Saturday, 16 April 2022 14:15

ምክንያታቸው ከጭራ የቀጠነ፣ ከጤፍ ያነሰም ቢሆን---

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

 “በኢትዮጵያ በሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካና የሃሳብ መሪዎች እንዲሁም የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል፣ እጅግ መሰረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሃሳብ ልዩነትና አለመግባባት እየታየ በመሆኑ፣ ይህን ልዩነትና አለመግባባት ለመፍታት ሰፋፊ ሀገራዊ የህዝብ ምክክሮችን አካታች በሆነ መንገድ በማካሄድ ሀገራዊ መግባባት መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ”
(የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1265/2014 መግቢያ)

በአዋጁ መግቢያ ላይ የሰፈሩትን ዋና ዋና ጉዳዮችን የያዙ ቃላትን በቅርበት ማጤን ስለ ሃገራዊ ምክክሩ ጠቃሚ ሃሳብን ለመሰንዘር ይረዳል፡፡ በመግቢያው ላይ  እንደሚታየው ብሔራዊ ምክክሩ ላይ በመሳተፍ የድርሻቸውን አስተዋፅኦ ያደርጋሉ ተብለው የታመነባቸው ሶስት ወገኖች አሉ፡፡ ከእነሱም የመጀመሪያዎቹ የልዩ ልዩ የፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎች ናቸው፡፡ እንደነሱ ሁሉ ያቋቋሙት ድርጅት ባይኖርም፣ ከዚህ በቀደመው ጊዜ በልዩ ልዩ መንገድ ወደ ህዝብ በሚያደርሱት ሀሳብ የታወቁ ብዙ ተከታይ ያላቸው “እከሌ ምን አለ” ተብለው የሚፈለጉ ሃሳብ አፍላቂዎች ናቸው፤ ሁለተኛዎቹ፡፡ ሌላኛው ባለ ድርሻ የህብረተሰብ ክፍሎች በመባል የተገለጡት ናቸው፡፡ የንግዱ ህብረተሰብ፣ የጤና ሙያተኞች ህብረተሰብ የሚል የተለመደ አጠራር አለ፡፡ ይህ እነሱን ብቻ ነው የሚመለከተው ወይስ ብሔረሰብን ያካትታል? በግልጽ ቢቀመጥ ወይም ኮሚሽኑ ማብራሪያ ቢሰጥበት በምክክር መድረኩ እንዳልገባ ተገፍቻለሁ የሚል ቅሬታ  እንዳይፈጠር ለማድረግም ይጠቅማል፡፡
አገራዊ ምክክሩን  አስፈላጊ ያደረገው ቀደም ሲል በተጠቀሱት ሦስት ክፍሎች መካከል እጅግ መሰረታዊ  በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሃሳብ ልዩነት በመታየቱና መግባባትም ባለመኖሩ መሆኑ ተገልጧል፡፡ የሚደረገው ጥረት ሁሉ ግብ ደግሞ አገራዊ መግባባትን በመፍጠር በሚመለከታቸው ክፍሎች መካከል መተማመንና መቀራረብ፣ በሂደትም አብሮ መስራት እንዲኖር ማድረግ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
በሀገራችን ያሉት የፖለቲካ ድርጅቶች በብሔርና በአገር አቀፍ የተደራጁ ናቸው፡፡ የብሔር ድርጅቶች ሲያብሰለስላቸው ውሎ ሲያብሰለስላቸው የሚያድረው ቆመንለታል የሚሉት የብሔር ጉዳይ ነው፡፡ አንዳንዶቹም ትልቋን ኢትዮጵያን አፍርሰው ትናንሽ መንግስታት ለማቆም የሚማስኑ ናቸው፡፡ ሌሎች ትልቅ ነን ብለው ራሳቸውን የሚያዩና ትናንሾቹ --- የሚይታያቸው፤ ትናንሾች  ሲደማመሩ የእነሱን ያህል ግዙፍነት ሊያመጡ እንደሚችሉ የማይገለጥላቸው፣ እንዲያውም ትናንሾችን ውጠው የበለጠ መግዘፍን የሚመኙም  ናቸው፡፡ ትናንሾችም ሆኑ ትላልቆች በትልቋ ኢትዮጵያ ውስጥ ክብራቸውን ማስጠበቅ፣  ጥቆማቸውም  እንዳይጎድል  ማድረግ አይታያቸውም፡፡
