Friday, 15 April 2022 16:31

የተካደው ሰሜን ዕዝ፣ ያልካደን ታሪኮች

Written by  ከሄኖክ ስዩም (ተጓዡ ጋዜጠኛ)
Rate this item
(0 votes)

 የአንድ ታፋኝ ወጥቶ አደር ማስታወሻ፣እንዲህ እንደ ፍቅር ታሪክ ጣፍጦኝ ያልቃል ብዬ አላሰብኩም ነበር፤ የአውደ ውጊያ ታሪክ የማሰስ መሻቴ የመጀመሪያውን ገጽ እንድገልጠው አደረገኝ።
ሰውዬው እግር ሳይኾን ሙያ ወደ ሰሜን የወሰደው ወታደር ነው፡፡ በውትድርናው ላይ የመጻፍ ክህሎትን የታደለ በመሆኑ ያየውን ለሌላ ለማሳየት ትርፍ ህይወትም ትርፍ ዕድልም አግኝቷል፡፡ የዚህ ዕድል ተጠቃሚ ሆኜ መጋቢት 2014 ዓ.ም. ለህትመት የበቃውንና 393 ገጾች ያሉትን መጽሐፍ አነበብኩት፡፡ ከዚያ ይሄ ተሰማኝ፤
መጽሐፉ የአንድ ወታደር ዕጣ ፈንታ ብቻ አይደለም፤ የአንድ ሀገር ሰራዊት አወቃቀር፣ አኗኗር፣ መከራና መራር ጉዞም ተሰንዶበታል፡፡ ሀገሩን የሚወድ ወጥቶ አደር ሞላልኝ ያለውን አመስግኖበታል፡፡ የጎደለበትን ደግሞ በሞላነው በሚያስብል ቁጭት አጋርቶናል፡፡
ሰሜን ዕዝ፣ የዕዙ ሠራዊት፣ የዕዙ ቀጠና ህዝብና ሀገር አብረው ታይተውበታል። እምነትና ክህደት አንድ አውድ ተከትበውበታል፡፡ ጽናትና ውድቀትም አብረው ይታያሉ፡፡ እዚህ የሚያናድደው፣ እዚህ መልሶ ልብ ያርሳል፡፡ ይሄንን መሳይ ታሪክ ዓላማው የታፈነው የሀገሪቱ ግዙፍ ዕዝ መከራና የትንሳዔ ተጋድሎ የተጋመደበት ነው፡፡
ጸሐፊው ወደ ትግራይ ተጓዘ፡፡ እራሱ በመጽሐፉ መጀመሪያ የኾነውን ሲነግረን፤ “ከወታደር ህይወት አንዱ መገለጫ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ነው፡፡ ከአሁን በፊት ብዙ ቦታዎች ላይ ነበርን፤ አሁን ደግሞ ወደ ሌላ ቦታ እየሄድን ነው፡፡” ይለናል፡፡
እዚያ ሌላ ቦታ በምናብ አብረን እንሄዳለን፡፡ ያየውን እያሳየ የሚሆነውን ሳይነግር ልብ አንጠልጥሎ ትረካውን ይቀጥላል፡፡ በ93ኛው ገጽ እየኾነ ስላለው ነገር ሲያካፍለን፣ "በትግራይ ትንሹም ትልቁም! ሴቱም ወንዱም፤ ባለስልጣኑም ሚሊሻውም፣ ከተሜውም ገጠሬውም ሁሉም ስለ ፓርቲ፣ ስለ መንግስት ያወራሉ" ሲል የሚወራውን ይነግረናል፡፡ ከእንዲህ ያሉ ወሬዎች ቀጥሎ ስለሚሆነው ማሰብ አልተቻለም ነበር፡፡
