Saturday, 16 April 2022 14:49

አሰቃቂው የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት እልቂት

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

  በወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት አዳዲስና በርካታ የጅምላ መቃብሮች መገኘታቸውን ባለፈው ሳምንት ይፋ ያደረገው የጎንደር ዩኒቨርስቲ የጥናት ቡድን፤ በርካታ የአካባቢው ሰላማዊ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ግድያ እንደተፈፀመባቸው በማስረጃ ማረጋገጡን አስታውቋል።
 ባለፉት 40 ዓመታት ህወኃት በወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት አካባቢ በአማራ ህዝቦች ላይ የፈፀመውን ማህበራዊ ፤ኢኮኖሚያዊና ሰብዐዊ የመብት ጥሰቶችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለማጥናት አልሞ የተነሳው ዩኒቨርስቲው፤ ጥናቱም የህግ፣ የማህበራዊ ፣የባህል ፣የቋንቋ፣የትምህርት ፣የጤናና ተያያዥ ጉዳዮችን የዳሰሰ መሆኑን የጥናት ቡድኑ መሪ ጌታ አስራደ (ረዳት ፕሮፌሰር) አውስተዋል። ለዚህም ከህግ ፣ሶስዮሎጂ ፣ታሪክ ፣ ቋንቋ፣ ስነ ወንጀል፣ አንትሮፖሎጂ ፣ምጣኔ ሀብት ፣ስነ አዕምሮ ፣ጤና፣ እንዲሁም ከአካባቢ ጥናት ባለሞያዎች የተዋቀረና 21 አባላት ያሉት የጥናት ቡድን  ተዋቅሮ ለአንድ አመት ከሶስት ወር ጥናት ሲያካሂድ መቆየቱን የጥናቱ ቡድን  መሪ (ረ/ፕ) መሪ ጌታ አስራደ ጨምረው ገልፀዋል።
ከጉዳዩ ጥልቀትና ስፋት አንጻር ጥናቱ ሙሉ በሙሉ ያልተጠናቀቀ ቢሆንም፣ አሁን የጥናት ቡድኑ የደረሰበትን ተጨባጭ ግኝት ይፋ ለማድረግ የተገደደው በጥናቱ ሂደት በርካታና አዳዲስ የጅምላ መቃብሮች በመገኘታቸው፣ መንግስትም ሆነ ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡት ለማሳሰብ ነው ብለዋል የጥናት ቡድኑ መሪ። በርካታ ስልቶችን በማቀናጀት በተሰራው በዚህ ጥናት፤ 912 አባወራዎች፣ ከ75 በላይ የፍትህ፣ የትምህርት ፣የእምነት፣ የጤና የአስተዳደር እና ሌሎች ተቋማት ተዳስሰውበታል ተብሏል። በጥናቱ የድብቅ መቃብሮች፣ እስር ቤቶች፣ ዋሻዎችና የጅምላ መቃብሮች የተዳሰሱ ሲሆን መረጃዎች ለማሰባሰብ የመስክ ምልከታ ፣ጥልቅ ቃለ መጠይቅ፣ የሰነድና የጂፒኤስ አመላካች ጠቋሚዎችን መጠቀሙን የጥናት ቡድኑ መሪ  አመልክቷል።
