Monday, 18 April 2022 00:00

ልዩ ፍላጎት ያላቸው ልጆችና የወላጆች ተግዳሮት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   “ከእያንዳንዱ ኦቲዝም ካለበት ልጅ ስኬት ጀርባ፣ ከሥራና ከህይወት ወደኋላ የቀሩ ወላጆች አሉ”


           ወይዘሮ መዓዛ መንክር ይባላሉ፡፡ የአዕምሮ ህክምና ባለሙያና አማካሪ ሲሆኑ የሻምፒዮንስ አካዳሚ ት/ቤት መስራችና ሥራ አስኪያጅም ናቸው፡፡ ት/ቤቱ በተለይ ከአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ጋር በተያያዘ ችግር የገጠማቸውንና ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ልጆች ተቀብሎ በማስተማር ይታወቃል፡፡ ወ/ሮ መዓዛ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን ወላጆች በእጅጉ የሚያግዝ “ሁሉም በአንድ” የተሰኘ ተግባር ተኮር መፅሐፍ አዘጋጅተው ለንባብ ያበቁ ሲሆን፤ በኦቲዝም ዙሪያ ግንዛቤ ለመፍጠር በኩል በርካታ ጥረቶችንና እንቅስቃሴዎችን ያደርጋሉ፡፡ የኦቲዝም ወር ተብሎ በተሰየመው በመጋቢት ወርም በርካታ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብሮችን ያካሄዱ ሲሆን በተለይ በኦቲዝም  ለተጠቁ ልጆች ወላጆች ባሰናዱት የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብር ላይ የተገኘችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ በጉዳዩ ዙሪያ ወይዘሮ መዓዛ መንክርን እንደሚከተለው አነጋግራቸዋለች፡፡ እነሆ፡-Psych ጤና - አዲስ መጽሐፍ #ሁሉም በአንድ#... | Facebook


             በአዲስ አበባ ያሉ አብዛኞቹ የግል ትምህርት ቤቶች ለትርፍ የተቋቋሙና መደበኛ የሚባሉ ልጆችን ብቻ ተቀብለው የሚያስተምሩ ናቸው፡፡ የእናንተም ሻምፒዮንስ አካዳሚ ኢንቨንስትመንት እንጂ በጎ አድራጎት አይደለም፡፡ ነገር ግን ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ልጆችም ተቀብላችሁ ታስተምራላችሁ፡፡ እንዴት ለማስተማር ፈቃደኛ ሆናችሁ?
በእውነቱ ይሄ ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡ ምን መሰለሽ በሀገራችን እንደ አጠቃላይ በተለይ የግል ት/ቤቶች ሲከፈቱ እንዳልሽው ቢዝነስ ሆነው ነው የሚቋቋሙት፡፡ ኢንቨስትመንት ናቸው፡፡ ያ ኢንቨስትመንት ደግሞ ውድድር አለው፡፡ ምን ዓይነት ውድድር ካልሽኝ፣  “እኔ ት/ቤት 8ኛ ክፍል ካስፈተንኳቸው 20ዎቹ  መቶ ደፍነዋል”፣ “እኔ 12ኛ ክፍል አስፈትኜ 30 ተማሪዎች ስትሬት A አምጥተዋል” እያሉ ደህና ውጤት ያመጡ ተማሪዎችን እንደ መፎካከሪያነትና ት/ቤቱ እውቅና እንዲያገኝ እንደ መሳሪያ ይጠቀሙበታል፡፡ ይህንንም በየትምህርት ቤቱ በር ላይ ተለጥፎ በግልፅ እናየዋለን፡፡ እንዲህ አይነቱ አመለካከት ወላጆች ት/ቤት ሲመርጡም ተፅዕኖ ያሳድርባቸዋል፡፡ በብዛት ጥሩ ውጤት ያመጡ ልጆች ያሉበት ት/ቤት ማስተማር እንዲፈልጉ ያደርጋቸዋል፡፡ ይሄ ደግሞ ትክክልም ነው፡፡ ወላጅ ለልጁ ያስባልና፡፡ልዩ ፍላጎት ያላቸው ልጆች አካታች የትምህርት ተቋማት ይፈልጋሉ
