Wednesday, 13 April 2022 17:40

ከደቡብ አፍሪካዊው ባለፀጋና ከኢትዮጵያዊቷ የጀበና ቡና ሻጭ የተወለደች የአርባ ምንጭ ታዳጊ

Written by  ልጅ አቤኑ (አቤንኤዘር ጀምበሩ)
Rate this item
(1 Vote)

የህይወት የመጨረሻ ጠርዝ ላይ የነበሩት ታዋቂው የደቡብ አፍሪካ የአካውንቲንግ ቢዝነስ ባለቤትና የፀረ አፓርታይድ ንቅናቄ ታጋይ ፖለቲከኛ፣ በጣርና በሰመመን ውስጥ ሆነው፣ አንድ ነገር ደግመው ደጋግመው ይናገሩ ነበር፤ “ልጄን ሳሊንን ከመሞቴ በፊት ልያት፣ ሳሊኒ እኔ እያለሁ ምንም አትሆኚም” እያሉ።  
የሳሊኒ ወላጅ አባት አቶ ድላሚኒ (ስማቸው የተቀየረ) ከህልፈታቸው ከቀናት በፊት አርባምንጭ ከተማ ለምትገኘው የሳሊኒ ወላጅ እናት በመደወል፤ “ልጄን ሳሊኒን አደራ፣ ሳሊኒ ራስሽን ጠብቂ እያሉ አስጠነቀቋት” ትላለች፤ ወላጅ እናት ሁኔታውን ስታስታውስ፤ “ለእኔና ለሳሊኒ ግዴለሽ ይመስለኝ ነበር፣ ያ የማልረሳውና የጠና ሁኔታ የገባበት መሆኑን ያረጋገጥኩበት ጊዜ ነበር” ብላኛለች፡፡
በዚህ ሁኔታ ውስጥ የአባትን ጉጉት የተመለከቱት የአቶ ድላሚኒ ቤተሰቦች፣ በጣዕረ ሞት ውስጥ ያሉትን ሰው ቃል ለመጠበቅ፣ ለታዳጊዋ ሳሊኒና ለእናትዋ ወ/ሮ ያይኔአበባ፣ የአውሮፕላን ቲኬት ቆርጠው፣ ወደ ደቡብ አፍሪካ እንድትመጣ ይጠይቋታል፡፡ ነገር ግን እናት ወደ እዚያ ማቅናት አልቻለችም፣ ምክንያቷን ስትገልፅም፤ “አንድም ቤተሰቦቹ በሆቴል እንድናርፍ ያሳወቁን ሲሆን እኔ እነሱን ተማምኜ በሆቴል ለመቆየት ያዳግተኛል፤ እዛ ስደርስ የምከፍለው ምንም ብር የለኝም፣ አርባምንጭ መተዳደሪያዬ የጀበና ቡና መሸጥ ነው፣ ሌላኛውና ዋናው ወደ ደቡብ አፍሪካ እንዳልሄድ ያደረገኝ ምክንያት ድላሚኒ ካጋጠመው የካንሰር ህመም በተጓዳኝ፣ በአዲሱ የደቡብ አፍሪካ የኮሮና ቫይረስ የተያዘ መሆኑን ስላወቅሁኝ፣ በወቅቱም ከፍተኛ መነጋገሪያ በመሆኑ፣ ለእኔና ለልጄ ጤና በመስጋት ጉዞዬን ሰርዤዋለሁ“ ብላለች፡፡
ከቀናት በኋላ ከደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ በአቶ ድላሚኒ ቤተሰቦች አማካኝነት የተደወለ ጥሪ ግን መልካም ዜናን ይዞ አልመጣም፣ ለሳሊኒና ለወ/ሮ ያይኔአበባ የአቶ ድላሚኒን ህልፈት የሚያረዳ ነበር፡፡ የአቶ ድላሚኒ ቤተሰቦች መጀመሪያ ላይ “ብቻችሁን አይደላችሁም፤ ተስፋ እንዳትቆርጡ፤ አባቷ የሷን ስም እንደጠራ አልፏል፣ ልጃችን የኛ ነች፤ አባቷ አደራ ሰጥቶናል አትዘኑ” አሉኝ ትላለች፡፡ እኔና ልጄ በከፍተኛ ጩኸት አለቀስን፤ ልጄ ያለአባት መቅረቷ አሳዘነኝ፤ ትላለች ወ/ሮ ያይኔአበባ፡፡