ባልተጠናቀቀውና የመጀመሪያ ደረጃ በተባለው በዚህ ጥናት የተገኙት ውጤቶች እንደሚጠቁሙት፤ ህወኃት በ1968 “አማራ ታሪካዊ ጠላቴ ነው” ብሎ ፍኖተ መርህ (ማኒፌስቶ) ቀርፆ ከተነሳ በኋላ ይህንኑ ለመተግበር በ1972 ዓ.ም ሰራዊት አሰልጥኖ  “ መዘጋ ወልቃይት” በሚባለው የወልቃይት ምስራቃዊ ክፍል በመግባት ወረራ ከፈፀመበት የመጀመሪያ ግጭት ጀምሮ በ1983 ስልጣን ከያዘ በኋላ ወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምትን  በግድ ወደ ትግራይ ማካለሉን ተከትሎ በነዚህ አካባቢ ህዝቦች ላይ ሞት፣ መፈናቀል፣ እንግልትና ስቃይ  ሲደርስባቸው ቆይቷል  ብሏል ቡድኑ፡፡ ከዚህ ጥናት በፊት በጉዳዩ ላይ ጥናት ሲያደርጉ የቆዩት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጉባኤ፣ ሞረሽ ወገኔ፣ የወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት ማንነት አስመላሽ ኮሚቴና የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የጥናት ግኝቶች ይህንኑ ሞት ማፈናቀልና ማሳደድ ይጠቁማሉ ብሏል የጥናት ቡድኑ፡፡
ይሁን እንጂ የአማራና የትግራይ ህዝቦች በተለይም ከህወኃት በፊት በሰሜን በኩል የመጣን ጠላት በጋራ ከመመከት፣ ጉርብትናን በመልካም ነገር ከመጋራት፣ የሚያቀራርቧቸውንና ተመሳሳይነት ያላቸውን ባህሎች ከማክበርና ከመተሳሰብ ውጪ የድንበርና የይገባኛል ጥያቄና ንትርክ እንዳልነበራቸው የጥናት ቡድኑ ማረጋገጡን ረዳት ፕሮፌሰሩ አመልክተዋል።
እንደ ጥናት ቡድኑ ገለፃ፤ ህወኃት እነዚህን አካባቢዎች ያለምንም ህዝበ ውሳኔና ህጋዊ መሰረት ወደ ትግራይ ማካለሉን ተከትሎ፣ ይህን የሚቃወሙ ታሪክ አዋቂዎችን፣ ተሰሚነት ያላቸውን ሰዎችና በአጠቃላይ  በዚህ ዙሪያ “ለምን?” የሚል ጥያቄ የሚያነሱት የወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት አማራዎችን ሲያሳድድ፣ ሲያሰቃይና ሲገድል እንደኖረ በጥናቱ ማረጋገጠጡን ቡድኑ ገልጿል።
ህወኃት በተጨማሪም የአካባቢውን ማንነት ለመቀየር ብዙ ተቋማዊና መዋቅራዊ ሂደቶችን አድርጓል ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ ለምሳሌም በትምህርት ቤቶችና በህክምና ቦታዎች የአማርኛ ስሞች በግዳጅ ወደ ትግርኛ እንዲቀየሩ ሲደረግ እንደነበር በመጠቆም በተለይም ከ2008 ዓ.ም የለውጥ እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ በአካባቢው አማርኛ መናገርና የንግድ ድርጅቶችን በአማርኛ መሰየም፣ እንደነ ፋሲል ከነማ ያሉ የአማራ ስፖርት ክለቦች ማልያ መልበስ ወይም መደገፍ ከእስራት እስከ ሞት ያስቀጣቸው እንደነበርና በዚህም ታስረው የተሰቃዩና የተገደሉ ሰዎች ስለመኖራቸው ጥናቱ ማረጋገጡን ቡድኑ አመልክቷል፡፡
“በወልቃይት፣ ጠገዴና |ጠለምት ህወኃት ምንም ዓይነት ሰፈራ እንዳላደረገ፣ ነገር ገን ነባሩን የአማራ ህዝብ በመሳሪያ አስገዳጅነት በማፈናቀል፣ አፍኖ በመውሰድና በመግደል እያስወጣ የራሱን ህዝብ ማስፈሩን በጥናታችን አረጋግጠናል” ብሏል ጥናቱ ቡድኑ፡፡
