Print this page
Wednesday, 13 April 2022 17:56

አጫጭር የፍልስፍና ወጎች

Written by  ብሩህ ዓለምነህ
Rate this item
(2 votes)

(በዛሬው ፅሁፌ በተለያየ ዘመን የተነገሩ አስቂኝና አስገራሚ አጫጭር የፍልሰፍና ወጎችን እንመለከታለን፡፡)
                                             ‹‹እኔ ንጉስ ነኝ ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?››
በጥንታዊት ግሪክ በ4ኛው ክ/ዘ ብህትውናን እንደ የኑሮ ፍልስፍና አድርገው ሲኖሩ የነበሩ ሲኒኮች የሚባሉ ፈላስፎች ነበሩ፡፡ ከሲኒኮች መካከልም በጣም ታዋቂ የነበረው ዲዮጋንስ ነው፡፡ እናም አንድ ቀን ዲዮጋን በሚኖርበት ቱቦ ራቁቱን ሆኖ የጠዋቷን ፀሐይ ከውሾቹ ጋር ሆኖ ይሞቃል። በአጋጣሚ ታላቁ አሌክሳንደር ከጠባቂዎቹ ጋር ሆኖ ዲዮጋን የሚኖርበትን የቆሮንጦስ ከተማ በ336 ዓ.ዓ ሲጎበኝ ዲዮጋንን አየውና ተጠጋው፡፡ በዚህ ወቅት ዲዮጋን የ70 ዓመት አዛውንት ሲሆን፣ አሌክሳንደር ደግሞ ገና የ20 ዓመት ወጣት ነበር፡፡ እናም ወጣቱ አሌክሳንደር ወደ ዲዮጋን ተጠጋውና እንዲህ አለው፣
‹‹እኔ ታላቁ ንጉስ አሌክሳንደር እባላለሁ፤››
ዲዮጋንም መለሰ፡- ‹‹እኔ ደግሞ ውሻው ዲዮጋን እባላለሁ፤›› (ዲዮጋን ከውሾቹ ጋር ስለሚኖር የአካባቢው ነዋሪ ‹‹ውሻው›› በማለት ይጠሩት ነበር)
ታላቁ አሌክሳንደር የአሪስቶትል የፍልስፍና ተማሪ ስለነበረና ለፍልስፍናም ቅርብ ስለነበረ የሲኒኮችን አስተምህሮ ያቀዋል፤ ስለ ዝነኛው ዲዮጋንም ታሪክ ሰምቷል፡፡ ያም ሆኖ፣ አሌክሳንደር በዲዮጋን መልስና በራስ መተማመን ተገርሟል፡፡ ንግግራቸውን ቀጠሉ፤
አሌክሳንደር፡- ‹‹እኔ ንጉስ ነኝ፤ የፈለከውን ነገር ብትጠይቀኝ ላደርግልህ እችላለሁ፡፡ ስለዚህ ጠይቀኝ፤ ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?››
ዲዮጋንም መለሰ፡- ‹‹ከአንተ አንድ ነገር እንድታደርግልኝ ብቻ ነው የምፈልገው፤ እሱም የጠዋቷን ፀሐይ እየጋረድከኝ ስለሆነ ዞር በልልኝ!!››
አሌክሳንደር አልተናደደም፤ ይልቅስ ተገረመ እንጂ፤ እሱ ለሚሳሳለት ሥልጣንና ዝና ዲዮጋን ግድ የለውም፡፡ እናም ንጉሱ እንዲህ አለ፤ ‹‹ድጋሜ የመፈጠር ዕድል ቢሰጠኝ ዲዮጋንን ሆኘ መፈጠርን እመርጥ ነበር!!››

‹‹ሰው እንዴት ቁጭ ብሎ ስለ ሞት ይማራል!?››
ዕለቱ ሰኞ ነው፣ ሐምሌ 12፣ 2011፤ በዘርዓያዕቆብ የፍልስፍና ት/ቤት ‹‹የግብረገብ ፍልስፍና›› በሚል ኮርስ ውስጥ ስለ ኤፒኩሪያንስ የሥነ ምግባር አስተምህሮ እየተማርን ነው፡፡ መምህሩ እንዲህ እያለ ያስተምራል፣ ‹‹እንደ ኤፒኩረስ አመለካከት፣ የሰው ልጅ በህይወቱ ደስተኛ እንዳይሆን ካደረጉት ነገሮች ውስጥ ዋነኛው ፍርሃት ነው፤ የሰው ልጅ ከሚፈራቸው ነገሮች ውስጥ ደግሞ ትልቁ ‹‹የሞት ፍርሃት ነው››፤ ሆኖም ግን እንደ ኤፒኩረስ አመለካከት፣ ለሞት ያለን ፍርሃት ሎጂካል አይደለም…››፡፡
ታዲያ በዕለቱ አንዱ ተማሪያችን አንዲት ሴት ጓደኛውን በስንት ልመና ይዟት መጥቶ ነበር፡፡ እናም ይቺ ሴት የኤፒኩረስን የሞት አስተምህሮ በተደበላለቀ ስሜት ውስጥ ሆና አዳመጠች፡፡ ልክ ትምህርቱ እንዳለቀ ጋባዡ ተማሪ ጠየቃት፣
‹‹ትምህርቱ እንዴት ነው? እንዴት አገኘሽው?›› አላት፤
እሷም እንዲህ አለችው፣ ‹‹ባልጠፋ ትምህርት፣ ሰው እንዴት ቁጭ ብሎ ስለ ሞት ይማራል!?››
እሱም ቀበል አድርጎ፣ ‹‹በዚህ ትገረሚያለሽ እንዴ!? ፍልስፍና ውስጥ የማይወራ ነገር የለም!! ፍልስፍና የሐሳብ ነውር የለበትም!! ፍልስፍና ውስጥ ስለ ሰው ልጅ ሞት ብቻ ሳይሆን፣ ስለ እግዚአብሔር ሞትም ይወራል፤›› አላት፡፡