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ልዩ ድጋፍ የሚፈልጉ፣ በራሳቸው ፍጥነት የሚጓዙና ከማንም ጋር የማይፎካከሩ፣ ምናልባት የሌሎችንም ድጋፍ የሚሹ ልጆችን አስተምራለሁ ብለሽ ስትነሺ፣ በጣም ከባድና ብዙ ዋጋ ያስከፍልሻል፡፡ ለምሳሌ የእኛን ብትጠይቂኝ፣ ብዙ ጊዜ ከወላጆች “ብር እየከፈልን እንዴት ከእንደነዚህ አይነት ልጆች ጋር ልጆቻችንን ቀላቅላችሁ ታስተምራላችሁ” በሚል በጣም ከባድ  ቁጣና ወቀሳ ይሰነዘርብናል፡፡ አንዳንዱ ወላጅ ደግሞ “አንድ ቀን ት/ቤት ስገባ አንድ ልጅ አንገቱን ሲያወዛውዝ አይቻለሁ ወይም እጁን እንዲህ ሲያደርግ አይቻለሁ፤ ስለዚህ ልጄ  ከዚህ ልጅ ጋር እንዳይቀመጥ አደራ!; ይላሉ፡፡ “የኔ ልጅ ይሄ ልጅ የሚማርበት ክፍል ውስጥ  ነው የሚማረው አይደለም!?” ብለው  አጥብቀው ይጠይቃሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ወላጆች ልጃቸው በጣም ጎበዝና ተፎካካሪ ከሚባለው ጋር እንዲማር እንጂ ልዩ ድጋፍ ከሚፈልግ ልጅ ጋር እንዲማር አይፈልጉም፤ እናም ፈተናው ቀላል አይደለም፡፡  እኛ ለረዥም ዓመት  ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ልጆች ተቀብለን ስናስተምር፣ ልጆቻቸውን ከዚህ አስወጥተው ሌላ ት/ቤት የሚያስገቡ ገጥመውናል፡፡ ለምን ስንል “አይ ሻምፒዮን አካዳሚ እኮ በሽተኛ ልጆች ተቀብሎ ያስተምራል ብሎ ጎረቤቴ ነግሮኛል” ይሉናል። አንዳንዱ ደግሞ ይመጣና፤ “ይሄ በሽታ ይተላለፋል ወይ?” ብሎ የሚጠይቅሽም አለ፣ ብቻ ብዙ ዓይነት ጥያቄዎች ወላጆች ውስጥ ይፈጠራል፡፡ ይሄ ሁሉ የሆነው ደግሞ በጉዳዩ ዙሪያ ትኩረት ተሰጥቶ ስለማይሰራና ግንዛቤው ስለሌለ ነው፡፡
እኛ ይህን ችግር ለመፍታት ዛሬ እዚህ ተገኝታችሁ እንዳያችሁት ወላጆችን በማገናኘት ልምድ እንዲለዋወጡ ግንዛቤ እንዲያገኙ፣ ስለችግሩ ይበልጥ እንዲያውቁ ተደጋጋሚ መድረኮችን እያዘጋጀን  የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲያመጡ እያደረግን ነው፡፡ ኦቲስቲክ ሆነው በዓለማችን ላይ ትልልቅ ስኬቶችን ያመጡ ሰዎችን ታሪክ በመንገር፣ ልዩ ድጋፍና እንክብካቤ ከተደረገላቸው ልጆቻቸው ስኬታማ እንደሚሆኑ እናስተምራቸዋለን፡፡ በፊልሙ በቢዝነሱ በፈጠራ ስራ ብቻ በበርካታ ዘርፎች ትልልቅ ስኬት ያስመዘገቡ ዓለም አቀፍ ሰዎች አሉ፡፡ እዚህ እኛም ት/ቤት ውስጥ በስዕል፣ በግጥም፣ በቋንቋ፣ በሳይንስና በአጠቃላይ ትምህርቱም ውጤታማና ተሸላሚ የሆኑ ልጆች አሉን፡፡ ለምሳሌ የUKG ተማሪ ሆኖ በአፍሪካ ካርታ ላይ ያሉትን ሀገራት ቦታውን ስታሳይው የሚነግርሽ ኦቲስቲክ ልጅ አለ፡፡ መደበኛ ሆኖ ግን አይደለም የአፍሪካን፣ የኢትዮጵያን የማያውቅ  ሊኖር ይችላል፡፡ እናም እነዚህ ልዩ ፍላጎት ያላቸው ልጆች እድል ከተሰጣቸው የበለጠ ክህሎት እንዳላቸው ስናሳይ፣ ወላጆች ግንዛቤ እያገኙ፣ ችግሩም እንደማይተላለፍ እያወቁ የእኛንም ጥረት እያደነቁ መጡ፡፡ ለምሳሌ አንድ መደበኛ ልጅ እድሜው ሲፈቅድ መናገር መጀመሩ ኖርማል ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንዱ ስንት ተደክሞና ተለፍቶ ነው የሚናገረው ብለው ይገረማሉ፡፡
