Print this page
Saturday, 16 April 2022 00:00

ፀረ-አሜሪካ የውጭ ፖሊሲና ዘመቻ አይጠቅመንም

Written by  ከኢሳይያስ ልሳኑ - ቤተሳይዳ ሜሪላንድ ከአሜሪካ
Rate this item
(1 Vote)

  እዚህ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የጦር መሳሪያ የመታጠቅ (ጠመንጃና ሽጉጥ አይነት) ከልካይ ህግ በፖለቲካው መድረክ ተረቅቆና ጸድቆ እንዲወጣ የሚፈልገው ሕዝብ ከሀገሪቱ 60 ከመቶ በላይ ነው፡፡ ይህ መረጃ እዚሁ አሜሪካ የሚገኘው ፒው የተሰኘ የጥናት ማዕከል ይፋ ካደረገው ሰነድ የተወሰደ ነው፡፡ ይሁንና የ’ጦር መሳሪያ መታጠቅ’ እንዲገደብ የሚለው ረቂቅ ወደ ፖለቲካው ማዕከል መጥቶ ለህግነት እንዲበቃ የሚያስችል በሀገሪቱ ህግ አርቃቂና ህግ ወሳኝ በሆኑት ምክር ቤቶች የአዎንታ ድምጽ ባለማግኘቱ እስካሁን ህግ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ እና አልፎ፣ አልፎ አንድ የተናደደ ወይም አእምሮውን ሳት ያደረገ ሰው ጥይት ባጮኸ ወይም ሰው በገደለ ጊዜ፣ የዚህ ‘የጦር መሳሪያን የመግዛትና የመያዝ መብት የሚገድብ ህግ’ አለመጽደቅ ነገር፣ በህዝቡ ውስጥ ውይይት አጭሮ፣ በየመገናኛ ዘዴው ሁሉም ሲነጋገርበትና ሰላማዊ ሰልፍ ሲደረግበትም ይስተዋላል፡፡ እና ተብሎ፣ ተብሎ ወሬው ሲደክም ያ ሰሞነኛ ጉዳይ ያልፋል፡፡ ጉድ አንድ ሰሞን እንደሚባለው ይሆናል፡፡ ሕዝቡ ይህን ያህል ህጉ እንዲጸድቅ እየሻተ ወይም እየፈለገ ስለምን ህግ ለመሆን አልቻለም? ብሎ የሚጠይቅ አይጠፋም። መልሱ ብዙም የተወሳሰበ አይደለም፡፡ የአሜሪካ ፖለቲካ በ’መርሐ ጽድቅ’ የሚመራ አይደለም፡፡ በአሜሪካ በተወካዮቹ ምክር ቤትና በህግ መወሰኛ ምክር ቤት ያሉት ፖለቲከኞችን በተለያዩ ጉዳዮች (ከሀገራዊ እስከዓለም አቀፋዊ ይደርሳሉ) ለማግባባትና ድምጻቸውን ለማግኘት የሚንቀሳቀሱ በርካታ አግባቢ ድርጅቶች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል የጦር መሳሪያ አምራቾችና አከፋፋዮች ከፍተኛ የገንዘብ መጠን መድበው የምክር ቤት አባላቱን በማግባባት፣ የጦር መሳሪያ መታጠቅ ላይ ገደብ እንዲጣል የሚለው ረቂቅ ህግ እንዳይጸድቅ ይደግፉ ዘንድ ሥራቸውን ይሠራሉ፡፡ በዚህ የተነሳ በዕለት ተዕለት ኑሮ የተጠመደው ሕዝቡ በተበታተነና አንዳንዴም በደካማ አቅም ይህን ፍላጎቱን ለማሟላት የሚያደርገው ጥረት ገና ከመሬት ሳይነሳ እንዲወድቅ ይሆናል፡፡
