Saturday, 16 April 2022 15:27

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

     ከግብፅ ተነስቶ ያልደረሰው አውቶብስ ጉዳይ
                                    ፉዣዥ

            “ከከንአን ወንድ እና ሴት ጋር መጋባት ለምን ተከለከለ? መሬቱን ወዶ ህዝቡን መጥላት ነው? ማርና ወተቱን ወዶ ነዋሪውን መጥላት ነው?” ወደ እነዚህ በሌላ ጊዜ እመለሳለሁ። አሁን ስለሌላ ጉዳይ ላውጋህ።
የከንአን ማርና ወተት ተራ ማርና ወተት እንዳይመስልህ።
ንብ አይደለም ማሩን የሚጋግረው። ከላም አይደለም ወተቱ የሚታለበው። የከንአን ምድር ናት ይሄን ማርና ወተት የምታፈልቀው።
እንዴት ሆኖ? እኔ ምናውቄ ወዳጄ።
ይሄንን የሰማ ሰው ለምን እና እንዴት ይላል እንዴ? ለጉዞ ይነሳል እንጂ። ጭራሽ ከመከራ ጋር ተጋብቶ ያለ ሰው።
እንግዲህ የእስራኤል ህዝብ በባርነት ቀንበር ከኖሩበት ግብፅ ተነስተው፣ ቀይ ባህርን ተሻግረው፣ በሲናይ በርሃ ጉዞ የጀመሩት ከንአን ለመድረስ ነው። መሃል ላይ የግብፅ ምስር፣ ዱባ ወጥ ይፈትናቸዋል።
የግብፅ ምስር ወጥ ግን ምን አይነት ይሆን? የግብፅ ዱባስ እንዴት ይሆን የሚሰራው?
በመከራ ነዋ። በመከራ በተያያዘ እሳት ላይ በመከራ የሰራኸውን ድስት ጥደህ፣ በመከራ በደቃቁ የተከተፈ ሽንኩርት አቁላልተህ፣ በመከራ የተገኘ በርበሬና ምስር ተጠቅመህ ነው፣ በመከራ የምትሰራው። ብቻ ግን ደም ደም፣ እንባ እንባ፣ መከራ መከራ ስለሚል ይጣፍጣል። ህዝቤ የናፈቀው ይሄን ነው። እንዴት አይናፈቅ?
ደግሞ እኮ በየቀኑ ከሰማይ መና ይወርድላቸዋል። ያለምንም መከራ። ጎንበስ ብሎ ማንሳት ነው። መጎንበስ ካልፈለክም አፍህን ከፍተህ ማንጋጠጥ ብቻ ነው። አንዳንዱ ብዙ መና ከመሬት ለቀመ። ሌላው ጥቂት አነሳ። ሁሉም መናውን በሉት። ብዙ የለቀመው ምንም አልተረፈውም። ጥቂት የለቀመውም ምንም አልጎደለውም። ሁሉም ጠገበ። ደበራቸው አይገልፀውም። መከራ የሌለበት ኑሮ። ግብፅ የሚለው ስም ራሱ እኮ ከመከራ ጋር መጋባት እንደማለት ነው። ብቸኝነቱን አልቻሉትም። መከራ ናፈቃቸው። ግብፅ ናፈቀቻቸው።
በየቀኑ የሚወርደው መና መቼ እንደሚያቆም ስለማይታወቅ አቁማዳ ወይም መክተቻ የሚመስል ነገር እየፈለጉ ከወረደው መና ጥቂት ይበሉና ብዙውን ማከማቸቱን ተያያዙት። በነጋው ሌላ መና ሲወርድም ያሳደሩትን ይጥሉና አዲሱን ጥቂት በልተው ብዙውን ለነገ ያሳድሩታል።
ያደረውን የሚጥሉት ስለሚተላ ነው። እንደሚተላም ተነግሯቸዋል። በየቀኑ መና እንደሚወርድላቸውም እንዲሁ። ግን ያከማቻሉ። ምን ያድርጉ፣ ግብፅ ስትናፍቃቸው።
አንዱ የሌላውን አቁማዳ ከነመናው ይሰርቃል። አንዱ የሌላውን ማጅራት መቶ አቁማዳውን ከነመናው ይቀማል። አንዱ ጉልበተኛ አስር ደካሞችን እያስፈራራ መና ያስለቅማቸዋል፣ ያሸክማቸዋል።