ለምሳሌ አንድ የገጠመኝ ምን መሰለሽ፣ አንድ ተማሪያችን ለእረፍት ከከተማ ውጪ ይሄዳል፡፡ እዛ ያረፉበት ሆቴል ውስጥ ሲዋኙ አንዱ ከውጭ የመጣ ኦቲስቲክ ልጅ አለ። ያ ልጅ ውሃ ውስጥ እንዳይደፍቃቸው ወላጆች ልጆቻቸውን በአይን ጥቅሻ ያስጠነቅቁ  ስለነበር፣ ሁሉም እየወጡና እየሸሹ መዋኛው ባዶ ሆነ፡፡ በዚህን ጊዜ ያ የእኛ ተማሪ ወደ ክፍሉ ሄዶ ኳስ አምጥቶ ያንን ልጅ ማጫወት ጀመረ፡፡ በዚህን ጊዜ የልጁ አባት ተደንቆ፤ “እንዴት ሌሎቹ እየሸሹ ሲሄዱ አንተ ልታጫውተው ፈለግህ?” ሲለው፤ “እሱ እኮ እብድ አይደለም! እኛ ት/ቤት እንደእሱ አይነት ልጆች ይማራሉ። እነሱም የሚፈልጉት የሚረዳቸውና የሚቀርባቸው ጓደኛ ነው” አለው፡፡ ይህን የሚለው የ7 ዓመት ሕጻን ልጅ ነው። ከዚህ በኋላ  አባትየው “እባካችሁ ይህ አስተዋይ ልጅ  የሚማርበትን ት/ቤት አድራሻ ስጡኝ; ብሎ ተቀብሎ ደውሎልኝ፤ “ትውልድ እየተቀየረ ነው፤ ትልቅ ስራ እየሰራችሁ ነው; ብሎ አመሰገነኝ። ይህ እንግዲህ አብሮ ከመዋል ባህሪያቸውን ከመረዳትና ጉዳት እንደማያደርሱ ከማወቅ የሚመጣ ነው። ችግሩ በድጋፍ፣ በክትትልና በተጨማሪ ስልጠና የሚለወጥ እንደሆነ ማስገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ይህንንም ለውጥ በተግባር በልጆቹ ላይ እያመጣን አስተሳሰብ እየቀየርን ነው፡፡ ወላጆችም “እንኳንም ዕድል ሰጣችሁን” እያሉ  የሚያመሰግኑም ብዙ ናቸው፡፡ እኛም ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥረት እየጨመርን፣ እየለፋንና እየታገልን ሌሎች ወላጆችን ለማስደሰትና ለገንዘብ ብለን ከአላማችን ዞር አንልም በማለት በመፅናታችን ሰዎችን ወደምንፈልገው መስመር እያመጣን እንገኛለን፡፡
ሻምፒዮንስ አካዳሚ መቼ ነው የተቋቋመው? ምን ያህል መደበኛ፣ ምን ያህል ልዩ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች ያስተምራል?
የእኛ የአካትቶ ትግበራ ከተጀመረ 15 ዓመት አስቆጥሯል፡፡ ቅድም እንዳልኩሽ፣ የት/ቤታችን ትልቁ ተግዳሮት ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ያስተምራል መባሉ ነው፤ ይሄ ወላጆችን ያስፈራቸዋል፡፡ ቀደም ብለው ደፍረው የገቡት ስለልጆቹ ሲያዩ ልጆቻቸው ስለነዚህ ልጆች ሲነግሯቸው፣ “እከሌ እኮ የክፍሉን ተማሪ ስም ከነአያታቸው ይሸመድዳል; ሲሏቸው "አሃ ለካ ልዩ ተሰጥኦና ኳሊቲ አላቸው" እያሉ ነው መቀበል የጀመሩት፡፡ ከውጭ ሲሆኑ ግን ደፍረው ወደ እኛ መምጣት ይቸገራሉ። ብቻ ያም ሆኖ ት/ቤታችን “ሻምፒዮንስ” በሚለው ስም ከተከፈተ 6 ዓመቱ ነው፡፡ 