Saturday, 16 April 2022 14:47

‘ትዌንቲ ታውዘንድ’ እና ድንኳን ሰበራ!

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 "--ቀደም ሲል እኮ አይደለም ውሎ አበል ጋዜጠኛው አንዲት ኩኪስ እንዳይቀምስ የሚከለክሉ ሚዲያዎች ነበሩ፡፡ ውሎ አበል ካስፈለገም ራሳቸው ʻቺክንፊድʼ የሚሏት አይነት ትንሽዬ ብር ይወረውሩ ነበር፡፡ ለዚያውም ደግሞ የሂሳብ ክፍሉን አለቃና የገንዘብ ከፋዩዋን ግልምጫ ችሎ! እንደሱ አይነት ነገር ቀረ እንዴ!--"
            
              እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው...እንግዲህ ጨዋታም አይደል...ለካስ ድራፍት ሠላሳ ብር ገባ የሚባለው ዝም ተብሎ አይደለም! አሀ...ምድረ ጋዜጠኛ ከውሎ አበል ብቻ በወር እስከ ሀያ ሺህ ብር (ትዌንቲ ታውዘንድ!) ያገኛል እየተባለ ድራፍቱ ሠላሳ ብር ላይ መቆሙም ተመስገን ነው ቂ...ቂ...ቂ...።  ኮሚክ እኮ ነው፡፡ አለ አይደል የአበል ፍራንክ በየወሩ ፔይሮል ላይ የሚፈረምበትን አልፎ ሲሄድ...ወይ የለቀቁ ክሮች  አሉ፣ ወይ ደግሞ ነገሮች በደንብ ሳይገቡን ዘመን ጥሎን እየሄደ ነው ማለት ነው፡፡ በዚህ ላይ እንዳልተጠራ የሰርግ ድንኳን ሰባሪ ሁሉ ውሎ አበልን በተመለከተ ጋዜጠኝነቱም ውስጥ ድንኳን ሰበራ የሚባል ነገር አለ መባሉን፣ ከተፈለገ መሀረብ እንደሚያስጨርስ ትራጄዲ፣ ከተፈለገም በሳቅ ሆድ እንደሚያቆስል ኮሜዲም መውሰድ ይቻላል፡፡ እናላችሁ... ፈረንጅ ʻኢንተረስቲንግʼ የሚላቸው እኮ እንዲህ አይነት ነገሮችን ነው፡፡
ምን ገረመኝ መሰላችሁ... መጀመሪያስ ቢሆን ድንኳን ሰበራ ብሎ ነገርን ምን አመጣው! ያው መቼም እዚችም፣ እዛችም የምንሰማቸው ነገሮች ቢኖሩም፣ የመጡበት ሳይታወቅ አበል የሚወስዱ ምናምን የሚለው ትንሽ ያልጠረጠረ... ምናምን ነገር አያስብልም! አሀ...ልክ ነዋ... አበሉን የሚያከፋፍሉት ለማን እንደሰጡ፣ ፍራንክዬው ስንት ስንት እንደሆነ ምናምን ʻየሚጥፉትʼ ነገር የላቸውም እንዴ!
ጋዜጠኛ የብርወርቄ አበላቸው... ሁለት ሺህ አምስት መቶ ብር!
ጋዜጠኛ ሞላልኝ አበሉ....ሁለት ሺህ አምስት መቶ ብር!
አስተባባሪ ጋዜጠኛ አበሌ ዳር ከዳር .... ሁለት ሺህ አምስት መቶ ብር!
