Saturday, 16 April 2022 14:33

67 በመቶ የዩክሬን ህጻናት መፈናቀላቸው ተነገረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   50 ቀናትን ያለፈው የሩስያና የዩክሬን ጦርነት እንደቀጠለ ሲሆን ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከአጠቃላዩ የዩክሬን ህጻናት መካከል 67 በመቶ የሚጠጉት ወይም 4.8 ሚሊዮን የሚሆኑት ለመፈናቀል አደጋ መዳረጋቸውን የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ አስታውቋል፡፡
ድርጅቱ ሰሞኑን ባወጣው መረጃ እንዳለው፤ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ 2 ሚሊዮን የዩክሬን ህጻናት አገራቸውን ጥለው ወደ ሌሎች አገራት ሲሰደዱ፣ ተጨማሪ 2.8 ሚሊዮን ህጻናት ደግሞ ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለው የከፋ ኑሮን በመግፋት ላይ ይገኛሉ፡፡
በአገሪቱ ከሚገኙ 3.2 ሚሊዮን ያህል ህጻናት መካከል ግማሽ ያህሉ በቂ ምግብ እንደማያገኙ የጠቆመው ድርጅቱ፤ በጦርነቱ ምክንያት የመጠጥ ውሃ ተቋማት በመውደማቸው ሳቢያ 1.4 ሚሊዮን ያህል የአገሪቱ ዜጎች የመጠጥ ውሃ እንደማያገኙም አመልክቷል፡፡
ሲቢኤስ ኒውስ በበኩሉ፤ ጦርነቱ 4.6 ሚሊዮን ያህል ዩክሬናውያንን ለስደት ቢዳርግም፣ በአንጻሩ ደግሞ ጦርነቱ ከተጀመረበት ዕለት አንስቶ በነበሩት 10 ቀናት ብቻ ከ200 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሩስያውያን አገራቸውን ጥለው መሰደዳቸውንና ጦርነቱን የተቃወሙ ከ15 ሺህ በላይ ሩስያውያንም በመንግስት ሃይሎች እንደታሰሩ ዘግቧል፡፡
ከዩክሬን ያልተጠበቀ መከላከልና ጥቃት ያጋጠማት ሩስያ በማሪዮፖል ፍልሚያዋን መቀጠሏንና ፊቷን ከመዲናዋ ኪየቭ ወደ ምስራቃዊዋ ዶባንስ አቅጣጫ ለማዞር ማሰቧ የተነገረ ሲሆን፣ ሩስያ ከሰሞኑ በማሪዮፖል የወደብ ከተማ በተደረገ ጦርነት 1 ሺህ 26 የዩክሬን ባህር ሃይል ወታደሮች እጅ መስጠታቸውን ይፋ ማድረጓ ተዘግቧል፡፡
ስዊድንና ፊንላንድ በቅርቡ የሰሜን ጦር ቃልኪዳን ድርጅት ኔቶን ለመቀላቀል ማሰባቸው ከሰሞኑ ይፋ መደረጉን ተከትሎ፣ የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ፣ አገራቱ የድርጅቱ አባል ከመሆን እንዲቆጠቡ ማስጠንቀቃቸው ተነግሯል፡፡
በሌላ በኩል፤ የሩስያና የዩክሬን ጦርነት አመታዊውን አለማቀፍ የኢኮኖሚ እድገት ከተገመተው በግማሽ ያህል ሊቀንሰው እንደሚችል የአለም የንግድ ድርጅት ያስታወቀ ሲሆን፣ አመታዊ እድገቱ ባለፈው ጥቅምት ወር ተገምቶ ከነበረው 4.7 በመቶ ወደ 2.4 በመቶ ዝቅ ሊል እንደሚችል አመልክቷል፡፡
አገራቱ ወደተቀረው አለም የሚልኩት ምርት በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱ ከፍተኛ የሆነ አለማቀፍ የዋጋ መናር ማስከተሉን የጠቆመው ድርጅቱ፤ በቀጣይም በተለይ ድሃ አገራትን ክፉኛ ተጎጂ ሊያደርግ እንደሚችል አስጠንቅቋል፡፡
በተያያዘ ዜናም፣ የሩሲያ መንግስት ወደ ውጭ አገራት በሚላክ የስንዴ ምርት ላይ የታክስ ጭማሪ ማደረጉን የአገሪቱ ግብርና ሚኒስቴር ባለፈው ረቡዕ ያስታወቀ ሲሆን፣ የታክስ ጭማሪው በበቆሎና ገብስ ምርቶችም ላይ መጣሉን ዘገባዎች ያመለክታሉ።
የተቀረው አለም በሩስያ ላይ ጫናውን እንዲያሳድር መወትወታቸውን የቀጠሉት የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ ከሰሞኑ ደግሞ በአፍሪካ ህብረት ንግግር ለማድረግ መጠየቃቸውን የህብረቱ ሊቀ-መንበር ማኪ ሳል ማስታወቃቸውን ኦል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡



Read 1652 times