500 ተማሪዎች አሉን፡፡ ከእነዚህ መካከል 80ዎቹ ልዩ ድጋፍ የሚስፈልጋቸው ናቸው። ልዩ ድጋፍ ከሚፈልጉት 30ዎቹ ይሄ ነው ብለሽ ከመደበኛዎቹ በማትለይው ደረጃ ውጤታማ ሆነው ከእኩዮቻቸው ጋር የሚማሩ ናቸው፡፡ ይህ ለውጥ የመጣው ባደረግንላቸው ክትትልና ድጋፍ ነው፡፡ ቀደም ሲል በዚህ የወላጆች የግንዛቤ መድረክ ላይ ሪፖርት ስናቀርብ እንደሠማችሁት፤ ከዚህ ከእኛ ወረዳ ተወዳድሮ በስዕል አንደኛ ወጥቶ ልዩ ተሸላሚ የሆነው፣ የልዩ ፍላጎት ተማሪያችን ነው፡፡ አሁንም እናቱ ልምድ ስታካፍል ነበር፡፡ ይህ ተማሪ አሁን ላይ የ3ኛ ክፍል ተማሪ ሆኗል፡፡ ምንም እንኳን ከፍተኛ ዋጋ ብንከፍልና ብንደክምም፣ ከ80ዎቹ ውስጥ 30ዎቹን አብቅተናል፡፡ 50ዎቹ ደግሞ የሙሉ ቀን ቴራፒ የሚወስዱና በከፊልም ቴራፒ እየወሰዱ የቀጠሉ ናቸው፡፡
በሀገራችን የአካትቶ ትምህርት በህግ ደረጃ የተቀመጠ ቢሆንም፣ ጉዳዩ ትኩረት ከማጣቱ የተነሳ የሚፈለገውን ያህል መፍትሄ እንዳላመጣና በዘርፉም የሰለጠኑ ባለሙያዎች ቁጥር አናሳ በመሆኑ ችግሩን መቅረፍ እንዳልተቻለ ይነገራል፡፡ እርስዎ እንደ ባለሙያም ጉዳዩን በቅርበት እንደሚከታተልም ምን ይላሉ?
በሀገራችን የልዩ ፍላጎት ትምህርት ከዲፕሎማ እስከ 3ኛ ዲግሪ (PHD) ድረስ ይሰጣል፡፡ ችግሩ ምንድን ነው ካልሽኝ፣ ትምህርቱ ተግባር ተኮር አይደለም፡፡ እዛው ዩኒቨርስቲ ውስጥ ተምረው ተመርቀው  ወደ ሌላ ስራ ይሄዳሉ እንጂ ወርደው ድጋፉን ከሚፈልጉት ልጆች ጋር፣ ወላጅ ካለበት ጫና ጋር ፊት ለፊት ተጋፍጦ ተግዳሮቱን በተግባር የሚጋፈጥ ባለሙያ የለም፡፡ አንድ የዘርፉ ተመራቂ አንድ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ወይም ኦቲስቲክ የሆነ ልጅ ይዞ አሰልጥኖ አስተምሮ፣ ለውጥ እስኪያመጣ ድጋፍ አድርጎ አይደለም የሚመረቀው። እዛው ዩኒቨርስቲ ውስጥ ንድፈ ሃሳቡን ይማራል ይመረቃል፤ አለቀ፡፡ በዚህ ምክንያት በዘርፉ የሰለጠነ፣ በተግባር የተፈተነ ባለሙያ ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ እኔም እራሴ በውጭ ሀገር የንግግር ቴራፒ፣ኦኪፔሽናል ቴራፒ (እጅና እግርን አቀናጅቶ የመጠቀም ቴራፒ)፣ባህሪ ማረቅ (ብሔቪየራል ቴራፒ) የሚባሉትን ትምህርቶች በመውሰድ፣ የትምህርት ዝግጅቴም (የስነ ልቦና እና የአዕምሮ ህክምና) ስለሆነ ነው የማሰለጥነው፡፡ ለምሳሌ ወደ 200 የሚጠጉ ቤት ለቤት የሚሰሩ፣የተለያዩ ት/ቤቶች የተቀጠሩና በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ እኛ ጋር እየመጡ ነው ስልጠና የሚወስዱት እንጂ አገሪቷ ላይ በተግባር የተደገፈ የሚሰራ ነገር  አይታይም፡፡ ነገር ግን ጠቅለል ብሎ የልዩ ፍላጎት ትምህርት እስከ 3ኛ ዲግሪ አለ። አንድ በልዩ ፍላጎት ፒኤችዲ ያለው ምሩቅ፣ እንዴት ነው አንድ  ኦቲዝም ያለበት ልጅ መናገር የሚችለው? የሚለውን በተግባር ያውቃል ብለን አናምንም::
እርስዎ ከላይ የጠቀሷቸውን ተግባር ተኮር ስራዎች ካላከናወነበት በዘርፉ ፒኤችዲ ይዞ ምንድን ነው የሚሰራበት?