ታሪኩ የሚጀምረው ከአርባ ምንጭ ከተማ ነው፡፡ መንግሥት መሥሪያ ቤት በሃላፊነት በመስራትና በሌሎች ተጨማሪ ሥራዎች አልቀና ያለ ህይወት፣ ወደ ጎረቤት ሀገር በህገ ወጥ አዘዋዋሪ ደላሎች አማካኝነት ብትሄድ የተሻለ ገቢ ማግኘት እንደምትችል በጓደኞቿ ውትወታ የተረዳችው ያይኔአበባ፤ አካሏ አርባምንጭ ልቧ ግን ወደ ካርቱም ይሸፍታል፡፡ ይሄን ህልሟን እውን ለማድረግ ከዚህ ከዚያም ተበድራና ተለቅታ ያገኘችውን 7000 ብር በመክፈል፣ በ2004 ዓ.ም. ወደ ሱዳን ጉዞ ትጀምራለች፡፡ በ20ዎቹ የእድሜ መጀመሪያ ላይ የነበረችውና የጉዞ ልምድ ያልነበራት ያይኔአበባ፤ ከመተማ ወደ ገላባት ሱዳን ስትሻገር ግን ነገሮች ያሰበችውን አቅጣጫ አልያዙም። ውቧና ተስፈኛዋ ወጣት ሰው አይን ውስጥ ገባች፣ አንድ በረሃ ውስጥ ባለ ማረፊያ እረፍት በሚወስዱበት ሰዓት ከአሸጋጋሪዎቹ ጋር ግንኙነት ያለው ሱዳናዊ ጎልማሳ፣ አይኔአበባና አንድ ሌላ የጎንደር ተወላጅ ኢትዮጵያዊ አንስት ተነጥለው በዛ እንዲቀሩ ያደርጋል፡፡ ሌሎች መንገደኞች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ጉዟቸውን ይቀጥላሉ። ኋላ ላይ ያይኔአበባን ከመንገድ ያስቀራት ሱዳናዊ የግዞት ሚስት ያደርጋታል፡፡ ወደ ውጪ መውጣት አትችልም፣ ከግቢ ውጭ ስላለው ህይወት መረጃ የላትም፣ ፆታዊ ጥቃት ይፈጸምባታል፡፡ በተወሰነ ሰዓት ከሚቀርብላት ምግብና ቤት ውስጥ ከምትመለከተው በአረብኛ የሚተላለፍ የቴሌቪዥን ጣቢያ ውጪ ከማንም ጋር ግንኙነት አልነበራትም፡፡ ከዛ አልፎ የነበረው ከፍተኛ ሙቀት ፋታ የሚሰጥ አይደለም፡፡
በአስፈሪውና ዳኝነት የሌለው በሚመስለው የህይወት ቀለበት ውስጥ የገባቸው ያይኔአበባ፤ ፊቷን ወደ ፈጣሪ ብቻ ታዞራለች፡፡ ባገኘችው የብቸኝነት ሰዓት ቀንም ሌሊትም ወደ ፈጣሪ መጮኋን ቀጠለች፡፡ ቅጥሩ የረዘመበት ውጭው በማይታይበት መኖሪያዋ ወደ መፀዳጃና መታጠቢያ ቤት ስትሄድ ስራዋ ተንበርክኮ ፈጣሪን አውጣኝ  ማለት ሆነ። “አላዛርን ከመቃብር ያስነሳህ፣ የኔን ህይወት መቀየር ለአንተ ቀላል ነው፡፡ ለኔ ከባድ ለአንተ ቀላል ነው፣ በሆነ ተዓምር አውጣኝ፣ ታወጣኛለህ እጠብቅሃለሁ፣ ጌታ ሆይ ፍጠን” ነበር የዓይኔአበባ የግዞት ፀሎት። ፈጣሪ ጩኸቷን ያልነፈጋት አንስት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ በመፀዳጃ ቤት ውስጥ ስታለቅስ፣ በሌላኛው ቅጥር ያለችና ተመሳሳይ የህይወት ገጠመኝ ውስጥ ገብታ፣ ከሌላ ሱዳናዊ ጋር በግዞት ትዳር እየኖረች፣ ስድስት ልጆችን