ብትነካኝ አለቅህም በሚል መንፈስ ነው፣ እያንዳንዱ በበርሃ የሚጓዘው። ምን ታየኛለህ በሚል እርስ በርስ እየተጋጨ ነው ጉዞው።
ከንአን በጣም ራቀች። እንዴት አትርቅ። ግብፅ እና ከንአን ምን ያህል ይራራቃሉ ግን?
ለማንኛውም ስለ ቃል ኪዳኗ ምድር ትንሽ ልበል። ምን አይነት ታምረኛ ምድር ብትሆን ነው፣ ማርና ወተት የምታፈልቀው?
ከንአን ከሚለው ስም ጋር የሚገናኙ የእብራይስጥ ቃላት ብዙ ትርጉም አላቸው። ሃምራዊ ወይም ራስን ዝቅ ማድረግ ወይም የላቀ የቡድን አንድነትን ለመፍጠር ሲባል ግላዊ መሻቶችንና ፍላጎቶችን መተው ማለት ይሆናል። ሃምራዊ ቀለም ከሃብት ንግስና ልእልና ጋር የተያያዘ ነበር። ብርቅና ውድ በመሆኑ።
እንዴት ሆኖ ነው ግን አንድ ቃል ከሁለት ተቃራኒ ነገሮች ጋር ሊያያዝ የቻለው? ከሃምራዊ (ንግስና ልእልና ሃብት) እና ራስን ዝቅ ከማድረግ ጋር።
ወይስ አንደኛው መንገድ ሌላኛው መዳረሻ ሆኖ ነው? ሶስተኛው አማራጭ ሁለቱን ቀላቅሎ እንዳስቀመጠው፣ ለላቀ የቡድን አንድነት ሲባል የግል መሻትን መተው። ራስን ዝቅ በማድረግ ንግስና ልእልና ከፍታ ላይ መድረስ አይነት።
ከንአን ስትደርስ ምን ታገኛለህ? ማርና ወተት የሚያፈልቅ ምድር፣ ልእልና፣ ንግስና። ከንአን ለመድረስ ምን ማድረግ አለብህ? ራስህን ዝቅ ማድረግ፣ የግል መሻትህን መተው አለብህ።
ራስህን ዝቅ ማድረግ የሞት መንገድ አይደለምን? ራሱን የተወ ራሱን ዝቅ ያደረገ ሰው ተረጋግጦ አይሞትም እንዴ? ማንም እየመጣ አይረግጠውም እንዴ? ለመኖር ብሎም ልኡል ለመሆን ራስን ከፍ ማድረግ፣ ራስን ማስቀደም፣ በየቀኑ ከፍታ ማከማቸት አያስፈልግም እንዴ? ራሱን የተው ሰው በርሃብ አይሞትም እንዴ?
ቀይ ባህርን ተሻግረው፣ በበርሃ መና እየበሉ፣ በደመና ተጠልለው አዩት። ግን ደግሞ ከመከራ ጋር ተጋብተው መኖር ናፈቃቸው። ደም ደም፣ እንባ እንባ፣ ጅራፍ ጅራፍ የሚል ምስር ወጥ፣ ዱባ ወጥ ናፈቃቸው።
ምንም እንኳ ዱባና ምስር ወጥ ከመና ባይበልጡም፣ የወጣባቸው መከራ ግን ከመና ያስበልጣቸዋል ብለው አመኑ። ስለ ራሳቸው እያሰቡ፣ ብትነካኝ አለቅህምን እየፎከሩት እየሸለሉት እየተራመዱት እየተናገሩት፣ እየተገዳደሉ እየተነጣጠቁና እየተሰራረቁ፣ እያንዳንዱ ራሱን እየተከላከለ ሌላውን እያስፈራ፣ እየፈራ፣ ቅኔ እየተቀኘ፣ ቅርፅ እየያዘ፣ እየተወጣጠረ ወደ ከንአን ነጎዱ።
እረ እነዚህን ሰዎች ማን በነገራቸው? የከንአን መንገድ እኮ እርሱ አይደለም። ይህኛው የከንአን መንገድ ሳይሆን የግብፅ መንገድ ነው። ከንአን እኮ ያን ያህል እሩቅ አይደለም። ቅርብ ነው። መንገድ ተሳስተው ባከኑ። ከአርባ ምናምን አመት ጉዞ በኋላ ከንአን ደርሰዋል የሚሉ አሉ። ሊሆን ይችላል።
የደረሱ ይኖራሉ። ግን ብዙው ሰው ገና የደረሰ አልመሰለኝም። ቢያንስ እንኳን እኔ አሁንም በመንገድ ላይ መሆኔን አውቃለሁ። ይልቅስ መንገድ ላይ ቆሜ ካንተ ጋር ሳወራ የሰበሰብኩትን መና እንዳይሰርቁኝ።