ሽሮዲንገርና ገበሬው
በ20ኛው ክ/ዘ ሽሮዲንገር የሚባል በጣም ታዋቂ ጀርመናዊ የቲዮረቲካል ፊዚክስ ሊቅ ነበር፡፡ እንዲያውም ‹‹Shrodinggar’s Equation››፣ ‹‹Shrodinggar’s Cat›› በሚባሉ ነገሮች ይበልጥ ይታወቃል፡፡ እናም ሽሮዲንገር በአንድ ወቅት ወደ አንድ ገበሬ ዘንድ ይሄድና ገበሬውን እንዲህ ይለዋል፤ ‹‹ይሄ የምታየው ጠረጴዛ ለአንተ ጠጣር (Solid) መስሎ ይታይሃል እንጂ ወደ ውስጥ ጠለቅ ብለህ ብታየው ጠረጴዛው የተሰራበት ጣውላ በጣም ደቃቃ ከሆኑ ተንቀሳቃሽ ብናኝ አተሞች ነው፡፡ የሚገርመው ደግሞ በእነዚህ አተሞች መካከል ክፍተት አለ፤ እንጂ ጠረጴዛውን እንደምታየው ክፍተት የሌለው Solid አይደለም፡፡ እናም የምታየው ጠረጴዛ Illusion ነው›› ይለዋል፡፡
ገበሬው ግራ ገባውና ጠረጴዛውን በእጁ ኳኳኳኳኳ….አደረገው፤ ድምፅም ሰጠው፡፡ ወዲያውም ወደ ሽሮዲንገር ቀና አለና፤ ‹‹It’s Solid to me!!›› ብሎት ሄደ፡፡

‹‹አላልኩህም…!!››
በጥንታዊ ግሪክ 3ኛው ክ/ዘ ላይ እንደ ፋሽን ሲታይ የነበረ ‹‹Stoicism›› የሚባል ፍልስፍና ነበረ፤ የፍልስፍናው ተከታዮችም ‹‹ስቶይኮች›› ተብለው ይጠራሉ፡፡ የስቶይሲዝም ዋነኛ አስተምህሮ ‹‹ግዴለሽነትን (indifference)›› ነው፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ‹‹ውጫዊ የሆነውን ነገር እኛ መቆጣጠር አንችልም፤ ልንቆጣጠር የምንችለው ስለ ነገሮች ያለንን አመለካከትና ስሜት ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም፣ እኛ ከማንቆጣጠረው ዓለም ጋር የስሜትና የስነ ልቦና ትስስር መፍጠር ነገሮች እኛ ባሰብነው መንገድ ካልሄዱ እንጎዳለን›› የሚል ነው፡፡
በዚህ አስተምህሯቸውም ስቶይኮች ከውጫዊ ክስተቶች ጋር ምንም ዓይነት የስሜትም ሆነ የስነልቦና ትስስር (ለምሳሌ - መጓጓት፣ መጠበቅ፣ በስሜት መነካት) እንዳንፈጥር አጥብቀው ይመክሩናል፡፡ በዚህ አስተምህሯቸውም የተነሳ ስቶይኮች በቀላሉ በስሜታቸው የማይነኩ፣ የማያዝኑ፣ የማይደሰቱ፣ ስሜታቸውን በበቂ ሁኔታ የመቆጣጠር አቅም ላይ የደረሱ ናቸው፡፡ ይሄንንም ከፍታ በሚከተለው የኤፒክቴተስ እውነተኛ ታሪክ ውስጥ እናገኘዋለን፡፡
ኤፒክቴተስ ከባሪያ ቤተሰብ የተወለደ፣ እሱም በባርነት ሲያገለግል የነበረ ሰው ነው። በዚህ ወቅትም በሮማውያን ዘንድ ፈጣን አእምሮ አላቸው ተብለው የሚታሰቡ ባሪያዎች ትምህርት እንዲማሩ ይፈቀድላቸው ስለነበር ኤፒክቴተስ በስቶይኮች ፍልስፍና ተማረከ፡፡ በጌታው ሞት ምክንያትም ነጻ እስከወጣበት ጊዜ ድረስም ኤፒክቴተስ በባርነት አገልግሏል፡፡
ኤፒክቴተስ በባርነት በሚኖርበት ቤት ውስጥ ጥፋት ያጠፋ ባሪያ በእንጨት እግሩ ይጎተታል፡፡ ኤፒክቴተስም የሆነ ጥፋት አጠፋ፤ ጌታውም በእጅጉ ተናደደበት። እናም በእጅጉ የተናደደው ጌታው እንደመቀጣጫ የኤፒክቴተስን እግሩን በእንጨት ይጎትተው ጀመር፡፡ የጌታው ንዴት የገባው ኢፒክቴተስም ‹‹ተው ይሄ ነገር (እግሩን ማለቱ ነው) ይሰበርብሃል›› ይለዋል፡፡ እንዳለውም እግሩ ተሰበረ፡፡ በዚያ ጊዜ ኢፒክቴተስ ‹‹ህይወቴ ጨለመ፤ እንዴት ብዬ ነው የምኖረው!!›› በማለት አላለቀሰም። ከዚህ ይልቅ ኢፒክቴተስ ለጌታው የተናገረው አንዲት ቃል ብቻ ነው፤ እሱም ‹‹አላልኩህም!!›› የሚል ነው፡፡