ያፈራችው ኤርትራዊ እናት፣ ድምጽዋን ሰምታ ልትረዳት ከእርሷ ጋር የምትገናኝበትን መንገድ ማፈላለግ ያዘች፡፡ አንድ ቀን ድምፅዋን ከፍ አድርጋ ጠራቻት። ያይኔአበባ እዚያ አካባቢ አማርኛ የሚናገር ሰው እሰማለሁ ብላ አስባ አታውቅም፡፡ የሰማችው ድምፅ አስደነገጣትም አስደሰታትም። ኤርትራዊቷ ግዞተኛ እናትም እንደምትረዳትና ከዚህ ህይወት እንደምታስወጣት ቃል ገባችላት። በሁለቱ ቅጥር ግቢ መካከል ቀዳዳ በመፍጠርም በየጊዜው ለሶስት ቀን የሚያገለግል የወሊድ መከላከያ ኪኒን ታቀብላት ጀመር፡፡ በዛች በተከፈተች ቀዳዳም ልጆቿን አሳየቻት፤ "አማርኛም ብዙም ባይሆን እንግባባ ነበር" ትላለች ስለ ሁኔታው ስታስታውስ፣ “ልጆቼን ጥዬ አሁን ወዴትም መሄድ አልችልም፣ ልጆቼ ደርሰው ግን ነጻ ያወጡኛል ትለኝ  ነበር" ትላለች ያይኔአበባ፡፡
ከቀናት በአንዱ ሁኔታው የተመቻቸላት ኤርትራዊቷ ስደተኛ እናት፣ መሰላል አዘጋጅታ ወደ እርሷ ቅጥር ግቢ ታስገባታለች። ወዲያው ሙሉ ጥቁር ሂጃብ፣ ጓንት፣ የዓይን መከላከያ ቬል እንድታደርግ ትሰጣታለች፡፡ ቀድማ ሂደቱን የጨረሰችው ኤርትራዊቷ ቅን እንስት፣ በእጇ  አንድ ሌላ ነገርም እንድትይዝ ትሰጣታለች፡፡ በሱዳን የሙስሊም ጋዜጣ በእጇ ታስይዛታለች፡፡ እና "ማንም በምትሳፈሪበት መኪና ውስጥ ያለ ሰው ሊያወራሽ ቢሞክር “ማሊሽ” ብቻ የሚለውን ቃል ተናገሪ፡፡ ማሊሽ ማለት ይቅርታ ማንም ሰው እንዲረብሸኝ አልፈልግም የሚል ተቀራራቢ ትርጉም አለው ብላናለች" ባለታሪኳ፡፡ በእንስት የአረብ ሱዳን ስም የተዘጋጀ የአውራጃ አስተዳደር የይለፍ ወረቀት፣ እንዲሁም በመንገድ እንዳይርባትና እንዳይጠማት፣ ደረቅ የሚበሉ ምግቦችንና ውሃ አስይዛት ጉዞዋን ወደ ካርቱም ታደርጋለች፣ በሰዓታት ውስጥ ወደምትመኛት የተስፋ ከተማ ሱዳን ካርቱም ትደርሳለች፡፡
ታላቋ ከተማ ካርቱም፣ የጥቁርና የነጭ አባይ መጋጠሚያ ካርቱም፣ የአፍሪካና የአረብ የንግድ ማሳለጫ ውብ ከተማ። በካርቱም ያጋጠሟት ከትውልድ መንደሯ ሳትወጣ ስራ እንደሚያስገቧት ቃል በገቡላት ኢትዮጵያዊያን ሬስቶራንት ውስጥ ሻይ ቡና ማቅረብ ጀመረች፡፡ በቀን ከ14 ሰዓት በላይ ሥራ መስራት፣ ተጨማሪ የማዕድ ቤት ስራዎች፣ ከሃበሾች ጋር በአማርኛ እያወሩና እየተገናኙ መስራት ቢያስደስታትም፣ የኑሮ ፈቃድ ያልነበራት ያይኔአበባ ደሞዝዋን ዛሬ ነገ ሲሉ ሳይሰጧት አመት ከስድስት ወር ያህል ቆይታ ያለክፍያ በግፍ ከነበረችበት የሃበሻ ሬስቶራንት ለቀቀች። ምንዱባኗ እንስት በዚህ በደረሰባት ስብራትና የመንፈስ ጭንቀት በካርቱም በሚገኘው የኢትዮጵያውያን መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን መጠለያዋን አደረገች። በዛም ያገኟት ሌሎች ኢትዮጵያውያን ወደ ቤታቸው አስጠጓት፣ ከዛ አልፎም ብራዚሊያን አግሪካልቸር በሚባል ድርጅት ውስጥ አስቀጠሯት፡፡ ህይወት መስመር መያዝ ጀመረ፤ አዲስ ተስፋ፣ ጨለማ ብርሃን፣ ከዛም ጨለማና ብርሃን፡፡
