Print this page
Wednesday, 13 April 2022 17:24

የማይጨው ጦርነት 86ኛ ዓመት!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

 “የኢትዮጵያ ጦር ለምን ማይጨው ላይ ተሸነፈ ብዬ ብዙ ጊዜ አስብ ነበር፤ የተሸነፈው ባለመሰልጠናችን ነው፡፡” - ብ/ጄነራል መንግስቱ ነዋይ
                     የቀድሞ የኢትዮጵያ መከላከያና ፖሊስ ጀግኖች (ቬትራን) ማህበር በማይጨው ጦርነት የተካሄደበትን 86ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ፣ መጋቢት 25 ቀን 2014 ዓ.ም በካፒታል ሆቴል አንድ ፕሮግራም አካሂዷል፡፡ በፕሮግራሙ ላይ በ1956 እና በ1970 ዓ.ም ከሞቃዲሾ ሠራዊት ጋር በተደረጉ ውጊያዎች  የተሳተፉ መኮንኖች፣ ባለሌላ ማዕረጎችና ወታደሮች እንዲሁም የአርበኛ ቤተሰቦች ተገኝተዋል። በፕሮግራሙ የመቅደላ፣የመተማ፣ የአድዋና የካራማራ አውደ ውጊያዎች የተዳሰሱ ሲሆን የፕሮግራሙ ምክንያት የሆነው የማይጨው አውደ ውጊያም ጎላ ብሎ ታይቷል።
በርዕሰ ጉዳዩ የመክፈቻ ሃሳብ አድርጌ ያቀረብኩት አቶ ጳውሎስ ኞኞ ከአርባ ስድስት ዓመት በፊት “ጣሊያኖች 40 ዓመት ሙሉ የአድዋ ቂማቸውን ይዘው ለጦርነት ሲዘጋጁ፣ እኛ እውነተኛውን ታሪክ ሳናወራ 50 ዓመት አለፈ” በማለት የገለጠውን ሃሳብ ነው። ዛሬም ቢሆን ታሪካችንን የመናገር ለአዲሱ ትውልድ የማሳወቅ አዝጋሚነታችንና ግድየለሽነታችን በግልፅ የሚታይ ነው።
ጣሊያኖች የቅኝ ግዛት ፍለጋ የተነሱት ከፈረንሳይና ከእንግሊዝ ከሌሎችም ጋር ሲነፃፀር በጣም ዘግይተው ቢሆንም፣ የካቶሊክ እምነትን ለማስፋፋት ካላቸው ፍላጎት ጋር ሲታይ ግን ወደ ኋላ 500 ዓመት እንዳለው፣ ዶ/ር አበበች ለቺሳ በጥናታቸው አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያዊያንን በጦርነት ለማሸነፍ አንችልም ብለው ያመኑት ጣሊያኖች፣ በመላ አገሪቱ በዋናና በትናንሽ ከተሞች ባቋቋሟቸው ቆንስላዎች አማካይነት ሕዝቡን ከመንግስቱ፣ መኳንንትና  መሳፍንቱን ከንጉስ ነገስቱ ለመነጠል ብዙ ሰርተዋል። ሐኪም፤ መሐንዲስ፣ የሃይማኖት  ሰባኪ፣ የመልክአ ምድር አጥኚ ወዘተ በሚል ስያሜ በየአካባቢው የበተኗቸው ዜጎቻቸው ዋናው ሥራቸው፣ ለጦርነት የተመቸ ሁኔታ መፍጠር ነበር።  ኮራዞሊ ስለ ፕሮፓጋንዳ ዘመቻው እንዲህ ይላል፤ አብዛኛው ሥራችን በትግሬና በአማራ መካከል “ጥላቻ እንዲፈጠር ማድረግ ነበር፡፡”