አርኖ ሚሼል ዳባዲ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ደጃች ውቤ ዘንድ ተቀመጠ፡፡ በዚያ ወሬው ሁሉ ስለ ጦርነት ነው ይለናል፤ ሚሼል ዳባዲ፣ ራስ ዓሊ ላይ ዛቻው ፉከራውና ቀረርቶው አይሏል፡፡ የተካደው ሰሜን ዕዝ ደራሲ እንደሚነግረን፤ ሁሉም ሰው የአራት ኪሎውን ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሳደበው፣ እንደሚፎክርበት ሁሉ ደጃች ውቤም ዘንድ እንዲሁ ኾነ። ወሬው በጌምድር ስላሉት ራስ ነው፤ አስገራሚው ነገር አርኖ ሚሼል ዳባዲ፣ ደጃች ውቤ በነገሩ የተስማሙ ይመስላሉ፤ አይገስጹትም ይሉናል፡፡ ህወሃትም ነገሩን የተስማማችበት ትመስላለች አትገስጸውም፡፡ የሁለቱም የጦርነት ነጋሪት ድምጾች ውጤት፣ በምናውቀው መልኩ ጣጣ አመጣ፡፡
ጋሻዬ ጤናው፤ ጤና የለውም እስክንል ድረስ በትረካዎቹ የመከራ ጉዞዎች ያልተለመደ ጸባይ የምንመለከትበት የመጽሐፍ ተሸክሜ ወደ መቃብር ልውረድ ባይነቱን ነው፡፡ ደጋግሞ የምናየው፣ ጓዶቹን የሚያበሽቅበት፣ እኛን ጭምር ሊያበሳጨን የሚችል፣ ሁሉን ትቶ መጻሕፍት ካልተሸከምኩና ወደ ሞት ካልሄድኩ ባይነቱ ነው፡፡
እንዲህ አፍቃሪ መጽሐፍ ባይሆን ደግሞ መች ይሄንን ድንቅ ታሪክስ እናነበው ነበር?
ወታደር ነው፡፡ ለሀገሩ ሰው የቆመ፣ ለሀገሩ ወጥቶ ያደረ፡፡ ዓይኖቹ እኩል ያያሉ፣ ልቡ ፍትሕ አያዛባም፡፡ በምረቃው ወቅት ድንገት ብሔራዊ ቲያትር የታደሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄንን ሀሳቤን ተጋርተውታል፡፡
እዳጋ ሐሙስ አንዱ መቼት ነው፡፡ እዚያ ስለኾነው ከሚገለጽበት ስፍራ መካከል ገጽ 119 ይገኝበታል፡፡ በዚያ ጥይት እዚህም እዚያም በሚፈነዳበት ቀውጢ ጦርነት፣ ለህይወታቸው ሳይሳሱ ባሎቻቸውን የወደቁበትን ለማየት በእግራቸው በመጓዝ ይመጡ ነበር ይለናል፡፡
ምስክርነት ነው፡፡ ባሏን አርዳ አስገድላለች የሚለውን ሰምተናል፡፡ መራር መረጃ ይሆናል። የታፈነው ወታደር ጨክኖ ክፋት ብቻ ለማውራት ብዙ ምክንያቶች ነበሩት፤ ግን አላደረገውም፤ ሀገር የሚያድኑ መልካም እሴቶችን አልካዳቸውም፡፡
ስለ ተገደሉ ትግራዋይ ሚስቶች፣ አጥንት ሰባሪ ስድብ ስለተሰደቡ የወታደር ሚስቶች የሚነግረን ያመናል፡፡ የታመምነውን ሁሉ የታመሙ ትግራዋይ የእኛ ሰዎች እንዳሉ አልደበቀንም፡፡
