Print this page
Monday, 18 April 2022 00:00

በምስራቅ አፍሪካ በ40 አመታት የከፋው ድርቅ ሊከሰት እንደሚችል ተነገረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   ሩብ ያህሉ የአለም ህዝብ ወደ ከፋ ድህነት ሊገባ ይችላል ተባለ

             ዘንድሮ በምስራቅ አፍሪካ አገራት ባለፉት 40 አመታት ታሪክ እጅግ የከፋ የተባለው ድርቅ ሊከሰት እንደሚችል ኢጋድ ከሰሞኑ ከናይሮቢ ቢሮው ባወጣው መግለጫ ያስታወቀ ሲሆን ኦክስፋም በበኩሉ፤ የሩስያና የዩክሬን ጦርነት ሩብ ያህሉን የአለም ህዝብ ወደ ከፋ ድህነት ሊያስገባው እንደሚችል አስጠንቅቋል፡፡
በምስራቅ አፍሪካ አገራት ባለፉት አመታት ከፍተኛ የሙቀት መጠን መጨመር መታየቱንና ከሚጠበቀው መጠን በታች ዝናብ መመዝገቡን የጠቆመው ድርጅቱ፤ በሶማሊያ ኬንያ፣ ኢትዮጵያና ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ አገራት የሚኖሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በድርቁ ክፉኛ ሊጎዱ እንደሚችሉና በ40 አመታት ታሪክ የከፋው ድርቅ ሊከሰት እንደሚችልም አስታውቋል፡፡
በአገራቱ ከ29 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከፍተኛ የምግብ ዋስትና ችግር እንዳለባቸው የጠቆመው ድርጅቱ፣ 16 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችም አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸውና የውሃና እጥረት ምርትን በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰና እንስሳትንም በመኖ እጥረት በከፍተኛ መጠን እየገደለ እንደሚገኝም አመልክቷል፡፡
በተያያዘ ዜና ደግሞ፤ አለማቀፉ ተቋም ኦክስፋም፣ የሩስያና የዩክሬን ጦርነት ያስከተለው የምግብ ዋጋ መናርና የሃይል ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱ ከአጠቃላዩ የአለማችን ህዝብ ሩብ ያህሉን ወደ ከፋ ድህነት ሊያስገባ እንደሚችል አስጠንቅቋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለው አለማቀፍ ቀውስ ሳያንስ ጦርነቱ መቀስቀሱ አለማችንን ወደባሰ ፈተና እንደሚያስገባት የጠቆመው ተቋሙ፤ ያደጉ አገራት የድሃ አገራትን ብድር በመሰረዝ ከከፋ ጥፋት ሊታደጓቸው እንደሚገባ ምክሩን ለግሷል፡፡
የአለም ባንክ ኮሮና 198 ሚሊዮን ሰዎችን በዚህ አመት ወደከፋ ድህነት ሊያስገባ እንደሚችል ማስታወቁን ያስታወሰው ዘ ጋርዲያን፤ ኦክስፋም በበኩሉ ማክሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ የሩስያና የዩክሬን ጦርነትና የሃይል ዋጋ መናር ተጨማሪ 5 ሚሊዮን ሰዎችን ለድህነት ሊዳርግ እንደሚችል ማስጠንቀቁን ዘግቧል፡፡


Read 1211 times
Administrator

Latest from Administrator