በአንድ አጋጣሚ ኢትዮጵያዊያን በጠሯት የልደት ክብረ በዓል ላይ ከልጇ አባት ጋር ተያየች፣ ልደት ካለፈ በኋላ በጓደኞቿ አማካኝነት ሊያገኟት እንደፈለጉ ተገለፀላት፤ እያንገራገረች ከጓደኛዋ ጋር ልታገኛቸው ሄደች፡፡ በ50ዎቹ አጋማሽ ያሉ፣ የደስ ደስ ያላቸው ጎልማሳ አቶ ድላምኒ። ኋላም ተቀራረቡ፣ ትልልቅ ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ግብዣ፣ ውድ የጌጣጌጥና የልብስ ስጦታ ይጎርፍላት ጀምር፡፡ በመጨረሻ ውለጅልኝ የሚል ጥያቄ አቀረቡላት። ይህን በሁለት ምክንያት መቀበል እንደማትችል ያይኔ ገለፀች። አንድም ቀጣይነት ለሌለው ህይወት ልጅ መውለድ፣ ሁለትም ሱዳን በደረሰባት ጥቃት ኤች አይ ቪ ይኖርብኛል ብላ በመስጋት፡፡ በሱዳን የሌላ ሀገር ዜጋ ተመርምሮ ኤች አይ ቪ ኤድስ ከተገኘበት ወደ ሃገሩ ይሸኛል ብላናለች፡፡ በኋላም በጓደኞቿና በአቶ ድላምኒ ግፊት ኤች አይ ቪ ተመርምራ ነጻ ሆነች፡፡ የአቶ ድላምኒን ጥያቄም ተቀብላ አረገዘች፡፡ እርግዝናዋ በህክምና ከተረጋገጠ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ እንድትመለስ የሚያስፈልጋትን ነገር አቶ ድላምኒ አሟልተው ላኳት፡፡ ሰውየውም  የሱዳን ስራቸውን ያጠናቀቁበት ጊዜ ስለነበር ወደ ደቡብ አፍሪካ ተመለሱ።
በሃገራችው ባለትዳር የሆኑትና በኢትዮጵያዊቷ ፍቅር የወደቁት አቶ ድላምኒ ደግ ሰው ናቸው፤ ትላለች ያይኔአበባ። “እንደ ጓደኛም ብቻ ሳይሆን እንደ ልጅ ይንከባከበኝ ነበር“ ትላለች፡፡ “ከዛም ሲያልፍ እንዳልተወው ነው መሰል ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር እንድገናኝም ብዙ አይፈቅድም፤ በተለይ ከሌላ ወንድ ጋር ካገኘኝ ይቀናል፣ ስልክ ተደውሎ በአማርኛ ካወራሁ ቀጣዩ ጥያቄው ማነው ነበር" ትላለች፡፡ “እኔም ግን ስለሱ ህይወት ብዙ አላቅም ነበር" ትላለች፤ ባለታሪኳ፣ “ቅር ብሎት እንዳይሸሸኝ ጥያቄ አላበዛባትም ነበር" ትላለች፡፡ "የሚይዘው መኪና MTN የሚል አርማ ያለው ነበር፣ እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አይነት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ ከሚሰሩ ሰዎች ጋር በብዛት ይገናኛል፡፡ እኔንና ጓደኞቼንም ይጋብዘንም ያዝናናንም ነበር፡፡”