________________________________________________


                 ገበያውን የሚመራው መንፈስ ምንድነው የተወጋው?
                           መላኩ ብርሃኑ             መንግስት መኪና አሽከርካሪዎችን የራሳችሁ ጉዳይ ሊል ጫፍ ላይ ደርሷል። በነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ምክንያት መንግስት ለድጎማ በማወጣው ወጪ 10 ቢሊዮን ብር ከስሬያለሁ እያለ ነው። ይህ መረጃ በርግጥም እውነት ከሆነ ከባድ ነው። ነዳጅ አምራች ሃገራት እንኳን የኢትዮጵያን ያህል በረከሰ ዋጋ ነዳጅ እንደማያቀርቡ ሲነገር ሰምተን እናውቃለን። በዚህ መጠን ኪሳራ ማስተናገድ ከጀመርን ግን የሆነ ቦታ ቆም ማለት ይኖርብናል።
በርግጥ ከድጡ ወደማጡ እየተንደረደረ ባለው ኢኮኖሚያችን ላይ ይህ ሲደመር ኑሯችንን ከባድ ያደርገዋል። አዳዲስና ብዙሃኑን የማይጎዱ መንገዶችን አጥብቆ ማሰብ ይጠይቅ ይሆናል። መፍትሄ ማመንጨት በመንግስት ሃላፊነት ላይ የተቀመጡ ሰዎች ስራ ነው። ይህንን ካልሰሩ ታዲያ የማንን ጎፈሬ ያበጥራሉ?
እኔን የሚያሳስበኝ ግን በከፋ መልኩ ወደኛ እየመጣ ያለው ከባድ የኑሮ ጫና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ እኩል የሚያሳስብ ነገር ሆኖ አለመገኘቱ ነው። የሆነ ክፍል ቋጥኝ ቢወድቅበት እንኳን ቅም የማይለው፣ ‘ኪሱ ጢቅ ብሎ የሞላ’ አይነት ነው። ብዙሃኑ ደግሞ ኪሱ ጭራሽ ሳንቲም ለመያዝ እንኳን ጥንካሬ አጥቶ የሳሳ ሆኗል። ሃብታሙ የበለጠ ሃብታም እየሆነ ሲሄድ፣ ደሃው የበለጠ ደሃ እየሆነ ነው።
መንግስት በቅርብ ቀን የነዳጅ ዋጋን ምናልባት በሊትር ከ47 እስከ 52 ብር ሊያደርሰው ይችላል። አንድ ሊትር በአንድ ዶላር ከሆነ ነው እሱም። በጥቁር ገበያ እንዳታሰሉት። እንዲያ ከሆነ ‘ኦልሬዲ’ 70 ብር ገብቷል። የኛ ገበያ ‘ክሬዚነት’ እዚህ ላይ ፍጥጥ ብሏል። የአዲስ አበባ መንገዶች በመኪኖች እየሞሉ ከቦታ ቦታ ለመዘዋወር ‘መንገድ ላይ የመኖር’ ያህል አሰልቺ ሆኗል። በተለይ ጠዋት እስከ 3 ተኩል፣ ከሰዓት ከ9 ሰዓት ጀምሮ እና ማታ ከ2 ሰዓት ጀምሮ መንገዶቻችን ‘በመኪና ጢቅ’ ይላሉ። ነዳጅ የሚያልቀው ጉዳይ በመሙላት ሳይሆን መንገድ ላይ በመንፏቀቅ ነው። አንዱ ብክነት እዚህ ላይ ነው።
የመኪና መብዛት ብቻ ሳይሆን ዋጋውስ ምን እየሆነ ነው?.
..በዓለም አቀፍ ደረጃ ነዳጅ ዋጋው ሲጨምር፣ በብዙ ሃገራት የመኪና ዋጋ ቀንሷል። በተቃራኒው ግን በኢትዮጵያ የመኪና ዋጋ በየቀኑ ሊባል በሚችል መልኩ እየጨመረ ነው። መንግስት መኪና ማስገባትን ላለማበረታታት ብሎ ቀረጡን ከፍ ቢያደርገውም፣ ሰዉ ግን አሁንም ነዳጅ በተወደደበት ጊዜ እንኳን ዋጋው ጣራ የወጣ፣ ነዳጅ በሊታ ባለከባድ ሞተር መኪና እንደቆሎ መሸመቱን አልተወም።
ለምን እንደሆነ ይገባችኋል ግን ? ....እኔ ግራ ገብቶኛል። ለነገሩ መንግስትም የመኪና ማቆሚያ ሰርቶ መሸቀሉን ሳይሆን አይቀርም እንደ ትልቅ ስኬት እየቆጠረ ያለው፡፡
እዚህ ሃገር ግን ስኳር ሲጠፋ የሻይ ቅጠል ዋጋ የሚወደደው ነገር...በግ ሲረክስ የቀይ ወጥ ዋጋ የሚጨምረው ነገር ምስጢሩ ምንድነው?
ገበያውን የሚመራው መንፈስ ግን ምንድነው የተወጋው?