እሱ ነው ዋናው አንገብጋቢው ጥያቄ፡፡ አብዛኛዎቹ ወደ ጥናት ነው የሚያዘነብሉት፤ ተመራማሪዎች (ሪሰርቸሮች) ናቸው። እኛ አሁን ክፍት የስራ ቦታ ማስታወቂያ እናወጣለን። በሳይኮሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪ  እንዲሁም በልዩ ፍላጎት የመጀመሪያ ዲግሪ ያለው ስንቀጥር፤ “እኔ ዲግሪ ይዤ አንድን በሽተኛ ልጅ አጨብጭብ፣ቁጭ በል፣እየኝ ስል ልውል ነው እንዴ” ብለው ትተው ነው የሚሄዱት። ከዚያ በኋላ የህፃናት መብት፣ ቀይ መስቀል  እና ሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ውስጥ ነው የምታገኚያቸው። ከአንድ ኦቲስቲክ ልጅ ጋር ተግባር ተኮር የሆነ ስራ መስራት፣ ራስን ዝቅ ማድረግ አድርገው ነው የሚቆጥሩት። “እንዴት ነው እጅ መታጠብ፣ መጸዳዳት፣ መናገር የማስተምረው?” ብለው ስራውን ለቀው ይሄዳሉ፡፡ ይሄ በጣም የሚያሳዝነኝ ጉዳይ ነው።  አንድ ልጅን ረድቶና አግዞ መቀየር፣ የዛን ልጅ ቤተሰብ መቀየር ማለት ነው፡፡ እዚህ 100 ሰው ቢኖር  500 ሰው መርዳት ማለት ነው፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች ይህንን እገዛና ለውጥ ሳይሆን የሚያስቡት እዚህ ጋ ያለውን ልፋትና ትግል ነው፤ እና ለምን ብዬ እንገላታለሁ ይላሉ፡፡ እዚህ አገር ትልቅ ተደርጎ የሚወሰደው የቢሮ ስራ ነው።
ለምሳሌ ቀላል ምሳሌ ልንገርሽ፡፡ እኛ ለግንዛቤ ሥራ አብዛኛውን ህዝብ የምናገኘው በእናንተ በሚዲያዎች በኩል ነው፡፡ ስለዚህ  እንዲህ አይነት መርሃ ግብሮች ስናዘጋጅ ብዙ ሚዲያ መጥቶ እንዲዘግበው፣ ጉዳዩ ትኩረት እንዲያገኝና ግንዛቤ እንዲስፋፋ እንፈልጋለን፡፡ ከጠራነው በርካታ ሚዲያ ውስጥ ጉዳዬ ብላችሁ የመጣችሁት ከአንድ እጅ ጣት አትበልጡም፡፡ ይሄ ሁሉ የሚያሳየው በብዙ መልኩ ለችግሩ ትኩረትና ቅድሚያ አለመሰጠቱን ነው። እኔ በልዩ  ፍላጎት ላይ ማስተርሴን ስሰራ የጥናት ፅሁፍ  የሰራሁት የሚዲያ ሽፋን ላይ ነበር። ብሔራዊ ሚዲያው ስለ ልዩ ፍላጎት ምን ያህል ዘግቧል የሚል ነበር ጥናቴ፡፡ በወቅቱ ኢቲቪና ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ምን ያህል ትኩረት ሰጥተውታል የሚለውን ለማየት የአንድ ዓመት ሂደታቸውን ስፈትሽ፣ በጣም በሚገርምና በሚያሳዝን ሁኔታ 0.06 ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ ይህም ቢሆን ዓመታዊ የዳውን ሲንድረም ቀን ሲከበር መግለጫ የተሰጠበት፣ ከአይነስውርነት ጋር የተያያዙ መግለጫዎች እንጂ ጉዳዩን ጉዳይ አድርጎ በስፋትና በጥልቀት የሰራ፣ የስኬት ታሪክ የፃፈ፣ እድል ካገኙ መስራት ይችላሉ የሚል አመላካች ነገር የዘገበ አንድም አላገኘሁም። ስፖርት፣ ፋሽን፣ ሙዚቃና ቢዝነስን ስንመለከት ደግሞ ምን ያህል ከሚፈለገው በላይ ሽፋን እንዳለው እንታዘባለን፡፡ የልዩ ፍላጎት ጉዳይ የሚናቅ ጉዳይ አይደለም፤ ምክንያቱም አሁን የሁሉንም ቤት እያንኳኳ ያለ ችግር እየሆነ መጥቷል፡፡
የኦቲዝም ወይም የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት እየጨመረ መምጣቱን የሚጠቁሙ የቅርብ ጥናቶች ይኖራሉ?
ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ ከሚወለዱት 44 ልጆች አንዱ ኦቲዝም አለበት፡፡ ይሄ ቀላል አይደለም፡፡ እንደ ስታቲስቲክ ስንወስደው ትልቅና የሚያስደነግጥ ቁጥር ነው፡፡ ከ44 ልጆች አንዱ ኦቲስቲክ ነው ማለት እዚህ ሰፈር ውስጥ ብዙ ልጆች አሉ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ችግሩ እየተስፋፋ  በመሆኑ  ሚዲያውም ግንዛቤ በመፍጠር ደረጃ ከፍተኛ ስራ መስራት አለበት። ዛሬም እዚህ ቦታ በመምጣታችሁ ትልቅ አክብሮት አለኝ፤ የእውነቴን ነው የምላችሁ፡፡
እናንተ የሥራችሁን ውጤታማነት የምትለኩበት አንዱ ጉዳይ የወላጆች እፎይታ ይመስለኛል፡፡ አሁን ያለንበት ወቅት ሰው በጦርነትና ግጭት፣ በኑሮ ውድነትና በሌሎች በርካታ ችግሮች የተወጣጠረበት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህ ላይ ወላጆች ኦቲስቲክ ልጆች ሲኖራቸው፣ በተለይ እናት ስራ ትታ ሙሉ ስራዋ ልጇ ይሆናል። ባለፈው በብሔራዊ ቴአትር በተካሄደ የዳውን ሲንድረም ቀን ላይ ያየሁት አንድ መሪ ቃል ትዝ ብሎኝ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ  ትንሽ ቢያወጉኝ…?
በጣም ትክክል ነሽ! ያ መሪ ቃል ከኔ መፅሐፍ የተወሰደ ነው፡፡ “ከእያንዳንዱ ኦቲዝም ካለበት ልጅ ስኬት ጀርባ ከሥራና ከህይወት ወደኋላ የቀሩ ወላጆች አሉ” ይላል፡፡ እውነት ነው። ልዩ ድጋፍ የሚሹ ልጆች  በራሱ ያለባቸው እክል አለ። መሻሻል ያለበት ሊሰራ የሚገባው ማለቴ ነው። በተለይ ልጆቹ ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ። አንድ ሰው አግብቼ ልጅ እወልዳለሁ ብሎ ሲያቅድ ምንም ይፈጠራል ብሎ አያስብም። እወልዳለሁ፣ አሳድጋለሁ፣ ጥሩ ት/ቤት አስተምረዋለሁ፣ ጥሩ እንዲመገብ አደርጋለሁ ብቻ  ነው የሚለው፡፡ እነዚህ ወላጆች ግን ፍፁም ከአዕምሮና እቅዳቸው ውጪ የሆነ ነገር ነው የሚገጥማቸው። ይሄ ችግር ሲከሰት ዘርፈ ብዙ ቀውስ አለ፡፡ በተለይ ወላጆች ራሳቸው ችግሩን እስኪቀበሉት ድረስ ከባድ ነው። "ለምን ለኔ ይሄ አይነት ልጅ ተሰጠኝ" በሚል ከፈጣሪና ከሁኔታዎች  ጋር ይሟገታሉ። ከዚህ ሙግት በረጅም ሂደት ከወጡ በኋላ ደግሞ እሺ መፍትሔውስ ምንድን ነው? እንደዚህ አይነት ልጅ አምኜ ለሰራተኛ ሰጥቼ፣ ለዘመድ ትቼ እንዴት ነው ስራ የምሰራው? ለተለያየ ጥቃት ይጋለጥብኛል በሚል ስራቸውን እርግፍ አድርገው ትተው፣ ሙሉ ስራቸው ልጃቸው ይሆናል። ከዛ ደግሞ ልጁን ማብቃት አለባቸው። ልጃቸውን ይዘው ወደ ውጪ ሲወጡ ማህበረሰቡ “እከሌ’ኮ ልጇ በሽተኛ ነው” እያለ ያሸማቅቃቸዋል። ይሄ ሁሉ ጫና ነው ያለው፡፡ አንድ እናት ሁለት የማይናገሩ ልጆች አሏት- ኦቲስቲኮች ናቸው፡፡ በጣም ራሳቸውን የሚጎዱ ናቸው። የእነዚህ ልጆች ወላጆች