ሌላ ታሪክ ልመርቅላችሁ፤ ገጽ 128 ስደርስ ያገኘሁት ነው፡፡ ሃያዎቹ መጨረሻ የምትገኝ ሴት እንደሆነች እድሜዋን ገምቷል፡፡ ነጋዴ ስትሆን በመንገድ ላይ ያልፉ ለነበሩ ታጋች ሰራዊት አባላት በሳፋ ከያዘችው ማንጎ ጁስና ስፕራይት ሸጠች፡፡ ከእነ ሳፋው የተቀበለው ወታደር መኪናው ሲነሳ ዕቃውን ይዞ ተጓዘ፡፡
ዕቃውን እያለች መከተሏን ምስል ከሳች በኾነ ትረካው አጋራን፡፡ ብሩንም ሳፋውንም ወረወሩላት፡፡ እነሱ አለፉ፤ ጸሐፊውን የያዘው መኪና በተራው ቆመ፡፡
ይሄኔ ያቺ ወጣት መጣች፡፡ “ይሄንን ብር ስጧቸው” ብላ መለሰች፡፡ መልሳቸው ነበር፡፡
ልጅቷ ምሳሌ ናት፡፡ እውነት ነው ወደ ጦርነቱ ለመግባት ምክንያት ከኾኑ ጣጣዎች አንዱ፤ ህዝብ የእኛ ያለውን ስልጣን በጉልበት የያዘ ፓርቲ፤ “ይሄንን ስልጣን ስጧቸው” ማለት አቅቶት ነበር፤ ከ1992 ምርጫ መኪና ያስተረፈውን መልስ በ1997 የነበረው ሲደርስ “እንኩ ይሄንን ድምጽ ስጧቸው” ብሎ የመራጮችን ንብረትና ምኞት መልሶ ቢኾን ጦርነት ቅዠት በኾነ፡፡
እሷ የሰው ሃቅ፤ ሊያውም ቀን የጣለውና ጠላት የተባለ ታፋኝ ወታደር ሃቅ መብላት አትፈልግም፡፡ እናም “ይሄንን ብር ስጧቸው” አለች፡፡ ስልጣኑን ለዓመታት ይዘው የኖሩት የትህነግ ጦር መሪዎች፣ እንደ ልጅቷ “እንኩ ለብቻችን ይዘነው የነበረውን መከላከያ ስጧቸው” ብለው ቢሆን፣ ብዙ የሌላ ድርሻ ነው ያሉትን፣ የራሳቸውን ድርሻ ወስደው እንደ ልጅቷ "የእኔ አይደለም" በሚል መንፈስ፣ እንኩ ስጧቸው ማለት ችለው ቢሆን፣ ያ ክፉ ውጤት በተቀየረ፡፡
የጭካኔ ታሪኮችን ተጋነውም፣ ተሞልተውም፣ ተደጋግመውም፣ ስፍራ እየቀየሩም ሰምተናቸዋል፡፡ ጋሻዬ ጤናው ግን የደግነት ማሳያዎችን ሳይክድ ያጋራናል፡፡ ሳያፍን የመታፈኑ ቂም መወጫ ሳያደርጋቸው ያካፍለናል፡፡
የወርቅ አምባ እናቶች ያላቸውን ማቃመስ፣ በገጽ 190 የሚነግረን የሽሬ እናት፣ ቀኗ የደረሰ የከበደች ወታደር እንደምን እንዳዋለዱና እንዳረሱ የሚያወራው ምስክርነት፣ የፋፄ ቸርነት የትናንት ብቻ ሳይሆን የነገም ተስፋዎቻችን ናቸው፡፡
የፋፄውን ላካፍላችሁ፤ ፋፄ በጦርነት ሳቢያ መከራዋን ያየች የድንበር ላይ መንደር ናት፡፡ በኢትዮጵያ ኤርትራ ጦርነት አበሳዋን አይታለች፡፡ ለአዲግራት ብትቀርብም እድገቷን ጦርነት የቀጨው ስለኾነ ምስኪን ቀዬ ናት፡፡
