታሳድሩ ክፍሎች፤ ግዴላችሁም እኛን እንኳን “ምስጋና አታውቁም፣” ብትሉን ለነፍሳችሁ እንዲሆን... ከይሉኝታ ጋራ ጡርን ፍሩማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1277 times