አንጀሎ ዶል በኮ  የተባለው ፀሐፊ፣ ለስልሳ አራት ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ የኖረው ጂኦሌጂስቱ ቱሊያ ፓስተር፣ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተዘዋወረ በሰራባቸውና በኖረባቸው አካባቢዎች፣ የሚያጋጥመውን ወንዝና ተራራ መለየት፤ ወንዙን በየትኛው መልኩ መሻገር እንደሚችል ማመልከት ብቻ ሳይሆን፤ መኳንንቱ በንጉስ ነገስቱ ላይ እንዲያምጹ መቀስቀስ እንደነበርና ጦርነቱ በተከፈተበት ጊዜ መዝመት ከነበረበት ውስጥ  ሶስት እጁ አለመዝመቱን፤ እንደ ደጃዝማች አያሌው ብሩ አይነቱ፣ የጣሊያንን ጦር ተቀብሎ ማስተናገዱን እንዳረጋገጠለት ፅፏል።
ከዚህ ጎን ለጎን የአስመራ አገረ ገዢ የነበረው ቀደም ሲል የጠቀሱት ከራዚሊ፣ በአፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግስት የተጀመረውን የራዘ እና አደል ዘመቻን ለጦር ኃይል ጥናት ሲጠቀምበት እናገኘዋለን።
ዋጅራቶችና ራያዎች ወደ አፋር እየወረዱ ከብት ይዘርፋሉ፤ ራያዎች የገደሉትንም ይሰልባሉ፤ ለእነሱ የወንድነትና የጀግንነት ማረጋገጫ፣ ለትዳር ብቁ መሆን ማስመስከሪያ ነው። ይህ “ራዘ ዘመቻ” በመባል ይታወቃል። አዳሎች እንደ  ራያዎች ባይሰልቡም፣ ወደ ደጋው እየወጡ ከብት ይዘርፋሉ፤ ሰው ይገድላሉ። በአካባቢው ጦርነት በመቀስቀስ አንዳንድ ጊዜም፣ በወሬ ጦር እንድልክ በማድረግ፤ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በምትወርበት ጊዜ አምስት መቶ ሺህ ጦር ሊኖራት እንደሚገባ ለማወቅ እንደተጠቀመበት መጠቆም  ለጥናት  ያስፈልጋል።
ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ለመውረር እየተዘጋጀች መሆኗን የንጉሱ መንግስት አምስት ዓመት ቀደም ብሎ ቢያውቅም፣ ህዝቡ በአድዋ ድል ይመካ በነበረ የኢትዮጵያ መንግስት፣ ጦርነት እየመጣ እንደነበር ለህዝብ ለመናገር መቸገሩን ራስ እምሩ ይመሰክራሉ።
የመንግስቱ ችግር ይህ ብቻ አልነበረም፤ በጌምድርና የጁ በራስ ወሌ፤ ጎጃም በራስ ሀይሉ ተክለሃይማኖት፤ ጎንደር በራስ ጉግሳና ወሎ በልጅ እያሱ ሞት የተነሳ አኩርፈው ስለነበር በዘመቻው ላይም የሚጠበቅባቸውን አለማድረጋቸውን፣ ደጃዝማች ከበደ ተሰማ፣ #የታሪክ ማስታወሻ; በተባለው መፅሐፍ መግለጣቸው ይታወሳል።
