Print this page
Saturday, 23 April 2022 13:57

አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ወሳኝ የቅድመ ዝግጅት ተግባራትን ማከናወኑን አስታወቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

  የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን የቅድመ ዝግጅት ተግባራትን ማከናወኑን ያስታወቀ ሲሆን የምክክር ሂደቱ በአራት ምዕራፎች ተከፋፍሎ የሚካሄድ እንደሚሆን ተቁሟል።
የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ባለፈው ሐሙስ ሚያዚያ 13 ለመጀመሪያ ጊዜ ከመገናኛ ብዙሃን ተቋማት የሥራ ሃላፊዎችና ጋዜጠኞች ጋር የግማሽ ቀን ምክክር ባከናወነበት ወቅት በኮሚሽኑ በኩል እስካሁን የተከናወኑና  በቀጣይ የሚከናወኑ ተግባራት በዝርዝር ቀርበዋል።
በ11 አባል ኮሚሽነሮች የተዋቀረው ኮሚሽኑ፤ እስካሁን ባሉት ጊዜያት በዋናነት የቅድመ ዝግጅት ተግባራት መከናወናቸውን ዋና ኮሚሽነሩ ፕ/ር መስፍን አርአያ ያስታወቁ ሲሆን ኮሚሽኑ ስራውን የጀመረው የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ፣ የዝግጅት ምዕራፍ፣ የምክክር ሂደት ምዕራፍና የትግበራ ምዕራፍ በሚሉ አራት ምዕራፎች ከፋፍሎ መሆኑን አስረድተዋል።
እስካሁን በነበረው የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍም፣ የኮሚሽን አባላት ትውውቅ መደረጉን፣ ስለ አዋጁ የግንዛቤ ማስጨበጭያ መድረክ መርሃ ግብር መካሄዱን አመቺ የስራ አካባቢ የመፍጠር፣ የድጋፍ ሰራተኞች ምደባ መከናወኑን፣ ከሃይማኖት አባቶች ጋር ምክክርና የፀሎት ስነ-ስርዓት መካሄዱን እንዲሁም ባለፈው ሃሙስ የተካሄደው ከሚዲያ ተቋማት አመራሮችና ጋዜጠኞች ጋር የትውውቅና ምክክር መድረክ ተጠቃሽ ሆነዋል።
በቀጣይ የሚኖረው የዝግጅት ወቅት ደግሞ የክልል ጽ/ቤቶችን ማደራጀት፣ አዋጁ የሚተገበርባቸውና የውስጥ አሰራሮችን የሚወስኑ መመሪያዎችን ማውጣት፣ የምክክር አጀንዳዎችን ማሰባሰብ፣ የምክክሩ ተሳታፊዎች የሚመለመሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ የአጋርነትና ሃብት የማሰባሰብ ተግባራት እንዲሁም የሕዝብ ግንኙነት ስራዎች የሚሰሩበት ምዕራፍ ይሆናል ተብሏል።
በሶስተኛው ምዕራፍ፣ የምክክር ሂደቱን ማስጀመርና ማከናወን ሲሆን፤ በአራተኛው ምዕራፍ ኮሚሽኑ በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሰረት በብሄራዊ ምክክር ሂደቱ ወቅት የተገኙ ምክረ ሃሳቦች የሚተገበሩበትና ይህንንም ኮሚሽኑ የሚከታተልበት  ይሆናል።
በምክክር ሂደቱ የተገኙ ምክረ ሃሳቦች በሁሉም ወገኖች ተግባራዊ መሆናቸውን የመከታተያ ስርዓት የመዘርጋት ሃላፊነትም የብሄራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሲሆን መንግስት የተገኙ ግኝቶችን ተግባር ላይ እንዲያውል  ግፊት ከማድረግ ባለፈ ስለመተግበራቸው ጠንካራ ክትትል እንደሚያደርግ ተጠቁሟል።
ከብሄራዊ ምክክሩ አላማዎች መካከልም በቀጣይ መተማመን የሰፈነበት አዲስ የመንግስት ስርዓት መገንባት፣ መተማመን የሰፈነበት ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን እውን ማድረግ፣ ለዘመናት ሲንከባለሉ ዛሬ ላይ የደረሱ ችግሮችን በፖለቲካዊ ውይይት መፍታትና ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህልን ማዳበር ይገኙባቸዋል።

Read 11716 times