Wednesday, 13 April 2022 17:34

ጦረኞችና አርበኞች ከነፈረሶቻቸው!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)

በቀደሙት ዘመናት በተለይ በጦርነት በተቃኙት የትግል ረድፎች የጀግኖች ስም ሲወሳ፣ አብሮ የሚከተል ታሪክና ገድል ፈፃሚ አለ፡፡ ያኔ ሰዎች በአየር እሳት የሚተፋ ጀት ሳይኖራቸው፣ ሠንሰለት ጫማ ያደረገ፣ እሳት የሚተፋ ብረት ለበስ ታንክ ሳይሰሩ፣ ያኔ ነዳጅ እየጠጣ ዘይት እየላሰ የሚሮጥ ተሽከርካሪ ለጦርነት ሳይውል፣ ጀግኖች ጦር ሜዳ የሚውሉበት፣ ፈጣን አድራሽ፣ የጦር ሜዳ ጓደኛ ፈረስ ነበር፡፡
ፈረስ በጣም የተወደደና የተዛመደ ለመሆኑ ማሳያውም፣ የፈረሱ ስም፣ እንደ አባት ሁሉ፣ ከጦረኛው ጋር አብሮት መጠራቱ ነው፡፡ በተለይ በእኛ ሀገር አንዳንዶቹ የሀገራችን ጀግኖች ከአባታቸው ስም ይልቅ የፈረሳቸው ስም አብሯቸው ሲጠራ እናያለን፡፡ ለምሳሌ ራስ አሉላን  አሉላ አባነጋ እንጂ፣ አሉላ አንላቸውም፡፡ ፊታውራሪ ገበየሁን (የአምባላጌ የዐድዋ ጀግና) አባ ጎራው እንጂ፣ የአባታቸውን ስም አንጠራም፡፡ ይህ የሚያሳየን ደግሞ በጀግናው ጦረኛና በፈረሱ መካከል ያለውን ጥብቅ ቁርኝት ነው፡፡
ይህንን ቁርኝት አንዳንዴ ጦርነት በተካሄዱባቸው ጊዜያት ለጀግኖቹ በተገጠሙት ግጥሞች መካከል ብቅ የሚሉትን የፈረስ ስሞች እናያቸዋለን፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ግንባታ ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ የያዙት ራስ ጎበና ዳጨን በተመለከተ የእሳቸው ሥራቤቶች ገጠሙት በሚባለው ግጥም እንዲህ ብለዋል።
እነ ራስ ጎበና ባቀኑት ሀገር፣
ቀኝ አዝማች ግራ አዝማች ይባሉ ጀመር፣
ጎበና አባጥጉ ሆድህን አይባሰው፣
ድሮም ልማድህ ነው እያቀናህ ለሰው፡፡
እንግዲህ ጎበናን ከፈረሳቸው መነጠል እንደማይችል አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ሌላም ቦታ እንደዚህ ስለፈረሳቸው ተገጥሟል፡፡
ጎበና ጎበና
ጎበና ፈረሱን አማን ቢያስነሳው
ዓባይ ላይ ገታው።
ጎበና ፈረሱን ፋሌ ላይ ቢያስነሳው
 ዓባይ ላይ ገታው።
ጎበና ፈረሱን ቼቼ ቢለው
ሱዳን ላይ ገታው፡፡
በኢትዮጵያ የጦርነትና የጀግንነት ታሪክ ፈረስ ትልቅ ስፍራ ስላለው፣ ስሙም ከጀግኖቹ የተዋፅኦ ስም ጎን ለጎን ሲጠራ የኖረው “አባ” የሚለው ቅፅል  ከኦሮሞ ማህበረሰብ ወይም የወረሽሆችን ልማድ በመከተል ከ1838 ዓ.ም ጀምሮ እንደነበር ይነገራል፡፡ ስያሜው ከኦሮሚኛ አጠራር ጋር ተላምዶ እንደመጣ ይነገራል፡፡ በተለይ በዚህ ጉዳይ ላይ ስራዬ ብለው ያጠኑት ብላቴ ጌታ ማህተመ ስላሴ ወልደ መስቀል ሰፋ ያለ ፅሁፍ አቅርበዋል፡፡