የገንዘብ አቅም ያላቸው ናቸው። ልጆቹ ከቤት አይወጡም። አንድ ቀን ሞግዚታቸው ከቤት ይዛቸው ወጣችና ጎረቤቶች “ሀይ ቤቢ ሀይ ሚጣ” ሲሏቸው ህፃናቱ መልስ አልሰጡምና “እነዚህ ልጆች ዲዳ ናቸው እንዴ?” ብለው ሲጠይቁ፣ ሞግዚታቸው “አዎ አይናገሩምኮ” አለች። ከዚያ በኋላ እናትየዋ ስትነግረኝ፤ "ልጆቼን ይዤ ከቤት ስወጣ ሰው ሙሽራ እንደሚያጀብ “ዲዳ ልጆች ናቸው” እያለ ለማየት ይወጣ ነበር ብላ እያለቀሰች ነው የነገረችኝ፡፡ ከማህበረሰቡ፣ ከፋይናንሱ፣ ከቤት አከራይ በርካታ ጫና ነው ያለው፡፡ ይህ ሁሉ ጫና ተደራርቦባቸው እኛ ጋ ሲመጡ፣ መጀመሪያ ወላጆችን እናበቃቸዋለን። "እጃችሁ ላይ መፍትሔ አለ፤ ኦቲስቲክ ልጆች የሚፈልጉት ትምህርታዊ ሥልጠና ነው” እንላቸዋለን። "ያልተቋረጠ ስልጠና ያለመታከት ከሰጣችኋቸው መፍትሔው እጃችሁ ላይ ነው” እንላለን፡፡ ይህን ሲሰሙ ጨልሞባቸው የነበረው ነገር ከላያቸው ላይ ይገፈፋል፡፡
ሁለተኛው ነገር፤ ልጆቻቸው አቅማቸው እንዲጎለብትና እንዲለወጡ ስልጠና እንሰጣቸዋለን፡፡ ሁለቱን እያቀናጀን ስንሄድ ለውጥ ይመጣል፡፡ ቅድም ሰምታችኋል “እከሌ እኮ እጁን እያውለበለበ ቻው አለ” ብለን ሰለብሬት እናደርጋለን፡፡ ለመደበኛው ሰው እጅ ማውለብለብ ከቁም ነገር የምንቆጥረው ጉዳይ አይደለም፡፡ አንድ ኦቲስቲክ ልጅ አንድ ቃል ሲያወጣ እልል ይባላል፡፡ አዲስ እንደተወለደ ነው የምንቆጥረው፡፡ ሌላው ነገር ልጃቸው ከዚህ በፊት ትኩረት አይሰጣቸውም፤ እናቱ ትሁን፣ ግንኙነት ይኑራት የማያውቀው ልጅ ከት/ቤት ልትወስደው ስትመጣ፣ ከሰው መሃል ለይቶ ሄዶ ሲያቅፋት በደስታ ይሰክራሉ፡፡ ትምህርት ቤታችሁ “Healing School” ነው ይሉናል፡፡ በዚህ በጣም ደስ ይለናል፡፡ ዛሬ በዚህ መድረክ ላይ የጠራናቸው እነዚህ ሁሉ ወላጆች ልጆቻቸው ኦቲስቲክ የሆኑ ናቸው፤ ሌሎች ወላጆች አልጠራንም። ዛሬ እነዚህ ወላጆች የሚመካከሩበት፣ ልምድ የሚለዋወጡበት፣ ስለ ልጆቻቸው ለውጥ ምስክር የሚሰጡበትና የበለጠ ግንዛቤ የሚያገኙበት ነው፡፡ በፊት እንደዚህ አይመጡም ነበር፤ ይፈሩና ይደበቁ ነበር፡፡ አሁን ግን ልጆቻቸው ዋጋ እንዳላቸው ሲያዩ፣ ያንን መደበቅና መፍራት አስወግደው በልበ ሙሉነት ለልጆቻቸው የበለጠ ለውጥ ይሳተፋሉ፤ ይመካከራሉ። የዚህ ሁሉ ወላጅ ለውጥ የእኛ የብዙ ጊዜ ልፋት ውጤት ነው፡፡ የዛሬ ስምንትና ዘጠኝ ዓመት ወላጅ እንደዚህ አይመጣም ነበር፡፡ ቢመጡም እንኳን ተሸፋፍነው ወይም ኮፍያ አድርገው አሊያም መኪና ውስጥ ሆነው ሰራተኛ ነበር የሚልኩት። አሁን እሱን አስቀርተናል፡፡ ውጤታችንን እንዲህ ነው የምንለካው፡፡ ለምሳሌ እኔ “ድንቅ ምክር” የተሰኘ የፌስቡክ ገፅ አለኝ፡፡ እዛ ላይ ብዙ ትምህርት እንሰጣለን፤ ኦቲስቲክ ሆኖ 7ኛ ክፍል የደረሰልንን ልጅ ስኬት ያካፈልንበት ታሪክ ይገኛል፡፡
ከመንግስት የሚደረግላችሁ ድጋፍ አለ ወይስ እንደሌላው ኢንቨስትመንት ብቻ ነው የምትታዩት?