አውቃታለሁ፡፡ ደግ ህዝቧንም አውቀዋለሁ፡፡ ጥቅምት ሃያ አራት ቀን እልቂት ከነበረበት ቦታ አንዱ እንደሆነ የሚነግረን ታፋኙ ወታደር፣ ከሚሊሺያውና ከልዩ ኃይሉ ጋር የተዋጋው የሰሜን ዕዝ ወታደር ገደለ ሞተ፡፡ የፋፄ ሰው ግን ጠላት የተባለውን ሠራዊት ለጅብ እንዲወድቅ አልፈቀደም፡፡ አለቀሰ፣ ገነዘ፣ ፍትሃት ፈታና ቀበረ፡፡ ይሄ ደግ ህዝብ ቂምና በቀል፣ ጥላቻና አንድ ዓይነት የመባል የጭካኔ ስሜትንም አብሮ ቀብሯል፡፡
ለቃል ስለታመኑ ወታደሮች የሚነግረን ልብ ይነካል፡፡ ሴሮ የታላቋ ኢትዮጵያ ዘብ ምልክት ነው፡፡ ከገጽ 229 ባገኘሁት መረጃ ስሙ አይደለም፡፡ የትውልድ ቀዬው መጠሪያ ስለኾነ እሱም እንደ ቅጽል ስም በዚህ ይጠራል፡፡ ሀምሳ አለቃ ነው፡፡ ገብረ ሥላሴ ይባላል፡፡ ብርጌዱ አራተኛ ሲሆን በወቅቱ ከሠራዊቱ ጎን ቆሞ በትውልድ ቀዬው በነበረ ጦርነት ተሰዋ፡፡
ደግሞ እንዲህ ያሉ ባለ ቃልኪዳኖች ብሔርም ጾታም አይወስናቸውም፡፡ ምክትል አስር አለቃ ምላሽ ማመን ቋንቋ ለሀገር መቆም ያልነጠላት ትግራዋይ ኾና፣ ከሠራዊቱ ጋር አብራ ስትዋጋ የቆሰለች፣ በዚያ ሳቢያ የተሰቃየች ስለመኾኗ ጸሐፊውን ይተርክልናል፡፡
የቃል ኪዳን ፍቅሩ በሞት ተገልጧል፡፡ በመውደቅና፣ በመቁሰል ታይቷል፡፡ በእንባና በቁጭት ስሜትን ፈንቅሏል፡፡ የሬንጀር ፍቅር ውስጥ አብሮ እስኪቃጠል ሠራዊት ሲያቃጥል አይተናል፡፡
ክፋት የእኛና የእነሱ ሰው ብሎ አጥር አልባነቱን ሳይሸሽግ የመሰከረው ጋሻዬ ከብዙ መከራ፣ ስቃይ፣ ህመምና ሞት አስናፋቂ ጉዞ በኋላ፣ ተከዜ ሲደርስ የእኛ ሰው ብሎ ሠራዊቱ በተደሰተበት ስፍራ ጥልቅ ውሃ መሃል ላይ ጀልባ አቁሞ፣ በራስ ቋንቋ የራስ ሰው ነኝ የሚል አውሬ ገንዘብ ሲደራደር፣ ዋጋ ሲያስጨምር፣ ከተስማማበት ቃል ሲያልፍ ተመልክተን እንታመማለን፣ ደግሞ እንባ እንራጫለን፡፡ ደግሞ ወታደር የትም ዘብ መኾኑን ለተማሪዎች ነፍስ የሚገደው ከአፈና የተተፋ ወገን እኛ እንክፈል ሲል ስሜታችን ይነካል፡፡
እንዲህ ባሉ ታሪኮች፣ ለሀገሩ ዘብ በቆመና፣ የሀገሩን ሰው ያለ አድልዎ በሚመለከት ሃምሳ አለቃ ወታደር ብዙ እንማራለን፣ ጓደኝነትና ህዝባዊነት፣ ሁሉን መናቅና ከሁሉ መጻሕፍትን መውደድ፣ ከሞት መትረፍና ከስደተኛ ማትረፍ ብቻ ብዙ ያስተምረናል፡፡ ነገን የሚሰራ መጽሐፍ እንደሆነ አምኛለሁ፡፡ ወታደራዊ ድርሰቶችን መንቀስ የሚችሉ ብቁ ሰዎች ብዙ ቢሉበት ደግሞ ካላየነው ወዲያ ያለ፣ የታፈነ አዳዲስ ነገሮች እንማርበታለን፡፡
እንዲህ አይነት ሰዎች መትረፋቸው ታሪክ ያተርፍልናልና፣ ጋሻዬ እንኳን ያንን አልፎ እኛ ጋር ተነበበ፡፡
Read 1441 times