አዲስ አበባ እንደተመለሰች ብርጭቆ ኮንደሚኒየም ቤት ተከራየች፡፡ በሳምንቱ ድላምኒ አዲስ አበባ መጥተው በሂልተን ሆቴል አረፉ፡፡ ስልክ ደውለው የት እንዳለች ከጠየቋት በኋላ የአስጎብኚ ድርጅት መኪና ልከው ወደ አረፉበት ሆቴል እንድትመጣ አደረጉ፡፡ በዛ ወቅት ፅንሱ ሁለት ወርም አልሞላውም ነበር፡፡ ድላምኒ ሲያይዋት ተደናገጡ፣ ልጁን እንዳስወረደችው ጠየቋት፣ እንዳላደረገችው ተናገረች፡፡ ፊቷ በምን ምክንያት እንደተጎሳቆለ አጥብቀው ቢጠይቋት፣ ኑሮዋን በማስተካከል ሂደት መሆኑን አሳወቀቻቸው። የሀበሻ ሴቶች ይህን እንደሚያደርጉ በወዳጆቻቸው የተነገራቸው ጎልማሳ ግን ሊያምኗት አልቻሉም፡፡ በከተማው በሚገኝ አንድ የግል ሆስፒታል ይዘዋት ሄደው የፅንሱን አለመጨንገፍ አረጋገጡ፡፡
ገና ያልተወለደችውን ሳላኒን በአልትራሳውንድ አብረው እንደተመለከቱ “ሳላኒ ነች በሆድሽ የያዝሻት፤ ፅንሱ ወንድም ሆነ ሴት ስሙ ሳላኒ ነው” አሉ በርከክ ብለው፣ ሆዷን ሳሙ፤ በማህፀኗ የቋጠረችውን ፅንስ ዳሰሱት፤ ሆዷን እየነኩ ሳሊኒን ተዋወቋት፡፡ በሃገራቸው በሚኖሩበት ደቡብ አፍሪካ ሳላኒ ማለት ሁለት ትርጉም እንዳለው ነገሯት፤ አንደኛው “በህይወት መንገድ አንዱ ሌላኛውን ሲጠብቅ” ማለት ሲሆን፣ ሁለተኛው ትርጉም “መደነቅ መገረም እንደማለት” እንደሆነ ይነግሯታል፡፡ ቀጣይ ወደ ባህር ዳር መዝናኛ፣ እንደገና ከወራት በኋላ ሁለት ጊዜ ተመላልሶ ወደ ኬንያ ሞምባሳ በመውሰድ በትልልቅ የቱሪስት መዳረሻ በሆኑ ሆቴሎችና ሞሎች እንዳዝናኗት ትናገራለች። ተነፋፍቀው በተገናኙ ቁጥር እየገፋ የመጣውን ሆዷን ተንበርክከው ይስሙት እንደነበር ስታስታውሰው፤  "አንዳንዴ ጉጉቱ ያስገርመኝ ነበር፣ በሰው መሀል እንደዛ ማድረጉ በኛ ሃገር ስላልተለመደ አፍር ነበር” ትላለች፣ ወደ ኋላ በትዝታ የሳላኒን እርግዝና ስታስታውስ፡፡
የአይኔአበባ እርግዝና ገፍቶ መውለጃዋ ጊዜ ደረሰ፡፡ አቶ ድላምኒ ባሉበት ሆነው ወሊዷን ይጠባበቃሉ፣ ምጧን ወሊዷን በቀጥታ ቪዲዮ ደውለው ተከታተሉ፣ ደስታቸው ወደር አልነበረውም፡፡ የሚያስፈልጋትን ወጪዎች በተከታታይ ይልኩላት ነበር፡፡ ሳሊኒ 5 ወር ሲሞላት አቶ ድላምኒ ወደ አዲስ አበባ የትራንዚት ቲኬት ቆርጠው ከሳሊኒ እና ከእናቷ ጋር አዲስ አበባ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት ተገናኝተው፣ ወደ ኬንያዋ የቱሪስት መዳረሻ ጉዞ አደረጉ። አባት ከልጃቸው