ሕብረ ብሔር ድርጅቶች የሚያስቡትና የሚጠነቀቁት  ለትልቋ ኢትዮጵያ ቢሆንም፣ በየአካባቢው ያሉት የብሔር ድርጅቶች እየሰሩ ስላለው ሥራ አይናቸውን የከፈቱ አይመስሉም፡፡ በ2013 ዓ.ም በተደረገው አገር አቀፍ ምርጫ አንዳንድ የብሔረሰብ ድርጅት ደጋፊዎች፣ ሕብረ ብሔር ድርጅቶችን በአካባቢያችን አትደርሱም ብለው መንገድ መዝጋታቸውን ማስታወስ ይገባል፤ ለመዘጋጀት ወይም ለመጠንቀቅ፡፡
አሁን የምንገኘው አንድ መረጃ ወደ ህዝብ ለማድረስ እጅግ ብዙ መንገዶች ባሉበት ዘመን ላይ ነው፡፡  ከጋዜጣ ከቴሌቪዥንና ራዲዮ በላይ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተከታታይ ያላቸው የማህበራዊ  ገፆች ጌቶች አሉ፡፡ የገፁ ባለቤቶች  “የሃሳብ መሪዎች” ተብለው የተገለጹት ይመስሉኛል፡፡ እነሱ ወደ ምክክር መድረኩ የሚመጡት እንዴት ነው የሚል ጥያቄን መሰንዘር አስፈላጊ ነው። ወደ ምክክር መድረኩ በመግባታቸው ብቻ ሳይሆን ምክክሩ ላይ ያልተፈለገ ጫና በመፍጠር የሚኖራቸው ተጽዕኖም አበክሮ ሊታሰብበት ይገባል፡፡
አስቀድሞ በኮሚሽኑ መቋቋም ከተቋቋመም በኋላ ተገለናል የሚሉ ፓርቲዎች ብዙ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹም ምርር ብለው ራሳቸውን ከምክክሩ ለማግለል መወሰናቸውን በመግለጫቸው እያስታወቁ ነው፡፡ የሚያቀርቡት ምክንያት ከጭራ የቀጠነ፣ ከጤፍ ፍሬ ያነሰ ቢሆንም እንኳ እንደምንም አሳምኖ እነዚህን ወገኖች ወደ ውይይቱ ማምጣት ወሳኝ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የሚመለከተው ወገን ጉዳዩን በቅጡ ሊያስብበት ይገባል፡፡ ካልሆነ ነገሩ ሁሉ የልጆች ጨዋታ ከመሆን አይድንም፡፡
ወደ ምክክር ኮሚሽኑ ስንመጣ፣ ከተሰጡት ስራዎች የመጀመሪያው፣ የምክክር አጀንዳዎችን መዘርዘር መፈተሽና ምክክር እንዲደረግባቸው መወሰን ነው፡፡ ከላይ የጠቀስኳቸው የፖለቲካ ድርጅቶችና ሃሳብ አፍላቂዎች ስለ ለሀገራዊ ጉዳይ ያላነሱትና ለህዝብ ያላደረሱት፤ መፍትሔ ይሆናል ብለውም  ያልወረወሩት ሃሳብ የለም። ከእነዚያ ውስጥ የቱ በምን መልክ ቀርቦ ምክከር ይደረግበት ብሎ መወሰን ከኮሚሽኑ የሚጠበቅ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ልዩ ልዩ ኮሚቴዎች ማቋቋም ይኖርበታል፤ በአዋጅም የተፈቀደለት ነውና፡፡
ለምክክር ኮሚሽኑ የተሰጠው የመቆያ ጊዜና ኃላፊነት ሲታይ ቀን ብቻ ሳይሆን ምሽትም እንደ ሌሊት ወፍ መብረር  ሳይኖርበት አይቀርም፡፡ ኮሚሽነሮቹ ከተሾሙ ወር የሞላቸው ቢሆንም እስከ አሁን ምን ላይ እንደደረሱ የሰማነው ነገር የለም፡፡ ምናልባት ማትጋት ወይም ነቃ በሉ ማለት ያስፈልግ ይሆናል፡፡
በመጨረሻ ቅድም ያነሳሁትን እደግመዋለሁ፡፡ በምክክር ኮሚሽኑ ላይ ቅሬታ የሚያነሱ ወገኖች አሁንም መደመጥ  አለባቸው፤ ምክንያታቸው ከጭራ የቀጠነ፣ ከጤፍ ፍሬ ያነሰም እንኳ ቢሆን ጆሮ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡

Read 1520 times