እያለ ሊቀጥል  ይችላል፡፡
ለነገሩማ...ለማሳበቅ ያህል...አንዳንድ ቦታ ውሎ አበል አዳዮቹም ʻለአምጪው እንዲሰጥ ህጉ  ያስገድዳልʼ የሚል ያልተጻፈ ህግ ያለ ይመስላል ሲባል ስንሰማ ኖረናል፡፡ እኔ የምለው ግን፣ እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... አለ አይደል...ያቺ ወሳኝ የነበረችው ሞዴል ስደስት ምናምን የሚሏት ነገር ቀረች ማለት ነው! ግርም የሚለው ደግሞ ጋዜጠኝነታቸው ወይም የትኛውን ድርጅት እንደሚወክሉ የማይታወቁ ሰዎች አሉ መባሉ ነው፡፡ እዚህ ሀገር እኮ በአግራሞትና አንዳንዴም በብሽቀት አለመሳቅ አይቻልም፡፡
እኔ የምለው.... ዘንድሮ የአበል ክፍያ ላለበት የፕሬስ መግለጫ ጋዜጠኞች ሲጠሩ እንደ እድር በጥሩምባ... “የሀገር ውስጥ ጋዜጠኛ ነን የምትሉ ሁሉ ከቀኑ ስምንት ሰዓት በእንትን አዳራሽ ፕሬስ መግለጫ ስለሚሰጥ በሰዓቱ እንድትገኙ። በፕሬስ መግለጫው ላይ የማይገኙ ጋዜጠኞች ወይም አርፍደው ለሚመጡ ጋዜጠኞች የቀበሌ ሰልፍ የማያስፈልግባት የውሎ አበል ... ስኳሯ እንዳማረቻቸው ትቀራለች፣” ይባላል እንዴ! ስሙኝማ...ስታንድአፕ ኮሜዲ አቅራቢዎች ...  የጋዜጠኝነት ድንኳን ሰባሪዎች የምትለዋ ነገር አሪፍ 'ኮንሴፕት' አይደለች!
እናላችሁ... የምር የተጻፉም፣ ያልተጻፉም ህጎች ተለውጠዋል ማለት ነው፡፡ ልክ ነዋ! ሊበራሊዝም ይሁን ምናምኒዝም ይሁን እንጃ እንጂ ይሄ የእውነተኛው ጋዜጠኛም የድንኳን ሰባሪውም ኪስና ቦርሳ እንዳይነፍስበት እያደረገ ላለው ʻውሎ አበልʼ ፈረንጅኛው ʻዊይርድʼ ከሚላቸው ሀገራችን--በተለይ ቦተሊካው--የተለያዩ ቡድኖች አንዱ ተነስቶ “መታሰቢያ ይታነጽለት፣” ቢል እንዳትገረሙ... “እዚች ሀገር ላይ ሊሆን አይችልም የሚባል ነገር አይኖርም!” የሚል ደረጃ ላይ ደርሰናልና! ለውጥማ አለ፣ (ቂ...ቂ...ቂ...) ቀደም ሲል እኮ አይደለም ውሎ አበል ጋዜጠኛው አንዲት ኩኪስ እንዳይቀምስ የሚከለክሉ ሚዲያዎች ነበሩ፡፡ ውሎ አበል ካስፈለገም ራሳቸው ʻቺክንፊድʼ የሚሏት አይነት ትንሽዬ ብር ይወረውሩ ነበር፡፡ ለዚያውም ደግሞ የሂሳብ ክፍሉን አለቃና የገንዘብ ከፋዩዋን ግልምጫ ችሎ! እንደሱ አይነት ነገር ቀረ እንዴ!
እናላችሁ...ከዚህ በፊት የደጋገምናትን ነገር ለማስታወስ ያህል ስሙኝማ፡፡ በቀድሞ ጊዜ አንዲት በወቅቱ “ጥይት!” የምትባል ጋዜጠኛ፣ ጋሽ ይድነቃቸውን ‘እየጠየቀች’ ነበር አሉ፡፡ እናላችሁ ለደቂቃዎች ዲስኩር የምትመሳስል ነገር ካወራች በኋላ “እዚህ ላይ እርሶ ምን ይላሉ?” የሚል ነገር ትጠይቃለች። ይሄኔ የጂብራልታሩ ዓለት ምን አሏት አሉ መሰላችሁ...“አንቺ ጨርሰሽው እኔ ምን እላለሁ!” ዘንድሮ እንዲህ የሚሉ ተጠያቂዎች ቢኖሩ ኖሮ፣ ምን ይሆን ነበር መሰላችሁ... በቃ፣ የቃለ ምልልስ ስቱዲዮ ሁሉ የሸረሪቶች ʻወርልድ ካፕʼ ምናምን የሚካሄድበት ይሆን ነበር፡፡ አሀ... ለቃለ መጠይቅ የሚጋበዙ ሰዎች “እኔ እዛ የምሄደው ተቀምጬ የእነሱን ዲስኩር ለመስማት ነው እንዴ!” ብለው ድርሽ አይሏትማ!