የጅምላ ግድያና የዘር ጭፍጨፋን በተመለከተ በዓለም አቀፉ የዘር ማጥፋት ወንጀል መከላከል ስምምነትና የወንጀለኞች መቅጫ ህግ መሰረት፣ የአንድን ቡድን አባላት ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ማንነቱን ወይም ዘሩን አሊያም ሀይማኖቱን ለማጥፋት ታስቦ ግድያ ሲፈፀም ወይም በሰውነትና ስነ ልቦና ላይ ጉዳት ሲደርስ፣ወይም በአንድ ቡድን በህይወታቸው ላይ ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ጉዳት ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ሲደርስ፣ወይም የአንድ ቡድን አባላት ያለፈቃዳቸው እንዳይራቡ (እንዳይዋለዱ)  ሲደረግ የዘር ማጥፋት ወንጀል መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በ1949 ዓ.ም ያወጣው ህግ እንደሚያሳይ የጠቆመው የጥናት ቡድኑ፣ በወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት ይህን መስፈርት የሚያሟሉ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች መፈፀማቸውን አረጋግጠናል ብሏል፡፡
የቅርቡን የማይካድራ ጭፍጨፋ ጨምሮ ይህ መግለጫ እስከተሰጠበት  ጊዜ ድረስ  በነዚህ አካባቢዎች ከ12 በላይ የጅምላ ጭፍጨፋና የዘር ማጥፋት የተካሄደባቸውን ቦታዎች መለየቱን የጠቆመው የጥናት ቡድኑ፣. ከነዚህ መካከል የተወሰኑትን ናሙና በመውሰድ የጅምላ መቃብር መሆናቸው መረጋገጡንና ቀሪዎቹን በቀጣይ በፎረንክሲክ ምርመራና በሌሎች ሳይንሳዊ ዘዴዎች ለማረጋገጥ እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡ የጥናት ቡድኑ አክሎም በተለይ   የጅምላ መቃብሮቹ የሚገኙበት ስውር፣ ምንም ዓይነት ኔትወርክና ሌሎች መሰረተ ልማቶች የሌሉበት መሆኑ ይበልጥ የዘር ጭፍጨፋውን የሚያረጋግጥ  ከመሆኑም በላይ አንዳንዶቹ ሳር የበቀለባቸው፣ሌሎቹ ደግሞ ሆን ተብለው የታረሱና እንዳይታወቁ ጥረት የተደረገባቸው መሆኑ በጥናቱ መረጋገጡን ጠቁሟል፡፡
ቡድኑ እነዚህ የጅምላ መቃብሮች ማህበረሰቡ በግልፅ የሚያውቃቸው ብቻ ሳይሆኑ እነማን እንደተቀበሩባቸው በስም ጭምር እንደሚያውቃቸው  ያረጋገጠ ሲሆን፣ “እነ እከሌ 10 ወይም 15 ሆነው በዚህ ቦታ ተቀብረዋል፣እስከዛሬ በፍርሃት ቆፈን ተውጠን ነው ያልተናገርነው” የሚል የሰዎች መስክርነት ጭምር መገኘቱን ጠቁሟል፡፡
ከጅምላ መቃብሮቹ ዙሪያ መልስ የፈራረሱ ዋሻዎች ድብቅ እስርቤቶችና ማጎሪያ ቤቶች  መገኘታቸውን የገለፀው የጥናት ቡድኑ፤ በነዚህ እስር ቤቶችና ዋሻዎችም ዙሪያ በሚገኙ የወንዝ ዳርቻዎችም በርካታ የጅምላ መቃብሮች መኖራቸውን  አረጋግጧል፡፡ ጥቅምት 24  ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን እዝ ላይ የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ በተከፈተው ጦርነት በማይካድራ፣ በጭና፣ በቦዛ በቆቦ፣ በአፋርና ሌሎችም አካባቢዎች የተፈፀሙ አሰቃቂ የጅምላ ጭፍጨፋዎች፣ ህወኃት ከዚህ በፊትም እንዲህ አይነት ጅምላ ጭፍጨፋዎች ሲያደርግ የቆየና ልምድ ያለው  መሆኑን ማሳያ ነው ብሏል የጥናት ቡድኑ፡፡  በአደባባይ በጅምላ ከተጨፈጨፉትና ማህበረሰቡ ከሚያውቃቸው መካከል የጥናት ቡድኑ በስም ጠቀሶ በማስረጃነት ያቀረባቸው  አሉ፡፡ ለምሳሌ መርሻ ሙሉ የተባለ በወልቃይት ወረዳ ጠለሎ ቀበሌ፣ አተት ገበያ በተባለ ቦታ በ1989 ዓ.ም በህወኃት የፀጥታ አባላት ከተገደለ  በኋላ በተቀበረ በአራተኛው ቀን ሰውነቱ ሲተላ አስቆፍረው በማውጣት ቤተሰቦቹን አሸክመው የአራት ሰዓት መንገድ እንዲጓዙ በማድረግ፣ ከፍተኛ ወንጀል መፈፀማቸውንና ሌላ ቦታ ወስደው ለጅብና ለአሞራ እንዳስበሉት ቤተሰቦቹ በአንደበታቸው ምስክርነት ሰጥተዋል ብሏል ቡድኑ፡፡
ዘውድነህ አስፋው የተባለ የጠለምት መያሚ ቀበሌ ተወላጅና ነዋሪ፣ በቁመቱ ልክ ጉድጓድ ቆፍረው ከነህይወቱ በመቅበር፣ አናቱ ላይ ጨው እየጨመሩ ከብት እንዲረግጠው በማድረግ ፣ዘግናኝ የግድያ ወንጀል መፈጸማቸውንም በጥናት ቡድኑ ተረጋግጧል፡፡
አደራጀው ጫቅሎ የተባለ በጠገዴ ወረዳ የማክሰኞ ገበያ ነዋሪ የነበረ ደግሞ ሀምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም “ከአማራ ክልል መንግስት ጋር ትገናኛለህ” በማለት የህወኃት ልዩ ሀይሎች አዳይጦ በተባለ ገደል ተወርውሮ እንዲሞት ማድረጋቸውን ቤተሰቦቹ መመስከራቸውን ቡድኑ አመልክቷል፡፡
በተመሳሳይ አታላይ ወልዴ የተባለ የጠገዴ ወረዳ ማክሰኞ ገበያ ነዋሪ የነበረ ሰው፣ ሃምሌ 11 ቀን  2012 ዓ.ም የህወኃት ሀይሎች በአደባባይ አንገቱን ቀጭተው ጥለውት፣ በሶስተኛው ቀን ህይወቱ ማለፉን፣ የጥናት ቡድኑ አረጋግጧል፡፡
ግርማይ በለጠ የተባለ የወልቃይት ወረዳ ብላምባ ቀበሌ ነዋሪ የነበረ፣ በ2009 ዓ.ም የማንነት ጥያቄ አንስተሃል” በሚል ሁመራ ሆስፒታል ተወስዶ በመርዝ እንደተገደለ፣ ቤተሰቦቹና በወቅቱ በሆስፒታሉ የነበሩ የጤና ባለሙያዎች  በአንደበታቸው መመስከራቸውን ቡድኑ አመልክቷል፡፡
ጥጋቤ አዲሱ የተባለ በጠለምት ወረዳ የሰብዬ ቀበሌ ነዋሪ፣ በማንነቱ በደረሰበት ከፍተኛ በደል በህወኃት ላይ ማመፁን ተከትሎ፣ አባቱን ጨምሮ ሶስት የቤተሰቦቹን አባላት ማለትም አዲሱ ዘሌ፣ዘለቀ ታዬ፣ጥላሁን መኮንን የተባሉትን ቤተሰቦቹን “ሰይጣን መጣያ” በሚባል አሰቃቂ ገደል በ1995 ዓ.ም  ተጥለው እንዲሞቱ መደረጉን አረጋግጠዋል፡፡
 በዚህ ቀበሌ የሚኖሩ 48 አባወራዎች “ሽፍታ ደብቃችኋል” ተብለው ቤታቸው በሙሉ እንዲቃጠል መደረጉን ተከትሎ፣ ከ400 በላይ ቤተሰቦቻቸው ጭምር አካባቢውን ለቀው በአጎራባች ወረዳዎች መበተናቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል-  ቡድኑ በጥናቱ፡፡
