Sunday, 17 April 2022 00:00

የኮሮና ተጠቂዎች ቁጥር ከግማሽ ቢሊዮን አልፏል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   የኮሮና ቫይረስ በወረርሽኝ መልክ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ በመላው አለም ተጠቂ ያደረጋቸው ሰዎች ቁጥር ባለፈው ረቡዕ ከግማሽ ቢሊዮን ማለፉን ጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ይፋ ቢያደርግም፣ ትክክለኛው ቁጥር ግን ከዚህ በእጅጉ ሊበልጥ እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡
አለማቀፉ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ረቡዕ ዕለት 500 ሚሊዮን 900 ሺህ ማለፉን የጠቆመው ዩኒቨርሲቲው፣ በቫይረሱ ለሞት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር ከ6.18 ሚሊዮን ማለፉንና ከ11.12 ቢሊዮን በላይ የተለያዩ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች መሰጠታቸውንም አመልክቷል፡፡
አሜሪካ ከ80.4 ሚሊዮን በላይ በሚሆኑ ተጠቂዎችና ከ986 ሺህ በላይ ሟቾች ከአለማችን አገራት በአንደኛ ደረጃ ተጎጂ ስትሆን፣ ይህ ቁጥር ግን እንደሌሎች አገራት ሁሉ ከእውነተኛው በእጅጉ ያነሰ ነው የተባለ ሲሆን በተለይ በአፍሪካ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ከሚባለው በ100 ጊዜ ያህል ሊበልጥ እንደሚችል የአለም የጤና ድርጅት አመልክቷል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2021 ብቻ በመላው አለም 77 ሚሊዮን ሰዎችን ለከፋ ድህነት መዳረጉንና በርካታ በማደግ ላይ የሚገኙ አገራትንም ወደከፋ የኢኮኖሚ ቀውስ በማስገባት ለማገገም የማይችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ተመድ አስታውቋል፡፡
በተያያዘ ዜናም፤ የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን፣ ብሔራዊ የኮቪድ ክልከላዎችን በመተላለፍ ከሰሞኑ በመኖሪያ ቤታቸው በተዘጋጀ የልደት ፕሮግራም ላይ ከብዙ ሰዎች ጋር በመታደማቸው የገንዘብ ቅጣት ተጥሎባቸው ክፍያውን ፈጽመው ይቅርታ ቢጠይቁም፣ በማህበራዊ ድረገጽ በተከፈተባቸው ዘመቻ ስልጣናቸውን እንዲለቁ ግፊት እየተደረገባቸው እንደሚገኝ አል አይን ኒውስ ዘግቧል፡፡

Read 2532 times