ታዲያ እኒህ ሰው እንደሚሉት፤ አፄ ቴዎድሮስ “የፈረስ  ሀገር ወዴት ነው?” ብለው ራሳቸውን ከጠየቁ በኋላ ራሳቸው መልሰው “የባለቤቱ ዐይን ነው” በማለት ተናግረዋል፡፡ ይህን ማለታቸውም የፈረሱ ባለቤት ዐይኖቹን ከፈረሱ ሳይነቅል፤ እንደሚጠብቀውና እንደሚንከባከበው ለማሳየት ነው፡፡ ይሁንና ለነገስታትም ሆነ ለመሳፍንቱና መኳንንቱ የሚወጣላቸው የፈረስ ስሞች፤ የአስተዳደር የዳኝነት የፖለቲካ አፈፃፀም ብቃት፤ ትዕግስት አንዳንዴም የፈረሶቹን መልክ የሚከተል ነበር፡፡
እንደ ማሳያ የዐፄ ምኒልክ የፈረስ ስም “አባ ዳኘው”፤ አስተዳደርና ዳኝነትን የሚያሳይ ሲሆን ውስጣዊ መልዕክቱ ሲመረመር ደግሞ፤ “የሁሉም ጌታ ነህ፤ አንድ አድርገህ ግዛቸው፤ በትክክል አስተዳድራቸው” ማለት እንደሆነ ብላቴ ጌታ ማህተመ ስላሴ ወልደ መስቀል ይናገራሉ፡፡
“አባ ሻንቆ” የሚለውን የራስ ሚካኤልን የፈረስ ስም ብናይ ደግሞ የፈረሱን መልክ ጠቋሚ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ “አባ ምቹ፣ አባ መስጠት፣” በቅድመ ተከተል ፀሐፊ ትዕዛዝ ሀይሌ ወልደ ሩፋኤልና ባላንበራስ ታፈሰ አደፍርስ የተሰጧቸው የፈረስ ስሞች፣ ለጋስነትና ችሎታን  የሚያሳይ የተፈጥሮ ባህሪያት መገለጫ ናቸው፡፡
ከፈረስ ስሞች ጋር በተያያዘ ስያሜና ትርጉም ብቻ ሳይሆን ማነቃቂያ፣ ግጥሞችና ዜማዎች አየሩ ላይ የሚናኙት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ብዙ  ጊዜ እንደተለመደው በቅርብ ዓመታትም ጦርነትን በተመለከተ የሚቀነቀኑ ሙዚቃዎች ውስጥ የሚገባው “ቼ በለው!” መነሻው ፈረስና ጦር ሜዳ የማይነጣጠሉ መሆናቸውን ማሣያ ነው፡፡
ቼ በለው! ይወስዳል መንገድ
ያመጣል መንገድ
አባት አሥረካሽ ልጅ አይወለድ፤
የሚያስነሳ እንጂ መንገድ ለመንገድ
ቼ በለው! ከጓደኞቹ ሌት የተለየ፤
እንደ አጥቢያ ኮከብ ሲነጋ ታዬ፤
ዙሪያውን ገዳይ በየንጉስ፤
የጀግናው ፈረስ ሊቀጳጳሱ።
እየተባለ በክራር በበገናና መሰንቆ አጀብ ፈረስ የሚወደሰው እንዲሁ አይደለም፡፡ የጀግንነት ታሪክ ተካፋይ፤የመሥዋዕትነቱ ተቋዳሽም ስለሆነ ነው፡፡ አንዳንዴ ፈረሱ ከባለቤቱ ቀድሞ የሚሞትበት ጊዜም አለ፡፡ የዐፄ ምኒልክ ፈረሶች ጎጃም (እምባቦ) ላይ ሁለቴ መመታታቸውን ማስታወስ ይቻላል።
ቀደም ሲል በፈረሶቹ ቀለም(መልክ) ስያሜ መሰጠቱን እንዳስታወስን እስቲ “ቼ በለው!” የተሰኘውን ግጥም እንመልከት፡-