እነዚህ ሁሉ የዘር ጭፍጨፋዎች በአካባቢው ህዝብ ላይ  ከዚህም የከፋ ዘር ጭፍጨፋ ሲካሄድ መቆየቱን አመላካች ናቸው ያለው የጥናት ቡድኑ፤ ከላይ የተጠቀሱት ግፎች ለቤተሰቦቻቸውና ለጎረቤት ብቻ ሳይሆን የአደባባይ ግፎች ሆነው  እና በአደባባይ ተፈፅመው ለሁሉም  አፍ ማዘጊያ ማስፈራሪያነትና መቀጣጫ ተደርገው መቆየታቸውን የጥናት ቡድኑ አመልክቷል፡፡ “በወልቃይት ጠገዴና ጠለምት የተካሄዱት የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ከጀርመኑ ናዚ የአይሁዶች የዘር ጭፍጨፋና የጅምላ ፍጅት ጋር እንደሚመሳሰል አረጋግጫለሁ” ያለው የጥናት ቡድኑ፤ ህወኃት በአካባቢው ማጎሪያ፣ ማሰቃያና መቅበሪያ ቦታ አለው፤ የጀርመኑ ናዚም ይህ ነበረው፤ ለዚህም ማሳያው ማጎሪያ ዋሻዎች፣ ድብቅ እስር ቤቶችና የጅምላ መቃብሮች”  ናቸው ብሏል”፡፡
በተለይም “ገሀነም” የተባለው ከሁሉም የከፋ የጅምላ መቃብር አስደንጋጩ ሲሆን ይህ ስውር ቦታ በወልቃይት ጠገዴና ጠለምት እንዲሁም አደርቃይ ወረዳዎች መካከል የሚገኝና በቃሌማ ወንዝ ተፋሰስ ላይ ሰው ሊደርስበት የማይችልበት ዙሪያውነ በትልልቅ ሰንሰለታማ ተራሮች የተሸፈነ መሆኑን አስተውለናል ያለው ቡድኑ በዚህ ስፍራ በደርዘን የሚቆጠሩ የጅምላ ማጎሪያዎችና የጅምላ መቃብሮች የተገኙ ሲሆን በጥናት ቡድኑ ኮድ  የተሰጣቸው መሆኑንም ቡድኑ ሪፖርት አድርጓል፡፡ በዚህ ቦታ የተገኙት 12 የጅምላ መቃብሮች እጅግ አስደንጋጭና በጉዳዩ ዙሪያ መንግስትና ዓለም  አቀፍ ተቋማት ትኩረት እንዲሰጡት፣ የሚያስገድድ ሲሆን አዳዲሶቹ የጅምላ መቃብሮች እስከዛሬ በደጀና፣ በማይካድራ፣ በፍየል ውሃ በቃቃ፣ በዲማ በበረከትና አድኖ በተባሉ ስፍራዎች የተገኙትን የጅምላ መቃብሮች አያካትትም ብሏል ቡድኑ፡፡ አክሎም ቀሪ ተጠርጣሪ 12 ያህል የጅምላ መቃብሮች እንዳሉ ጠቋሚ ምልክቶች መኖራቸውን ገልፆ እስካሁን የተገኙትም ሆነ ገና የተጠረጠሩት የጥናት ቡድኑ በፎረንሲክና በሌሎች ሳይንሳዊ ዘዴዎች ተረጋግጦ አጥፊዎች እንዲጠየቁና ጎንደር ዩኒቨርስቲም በቀጣይ “የዘር ማጥፋት ጥናት ማዕከል” (ሴንተር ፎር ጄኖሳይድ ስተዲስ) እንዲያቋቁም ለማሳሰብ ጥናቱ ሳይጠናቀቅ ለሚዲያ  ይፋ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን የጥናት ቡድኑ መሪዎች ገልጸዋል፡፡  በዘር  ጭፍጨፋው የሞቱ ሰዎች አፅም ተሰብስቦ በአንድ ማረፊያ ሙዚየም ውስጥ እንዲቀመጥና ለትውልድ መማሪያ እንዲሆን የጥናት ቡድኑ የጠየቀ ሲሆን፣ በዚህ የዘር ማጥፋት ወንጀል ዙሪያ  በአማርኛ ቋንቋ መጽሀፍ እየተዘጋጀ መሆኑም ታውቋል፡፡


Read 3641 times Last modified on Saturday, 16 April 2022 15:11