ጦሩ ወደ ግንባር እየተጓዘ ባለበት ጊዜ ለምሳሌ፣ ከራስ ሙሉጌታ ሠራዊት ውስጥ በየቀኑ ከ15 እስከ 20 ሰው ይገደል ነበር። ራስ ሙሉጌታም ከጣሊያን መሳሪያ ተቀብለው ከወጡ ሰዎች ጋር ተዋግተው 200 የሚሆኑትን ተማራኪዎች በጉቦ ተኩሰዋቸዋል። ከሳቸው ስር የዘመቱት ደጃዝማች መሸሻ በአንድ ጓደኛቸው መገደል 1200 ሰዎች ገድለው ቆቦን አጥፍተዋል፡፡ እንዲህ አይነቱ ድርጊት ቀድሞም የሻከረውን የህዝብና የመንግስት ግንኙነት የበለጠ እንዲሻክር ማድረጉ መዘንጋት የለበትም። ሌላው የራስ ሙሉጌታ ከጦር ሚኒስቴርነት መነሳት መሆኑም ሊታወስ ይገባል።
ይህ ብቻ ግን አይደለም። የኢትዮጵያ መንግስት ድንበር እየተሻገሩ በቅኝ ግዛታችን ሰዎች ላይ ጥቃት የሚያደርሱትን ዜጎቹን መከላከል  አልቻለም በማለት ፈረንሳይ እንግሊዝና ጣሊያን ወደ ኢትዮጵያ የጦር መሳሪያ እንዳይገባ በ1923 ማዕቀብ መጣላቸው፤ ለኢትዮጵያ የጦር መሳሪያ ያቀርቡ የነበሩ እንደ ቤልጂየም ያሉ ከማቅረብ መቆጠባቸው ከዋና ዋና ችግሮች አንዱ ሆኖ የሚታይ ነው። በዚሁ ክልከላ ምክንያት ኢትዮጵያ ገንዘቧን ከፍላ ያስመጣችው ሰባት ሚሊዮን ጥይት፣ 2850 ከባድ መሳሪያና 1400 ጠመንጃ ጅቡቲ ላይ ተይዞ ቆይቶ  ለጣሊያን መሰጠቱንም እናስታውሳለን።
ትጥቅና ሰራዊት ሲታይ፤ ጣሊያን 509.700 የሰለጠነ እግረኛ ወታደር፣ 25 ሺህ የጦር መኮንን፣ 2525 መትረየስ፣ 2608 መድፍ፣ አንድ ቢሊዮን 28 ሚሊዮን 816 ሺህ ልዩ ልዩ ጥይቶች ነበሯት። ታንኩን የጦር አውሮቶፕላኑን፣ በቦምቡንና የመርዝ ጋዙን ሳይጨምር ማለት ነው። ኢትዮጵያ ድግሞ 700 ሺህ ያልሰለጠነ ወታደር፣ 200 መድፍ፣ 3500 መትረየስና 150 ሚሊዮን ጥይት ነው የነበራት። ይህን “ለአንድ ሺህ ወታደር የሚበቃ አንድ አይነት ጠመንጃ እንኳ አልነበረንም” ከሚለው የራስ እምሩ ምስክርነት ጋር ስናገናኘው፣ ልዩነቱ የሰማይና የምድርን ያህል የተራራቀ እንደነበር እንረዳለን።
ቀደም ብለው በኢጣሊያ ሶማሌ አንድ አዋሳኝ የሚገኙ ብዙ ቦታዎችን የያዙት ጣሊያኖች፣ በይፋ ጦርነት የጀመሩት መስከረም 21 ቀን 1928 ዓ.ም ነው፤ ውጊያውንም የከፈቱት በአራት አቅጣጫ ነው። አንደኛው  ከአስመራ ተነስቶ አዲግራት መቀሌ አዲስ አበባ፣ ሁለተኛው ከአስመራ ተነስቶ አዲኳላ፣ ጎንደር፣ ጎጃም፣ ወለጋ ኢልባቡር፤ሶስተኛው ከሞቃዲሾ ተነስቶ ቀብሪ ድሐር፣ ጅጅጋ፣ ሐረር፣ ድሬድዋ፤ አራተኛው ከሞቃዲሾ ተነስቶ ደሎ ነገሌ፣ ቦረና፣ ደቡብ ኢትዮጵያን እንዲቆጣጠር ነው።