ይህን ምሳሌ ያነሳሁት የአሜሪካ የፖለቲካ ስርዓት እንዴት እንደሚሠራ አንዳንድ ፍንጮችን ለማሳየት ይረዳል በሚል ነው። ብዙውን ጊዜ ከውጭ ሆነው የሚያዩትና በቅርበት የሚከናወነውን በመረዳት መካከል ሰፊ ልዩነት አለ፡፡ በዚህ በአሜሪካ ውስጥ ረቂቅ ቀርቦ ህግ እስከሚሆን ድረስ ያለው ሂደት እጅግ ውጣ ውረዱ የበዛና አካሄዱ አስቸጋሪ ነው፡፡ የጀርመን ቻንስለር የነበረው ቫን ኦቶ ቢስማርክ፤ “ህግና ቋሊማ (ሶሴጅ) ትወድ እንደሆነ እንዴት እንደሚሠሩ ግን ባታይ ይሻልሃል፤” እንዳለው ነው፡፡ በእርግጥም ‘ቋሊማ’ (ሶሴጅ) እንዴት እንደሚሠራ ሰዎች ከተመለከቱ ‘ቋሊማ’ መብላት ያቆማሉ ይባላል፡፡ እናም እዚህ አሜሪካ የህግ ረቂቅ እንዴት እንደሚሠራ ማወቅ አሁን፣ አሁን ከሀገር ቤት የምንሰማውን የተዛነፈ አካሄድ ያስተካክለዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ሲጀመር ይቅርታ ይደረግልኝና አሜሪካ የኢትዮጵያ ወዳጅ ናት፡፡ በምዕተ ዓመት ጉዟችን በተለያዩ የታሪክ መስቀለኛ መንገዶች ላይ በወዳጅነት የቆመችባቸው አብነቶችን ማንሳት እንችላለን፡፡ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነቶች መሰረታቸው ጠንካራ ነው፡፡ አሜሪካ ለኢትዮጵያ በሰብዓዊ እርዳታም ይሁን በልማት መጠነ ሰፊ ንዋይ ታፈሳለች፡፡ የፕሬዚዳንት ባይደን አስተዳደር ‘ኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ’ እያለ በሚልበት በ2021 ዓ.ም ውስጥ እንኳን በዓለም ከፍተኛ መጠን እርዳታ ካገኙት ሦስቱ ሀገራት ቀዳሚዋ ኢትዮጵያ ናት፡፡ $1.13 ቢሊዮን ዶላር - ኢትዮጵያ፣ 1.03 ቢሊዮን ዶላር - ዮርዳኖስ፣ 860 ሚሊዮን ዶላር- አፍጋኒስታን አግኝተዋል፡፡ የዚህ ጽሁፍ ዓላማ አይደለም እንጂ የአሜሪካ ተጽዕኖ ካለባቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት ኢትዮጵያ በዚህ ‘ሦስት ዓመታት ያገኘችው እርዳታና ብድር ሰፊ ነው፡፡ ይህ የተነሳበት ምክንያት አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ወዳጅነት አመልካች እንደሆነ ለማስመርም ነው፡፡ አንድን ኹነት አጠቃሎ መመልከትና ‘በቃ ላንተያይ ተለያየን’ አይነት ግንኙነት በዓለም አቀፉ ዲፕሎማሲ ውስጥ አይሠራም፡፡ እንደ ክሊሼ ቢቆጠርም ደጋግሞ መባል ያለበት - ‘ዘላቂ ብሔራዊ ጥቅም እንጂ ዘላቂ ወዳጅና ጠላት በሀገራት ውስጥ የለም’፡፡
ይህ ሲባል ግን ኢትዮጵያም ሆነች አሜሪካ ብሄራዊ ጥቅማቸውን አያሰሉም ወይም ለዚያ ሲሉ የግንኙነታቸውን ኢላማ አያስተካክሉም ማለት አይደለም፡፡ ብሔራዊ ጥቅምን አስልቶና ጥበባዊ ሆኖ፣ የግንኙነት ፈትሉን ማገናኘት የዲፕሎማሲ ሥራ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ያለብን ፈተናና የቤት ሥራ ቀላል አይደለም፡፡ በተለይ አሁን የምንሄድባቸው ወይም የምናጮሃቸው በስሜት ላይ ብቻ የተመረኮዙ አካሄዶች፣ አሁን ላለንበትም ሆነ ወደፊትም እናደርገዋለን ብለን ለምንገበዝበትም የሚረዳ አይደለም፡፡
