Saturday, 23 April 2022 14:13

ዳግም ውዝግብ ያስነሳው በእስራኤል የዴር ሱልጣን ገዳም

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    • ግብፃዊያን ከጥንት ጀምሮ ነው የኢትዮጵያን ይዞታዎች መጋፋት የጀመሩት
          • በእስራኤል ያሉ ዲፕሎማቶች ጉዳዩን በአንክሮ ሊከታተሉት ይገባል
          • አፄ ዮሐንስ ለዴር ሱልጣን ገዳም ትልቅ ባለውለታ ናቸው


          የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፣ በእስራኤል አገር ካሏት ይዞታዎችና ገዳማት አንዱ ታላቁ የዴር ሱልጣን ገዳም ነው፡፡ በዚህ ገዳም ላይ የግብጽ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያንም የይገባኛል ጥያቄ የምታነሳ ሲሆን በዚህ ምክንያትም በየጊዜው ውዝግቦች የሚያስተናግድ ስፍራ ሆኗል፡፡ ከሰሞኑም ግብጻዊያን የኢትዮጵያ ስለመሆኑ በቂ ማስረጃዎች ባሉት የዴር ሱልጣን ገዳም ላይ የሃገራቸውን ሠንደቅ ዓላማ ቀለም በመቀባት የራሳቸው ለማስመሰል ያደረጉት ሙከራ ውዝግብ ፈጥሯል፡፡
በገዳሙ ዙሪያ የሰሞኑን ጨምሮ በየጊዜው በሚፈጠሩት ውዝግቦችና በገዳሙ ይዞታ ጉዳይ ላይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ የትንሳኤ ጉባኤ ማተሚያ ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅና የአብያተ ክርስቲያናት ገዳማት ጥናት ባለሙያ የሆኑት  ቀሲስ ሰለሞን ቶልቻን የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ አነጋግሯቸዋል፡፡ እነሆ፡-


                   ከሰሞኑ ኢየሩሳሌም በሚገኘው የዴር  ሱልጣን ገዳም ላይ የተከሰተው ምንድን ነው? እስቲ ስለ ዴር ሱልጣን ማብራሪያ ይስጡን?
መልካም! ዴር ሱልጣን የንጉስ ቦታ ነው የሚባለው፡፡ በእስራኤል ሃገር ኢየሩሳሌም ጎለጎታ ውስጥ የሚገኝ የኢትዮጵያ ገዳም ነው። ታሪካዊ መነሻውን በአጭሩ ስንመለከት፣ ከልደተ ክርስቶስ  በፊት ለንግስት ሳባ፣ ከንጉስ ሰለሞን የተሰጣት ቦታ ነው፡፡ ቦታው ከኢትዮጵያ ጋር የሚተሳሰረው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ በንግስት ሳባና በንጉስ ሰለሞን የጀመረው ታሪካዊ ግንኙነት፣ በታሪክም በባህልም በሃይማኖትም ጭምር የተሳሰረ ሆኖ ነው የዘለቀው፡፡ አብዛኛው ቤተ-እስራኤላውያን ጭምር በከፍተኛ ቁጥር ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኖረዋል፣ ትስስሩ የጠለቀ ነው፡፡ እንግዲህ ይሄ ቦታ ከልደተ ክርስቶስ በፊት ጀምሮ የኢትዮጵያ የነበረ ነው፡፡ ይሄን ታሪካዊ ግንኙነትም ዓለም የሚያውቀው ነው፡፡ መፅሐፍ ቅዱሳዊም ነው፡፡ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በሁለቱ ሃገራት መካከል የነበረው ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ግንኙነት ቀጥሏል፡፡ በየአመቱ ኢትዮጵያውያን የፋሲካ በዓልን ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም ይጓዙ ነበር፡፡ በሐዋርያት ስራ ላይ እንደተገለፀውም፤ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ወደ ኢየሩሳሌም የሄደው ያንን ግንኙነት መነሻ በማድረግ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ነው በጃንደረባው አማካይነት ክርስትና በ34 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ የገባው፡፡
