Saturday, 23 April 2022 14:07

የዋጋ ንረቱ የማይቀመስ ያደረገው የበዓል ገበያ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(1 Vote)

  “የዋጋ ማሻቀቡ የበዓሉን መንፈስ አጥፍቶብናል”
                                     
             የብሔራዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ወቅታዊ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ባለፈው መጋቢት ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበቱ 34 በመቶ ሲደርስ፣ የምግብና ምግብ ነክ ሸቀጦች የዋጋ ግሽበት ደግሞ 43 በመቶ የደረሰ ሲሆን፤ ይህም በአገሪቱ እስካሁን ታይቶ የማይታወቅ ነው ተብሏል፡፡
የትንሳኤን በዓልና ከቀናት በኋላ  የሚከበረውን የረመዳን ጾም ፍቺ በዓል ምክንያት በማድረግ፣ በሸቀጦች ላይ የተደረገው የዋጋ ጭማሪ ለብዙዎች አስደንጋጭ ሆኗል፡፡ በተዘዋወርንባቸው የገበያ ስፍራዎችም የዋጋው መናር የሸማቹን አቅም የሚፈትንና ክፉኛ የሚያማርር መሆኑን ለመታዘብ ችለናል።
ከአዲስ አበባ ከተማ ትላልቁ ገበያዎች አንዱ በሆነው የሾላ ገበያ ባደረግነው ቅኝት፤ በሁሉም የፍጆታ ዕቃዎች ላይ በተለይም ለበዓሉ አስፈላጊ በሆኑ የምግብ ሸቀጦች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ መደረጉን ተመልክተናል፡፡ በሾላ ገበያ አንድ ዶሮ  ከ850 ብር-1 ሺ ብር እየተሸጠ ነው። የቅቤ ዋጋ እንደ ቅቤው ሁኔታ (ለጋ እና የበሰለ በሚል)  የሚለያይ ቢሆንም፣ በአማካይ በኪሎ 850 ብር ይሸጣል። አንድ ኪሎ ሽንኩርት ከ42-45 ብር ሲሸጥ አይተናል። በገበያው ስፍራ ያገኘናቸው ሸማቾች፣ የዋጋ ንረቱ የበዓል መንፈሱን እንዳጠፋባቸው ነግረውናል፡፡ አብዛኞዎቹ  በዋጋ ጭማሪው ሲማረሩና ገበያውና አቅማቸው አልመጣጠን ብሏቸው ግራ ሲጋቡ ተመልክተናል፡፡
ከልደታ ኮንዶሚኒየም ሾላ ገበያ ለበዓል ሽመታ መጥተው ያገኘናቸው ጎረቤታሞቹ ወ/ሮ ገነት ታመነ እና ወ/ሮ ስናፍቅሽ ተስፋዬ እንደነገሩን፤ የበዓል ገበያ ዋጋ ከጠበቁት በላይ በእጅጉ መናሩን በመግለጽ፣ ለመግዛት አስበው የመጡትና የገበያው ዋጋ ባለመመጣጠኑ፣ ግማሹን ትተው ለመመለስ ተገድደዋል። የአንድ ኪሎ ቅቤ ዋጋ አምና በተመሳሳይ ጊዜ ከነበረው በእጥፍ መጨመሩ እንዳስደነገጣቸውና ሁለት ኪሎ ለመግዛት አቅደው አንድ ኪሎ ብቻ መግዛታቸውን ገልፀዋል። “ሆድ ያው ለአንድ ቀን ብቻ አይደለም፡፡ ምነው ባይበላስ ቢቀር”  ሲሉ ተማረዋል ገበያተኞቹ፣ እነ ወ/ሮ ገነት፡፡
እዚሁ ሾላ ገበያ ውስጥ ከልጃቸው ጋር በሸመታ ላይ ያገኘናቸው ወ/ሮ ትዕግስት ደረጀ፣ የበዓል ገበያው የማይቀመስ መሆኑንና ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን ነግረውናል፡፡ “በደህና ጊዜ የገዛሁትን የልብስ ማጠቢያ ማሽኔን” ለመሸጥ የተገደድኩት ልጆቼን በበዓል ምድር ከሰው በታች እንዳላደርጋቸው ነበር፤ ነገር ግን ገበያው በጣም ያስፈራል፤ አንድ ኪሎ ቅቤ 850 እና 900 ብር እየተሸጠ እንዴት ሊከረም ነው ወ/ሮ ትዕግስት።
በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ የከብት ገበያዎች መካከል ትልቁ ወደ ሆነው የካራ ገበያ አመራን፡፡ ገበያው ለቁጥር የሚታክቱ ከጠቦት እስከ ሙክት፣ ከወይፈን እስከ ደለበ በሬ የሚሸመትበት ስፍራ ነው፡፡ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ወደዚህ ስፍራ የሚጋዙት የቁም ከብቶች ለቁጥር የሚታክቱ ናቸው፡፡
ወደ በግ ገበያ ተጠጋን። ሸማችና ነጋዴ የጎሪጥ ይተያያል፡፡ ሸማቹ የሚፈልገውን በግ ነካክቶና በአይኑ መዝኖ ነጋዴውን ዋጋ ይጠይቀዋል፡፡ ነጋዴው ዋጋውን አጠር አድርጎ ይናገራል፡፡ ሙሉ ዋጋ አይጠራም ወይም ሲጠራ አልሰማንም፡፡ አስር አሊያም አስራ አንድ ይላል-ነጋዴው፡፡ ሸማች የተጠራለት ዋጋ ይገባዋል፡፡ አስር ሺ ወይም አስር ሺ አንድ መቶ ማለት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ የሸማቹን ምላሽ ማየት ወይም መስማት ፈገግ ሊያሰኝም ያችላል፡፡ “ሰዓቱን ነው” ይላል አንዳንድ ሸማች በቀልድ። ነጋዴው ኮስተር ብሎ ፊቱን ወደ ሌላ ሸማች ይመልሳል። ተመሳሳይ  ነው ጥያቄና  ምላሹ። 95 እና አስር ተደጋግመው የሚጠሩ ቁጥሮች ናቸው፡፡ “በጉ እስከ ስንት የተማረ ነው?” ሲሉም ይቀልዳሉ ሸማቾች፡፡ የተጠራውን ዋጋ በጥቂቱ አስቀንሰው በጉን ሸምተው መኪናቸው ላይ ጭነው የሚሄዱ ሸማቾችም አልጠፉም፡፡ ከጥቂት  ዓመታት በፊት በሬ ይገዛበት በነበረ ዋጋ አንዲት ጠቦት ቢጤ በግ መግዛት በርግጥም ያስደነግጣል፡፡
በቡድን ወደ ገበያው ከመጡት ሸማቾች መካከል አንደኛውን ተጠግቼ” ገበያው እንዴት ነው?” ብዬ ጠየቅኩት፡፡ “ኧረ ጣራ  ነክቷል”፡፡
“እንደው ገንዘቡን ሲጠሩት አይሰቀጥጣቸውም” መልሰው እኔን የሚጠይቁኝም ነበሩ፡፡ “አሁን ለዚያ ዳልቻ በሬ 70 ሺ ብር ይጠየቃል?” በጣም ተገርመዋል- በሰሙት የበሬ ዋጋ፡፡ “ታዲያ ምን ልታደርጉ ነው? ጠየኳቸው- ሰውየውን። “ምን እናደርጋለን ያው ትተን እንሄዳለን እንጂ፡፡ እንግዲህ ተመልሰን ለቅርጫው ሰው ጨማምረን እንመለሳለን እንጂ ምን እናደርጋለን።” አሉኝ ትክዝ ብለው። በቄራውና በአዲሱ ገበያው የከብት ገበያም ተመሳሳይ ነገር እንዳለ መስማታቸውንም ነገሩኝ፡፡
ወደ ታላቁ የገበያ ስፍራ መርካቶ አመራን። “እምዬ መርካቶ” ይሏታል። የመርካቶ ደንበኞች። ሁሉ እንደ አቅሙ የሚሸምትባት፣ሁሉ ቀምሶ የሚያድርባት እናት ጓዳ ናት ይላሉ- የሚያውቋት፡፡
በቀጥታ ያመራሁት ወደ ዶሮና ሽንኩርት ተራ ነው፡፡ ዶሮና ሽንኩርት በመርካቶ ጎን ለጎን ይሸጣሉ፡፡ የገበያ ግርግሩ ከተዘናጉ ለበዓል ሸመታ ይዘውት የመጡትን ገንዘብ የኪስ አውላቂዎች ሲሳይ ያደርጋል፡፡ ጥንቃቄ ያሻል።
በመርካቶ ገበያ የሰማሁት የዶሮ ዋጋ ከሾላ ገበያው ጋር ሲነጻጸር በእጅጉ ይቀንሳል። ከ500-650 ባለው ዋጋ ማግኘት ይቻላል-አንድ ዶሮ። የቅቤ ዋጋም ከሾላው በ150 ብር ይቀንሳል። ከ650-700 ባለው ዋጋ ሲሸጥ ተመልክተናል። ሽንኩርት መርካቶ ላይ በኪሎ 38 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ ሌላው በመርካቶ ገበያ ውስጥ  ያየሁት በጎ ነገር ሸማቹ አቅሙ በሚፈቅደው መጠን ለመሸመት መቻሉ ነው። ሩብ ኪሎ ቅቤ ተመዝኖ ለሸማች የሚሸጠው መርካቶ ገበያ ውስጥ ነው፡፡ ሴት ዶሮዎች ከ300-350 ብር ሲሸጡም አይተናል፡፡ ከወቅቱ ዋጋ አንጻር “እውነትም እምዬ መርካቶ” አልንና ያሰኛል ገበያው።


Read 10925 times