ጋር ሲገናኙ እጇን እግሯን ሁለንተናዋን በአንክሮ እየተመለከተ ይስሟታል “ቁርጥ እኔን የምትመስል ልጅ” እንባ በአይናቸው እየወረደ ”ማንም የሷን ያህል አይመስለኝም” አሉ፡፡ ባረፉበት የሞምባሳዉ ክራውን ፕላዛ ሆቴልም ሰዎች ደጋግመው አንተን ትመስላለች ይሉት ነበር ትላለች ያይኔ፡፡ አይኔአበባ የ3 ወር የኬንያ ቪዛ ኬንያ እንደገባች ቢመታለትም በሦስተኛው ቀን አቶ ድላምኒ “በጣም ደንገጦ ላብ በላብ ሆኖ አንደበቱ እየተንተባተበ እኔና ሳሊኒ ወዳለንበት ክፍል መጣ" ትላለች፡፡ "ዛሬውኑ ወደ አዲስ አበባ መመለስ አለብሽ" ይላሉ፡፡ በነገሩ ክፉኛ የተደናገጠችው ያይኔ፣ ምነው ብትል ከህጋዊ ባለቤታቸው ጋር ሌላ ሆቴል የያዙት አቶ ድላምኒ ባለቤታቸው ስለጉዳዩ መረጃ እንዳገኙ እና ወደ ሆቴል በማንኛውም ሰዓት ሊመጡ ስለሚችሉ፣ ወዲያው ከሆቴል ክፍሉ መልቀቅ እንዳለባትና ወደ አዲስ አበባ መመለስ ግድ መሆኑን ያሳውቋታል። በዚሁ ተስማምተው በእለቱ  ወደ አዲስ አበባ ምላሽ ሆነ።
ከአዲስ አበባ እንደተመለሱም እስከ 3 ወር ግንኙነታቸውና የእርሳቸውም እርዳታ ቀጠለ፡፡ ከሶስተኛው ወር በኋላ በህይወታቸው መልካም ያልሆነ ነገር እንደተከሰተ ይነግሯታል፣ ምክንያቱም ከመንገር የተቆጠቡት አቶ ድላምኒ፤ ከዛ በኋላ የሚልኩትን ገንዘብ በአግባቡ እንድትጠቀም አሳስበው፣ ችግር ስለተፈጠረ እንደቀድሞ የበዛ ነገር እንደማይልኩም አስገነዘቧት። ከዚያ በኋላ ግንኙነታቸው በጣም እየቀዘቀዘ መጣ። ስልክ ስትደውል የአቶ ድላምኒ ትላልቅ ልጆች እያነሱ የአባታቸው ስልክ እንደሆነ በመግለፅ፣ መልዕክት እንዳታስቀምጥ ይነግሯታል፡፡
በሁኔታው ግራ የተጋባችውና የአዲስ አበባን ኑሮ አቶ ድላምኒን ተማምና የሷንና የልጇን ህይወት የምትመራው ያይኔአበባ፤ ችግር ሰተት ብሎ ቤቷ ሲገባ የመጨረሻ አማራጭ የነበረው የአቶ ድላምኒን ወንድም አድራሻ ከፌስ ቡክ ላይ ፈልጋ በሜሴንጀር መደወል ነበር፣  ወንድሙ ይሄን ማድረጉን ሲጠራጠር የነበረውና ምላሹን ጥሩ ያልነበረው ወንድም የሳሊኒን ፎቶ ባየ ጊዜ ግን ልቡ ተተረተረ፤ ቁርጥ አባቷን የምትመስል ልጁ “የኛ ልጅ መሆኗን እርግጠኛ ነኝ” አለ “መጀመሪያ እሱን ላናግር” ያለው የሳሊኒ አጎት፤ በሌላ ጊዜ ደውሎ አባቷ እንዳልተቀበለው ገልፆላት፣ ግንኙነቱን አቋረጠ፣ ለምትልከው መልዕክትም ምላሹ ዝምታ ሆነ። በህይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ያለችው ያይኔአበባ፤ ምንም እንኳን የአቶ ድላምኒ ህይወት በሷ ምክንያት መበጥበጥ ባትፈልግም