የኢትዮጵያን ታሪክ በሶስት ከፍለን ነው የምንመለከተው፤ጥንታዊ፣መካከለኛና ዘመናዊ በሚል፡፡ የዴር ሱልጣን ገዳም የኢትዮጵያ ለመሆኑ ማስረጃዎች በዝርዝር የሚሻ ሰው፣ ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ፣ ታላቁ አባት፣ በቅድስት ሃገር ይዞታችን ላይ የሰነድ ማስረጃዎች አካትተው የፃፉት መፅሐፍ አለ፡፡ እስራኤላውያን በየአገሩ በተበተኑና እስራኤል በሌላ አስተዳደር ስር በነበረችባቸው ዘመን እንኳ የኢትዮጵያ ቅርሶችና ቦታዎች፣ በአባቶች መስዋዕትነት ተጠብቀው ነው የቆዩት፡፡  ዴር ሱልጣን ገዳም የኢትዮጵያውያን ስለመሆኑ ብጹዕ አቡነ ፊሊጶስ በደንብ አድርገው በማስረጃ ሰንደው ነው ያቀረቡት፡፡
እንግዲህ ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል ሲያለቅስ ይኖራል እንደሚባለው ሆኖብናል፤ ግብፃዊያን ዛሬ ብቻ ሳይሆን ከጥንት ጀምሮ ነው የኢትዮጵያን ይዞታዎች መጋፋት የጀመሩት፡፡ በርካታ ቦታዎችን በዚህ መንገድ ቀምተውናል፡፡ በብዙ አሻጥሮች ነው ይዞታዎችን በየጊዜው ሲቀሙን  የነበረው። አባቶቻችን ግን ተጋድሎ ማድረጋቸውን አላቋረጡም፡፡ ለምሳሌ አሁን እንደዋዛ በዚያው በኢየሩሳሌም የምኒልክ በር የሚባል ቦታ አለ፡፡ ይህ የሆነው በአፄ ሚኒልክ ዘመን ግብጻውያን ልክ አሁን እንደሚያደርጉት፣ የኢትዮጵያውያኑን ይዞታ ከመጋፋት አልፈው መተላለፊያ በሮችን ሁሉ እየዘጉ፣ አስክሬን ሶስት አራት ቀን እንዲቆይ ሁሉ ያደርጉ ነበር። በወቅቱ አፄ ምኒልክ የሚፈጸመውን ደባ በብዙ ጥረት ለአለም መንግስታት እያሳወቁ ባደረጉት ትግል፣ በሩ ተከፍቶ አስክሬን ወጥቶ እንዲቀበር ስላስደረጉ፣ዛሬም ድረስ እሳቸው ያስከፈቱት በር የምኒልክ በር ተብሎ ይጠራል፡፡
ሁሉም ሰው ስለ ግብፃዊያኑ ሊያውቀው የሚገባው አንድ ነገር አለ። ግብጽ አጠቃላይ ህዝቧ 100 ሚሊዮን አይሞላም፡፡ ክርስቲያኖቹ ደግሞ ከ10 በመቶ አይበልጡም፤ ነገር ግን የግብፅ ህዝበ ሙስሊሙ በዴር ሱልጣን ገዳም ይገባኛል ክርክር፣ ልክ እንደ ክርስቲያኖቹ ሲሟገቱ ነው የምንመለከተው፡፡ በብሔራዊ መንግስት ደረጃ ነው የሚያሳስባቸው እንጂ ለአንድ እምነት ብቻ ትተው አይቀመጡም። በአጠቃላይ በቅድስት ሃገር ኢየሩሳሌም ባላቸው ይዞታ በብሔራዊ ደረጃ ነው ጉዳዩን የሚመለከቱት፡፡ ወደ እኛ ሃገር ስንመጣ ግን ይሄን አንመለከትም፡፡ እርግጥ በነገስታቱ ጊዜ ከአፄ ዮሐንስ ጀምሮ ብዙ ለፍተውበታል፡፡ አፄ ዮሐንስ ለዴር ሱልጣን ገዳም ትልቅ ባለውለታ ናቸው፤ በተለይ ለደብረ ገነት ቤተክርስቲያን፡፡ አጼ ዮሐንስ በዚህ ረገድ ትልቅ ስራ የሰሩ ናቸው፡፡ ቀጥሎ ያሉ ነገስታትም ቦታውን ከማስከበር አንፃር ትልቅ ስራ ሠርተዋል፡፡ አባቶቻችን እኮ ከዚህ ኢየሩሳሌም ድረስ በእግራቸው እየሄዱ ነበር ገዳሙን የሚሳለሙት፡፡ እኔ ከዚህ ኢየሩሳሌም ድረስ ከሄዱ አባቶች መካከል ብፁዕ አቡነ ጣሊሞን አውቃቸዋለሁ፡፡ አባቶቻችን ያንን ይዞታ ለማቆየት ብዙ ዋጋ ከፍለዋል፡፡
በነገስታቱ ዘመን በምን መልኩ ነበር ይዞታው ይጠበቅ የነበረው?