_______________________________________________


                     የተሳሳተ
                         በእውቀቱ ስዩም

            ከምኡዝ ጋራ ከረጅም ጊዜ በሁዋላ ተገናኘን፥ ከመንገድ ዳር ካለ አንድ ካፌ በረንዳ ላይ ቁጭ ብለን አቧራና ቡና እየጠጣን አላፊ አግዳሚውን እያየን እናወራለን፥ ድንገት አንዲት ሴት ብቅ አለችና ወደ ምኡዝ እያየች “አንተ አለህ?” ብላ ባድናቆት ጮኸች፤ ሁለት እጆቿን በሰፊው ዘርግታ እቅፍፍፍፍፍ አደረገችው፤ ቀጥላ እኔንም እቅፍ ታደርገኛለች ብዬ ተስፋ አደረግሁ፥
ከእቅፉ ወጣችና እንደገና እጅጌዋን እስከ ክርኗ ሰብስባ ባዲስ ጉልበት ተጠመጠመችበት፤ ወረፋው እስኪደርሰኝ ከኪሴ ዶዶራንት አውጥቼ ብብቴ ላይ ነፋሁ፤ አሁንም እንደገና ተቃቀፉ፤ ስራ ከምፈታ ብዬ ከግራ ብብቴ ላይ በላብና በዶዶራንት የፋፉ ሁለት የጸጉር ዘለላዎችን ነቀልሁ፤ በመጨረሻ ፈገግታዬን እንደ ደጋን ወጥሬ፥ እጄን እንደ በረኛ ዘርግቼ ተጠጋሁዋት። ልጂቱ ግን ጸጉር የከበደውን ራሷን ዘንበል አድርጋ ሰላምታ አቀረበችልኝና ሄደች! በቴስታ ብትነቀንቀኝ ራሱ እንደዚያ አያመኝም! ላለማፈር በዙርያዬ ባለው ማህበረሰብ ፊት የምንጠራራ መስዬ ለመታየት ሞከርኩ፥
“የት ነው የምንተዋወቁት?” አልኩት
“ከምታውቀው ሰው ጋራ ተምታትቸባት መሰለኝ” አለኝ፥
“እንደ ሀረግ እሬሳ የተጠመጠመችብህ ሳታውቅህ ነው?
“ምን ታረገዋለህ፥ እድለኛ ከሆንክ ለሌላው የተላከ እቅፍ ይደርስሀል፥ እድለቢስ ከሆንክ ደግሞ ለሌላው የተወረወረ ድንጋይ ይፈነክትሀል! እድል ነው”