ጦሩ ወደ ግዳጅ በሚወጣበት ጊዜም አሰላለፉ ከፊት ባንዳ፣ከመሐል ከኤርትራ ከሶማሊያና ከሊቢያ የቅኝ ግዛት የመጣ ወታደር ከጀርባ ወይም ደጀን ኃይሉን ጣሊያኖችን በማድረግ ነበር። ይህ የመጀመሪያ ጉዳይና ሟች ኢትዮጵያዊያን እርስ በእርስ  በማድረጉ በሴራው ላይ የነቁ አርበኞች ደጃዝማች በላይ ዘለቀ፣ ጥዝጥዝ በሚል ስልት፣ ሠራዊታቸው ጣሊያኖችን ብቻ እየመረጠ እንዲገድል በማድረግ፤ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ተመሳሳይ መንገዱ በመከተል፣ራስ አሞራም ውብነህ ደግሞ ጥቁር የገደል ግደዩ አያቆርጠርለትም የሚል አዋጅ በማወጅ፣ ጥቃቱ ሙሉ በሙሉ በወራሪው ኃይል ላይ እንዲያርፍ ማድረጋቸውን በአፅንኦት መግለፅ እወዳለሁ።።
የማይጨው የውጊያ እቅድ የወጣው ንጉሱ ሐዩ በተባለ ቦታ በቆዩበት ጊዜ ነው። እቅዱን በማዘጋጀት ስራ ላይ  እነራስ  መንገሻ የንጉስ የጦር አማካሪዎች እነ ደጃዝማች ወንድራድ፣  እነሊጋባ ጣሰውና ሌሎች የጦር መኮንኖች የበታች ሹማምንቶች ተሳታፊ ሆነዋል።
በዚህ መሰረት አንደኛው ምድብ በራሳቸው በንጉሰ ነገስቱ የሚመራ ሲሆን ከእሳቸው ሥር  ቀኛዝማች መኩሪያ ባንትይርጉ አሉ። ዘመናዊ ውትድርና ትምህርት ያገኘው የክብር ዘበኛ ጦር የተመደበው እዚህ ነው። ሁለተኛው  ማለትም በግራ በራስ ጌታቸው አባተ የሚታዘዘው ጦር ሲሰለፍ፣ በቀኝ በራስ መንገሻ ዮሐንስ የሚመራ ጦር እንዲንቀሳቀስ ተደረገ። በመሐል የሚገኘውን ጦር እንዲመሩ የታዘዙት  ራስ ካሳ ኃይሉ ናቸው። በጦርነቱ ላይ አንዳንድ ፀሐፊዎች፣ እስከ ሰላሳ አራት ሺህ ሰው እንደተሳተፈ ሲጠቁሙ፣ ንጉሱ ግን “ሕይወቴ የኢትዮጵያ ርምጃ; በተባለው መፅሐፋቸው፤ ሃምሳ አንድ ሺህ እንደሆነ ገልጸዋል።
ጦርነት ለሊት 10 ሰዓት አካባቢ ነው የተጀመረው። ንጋት ላይ ኢትዮጵያ ጦር ከፍተኛ ጥቃት እያደረሰ ምሽግ እያስለቀቀ ነበር። ጣሊያኖች የሚመኩበትን “ፑስቴሪያ” የተባለውን ጦራቸውን እያርበደበደው ነበር። ሁለት ሰዓት ላይ 70 የጣሊያን የጦር አውሮፕላኖች መጥተው መደብደብ ጀመሩ። ይህም ወደ ኋላ እንዲመለስ ወይም እንዲያፈገፍግ  አላደረገውም። በወንድሙ መገደል ተበሳጭቶ የራሱን የወጣቶች ጦር ያደራጀው አብቹ (የሰላሌው) ጦር በአንድ ወገን ገብቶ፣ የጣሊያንን ጦር ወገቡን ሰብሮ ይዞት ነበር።
“ውጊያው በጣም ከበደን፤ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት የሰባተኛው ብርጌድ አዛዥ ተገደለ። የ24ኛው ብርጌድ አዛዥ እርዳታ መጠየቂያ ርችት ተኮሰ፤ ወደቀ። ከሐረርጌ የመጡ የጦር ትምህርት የተማሩ ወጣቶች የ8ኛ መድፈኛ ባታሊያንን ወታደሩን ብቻ ሳይሆን መኮንኖችንም ፈጇቸው” በማለት ጣሊያኖች የሰጡትን ምስክርነት ማየቱ መልካም ነው።