አሁን ያለው አካሄድና የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ድኩምና ጅረት የማያሻግር እየሆነ መምጣቱትን ከአድማስ ባሻገር   ሆኜ በምኖረው ታዝቤያለሁ፡፡ ከሀገር ቤት እስከ እዚህ በ’መንግሥት’ ድጋፍ የሚጮኸው አካሄድም በአብላጫው አሜሪካን በመርገምና በመዝለፍ ላይ ያተኮረ፣ መረጃንም ያላካተተ እንደሆነ ብዙ ማስረጃዎችን አነሳለሁ፡፡ አሜሪካንን ለማግባባት ትውልደ ኢትዮጵያውያን ደፋ ቀና በምንልበትም ጊዜ የሚገጥመን ፈተና - ‘ሀገራችሁ ውስጥ ፀረ- አሜሪካ ቅስቀሳ ለምንድን ነው የሚደረገው?’ የሚል ነው። አይሆንም አይደረግም ብሎ በተለይ በማዕከል ደረጃ ለመሞገት አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል፡፡ ለዚህ ደግሞ አስረጂ ወይም ምሳሌ የማደርገው በሰሞኑ በሀገር ቤት በመንግሥት ይዞታ በሚገኙት የመገናኛ አውታሮች የሚሰራጩትን ዜና መሰል ሀተታዎች ነው። በአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት (ኮንግረስ) ኤች አር 6600 እና በህግ መወሰኛ ምክር ቤት (ሴኔት) ኤስ 3199 የሚሉ ረቂቅ ህጎች ቀርበው እንዲጸድቁ ወይም ውድቅ እንዲሆኑ ያለው ፈተና ቀላል አይደለም፡፡ ብዙዎቻችን ይህ ረቂቅ ሀገርን ይጎዳል - የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት ያሻክራል በሚል ስንቃወመው ቆይተናል፡፡ በአምባሳደር ፌልትማን እግር የተተኩት አምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድ ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘው ከተነጋገሩ በኋላ በመንግሥት በኩል በተወሰደው እርምጃ፣ በዓቢይነት ረቂቆቹ በይቆይ መያዛቸው ፋታ ማስገኘቱ ይታወቃል፡፡
የአሜሪካ ሁለቱ አካላት ረቂቅ ህጎቹን ለማጽደቅ በቂ ድምጽ አላቸው የሚለው ምናልባታዊ ስሌቱን ገምግመን ብንቀበል - ይህን ለማስቆም በአሜሪካ የፖለቲካ ስሪት ውስጥ እንዴት ይቻላል? ብሎ በጥንቃቄ ማሰብ ያሻል። ከዚህ ጋርም ‘በቃን’ “No More’ የሚለው ዘመቻ በተወሰነ ደረጃ መዳከሙን ታዝበን  - ይህን አደገኛ የህግ ረቂቅ በተመለከተ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉም ሆኑ እዚህም የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የማይጠበቅ ድጋፍ እያሳዩ መምጣታቸው ብዙዎችን አደናግሯል። የህግ ረቂቆቹ ያላቸው አሉታዊ ተፅእኖ ጠፍቷቸው እንዳልሆነ ስለምንረዳ ምክንያቱን መፈተሽ ግድ ይላል፡፡  ወደዚህ ጥያቄ ከማምራታችን በፊት በአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤትና በሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ ውስጥ ካሉት የተወሰኑት አባላት ላይ የተያዘውን የእርግማንና የስድብ ዘመቻን እናንሳ፡፡ ከጉዳዩ ወይም ከህግ ረቂቁ ጋር ቅርበት ያላቸው የሚባሉትን መርጦ በስምና በፎቶ እየጠገለጹ፣ በሀገሪቱ ቴሌቪዥን ‘ጉቦ’ በልተዋል በሚል ሲዘለፉ አስተውለናል። ይህ ግን የሚጠቅመው ማንንና እንዴት ብለን ፈንጂ ጥያቄ እናንሳ። ይህን መሰል እርምጃዎችና ዘመቻዎች ምን ይፈይዳሉ? ምንስ ያስገኙልናል? ለአስረጂነት በተመለከትኩት ዘገባ ውስጥ አቀራረቡን ሳጤነው፣ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝን እረዳለሁ፡፡ እንደውም የህግ ረቂቆቹ በህግነት እንዲጸድቁ የፈለገ አካል ሆነ ብሎ ከምክንያታዊነት በወጣ የስሜት ግፊት ለመፍጠር ያሰበውም ይመስለኛል። የአሜሪካ የፖለቲካ ስርዓት በአግባቢ ድርጅቶች (ሎቢዪስቶች) የሚዘወር ነው። አባላቱ በኮንግረስም ይሁን በሴኔቱ ያሉት አንዱ የሚያቀርበውን ረቂቅ ሌላው የሚደጋገፉበት ስርዓትም ብዙውን ጊዜ ድምጽ የሚሰጡበትን አውቀውት ሳይሆን፣ አንዱ ጉዳዬ ብሎ ያቀረበውን ሌላኛው ሲደግፍ ይሁን በማለት (benefit of doubt በመስጠት) የሚከናወን ነው፡፡ አግባቢ ድርጅቶች በከፍተኛ ወጭ ተቀጥረው የሚሠሩትና የሚያግባቡበት ሁኔታም በአሜሪካ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ ያለና የሚኖር ነው፡፡ በኢትዮጵያ የመንግሥት ሚዲያዎች የሚጠቀሰው ‘ጉቦ’ የሚባለው ክስ እንዴት እንደሆነ ማስረጃውንም ማቅረብ ይገባል፡፡ ለኢትዮጵያ ይህ ረቂቅ ህግ አይበጅም ለሚለው ግፊትና ማግባባት እንንቀሳቀስ ሲባል፣ ለምሳሌ እኔ በምኖርበት አካባቢ ላለ ተመራጭ፣ ለምርጫው ማካሄጃ ገንዘብ ላዋጣ እችላለሁ፡፡ ገንዘብም አዋጥቼ ስሞታዬን ወይም ድምጼንም ለማሰማት ቀጠሮ ይዤ በአካል ወይም በደብዳቤም ላቀርብ እችላለሁ፡፡ እኔን የሚመስሉ በዝተውና ተፅዕኗቸውን አሳይተው - "ለምርጫው እንረዳሃለን፤ ድምፅም እንሰጣለን" ብለን የእኛን ሀሳብ የሚገዛ ሁኔታ ልንፈጥር እንችላለን፡፡ ወይም ተጻራሪ ሀሳብ ያላቸው በተመሳሳይ ሁኔታ ተደራጅተው በአሜሪካ ፖለቲከኛ ላይ ተመሳሳይ ተጽእኖ ለማድረግም ይቻላቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ጠንካራ የሆነ የአግባቢ ድርጅት የለውም ወይም አልቀጠረም፡፡ የፖለቲካ ዘርፉን - የመገናኛ ዘዴውን በትይዩ ይዞ ለመሻገር አልቻለም። እዚህ አሜሪካ፣ ሀገራት በአግባቢ ድርጅቶች የፖለቲካ ዘርፉን በመያዝ ሰፊ ድጋፍና እርዳታም የማግኘት ስልት ይዘዋል፡፡ ይሄ ነው አሠራሩ። የዲፕሎማሲ ሥራ የሚሠራው፣ የልዕለ ሀያሉዋን አሜሪካ የፖለቲካ ገበያ ትኩረት የሚሸመትበት ዘዴውም ይህ ነው፡፡
እዚህ ላይ የአሜሪካ የፖለቲካ ስርዓት እስከነ ግድፈቱ ለመሻሻል ያለው መንገድ እጅግ የሚበረታታ ነው፡፡ የአሜሪካ አበው መስራቾቹም ወደ “ምሉዕ ህብረት” (perfect union) የሚደረግ ጉዞ አድርገው ያዩታል፡፡ በአሜሪካ ማህበረሰብ ውስጥ በዜግነት የምንገኝ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ብዙ ነን፡፡ ከእነርሱ የሚወለደው አሜሪካዊ የሆነው ቁጥሩም እጅግ የበዛ ነው፡፡ በአሜሪካ የፖለቲካ አድማስ ውስጥ ይህ ቁጥሩ የበረከተው ትውልደ ኢትዮጵያዊና በሁለተኛ ከቶም በሦስተኛ ትውልድነት ‘ከኢትዮጵያ’ ጋር የተያያዘው ያለው ተጽእኖ ቀላል አይሆንም፡፡ ይህን ማስተባበርና አቅጣጫ ማስያዝ ግን ይገባል፡፡ በቀላሉ በፖለቲካው ስሌት ውስጥ ተጽእኖውን ለማሳደር የሚያስችል አቅም እንዳለው መረዳት አያዳግትም፡፡