ከጥቂት ቀናት በፊት የደረሰብኝ ነገር ትዝ አለኝ፥
የሆነ ቦታ ደወልኩ፥ የደወልኩት ስልክ አይነሳም፤
“ውድ አቤል! ከአሜሪካ የተላከልህ እቃ ስላለ መልሰህ ደውልልኝ” የሚል መልክት ጽፌ ሰደድሁ፤
ከጥቂት ጊዜ በሁዋላ ስልኩ ተደወለልኝ::
“ቁጥር ተሳስተሀል” የሚል የሴት ድምጽ መጣ፤
ይቅርታ ጠይቄ ስልኩን ዘጋሁት፤ ጥቂት ቆይቼ ግን መልሼ ደወልኩ፤
“ሄሎ"
“ተሳስተሀል አልኩህኮ” አለቺኝ ሴቲቱ፥
“ገባኝ”
“ከገባህ ምን አስደወለህ?”
“ምናልባት ለምክንያት የሆናል የተሳሳትሁት የኔ እመቤት! ደሞ ማን ያውቃል፥ የተሳሳተ ቁጥር የተሳካ ትዳር መሰረት ሊሆን ይችላል”
“ተው ባክህ”
“ቁንጅናዬን ይንሳኝ!”
“ሆሆ። ለመሆኑ ማን ልበል?;
“በውቄ እባላለሁ”
“ለማቆላመጥ እስኪያበቃኝ ሙሉ ስምህን ብታስተዋውቀኝ”
“በእውቀቱ"
“እሺ አቶ በወቅቱ ፤ እስቲ ስለ ራስህ ንገረኝ”
“መልኬ በጠይም እና በቀይ መሀል ነው-ቀይም!”
“ቁመትህ? ስንት ሜትር ነው?”
“እሱን በሚሊሜትር ብንነጋገር ደስ ይለኛል የኔ እመቤት”
“ሄሎ፤ የስልኩ ድምጽ ይቆራረጣል ፥ የት ሆነህ ነው?”
“ቤንዚን እያስቀዳሁ ነው”
“ለመኪናህ?”
“በምን እድሌ! ለፋኖሴ ነው እንጂ”
የተራዘመ ዝምታ፥
“ስምሽ ማን ነው” አልኩዋት በመጨረሻ፥
“ጄሪ”
“ለማቆላመጥ እስከደርስ ሙሉ ስምሽን ብትነግሪኝ”
“ማን ይመስልሀል”
“ጀሪካን?”
ስልኩ ተዘጋ::
ምን አናደዳት? ባሁኑ ጊዜ በያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ቤት ውስጥ ከጀሪካን የተሻለ ፋይዳ ያለው ነገር እንደሌለ ባይገለጥላት ይሆናል፡፡
መልሼ ለመደወል ተሰናዳሁ፡፡