በጣም በሚገርም ሁኔታ ለመንግስት ት/ቤት፣ በቃ ት/ቤት ነው፤ አካተትሽ አላካተትሽ የማንም ጉዳይ አይደለም። የአካል ጉዳት የአዕምሮ ጤና ችግር ምንድን ነው? ሰው ሲደርስበት ብቻ ነው የሚያውቀው፤ ያልደረሰበት ሰው ነገ እኔ ላይ ይደርሳል ብሎም አያስብም፤ ጉዳዩንም ነገሬ አይልም። ትምህርት ቢሮ  ትምህርት ተደራሽ ይሁን ይላል፡፡ አካቶ ስናስተምር በግላቸው ቅን ሰዎች አሉ - በርቱ ጠንክሩ የሚሉና የሚያበረታቱ። እንደ መንግስት ግን ድጋፍ የለም፡፡ ግቢ ተከራይተን ነው የምናስተምረው፡፡ ቢያንስ ልዩ ፍላጎት ላላቸው የአስተማሪ ከፍለው የቦታ ነፃ እንዲሆንላቸው መሬት ስንጠይቅ መልስ የለም፡፡ እኛ ሶስት ቅርንጫፍ አለን፡፡ ለቤት ኪራይ በዓመት ወደ 10 ሚ. ብር እንከፍላለን። ሰራተኛም በርካታ ነው ያለን፡፡ እያንዳንዱ ልዩ ድጋፍ የሚፈልግ ልጅ አንድ አጋዥና ተንከባካቢ ይፈልጋል፡፡ ባህሪውና ፍላጎቱ የተለያየ ስለሆነ። ይህን ሁሉ አይቶ "ይህን እናግዛችሁ"  የሚለን አካል እስካሁን አላገኘንም፡፡
እስቲ በመጨረሻ በኦቲዝም ዙሪያ ስላሳተሙት መፅሐፍ ጥቂት ይንገሩን?
በ2013 ዓ.ም “ሁሉም በአንድ” የተሰኘ ተግባር ተኮር የህክምና መፅሐፍ ኦቲዝም ላለባቸው፣ የመማርና ትኩረት የማድረግ ችግር ላለባቸው፤ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ላለባቸውና በአጠቃላይ ከንግግር ጋር የተያያዘ ችግር ላለባቸው ልጆች አዘጋጅቻለሁ፡፡ “ሁሉም በአንድ” ያልኩት ማንኛውም ድጋፍ የሚፈልግ ሰው ድክመቱ ነው ጎልቶ የሚታየው፡፡ ነገር ግን ብዙ ተሰጥኦ ብዙ ጸጋ አላቸው፡፡ እኔ ለረጅም ዓመት ከብዙ መቶዎች ልጆች ጋር አብሬ ስለቆየሁ ድክመት ብቻ አይደሉም፡፡ ልብ ብለን ካስተዋልን ለአለም የሚጠቅም ብዙ ጸጋ አላቸውና  ያንን ለመግለፅ ነው፡፡ መፅሐፉ 10 ምዕራፎች ያሉት ሲሆን አስር እውነተኛ የወላጆችን ታሪኮች ይዟል፡፡ የደረሰባቸው ውጣ ውረድ፣ የትዳር መበተን፣ ልጆቻቸውን የሚያስተምሩበት ት/ቤት ማጣት፣ ብዙ መከራ ያሳለፉ ወላጆች ታሪክ አለው፡፡ #ኦቲስቲክ የሆኑ ልጆች የምታሳድጉ እኛም ይህንን ችግር አሳልፈናል፤ ነገር ግን ልጆቻችን እዚህ ስኬት ላይ ደርሰዋል; የሚል አስተማሪ ታሪክ የያዘ ነው፡፡
መፅሐፉ ማኑዋል ነው፡፡ መሬት ወርዶ በተግባር የሚሰራ  ባለሙያ ስለሌለ ወላጆች በተግባር ልጆቻቸውን ማገዝ ቢፈልጉ ምን ይስሩ፣ ከምን ይጀምሩ የሚለውን ሁሉ ያካተተ ነው፡፡ እኛ በግላችን ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ልጆች ለማገዝ ዘርፈ ብዙ ስራ ለመስራት ጥረት እያደረግን ነው፡፡ እናንተም እንደ ሚዲያ ለጉዳዩ ሽፋን ለመስጠት ስለመጣችሁ በእጅጉ እናመሰግናለን፡፡


Read 8922 times