Saturday, 16 April 2022 13:53

በኢትዮጵያ ባለፉት 18 ወራት መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

   ባለፉት  18 ወራት በኢትዮጵያ በመንግስት የፀጥታ ሃይሎችና በታጣቂ ቡድኖች መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈፀማቸውን የአሜሪካ የውጭ  ጉዳይ መስሪያ ቤት አመልክቷል፡፡
የውጭ  ጉዳይ መስሪያ ቤቱ የዓለም አገራት የሰብዓዊ መብት ይዞታን በገመገመበት ዓመታዊ ሪፖርቱ ከአፍሪካ ሃገራት ኢትዮጵያና ኤርትራን በከፋ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ወንጅሏል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ ላለፉት አንድ ዓመት ከ6 ወራት በዘለቀው ጦርነትና ግጭት እንዲሁም በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች በነበሩት የመንግስት የፀጥታ ሃይሎችና የታጣቂ ቡድኖች ግጭት ሳብያ  በርካታ ኢትዮጵያውያን ለሰብአዊ መብት ጥሰቶች መዳረጋቸውን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
 በመንግስት የፀጥታ አካላት ተፈፅመዋል ተብለው በሪፖርቱ ከተጠቀሱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መካከል ከህግ ፍቃድ ውጪ በሰዎች ላይ ግድያ መፈጸም፣የሰዎችን ደብዛ ማጥፋት፣የጭካኔ ተግባራትና ማሰቃየት፣ እስረኞችን ያለጥፋት አግቶ ማቆየትና ያልተገባ የእስር ቤት አያያዝ እንዲሁም በፖለቲካ ልዩነትምክንያት ሰዎችን የማንገላታትና የማሰር ተግባራት ይገኝበታል፡፡
በመንግስት ሃይሎች ከተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በተጨማሪ በተለያዩ አካባቢዎች  የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ቡድኖችም የከፋ ድርጊት መፈፀማቸውን  አስገንዝቧል ሪፖርቱ፡፡
በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣በአፋር፣በሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች ታጣቂዎች በሠላማዊ ሰዎች ላይ የከፋ ጥቃት እንደፈፀሙ ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡
በአፋርና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ  አካባቢዎች በተፈጠረ ግጭት የአካባቢው ሚሊሻ አባላት ንፁሃን ዜጎችን መግደላቸውን፣ በኦሮሚያ መንግስት “ሸኔ” ብሎ የሚጠራው ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ጦር ብሎ የሰየመው ቡድንም፤ በንፁሃን ዜጎችና  የመንግስት ባለስልጣናት ላይ ግድያዎች መፈፀሙን የውጭ ጉዳይ መ/ቤቱ ሪፖርት አመልክቷል፡፡
በትግራይ  የሚንቀሳቀሰው የህወኃት ታጣቂ ቡድንም በተመሳሳይ በንፁሃን ላይ ከፈጸማቸው ግድያዎች በተጨማሪ ህጻናትን ለጦርነት በመጠቀምም በሪፖርቱ ተወንጅሏል፡፡ ኤርትራን በተመለከተ ደግሞ በሃገሪቱ ያለው መንግስት በገዛ  ዜጎቹ ላይ ከፈፀማቸው የመብት ጥሰቶች በተጨማሪ የሃገሪቱ መከላከያ ሰራዊት በኢትየጶያ ውስጥ የሰላማዊ ሰዎች ግድያን ጨምሮ በአስገድዶ መድፈር፣ማሰቃየትና በበርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂ መሆኑን አመልክቷል  የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መ/ቤት ሪፖርት።

Read 10723 times