_________________________________


                          ምን እየሆነ ነው?
                               ጌታሁን ሔራሞ

            ደቡብ አፍሪካ እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ መባቻ ከአፓርታይድ አገዛዝ ነፃ በወጣችበት ዋዜማ ነጮቹ የአፓርታይድ ጠንሳሾች እነማንዴላ ለ27 ዓመታት ያህል የታሰሩበትን የሮበን ደሴትን ወደ መካነ እንስሳት(Zoo) በመቀየር ትውስታውን ለመደምሰስ ሙከራ አድርገው ነበር። የነጮቹን ሴራ ቀድመው በተረዱ የደቡብ አፍሪካ ጥቁር የአካባቢ ዲዛይነሮችና አርክትክቶች ጥረት ግን የሮበን ደሴት ትውስታ ሳይሰደድ፣ የጥቁሮቹ  የነፃነት ትግል መዘከሪያ ሙዚየም ሊሆን በቃ። ዩኔስኮም እ.ኤ.አ. በ1999 የሮበን ደሴት “World Heritage Site for its importance to South Africa’s political history and development of a democratic society” እንደሆነች በመዝገቡ ከትቦ ለዓለም አሳወቀ።
ሰሞኑን በተለይም የኢትዮጵያ ሠዓሊያን፣ የታሪክ ምሁራንና አርክቴክቶች በሁለት በከተማችን እየተፈፀሙ ባሉ ሁኔታዎች ድምፃቸውን እያሰሙ ነው። የመጀመሪያው ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረውና በ1887 ዓ.ም. ተመስርቶ በቅርስነት የተመዘገበው በተለምዶ ‹‹ሰይጣን ቤት›› ይባል የነበረው የጥበብ ቤት በአሁኑ ወቅት ለሱቅነት መሸንሸኑ ነው። ሁለተኛው ታላቁ ብሔራዊ ሙዚየም ለቢሮ አገልግሎት ሊሸነሸን እንደሆነ መነገሩ ነው። ነጮቹ “What is going on!” እንዲሉ፣ እኛም “ምን እየሆነ ነው?” ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን። ያለፈውን የታሪክ አሻራ ደብዛውን አጥፍቶ በምትኩ የራስን አሻራ ማስቀመጥ? እንደ ደቡብ አፍሪካ ነጮች የትናንት ትውስታን ገርስሶ አዲስ ትውስታን የመትከል እርምጃ? የምር አዲስ አበባ ውስጥ ለሱቅና ለቢሮ የሚሆን ቦታ ጠፍቶ ነው...እነዚህ ቅርሶች ኢላማ የሆኑት? ይህ ቅርሶቹን ከማፈራረስ የማይተናነስ ድፍረትና እብሪት የተጠናወተበት እርምጃ ነው።
በነገራችን ላይ ሙዚየሞች በሀገር ግንባታ (Nation building) ላይ ስላላቸው አይተኬ ሚና  በቅርቡ ሰፋ ያለ ፅሁፍ አስነብባችኋለሁ። ግን ግን...መንግስት ሀገሪቱ በየአቅጣጫው በሰላም መደፍረስና በኢኮኖሚ ድቀት ተወጥራ ባለችበት ወቅት ሌሎች ተጨማሪ የውጥረት አጀንዳዎችን እያመረተ ወደ ሕዝቡ የሚልከው ለምን ይሆን? የሕዝብን ንቃተ ሕሊና ዝቅ አድርጎ መገመትና ምክሩን መናቅ በሂደት ዋጋ ማስከፈሉ የማይቀር ስለመሆኑ ከወዲሁ በደማቁ ማስመር ግድ ይላል። ሌላው ይቅርና እንዲመራው የመረጠውን ሕዝብ በማስከፋትና በማበሳጨት የብልፅግናን መንግስት የሚመስል በዓለም ላይ ይኖር ይሆን?

___________________________________________

                 የማርያም መንገድ
                      አበረ አያሌው


            አታውቁም እናንተ…
ከሷ የሚመዘዝ - የኑሮ ጠመኔ፥
ስንት ምልክቷን - እንዳስቀረ በኔ፤
እንከን የሚሸሸው - ቀና፥ ቀና ኑሮ - ከሩቁ ሲጠቅሳት፥
እኔን፥ እኔን ብላ - ስንት እራፊ ዘመን - እንዳለፈች በ’ሳት።
አታውቁም እናንተ…
ጫንቃዋ ላይ ጥዬ - መዝገብ ሙሉ ቀንበር፥
ላሸሼ ገዳሜ - ክጃት እንደነበር፤
የከዳኋት ጊዜ - የጎረቤት አሽሙር - ሳይበርዳት፥ ሳይሞቃት፥
እኔን ስትጠብቅ - ስንት’ዜ ‘ንዳለፋት - የ’ናቷ ምርቃት።
አታውቁም እናንተ…
ከትዝታዬ ጋር - ስለሷ ሳወጋ፥
እልፍ ቀን ቢጨልም - እልፍ ሌት ቢነጋ፤
ልክ እንደኼደችው - ቀርታ አት’ቀርም - ትመጣለች አኹን፤
ከዘገየች እንኳን - እያዘገመች ነው - ተዉ ሟርታችኹን።