የኢትዮጵያ ጦር ለድል እየተቃረበ እያለ ሃገራቸውን በከዱና ለጣሊያን ባደሩ የአካባቢው ሰዎች ከጀርባ ተወጋ። ድል አድራጊነቱ ተነጠቀ። “የገዛ ወንድማቸውን ከጀርባ ገብተው ጨፈጨፉት፤ አዎ እነዚያ ከሐዲዎች ጦርነቱን ወስነዋል” በማለት ይገልጠዋል፤ #የአበሻ ጅብዱ; ደራሲ፡፡
ጦሩ ተበታትኖ እየተመለሰ ባለበት ጊዜ አሸንጌ ሐይቅ ላይ ጣሊያኖች 150 ጦር አይሮፕላኖች አዝምተው ያደረሱበት ጭፍጨፋ የግድ መጠቀስ ያለበት ጉዳይም ነው፤ የተከፈለውን መስዋዕትነት ለመረዳት። ከመስከረም እስከ መጋቢት በሰሜን ግንባር የተደረገው ጦርነት፣ ማይጨው ላይ በተሸናፊነት መቋጨቱ ሁለት ዋና ዋና ውጤቶች እንዲከሰቱ  አድርጓል።
አንደኛው የንጉሱ መሰደድ ነው። ቀደም ሲልም ከታዩ ሁኔታዎች በኋላም የአንዳንድ መኳንንቶች ወደ ጠላት መግባት ሲታይ ባይሰደዱ ኖሮ፣ የንጉሱ መማረክ ወይም መገደል የማይቀር ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ተማርከው ቢሆን ኖሮ፣ ጣሊያኖች ቀደም ሲል ያቀርቡት ከነበረው የመደራደሪያ ሃሳብ አንጻር ለስሙ  የሚቆሙ ንጉስ  ሆነው፣ የቅኝ ተገዥነቱን ዘመን የተራዘመው ያደርጉት ነበር።
ሁለተኛው የፊት ለፊት ጦርነቱ ወደ ደፈጣ ውጊያው እንዲቀየር ማድረጉ ሲሆን የንጉስ ማዕከልነት እንደተጠበቀ ሆኖ እያንዳንዱ አካባቢ የራሱን የጦር መሪ ማውጣትና የጦር ሜዳውንም በመላ ኢትዮጵያ የተዘረጋ እንዲሆን ማድረጉ ነው።
በዚህ ጊዜ ከተፈጠሩ የጦር መሪዎች ከጎጃም ደጃዝማች በላይ ዘለቀን፣ ደጃዝማች ነጋሽ በዛብህን፤ ከሲዳሞና ከጋሞ ከፋ ደጃዝማች ተስፋዬ ወልዴን፣ ከኤልባቡር ፊውታራሪ አበባን፤ ከወለጋ ልጅ ዳርጌ ፈይሳን፤ ከግንደበረትና አካባቢው ብርጋዴር ጄነራል ጃጋማ ኬሎን፤ ከወሎ ጀነራል ኃይሉ ከበደ፣ እሳቸው ከተገደሉ በኋላ ባላምባረስ ግዛው አማረን፤ ከትግራይ ደጃዝማች አቢይ ከሳን፤ ከጎንደር ራስ አሞራው ውብነህ፤ከሴቶች ወይዘሮ ልከየለሽ በየነንና ወይዘሮ ከበደች ስዩምን መጥቀስ ይቻላል። በመረጃ ወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌ አሉ።
ይህን ጉዳይ የምጨርሰው በብርጋዴር ጄኔራል መንግስቱ ነዋይ ንግግር ነው፤ “የኢትዮጵያ  ጦር ለምን ማይጨው ላይ ተሸነፈ ብዬ ብዙ ጊዜ አስብ ነበር፤ የተሸነፈው ባለመሰልጠናችን ነው፡፡”
እኔም እላለሁ፡፡ ሁልጊዜ የምንጠቃው ባለንበት ስለምንረግጥ ነው።

Read 1399 times