‹‹በሉ ሁላችሁም ተከባብራችሁ ኑሩ››!!
ከክ.ል.በ በ4ኛው ክ/ዘ ንጉስ ዳርየስ በሚያስተዳድረው የፐርሺያ ኢምፓየር ውስጥ በከተማው ሁልጊዜ የግሪክና የህንድ ሰዎች አንዳቸው የሌላኛውን ባህል እያንቋሸሹ ይጨቃጨቁ ነበር፡፡ አንድ ቀን ታዲያ ንጉስ ዳሪየስ እነዚህን ግሪካውያንንና ህንዳውያንን ወደ ቤተ-መንግስት እንዲመጡ አዘዛቸውና እያንዳንዳቸውን በየተራ ጠየቃቸው፤
ዳሪየስ ከግሪኮቹ ጀመረ፡- ‹‹እናንተ ሰው ሲሞትባችሁ ምንድን ነው የምታደርጉት?›› አላቸው፡፡
ግሪኮቹም፡- ‹‹እንዴ! ምን ጥያቄ አለው! ሰው ሲሞትብን በክብር አስፈላጊውን ሥነ ሥርዓት አሟልተን ሬሳውን እንቀብረዋለን፤›› ብለው መለሱ፡፡
ዳሪየስም ፊቱን ወደ ህንዶቹ አዙሮ፤ ‹‹እናንተስ ሰው ሲሞትባችሁ ምንድን ነው የምታደርጉት?›› አላቸው፡፡
ህንዶቹም፡- ‹‹የሞተብን አባት ከሆነ አባት በጣም ትልቅ ክብር ያለው ሰው ስለሆነ ሬሳውን እናቃጥለዋለን›› አሉት። ይሄንን ሲሰሙ ግሪኮቹ በድንጋጤ ጮሁ!!
ዳሪየስም ወደ ግሪኮቹ ዞሮ፤ ‹‹እናንተ የሞተባችሁን አባታችሁን ብታቃጥሉት ምን ይሰማችኋል?›› ብሎ ጠየቃቸው፡፡
ግሪኮቹም፡- ‹‹በዓለም ላይ ምንም ዓይነት ሃብት ቢሰጠን የአባታችንን ሬሳ እንድናቃጥል ሊያደርገን አይችልም፤ ይሄ ለእኛ እጅግ የበዛ ነውርነው›› አሉት፡፡
ዳሪየስም ወደ ህንዶቹ ዞሮ፤ ‹‹እናንተስ የሞተው አባታችሁን መሬት ውስጥ ብትቀብሩት ምን ይሰማችኋል?›› በማለት ጠየቃቸው፡፡ ህንዶቹም ‹‹ኡኡ!!›› ብለው ጮሁ፤ በጣም ዘገነናቸው!! ‹‹ይሄ ምን ዓይነት እብደት እና ጭካኔ ነው!! እንደዚህ ዓይነት ጭካኔ መስማትም ሆነ ማየት አንፈልግም›› አሉት፡፡
ዳሪየስም፤ ‹‹የራሳችሁ ባህል ለራሳችሁ ትክክል ነው፤ በሉ አንዳችሁ የሌላችሁን ባህል ሳታንቋሽሹ ተከባብራችሁ ኑሩ!!›› በማለት አሰናበታቸው፡፡
ከአዘጋጁ፡-ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 4636 times