ከመጣባት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር ባለፈ መጀመሪያ እንደፈራችው ልጇን አባት አልባ በማድረጓ እያዘነች፣ በቀጣይም ከአቶ ድላምኒ የመጀመሪያ ሴት ልጅና የእድሜ እኩያ የሆነችውን ሌላዋን ሰው ለማግኘት ብትሞክርም፣ “ሃብታችንን አይተሽ ለውርስ እንደምታደርጊ አውቃለሁ፤ ይቅርብሽ አትልፊ አባቴ እንዲህ አያደርግም” ሆነ ምላሽዋ ።
በዚህ ሁኔታ ልጅቷን ለማሳደግ ስራ መስራት እንዳለባት የተገነዘበችው ያይኔ፤ ውልና ማስረጃ አካባቢ ተቀጥራ የፅህፈት ስራ ጀመረች። የቤት ዕቃዋንም ቀስ በቀስ መሸጥ ያዘች። ከተከራየችው ኮንደሚኒየም ወጥታ የሚቀንስ ቤት ተከራየች። በዚህ ሳትበገር ለሊት ልጇን እያስተኛች እንጀራ እየጋገረች ማከፋፈል ጀመረች። በተጨማሪም ባር ውስጥ እስከ ምሽቱ 5 ሰዓት መስተንግዶ መስራት ቀጠለች፤ ልጇን እንድትይዝላትም ሞግዚት ቀጠረች፡፡ በዚህ ሁኔታ ለ8 ወር የቆየችው ያይኔአበባ፤ አያት ሰሚት ኮንደሚኒየም አካባቢ አንድ ግንባታ ያለበት ቦታ ሰራተኞች ሲርመሰመሱ ተመለከተች፤ ወፈ ሰማይ ይመስላሉ። አጋጣሚው የቢዝነስ ሀሳብ አመጣላት። ሱዳን ካርቱም ላይ የምታቀላጥፈውን ሻይ ቡና መስራት። ስራዋን ሳትለቅ አንዱን ቅዳሜ በፔርሙዝ ሻይና ቡና ይዛ ሄደች፤ ወዲያው አለቀላት፤ በእግር ወደ መኖሪያዋ ተመልሳ በድጋሚ አፍልታ ሄደች፡፡ ይህን ያዩ ሰዎች ትንሽ መጠለያ መሸጫ ነገር እንድታገኝ አደረጓት። ሌላ ስራዋን ትታ ይሄን ያዘች ሻይ፣ ቡና፣ አንባሻ፣ ዳቦ በለውዝ መሸጥ ጀመረች። በዚህ ሁኔታ አንድ አመት ለሚጠጋ ጊዜ የቆየችው ያይኔአበባ፤ ድጋሚ ስደት ወደ ልቧ መጣ፡፡ እናቷን ከአርባምንጭ ጠርታ የልጅ ልጃቸውን አስይዛ ላከቻቸው አባት ምጥ ይግባ ስምጥ ድምፅ ጠፋ፡፡ የሱዳኑ ብራዚሊያና ካምፓኒ ጋር ለዳግም ስደት ግንኙነት  ጀመረች፡፡ ሂደቱ ወራትን ወሰደ ካምፓኒው ወደ ታንዛኒያ እንደሚልካት ቃል ገባላት፡፡ ለወራት ከአይኗ ርቃ የነበረችውን ሳላኒን ለመጨረሻ ጊዜ ለመሰናበት አርባምንጭ አቀናች፡፡ በዛ ያየችውን ነገር ግን ጉዞዋን መተው እንዳለባት አረጋገጠላት። ልጇ ሳላኒ  ታማለች በብርቱ ተጎሳቁላለች፣ ሰውነቷ በቁስል ተመቷል። ልጄ እንደምትሞት በጣም ያቃዠኝ ነበር የምትለው ባለታሪኳ፣ በዛም ምክኒያት ነገሩን እርግፍ አድርጋ ኑሮዋን አርባምንጭ ላይ አደረገች፡፡