ቼ በለው ፈረሱ! ጥቁር ፤ጭራው ገብስማ፤
አባሮ ገዳይ በሐምሌ ጨለማ፤
አይመለስም ያለ ደም ሸማ፡፡
ቼ በለው! በዳማ ገዳይ ፤በፈረሶቹ፤
በቡሎ ገዳይ ፤በፈረሶቹ፤
በጥርኝ ገዳይ፤በፈረሶቹ፤
አሻራ ማይመርጥ እንደ ሰዎቹ፡፡
የፈረስ ስምና የፈረስ ስም ክብር በባለቤቱና በጦረኛው ብቻ አያበቃም፤ አንዳንዴም አልፎ በአሽከሮቹና በሚስቶቻቸው፣ በሎሌዎቻቸውም አንደበት በፉከራና በሽለላ ይወደሳል፤ ይነሳል፡፡
በአምስት አመቱ የአርበኝነት ጊዜ ጌታውን ያወድስ የነበረ፤አንድ አሽከር ረዥም ለበኑን ወደ መሬት ዘቅዝቆ እንዲህ ብሏል፡-
የተገብ አሽከር ያባ ጠቅል ሰው፤
እንደደረሰ በእርሳስ የሚያርሰው፡፡
“አባ ጠቅል” የንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ-የፈረስ ስም ነው፡፡ በተመሳሳይ የታሪክ ወቅት ታላቅ አርበኛ የነበሩ ኃያለማርያም ማሞም፣ በፈረሳቸው ስም ተገጥሞላቸዋል፤ ተሸልሏልም!
በጊዜው ቶኬ፣ መረሬና አዳበርጋ በሚባሉ ቦታዎች ላይ ከፋሽስት ጦር ጋር ከፍተኛ ውጊያ ገጥሞ፤ ድል ያደረገው የኃይለማርያም ማሞ ጦር፣ ከቦታ ቦታ እየለዋወጠ ተዋግቶ፤ በርካት ጠላት ገድሎና ማርኮ ስለነበር፣ አጋፋሪ ሞላልኝ የተባሉ ጀግና የገጠሙት ግጥም ሦስት ጊዜ የፈረስ ስም ይጠቅሳል፡፡
እሰይ የምስራች ሞላልኝ ሙገር ፤
ያባ ጎፍን ቀኝ እጅ ቅደም ተሻገር፡፡
ተርቦ የነበር የፋሽስት ወገን ፤
ቶኪ አፋፍ ላይ ቆየው ገበያው ጎፍን፤
አስቆርጦ ሄደ ሦስት መቶ ስድሳ ከሀድያን፤
ማጉም ለሰለሰ ሸማኔው ተቆጣ፤
አባ ጎፍን ኃይሌ መጠቅለያው መጣ፡፡
በተለይ ለዳግማዊ ዐጼ ምንሊክ የተገጠሙ ግጥሞች ላይ የፈረሳቸው ስም ደጋግሞ ይነሳል፤ይወደሳል፡፡ ለምሳሌ ታደለ ገድሌ (መዝሙረ ምኒልክ)፡-
ጣልያን ከገጠመ ከዳኘው ሙግት፤
አግቦ አስመሰለው በሰራው ጥይት፡፡
አሁን ማን አለ በዚህ አለም ፤
ጣሊያን አስደንጋጭ ቀን ሲጨልም፡፡
ግብሩ ሰፊ ነው ጠጁ ባህር፤
የዳኘው ጌታ  ያበሻ  አድባር፡፡
ሺዋ ነው ሲሉት ዓድዋ የታየው፤
ሺናሻ መላሽ ወንዱ አባ ዳኘው፤…………..እያለ ይቀጥላል፡፡
እንግዲህ ከላይ ለማለት እንደሞከርነው፣ በሀገራችን ኢትዮጵያ የተወለዱ ጀግኖች ሁሉ ታሪካቸው ከፈረሶቻቸው ጋር የተያያዘና የማይነጠል ነው፡፡ ስለዚህ ሰዎቹን ስናስታውስ  አብረዋቸው በእሳት የተፈተኑትንና ሀገርን በልዕልናዋ ያቆዩትን ፈረሶች ልንረሳቸው አይገባም፡፡ ምናልባትም ከፈረሶቹ ጀርባ ያሉትን ባልደራሶች ማስታወስም ሳያስፈልገን አይቀርም፤ ምክንያቱም የታሪካችን አካል ናቸውና!!.

Read 574 times