_________________________________________________


                          "ሰለባዎች ጥሩ አስተዳዳሪዎች አይሆኑም?"
                               ኦሃድ ቤንዓሚ

            የኢትዮጵያን ፖለቲካ ከብሔር ብሔረሰብ ተኮርነት ወደ ኢትዮጵያ ተኮርነት የመለወጥ ሂደት የተሻለው አማራጭ ነው፤ የኢሕአዴግ ፖለቲካ ትውልድ ይህን ለመቀበልና ከብሔር ውጭ ለማሰብ እንደሚቸገር ግልጽ ነው፤ ነገር ግን ፍጹም የማይለወጥ ነገር የለም፤ እና እርስ በርሳችን ከመበላላታችን በፊት ቆም ብለን ማሰብ አለብን፤ ትግራይ ውስጥ ከ500 ሺህ በላይ ዜጎቻችን ያለቁት በዚህ እኩይ የማንነት ተኮር ፍልስፍና ምክንያት መሆኑን ለብሔረተኞች ማስረዳት ከባድ ነው፤ የባሰውኑ ደግሞ ሌሎቻችን እልቂቱ የክብደቱን ያክል ድንጋጤ ያልፈጠረብን ፖሊሲው ያመጣብንን ግርዶሽ ገልጠን ማየት በአለመቻላችን ምክንያት ወያኔንና የትግራይን ህዝብ አንድ አድርገን ማየት ስለለመድን ነው፡፡ (የፖሊሲው ችግር ነው)
ለጠባብ ብሔርተኞች፣ ችግሩ አጎራባቹ ክልል እንጂ የወያኔ ፍልስፍና አይደለም፤ ነገር ግን ዜጎች ተጎረባብተው በመቶ የሚቆጠሩ ክፍለዘመኖችን አስቆጥረዋል፤ የተባሉት ግን ይህ ፖሊሲ እግር አውጥቶ መሄድ ከጀመረ በኋላ ነው፡፡ መንግስትም ይህን የቤት ሥራ ቢጀምረው ጥሩ ነው፤ አራት አመት ቀላል ጊዜ አይደለም፤ እስካሁን የተጀመረ ነገር የለም፡፡
አገርን የማስተዳደርን እድል ማግኘት እንዴት መስተዳደር ትፈልግ እንደነበረ የምታስተዳድርበትና ለዚህም መሰጠትህን የምታስመሰክርበት አጋጣሚ ነው። አለበለዚያ መዳን ከሌላ መምጣቱ አይቀርም፡፡
የማንነት ተኮር ፖለቲካ ከጥቅሙ አደጋው ይከፋል የሚል እምነት ያለባቸውም የብሔረተኛነት ጽንፈኝነት አቀንቃኞች ለዘመናት የተዘራባቸውን የጥላቻ መርዝ መረዳት ያስፈልጋል፤ ምክንያቱም እነሱ ራሳቸው ሰለባ መሆናቸውን አያውቁትም፤ ችግር ነው፡፡
ሰለባዎች ጥሩ አስተዳዳሪዎች አይሆኑም የሚሉ አሉ፤ ይህንን የሚቃወሙም አሉ፤ ሁሉም እንደ አመለካከትህ ነው፡፡ አሁን ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አካሄድ ልብ የሚያሳርፍ አይደለም፤ ወደ ሌላ ማንነት ተኮር ቀውስ ልናመራና ሌላ ከሰሜኑ የበለጠ አደጋ አንዣቦብን ሊሆን ይችላል፤ መዘውሩ ያለው በመሪው እጅ ነው፡፡
የትግራይ አይነት ቀውስ እንዲደገም የሚያደርግ አካሄድ የተለያዩ ሰበቦችንና የታሪክ ጥቅሻዎችን እየተመገበ ነው፤ ኃላፊነቱ በገዢው ኃይል መዳፍ ነው፤ በጊዜ ትክክለኛውን ማስተካከያ መውሰዱ መልካም ነው፡፡

Read 672 times