በዚህ ረገድ ቀደም ሲል ወዳነሳሁት ነጥብ ልሂድ፡፡ - በቃን’ በሚል ተደራጅቶ ስኬታማ የሆነው እንቅስቃሴ ስለምን የመዳከም ምልክት ታየበት ብለን እንጠይቅ። በዲፕሎማሲው ዘርፍ ሰፊ ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችልና በአጭር ጊዜ እጅግ አመርቂ ውጤት የተገኘበት ስብስብ ነበርና ጥያቄው ተገቢ ነው፡፡ የዚህ እንቅስቃሴ አፈጣጠር ድንገቴው የበዛ ቢሆንም በአዲስ አበባው መንግሥት በኩል የንቅናቄውን ትኩሳት የሚያበርድና የሚያቀዛቅዝ ሂደት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ተከናውኗል። የንቅናቄው ዋና ተዋናዮች ገለል ተደርገው በንቅናቄው ውስጥ የሌሉና በሌላ መልክ በውጭ ‘ግብረ ሀይል’ በሚል የሚንቀሳቀሱትን እንደ’በቃን’ ንቅናቄ አካል መቀበልና በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ሳይቀር ‘አቀባበል’ ተደረገላቸው የመባሉን ዜና ማየት ይቻላል፡፡ በምድረ አሜሪካ የነበረው ተጽእኖ እንዲለዝብ በተጨማሪ በህወሀት ገንዘብ በተቀጠሩ አግባቢ ድርጅቶች በአሜሪካ መንግሥት (ስራ አስፈጻሚ ዘርፍ) ውስጥ ተሰሚነት እንዳይኖራቸው ለመከፋፈል የተደረገውንም ሂደት ተከታትለናል፡፡ የነጩ ቤተ መንግሥት በዝግ ስብሰባ በሚጠራባቸው ሂደቶች ውስጥ በመጀመሪያዎቹ ምዕራፎች ይህን የበቃ ንቅናቄ የማግለል አዝማሚያዎች - የመከፋፈልንም ጨምሮ ተስተውሏል፡፡
በውጭ የሚገኘው ትውልደ ኢትዮጵያዊው ትልቅ ሀይል መሆኑን መረዳትና ልምዱንና እውቀቱን መጠቀም በእጅጉ ያሻል፡፡ መንግሥት የሚጓዝባቸው የውጭ ፖሊሰ አቅጣጫዎቻችን በአመዛኙ ያልተጠኑና ይህንን ሀይል ያላገናዘቡ ናቸው። ለምሳሌ ወደ አሜሪካ ለመምጣት ያለ ፍላጎትን ብቻ የያዘ የሚመስል - ‘በውጭ ባለው ማህበረሰብ ብቻ ተማምነን መቀመጥ የለብንም’ የሚል አመለካከት አለ - በመንግሥት በኩል፡፡ እርግጥ ነው በፊታውራሪነት ጉዳዩን መስመር በማስያዝና አቅጣጫውን በመወሰን ረገድ የመንግሥት የውጭ ፖሊሰ ቀራጽያንና ተግባሪዎች ወሳኝ ሚና አላቸው፡፡ ይሁንና በውጭ የሚኖረው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ከፍተኛ ምርኩዝ ሊሆን መቻሉን ከግምት ውስጥ ማስገባት ይገባል፡፡ አሁን፣ አሁን የተለመደ የሚመስለውና በዚህ በሽግግር ዘመን የታየው ትልቁ ሳንካ - አዳዲስና ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን ሰዎች በከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ሥራ ውስጥ የመደንጎር ነገር ነው፡፡ ለጉዳዩ ብቃት ያለው ከላይ እስከ ታች በተዋረድ ያለመመደብ ችግርም በእርግጥ ይስተዋላል፡፡