እንግዲህ ነገስታቱ ፈርሃ እግዚአብሔር የነበራቸው ስለነበሩ በተለይ የቤተ ክርስቲያንን ይዞታ ያስጠብቁ ነበር፡፡ ከደርግ ወዲህ ነው የቤተ ክርስቲያን አብዛኛው ክብሯም መብቷም እየተነፈገ የመጣው፡፡ በነገስታቱ ጊዜ ቦታዎቹ ክብራቸው ተጠብቆ፣ ይዞታቸው ተረጋግጦ ነበር የዘለቀው። በቦታዎቹ ላይም በየዘመናቱ አብያተ ክርስቲያናትን ያሳንጹ ነበር፡፡ ለምሳሌ ኢያሪኮ በረሃ ላይ ዮርዳኖስ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያንን ያሳነጹት እቴጌ መነን (የቀ.አፄ ኃ/ስላሴ ባለቤት) ናቸው፡፡ በዮርዳኖስና ኢያሪኮ ላይ ያሉ ቅርሶቻችን ተጠብቀው የዘለቁት በነገስታቱ ነው፡፡ ነገስታቱና በኢየሩሳሌም ያሉ አባቶች መንፈሳዊ ግንኙነትም ከፍተኛ ቁርኝት ያለው ነበር፡፡
ከደርግ መንግስት ወዲህ ግን ያ ይዞታና ቅርስ ሃገራዊ ሃብትነቱ እየቀረ መጣ፡፡  ይሄ ነው ትልቁ ስህተት፡፡ የዴር ሱልጣን ጉዳይ የብሔራዊ ጉዳያችን ሆኖ ነበር መታየት የነበረበት፡፡ ልክ እንደ አባይ መታየት ነበረበት፡፡ ግብጾች ልክ እንደ ናይል ብሔራዊ ጉዳያቸው አድርገው ነው የሚሟገቱበት። የኛ ግን በቤተ ክርስቲያኒቷም ሆነ በመንግስት በኩል የተሠጠው ትኩረት አጥጋቢ አይደለም፡፡ የአካባቢውን ቋንቋ አውቆ፣  በደንብ በሰነድና በማስረጃ  የሚሞግት ባለሙያ መመደብ ያስፈልጋል፡፡ እርግጥ ነው  እዚያ ያሉ መነኮሳት የተማሩ ናቸው፡፡ አረብኛም ሌላም የአካባቢውን ቋንቋ የሚናገሩ፣ ቴክኖሎጂን በአግባቡ መጠቀም የሚችሉና የተለያየ ተፅዕኖ ማሳረፍ የሚችሉ ናቸው፡፡ ወደ ሃገር ውስጥ ስንመጣ ግን ጉዳዩን  በትኩረት ያለመከታተል  ችግር አለ፡፡ አሁን  እንዳጋጠመው አይነት ችግር ሲመጣ ብቻ የአንድ ሰሞን አይነት ወሬ ሆኖ ያልፋል፡፡ የዴር ሱልጣን ጉዳይ ከሃይማኖት ቦታነትም በላይ ሃገራዊ ገፅታ ያለው ነው። ስለዚህ ክርስቲያኑም፣ ሙስሊሙም ካቶሊኩም፣ ፕሮቴስታንቱም፣ ዋቄፈታውም ማናቸውም ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ፣ ቦታው የኢትዮጵያ ይዞታ እንደሆነ አውቆ፣ የባለቤትነት ስሜት ሊሰማውና ሊሟገት ይገባዋል፡፡ መንግስትም በዚህ ጉዳይ የሚጠበቅበትን ሚና መወጣት አለበት፡፡ ብዙ ጥቅሞች አሉት፡፡ ለምሳሌ  የእስራኤል ኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያ በቤተ ክርስቲያኒቱ ህንጻ ላይ ነበር