ስሙኝማ...የምር ግን የውሎ አበልዋ ነገር እንዳለ ሆኖ...እንደው ከጊዜ ጋር የማይሻሻሉ ነገሮች መኖራቸው በዚህ ዘመን ግርም አይላችሁም! የተጠያቂውን ስም፣ ሥራ፣ በሆኑ ጉዳዮች ፈጽሟቸዋል የሚባሉ ነገሮችን ከዘረዘሩ በኋላ... “እንግዳችን ስምዎትንና የሥራ ድርሻዎትን ቢገልጹልን...; የሚሉት ምን የሚሉት ስቲፈን ሰከርነት ነው! ቂ...ቂ...ቂ... (አንተ ስቲፈን ሰከር የሚሉህ ‘እንግሊዙ’ ሰውዬ “የእንግሊዝ ሆዱ አይታወቅም...” ሲባልባት በኖረች ሀገር ውስጥ አንተን ለመምሰል ፈላጊዎች በዛንማ! “ስቲፈን ሰከርን መሆን ወይም አለመሆን...” ምናምን የሚል ወርክሾፕ ይዘጋጅልንማ! ልክ ነዋ...ከገባንበት አይቀር አንደኛውኑ እንዋኝበትና ይለይልን ብለን ነው፡፡)
እናላችሁ...ተጠያቂው እኮ “ራሱ ስሜንና የሥራ ድርሻዬን ከዘረዘረ በኋላ እንደገና ካሜራ ፊት የሚጠይቀኝ ʻፌክʼ ነው ብሎ ጠርጥሮኝ ይሆን እንዴ!” ሊል ይችላል፡፡ (ዘንድሮ የማይጠረጥርና ለመጠርጠር ምክንያት የማይሆን ነገር የለም ብለን ነው፡፡)
ታዲያላችሁ...መረጃን ይዞ ከመሞገትና አቋም ይዞ ʻከማፋጠጥʼ መሀል ያለው መስመር (ሳይኖር አይቀርም በማለት ነው!) ደመቅ ብሎ ይሰመርልን፡፡ እናማ...እኔ ተጠያቂ ብሆን አስቀድሜ የማጣራው ጠያቂዬ ወንበሩ ስር ወይ ፍልጥ ወይ ቆመጥ ደብቆ እንደሆን ነው። አሀ...ማን ሞኝ አለ! ዘንድሮʼኮ አንዳንዶቹ ቁጣቸው ያስፈራላ! የሚተማመኑበት የደበቁት ነገር ሳይኖራቸው እንደዛ መሸሻ በሌለበት ስቱድዮ ውስጥ አግተው ቴረር አይለቁብንም ነበራ! ሀሳብ አለን...ስቱድዮ ውስጥ የቦክስ ጓንት ይቀመጥልንማ! አሀ...ነገሩ ጠንከር ካለ “ወንዝ እንውረድና ይዋጣልን፣” ማለት ሳያስፈልግ እዛው የሚሆነው ሊሆን ይችላላ! “አቦ የጠራኸኝ ለቦክስ ከሆነ ጓንት ይሰጠንና እዚሁ ይለይልን፤ ይሞታል እንዴ!” ማለት ይቻላላ! ደግሞ ላይቭ መሆን አለበት!
ሀሳብ አለን ʻትዌንቲ ታውዘንድʼ ውሎ አበል ምናምን ለማያውቁት ለቀድሞ ጋዜጠኞች ሞራል መጠበቂያ ʻኮመፕንሴሽን ይሰጥልንማ! አሀ..ልከ ነዋ! እነሱ ያንን ሰማያዊ ካኪ እያስያዙ ʻመስዋእትነትʼ ባይከፍሉ ʻትዌንቲ ታውዘንድʼ ላይ አይደረስም ነበራ! ስሙኝማ... ከዚህ ቀደም ያወራናት...አንድ መሀል ከተማ የነበረች ባለመጠጥ ቤት ደንበኞቿ ጋዜጠኞች፣ በዱቤ እየላፉ እዳ አንከፍል ቢሏት፣ ያስያዟቸውን ካኪዎች ሰብስባ፣ በጊዜው የነበሩት ሚኒስትር ቢሮ ገብታለች የሚባል ወሬ አለ፡፡ (እነ እንትና... ስንትና ስንት ነገር እየታተመ በሚወጣበት በአሁኑ ጊዜ፣ ምነው የዛ ዘመን የጋዜጠኝነት ‘አድቬንቸር’ መጽሐፍ ሆኖ አልወጣምሳ! ልክ ነዋ...አሁን እኮ አድቬንቸር የሚባሉ ነገሮች ለመኖራቸው፣ ቃሉ ራሱ ያለም አይመስልም፡፡)
ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታም አይደል...አንድ የብሮድካስት ጋዜጠኛ እስኪበቃው ‘ሲፑ’ን በመገልበጥ ይታወቅ ነበር...በማንኛውም ሰዓት ማለት ነው፡፡ እናማ፣ ሁልጊዜ ነበር በአለቆች ማስጠንቀቂያ አልፎ፣ አልፎም ቅጣት የሚደርስበት ይባል ነበር፡፡ ነገርዬውማ ‘ሲፑዋ’ ላይ የሚበረታው እሱ ብቻ ስለነበረ ሳይሆን በቃ እድሉ ሆነና ዓይን ውስጥ ስለገባ ሳይሆን አይቀርም! ቂ...ቂ...ቂ... ታዲያማ...አንድ ጊዜ  ለ‘ሲፕ’ ያለመስነፋቸው በአደባባይ የሚታወቅላቸው ሚኒስትር ተሹመው ይመጣሉ፡፡ ይሄኔ እሱዬው ለሥራ ጓደኞቹ ምን ቢል ጥሩ... “ከእንግዲህ አንድሽ ታናግሪኝና ዋጋሽን ታገኛለሽ!” ጋዜጠኛ ቢሮ አካባቢ ሲታጣ አለቆቹ “እስቲ እንትን ባር ሄዳችሁ ፈልጉት፣ ይባልበት የነበረ ዘመን ‘ፐረሰናል ፍሪደም’ የሚከበርበት አይመስላችሁም! ቂ...ቂ...ቂ...
ያኔ ታዲያ አይደለም በየወሩ ከውሎ አበል ‘ትዌንቲ ታውዘንዷንʼ ላፍ ሊያደርግ ጋዜጠኛው አስር ሺህና ሀያ ሺህ የሚባሉ ቁጥሮችን የሚያውቃቸው በሆነ ጉዳይ ሰልፍ ስለወጣ ህዝብ ብዛት ምናምን ዜና ሲጽፍ ወይም ሲያነብ ነበር፡፡ እናማ ለውጥማ አለ የምንለው በምክንያት ነው ለማለት ነው፡፡
ስሙኝማ... እግረ መንገድ በዜናዎች አዘጋገብ የሆነ ነገር ጠቀስ አድርጎ ለማለፍ፣ ይሄ ቅጽል ማብዛት የሚሉት ነገር ትንሽ ነገሮችን እያበላሸ አይመስላችሁም! እናላችሁ...እሺ ባላየነው ነገር አንድ መቶ አንድ ቅጽል ቢደረደር አናውቅምና ሊሆን ይችላል በሚል ጭጭ ብለን እንቀበላለን። ግን አሁን በዩቲዩብና በመሳሰሉት ስለ ዩክሬይን እየዘገብን ያለነውን ልብ ብላችሁልኛል? እንደ አንዳንዶቻችን አዘጋገብ እኮ በዩክሬይን ምክንያት ሦስተኛው የዓለም ጦርነት እስካሁን ዘጠኝ ጊዜ ተነስቶ ነበር፡፡ የምር!
“አለቀለት! ሦስተኛው የዓለም ጦርነት የመጀመሪያ ጥይት ተተኮሰች!” ወይም ደግሞ...
“ፑቲን በማንኛውም ሰዓት ኑክሌር እንዲተኮስ ትእዛዝ ይሰጣሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡”
ነገርዬውማ ዘገባውን የሚያቀርቡልን ሆነ ብለው ለማሳሳት ሳይሆን አንዱ ትልቅ ችግር የሚያገኟቸውን ዜናዎች የሚተረጉሙበት መንገድ፣ እንዲሁም ዜናዎቻቸውን የሚወስዱባቸውን ሳይቶች መምረጡ ላይ ይመስለናል፡፡ ሌላኛው ጉዳይ ደግሞ ምኑንም አይነት ወሬ ሰበር ዜና የማድረግ ልማድ ነው፡፡ ፕላስ ...
ይልቅ የ‘ትዌንቲ ታውዘንዷ’ የውሎ አበል ወሬ ከድንኳን ሰባሪ አበል ተቀባዮች ጋር ‘ፕላስ’ ስትደረግ ሰበር ለመሆን ምን ይቀራታል!  
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 647 times