ከዚሁ ጋር መነሳት ያለበት አሁን ይህን ጽሁፍ እየጻፍኩ እያለሁ፣ ከውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአሜሪካ ሹማምንትን ለማነጋገር አንድ የልዑካን ቡድን ለመላክ ዝግጅት የመኖሩን ነገር ሰማሁ፡፡ በአሜሪካ ምክር ቤቶች ተወካዮችን ለማነጋገር በሚል የሚመጣው የልዑካን ቡድን - እንዴትና ማንን እንደሚያነጋግር ሳይጠናና ቀጠሮ ሳይያዝ - የሚመጣበት የግብር ይውጣ አሠራር እንደሆነም ነው ምንጮቹ የሚገልጹት። ሆኖም የአሜሪካ ምክር ቤት አባላትን ለማግኘት የሚከናወኑ ቅድመ ዝግጅቶች አሉ፡፡ ተወካዮቹ ሲጀመር ማንም እንዳሻው የሚያገኛቸው ሳይሆን ቀጠሮና ቅድመ ዝግጅት መደረግ አለበት፡፡ የሚመጡትም ልዑኮች ብቃትም ይመዘናል። የሚያሳኩት ግብም በጥሞና መጤን አለበት፡፡ ለዚህ ነው በየሀገራቱ የሚኖረው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ትልቅ ጉልበትና አቅም ነው የምለው፡፡
የውጭ ፖሊሲ አካሄዳችን ከውስን የፓርቲ አመለካከትና መስመር የተላቀቀ - ሀገራዊ ይዘት ያለውና ዲፕሎማሲን እንደ ጥበብ በሚያዩ ብቃት ባላቸው ሙያተኞች የሚመራ መሆን ይገባዋል፡፡ የውጭ ፖሊሲ አሠራር የመልመጃ መስክ አይደለም፡፡ የስሜታዊነትን አካሄድ ቅራኔን የማክረር አዝማሚያንም አይሻም። ለብሄራዊ ጥቅማችን እንዴት እናሰልፈው፣ እንዴት እናጣጥመው ነው ጥያቄው፡፡ ዓይንህን ላፈር - እየተባባሉ በጥላቻና በቅራኔ የሚጦዙበት አይደለም፡፡
እርግጥ ነው ስንወድም ስንጠላም ለከት የሚሉት ነገር የለንም ተብለን እንታማለን። በተለይ የፖለቲካውና የዲፕሎማሲው ዓለም ከዚህ ስሌት ነፃ የመሆን ፈለግን ካልተከተለ፣ በጽንፍና ጽንፍ - አንፃር ላንፃር ቆመን መጠፋፋታችን (እርስ በርስ) ወይም ከሌሎች ጋር መጋደላችን አይቀርልንም። ቤታችንንም ለአደጋ አጋልጠን - ‘ባዶ ጩኸት’ ብቻ ሆነን እንዳንቀርም መጠንቀቅ አለብን፡፡ ችግሮቻችን ብዙ ናቸው፡፡ እና እንዴት እናቃላቸው እንጂ  - እንዴት እናባብሳቸው ወይም እናባዛቸው አይባልም። የሚያስማማንን መፈለግና ከብሄራዊ ጥቅማችን ጋር ለመፍተል መትጋት - ግራጫውን መንገድ የመሻት ብልህነት በርግጥ ያስፈልገናል፡፡ ሁሉን ጠልተን - ጥላቻ ውጦን እንዳንቀር ማሰብ ያሻናል፡፡ የውጭ ፖሊሲ የሀገር ውስጡ ተቀጽላ ነው ይባላልና ከስሜቱ ክረት ወጣ ብለን በብልሃት መጓዝን አንርሳ። ከአሜሪካ መንግሥት ጋር በዲፕሎማሲያዊ ጥበብ የሀገራችንን ጥቅምና ልዕልና ለማስጠበቅ ስንሠራ መዳረሻችን መወዳጀትና መግባባት እንጂ እርግማንና ዘለፋ ሊሆን አይገባም፡፡ ግን ግን የቱ ይሆን ምርጫችን? በመግባባትና በጋራ ጥቅም የሚራመድ የውጭ ፖሊሲ ወይስ በመጎነታተልና በመገፋፋት ለግጭት የሚጋብዝ አካሄድ?

Read 1571 times