የተከራየው። ህንጻው በንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ ነበር የተሰራው፡፡ ከዚያም በኋላ በርካታ ህንጻዎች ተሰርተው የእስራኤል መንግስት ተከራይቷቸው ይገኛሉ፡፡ በአልአዛር እና ቤተልሔም በነገስታቱ የተገነቡ ህንጻዎች አሉ፡፡ እነዚህ ህንጻዎች ሃገራዊ ፋይዳቸው ትልቅ ነው፡፡ ይሄን ሁሉ በቸልታና በምን አገባኝ ስሜት ማየቱ ነው፣ ዛሬ ላይ ግብፆች የራሳችን የሆነን ነገር ሊነጥቁን የታገሉት። አያያዙን አይተህ ጭብጦውን ቀማው እንደሚባለው ነው ያደረጉት፡፡ እኔ ቅድስት ሃገር ኢየሩሳሌም ከአንዴም ሶስቴ ሄጃለሁ፡፡ መሄድ ብቻ አይደለም፤ ተቀምጬም ያሉትን ቦታዎችና ታሪክ ለማጥናት ሞክሬያለሁ። "የኢየሩሳሌም ማስታወሻዎቼ" የምትል አነስተኛ መጽሐፍም ለንባብ አብቅቻለሁ፡፡ በአቶ አማከለ ገበየሁ የተዘጋጀው “ቅድስት ሃገር” የሚለው ሙሉ ይዞታዎቻችንን ያካተተው መፅሐፍም በእስራኤል ታትሞ ነበር፡፡ እዚህም እንዲታተም ተደርጎ በኢየሩሳሌም ስለሚገኙ ይዞታዎቻችን ትልቅ ግንዛቤ እንዲገኝ አድርገናል፡፡
አሁን የተፈጠረው ችግር ምንድን ነው?
አሁን ወደ ተፈጠረው ችግር ስንመለስ፣ ግብጻዊያኑ ሆን ብለው፣ ጊዜ ጠብቀው ነው ይሄን ችግር የፈጠሩት፡፡ የእስራኤልን ባለህበት እርጋ የሚል ህግ (ስታተስኮ) ሽረው ነው ይሄን ችግር የፈጠሩት፡፡ ይሄ ባለህበት እርጋ የሚለው  ህግ እንዲጣስ ማን ፈቅዶላቸው ነው፣ የራሳቸውን ባንዲራ  የኛ ገዳም ግድግዳ ላይ የቀቡት? ስለዚህ ጉዳይ የእስራኤልንም መንግስት  አጥብቆ መጠየቅ ይገባል፡፡ የኛ አባቶች በዚህ ገዳም ውስጥ ሲኖሩ ባለው ህግ የተነሳ ጥገና እንኳ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተው እንዲሁ ነው የሚኖሩት። ይሄ በሆነበትና የባለህበት እርጋ አዋጁ ባልተሻረበት፣ ግብፃውያኑ እንዴት ይሄንን ሊፈፅሙ ቻሉ? ብሎ መጠየቅ  ያስፈልጋል፡፡ ይሄ ወቅት የፀሎት ወቅት ነው፡፡ በአለም ያለ ክርስቲያን በሙሉ ወደ እስራኤል ለመሳለም ይሄዳል፡፡ ኢትዮጵያውያን በብዛት ይጓዛሉ። እዚያ ሄደው በንጹህ ህሊናቸው መፀለይ መሳለም ሲገባቸው፣ ይሄንን የሚያሳዝን ነገር ሲያዩ፣ ለእስራኤልም ገፅታ ጥሩ አይደለም። ግብጻዊያኑ ሆን ብለው አለማቀፍ ቀልብ ለመሳብና ተፅዕኖ ለመፍጠር የሚያደርጉት ነገር ነው፡፡ ሆነ ተብሎ ጊዜ ተጠብቆ የተጫረ እሳት ነው፡፡
የግብጻውያኑ ዓላማ ምንድን ነው?