አርባምንጭ በሆቴል ሪሴፕሽን እንዲሁም ቡናና ሻይ በመሸጥ ኑሮዋን ቀጠለች፣ አሁንም አባት ግንኙነቱ ቆሟል። ሳሊኒ እያደገች  ሶስት አመት ሲሆናት፣ ስልኳ ላይ የሃዋላ ቁጥር ገባ፤ አባቷ ሌላ መልዕክት ሳይተው 95 የአሜሪካ ዶላር ላከላት፡፡ ከዛ በኋላ ሳሊኒ 6 አመት እስኪሞላት ድረስ አልተገናኙም። በመሀል የስልክ አድራሻውም ጠፋ፡፡ እናትም ጉዳዩን እርግፍ አድርጋ ተወችው፡፡ ነገር ግን አንዳንዴ የልጁን የስም ትርጉም "ሳሊኒ ማለት አብዝቶ መጠበቅ ነው" ያላትን አልረሳችውም፤ እያስጠበቃት እንደሆነም ታስባለች፡፡ ከምትሰራው ስራ አንዱ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መምህራንን ልብስ ማጠብና መተኮስ ነው፡፡ ልብስ ከምታጥብላቸው ውስጥ የህንድ ዜግነት ያላቸው መምህራን፣ ስለ ልጅቷ አባት አይኔን ይጠይቋታል፡፡ ነገሩን ነግራቸው አሁን ላይ ከአባቷ ጋር እንደማይገናኙ ትጠቅሳለች፡፡ እንዲህ አይነት ሰው ወይ አደጋ አልያም ሌላ ችግር ካልገጠመው በቀር ልጁን አይተውም፤ ሙሉ ስሙን ንገሪንና እንፈልግልሽ አሏት። ከዛም አፈላልገው ሊያገኙት ቻሉ፡፡ በድጋሚው ግንኙነት አቶ ድላምኒ  ሚስቱን ጨምሮ ከመላ ቤተሰቡ ጋር እንድትተዋወቅ አደረገ። ከ200-500 ዶላር በየተወሰነ ጊዜ ልዩነት መላክ ጀመረ። ሳሊኒም በተሻለ ትምህርት ኑሮ መቀጠል ገፋች፣ በመሀል ግን አባቷ አቶ ድላምኒ በካንሰር እንደታመሙና ህክምና እየተከታተሉ እንደሆነ ገለፁላት። ህመሙ የተባባሰበት አቶ ድላምኒ እ.ኤ.አ ጃንዋሪ መባቻ 2022 ህይወቱ አልፎ፣ በፌብሪዋሪ 3 የቀብር ሥነ ስርዓቱ ተፈፀመ፡፡ ያይኔአበባ እና ሳሊኒ የአቶ ድላምኒን የቀብር ስርዓት በተላከላቸው ዩቲዩብ የቀጥታ ሊንክ፣ አርባምንጭ ላይ ከወዳጅ ዘመድ ጋር ሆነው ተመልክተው ሃዘናቸውን አወጡ። እስከ ተወሰነ ጊዜ ድረስ ከልጆቹና መላ ቤተሰባቸው ጋር የነበራት ግንኙነት በጥሩ ሁኔታ የቀጠለ ቢሆንም፣ በመጨረሻ ግን ልጆቹ  በግንኙነቱ ለመቀጠል ፈቃደኝነት አላሳዩም። ከህልፈታቸው ከአንድ ወር አካባቢ በኋላ፣ አቶ ድላምኒን የሚያውቁ ሰዎች ስልክ በመደወል፣ አቶ ድላምኒ "ከትዳር ውጪ ከአንቺም ሌላ አንድ ልጅ ደቡብ አፍሪካ ያለው ሲሆን፤ ቤተሰቦች ውርስ ለመስጠት ስላንገራገሩ፣ ክሱን መጀመራቸውን አሳውቀዋል፤ አንቺም በዛ መንገድ ብትሄጂ ጥሩ ነው" ብለዋታል፡፡
በቅርቡ ያይኔአበባና ልጇ ከአርባ ምንጭ ወደ አዲስ አበባ መጥተው ይሄን ጉዳይ የሚረዳቸው ሰው በመፈለግ ላይ ሳሉ ነው ያገኘኋቸው። በተለይ በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ አካባቢ ያላችሁ የኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ ተወካዮች፣ አለንልሽ ብትሏት የሷና የታዳጊ ልጇ ዳግም መከራ ያቆም ይሆናል፡፡

Read 764 times