ያው በኛ ቦታ ላይ ባንዲራቸውን የሚያመለክት ስዕል መሳላቸው፣ ይሄ የኛ ነው ማለታቸው ነው፡፡ የኛ ነው እያሉ ፎቶ እያነሱ ለዓለም ለማሳወቅ  ነው፡፡ ምንድን ነው አላማው? ይሄ እኮ ግልፅ ነው፡፡ አይን ያወጣ ትንኮሳ ነው፡፡ የእስራኤል መንግስት ይሔን ጉዳይ በትኩረት ማየት አለበት፡፡
በትክክል በቦታው ላይ የተፈጸመው ምንድን ነው?
የግብፅ ባንዲራን ቀለም ነው በገዳሙ አካባቢ የቀቡት፡፡ እንዲህ ያለ ትንኮሳ ነው የፈፀሙት፡፡ በገዳሙ በር አጠገብ ነው ይሔ ምልከት የተቀመጠው፡፡ ይሄ በግልፅ ወቅቱ በርካቶች ወደ ስፍራው የሚሄዱበት በመሆኑ "ይሄ የግብፅ ነው" ብለው እንዲረዱ ለማድረግ ነው፡፡ ይሄ በጣም ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ አደገኛ ስልት ነው፡፡ በመላው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ በመሆኑ ሁሉም  ሊቃወሙት ይገባል፡፡
ይሄ ችግር በየጊዜው ነው የሚፈጠረውና ዘላቂው መፍትሔ ምንድን ነው?
 በኔ በኩል ሶስት መፍትሔዎች አሉ፡፡ አንደኛው በእስራኤል ያለን የይዞታና የቅርስ ጉዳይ በ,ንብረትነቱ የቤተ ክርስቲያኒቱ መገልገያ ይሁን እንጂ ጉዳዩ የሃገር ገፅታን የያዘ ነው፡፡ የእስራኤልና የኢትዮጵያን ግንኙነት ታሪክ የያዘ ሃብት ነው፡፡ ይሄ ሃብት የሃገር ሃብት እንደመሆኑ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ፣ ልክ እንደ ግብፆች ወይም ከዚያም በተሻለ መንገድ፣ የዴር ሱልጣን ጉዳይ የኢትዮጵያውያን ሁሉ ጉዳይ እንደሆነ ማሳየት አለባቸው፡፡ ይሄ ገዳም ብቻ አይደለም፤ ሌሎችም አሉ፡፡ ረጅም ዓመታት ያስቆጠሩ ቅርሶችም አሉን፡፡ የእነዚህ ገዳማትና ቅርሶች ታሪክ በትምህርት ካሪኩለም ውስጥ ተካትቶ ለተማሪዎች መሰጠት አለበት፡፡ ልክ ሃገር ውስጥ ያሉት ቅርሶች እንደተካተቱት ሁሉ እነዚህም የኛ ቅርሶችና ንብረቶች ስለሆኑ በስርዓተ ትምህርት ውስጥ መካተት አለባቸው፡፡ ይሄ መደረጉ አንደኛ  ጉዳዩ እንደ ሌሎች ቅርሶች ሁሉ በትውልዱ ዘንድ ትኩረት እንዲያገኝ  ይረዳናል፡፡
ሁለተኛው መፍትሔ፣ እያንዳንዱ በመላው ዓለም የሚገኝ ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ በሙሉ በጉዳዩ ላይ የትዊተር ዘመቻ ሊያደርጉ ይገባል። ጉዳዩ አለማቀፍ ትኩረት እንዲያገኝና ህጋዊ መብታችን እንዲከበር፣ አለም ከኛ ጎን እንዲሰለፍ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ለዚህ በርካታ የሰነድ ማስረጃዎች አለ፡፡
በሶስተኛ ደረጃ ሃገሪቷን የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ መንግስት የዴር ሱልጣን ጉዳይን የአንዲት ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ብቻ አድርጎ አይደለም ማየት ያለበት፡፡ በእስራኤል ያሉ ዲፕሎማቶች ጉዳዩን በአንክሮ እንዲከታተሉ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም ጉዳዬ ብሎ ትኩረት ሰጥቶ ሊይዘው ይገባል።

Read 3394 times