Monday, 25 April 2022 00:00

አገርን የሚፈውስና የሚያፀና፣ ፈዋሽ ጥበብ!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

  1. ሁሉንም ሰው የሚያቅፍ ጥቅል የጤና እውቀት (ዘላለማዊ መርህ) ከሌለ፣ ህክምና የለም።
ብዙ ገፅ የምርመራ ውጤቶች ቢመጡልን እንኳ፣ ምንነታቸውንና ትርጉማቸውን አናውቅም። የተዛባውንና የተቃናውን መለየት አንችልም -መሠረታዊ የጤና እውቀት ካልተማርን፣ ጥቅል እውቀት ካልጨበጥን።
በዘፈቀደ፣ በስሜትና በሆይሆይታ፣ “ይሄኛውን ቅጠል አኝክ፣ ያኛውን ክኒን ዋጥ፣ የወዲያኛውን ፈሳሽ ተቀባ” እያልን እንደናበራለን። ሕመሙ እየፀናበት፣ በመላ ሰውነቱ እየተዛመተ፣ ውስጡ እየተመረዘ፣…በቃ. ያልነበረበትን በሽታ እንጨምርበታለን።
ዘላለማዊ ሁሉን አቀፍ እውነቶችና እውቀቶች፣ የስነምግባርና የፖለቲካ መርሆች ከሌሉን፣ ወቅታዊ ችግሮችን የሚፈውስ ዘመኑን የሚዋጅ ሁነኛ መፍትሄ አይኖረንም።
2. የታካሚውን  የግል የጤንነት ሁኔታ የሚያስረዳ የምርመራ መረጃ (ወቅታዊ ግንዛቤ) ከሌለ፣ ህክምና የለም። ከውጭም ከውስጥም፣ አስተውለንና መርምረን፣ ህመሙን በትክክል  ጠንቅቀን መገንዘብ ካልቻልን፣ በሽታውን መለየትና ማከም አንችልም።
ህመሙ በዝቶ፣ የስቃይ ጩኸቱ አካባቢውን እስኪያናውጥ ድረስ፣ ህመሙን አንሰማውም።
የበሽታ መንስኤው ተራብቶ፣ ውስጡ ተበልቶ፣ ከሰውነት ተራ ወጥቶ በአደባባይ በግላጭ እስኪታይ፣ አንድ ሐሙስ እስኪቀረው ድረስ፣ በሽታውን አናየውም። ስር በሰደደ በሽታ የሚያስልና የቅዝቃዜ ሽውታ ተሰምቶት የሚያነጥስ፣… አንዱን ከሌላው ለይተን አንገነዘብም።
ትንሹን እክል አግንነን፣ አደገኛ ሊሆን ይችላል በሚል ስሜት፣ እንደመሰለንና እንደመጣልን፣ የሌለበትን በሽታ እንደሚኖርበት እየገመትን፣ መዓት ዓይነት መድሃኒቶችን እንግተዋል።
ትልቁን ችግር አቅልለንና እንደ ጊዜያዊ አጋጣሚ ችላ ብለን፣ እንዲባባስ እንለቀዋለን። “ሁሉም ደህና፤ ሁሉም ጤንነት” እያልን፣ አደገኛው ህመም እንደ መልካም እድል እንዲባዛ እንዲዛመት እንዘምርለታለን፤ እንዘምትለታለን።  
              


             የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነቱ፤ መንስኤውና መድሃኒቱ፤ ኑሯችንን ብቻ ሳይሆን ሃሳባችንም እንዴት እያምታታ እንደሆነ ተመልከቱ፡፡ አዎ፤ በዋጋ ንረት ዙሪያ ፤ብዙ ስራስሮች፣ ቅጥያዎችና ቅርንጫፎች  መኖራቸው አይካድም፡፡ ሃሳብን ያምታታሉ፤ ያወሳስባሉ፡፡ ነገር ግን፤ ያህልም የተወሳሱ ጉዳዮች አይደሉም፡፡
“ከኢኮኖሚ ሁኔታ ጋር ያልተመጣጠነ የገንዘብ ሕትመት ነው” የዋጋ ንረት ዋና  መንስኤ። ወደ ገበያ የሚመጣ ምርት ሳይጨምር፤ ወደ ገበያ የሚወጣ የገንዘብ ቁጥር ከተበራከተ፤ የዋጋ ንረት ይከሰታል፡፡ “ብር ረከሰ፤ የሸቀጥ ዋጋ ጋሸበ” የሚስብል ይሆናል ነገሩ፡፡
“ኢንፎሌሽን” የሚባለው አገላለጽም፤ የረከሰ ገንዘብን የሚያመላክት ነው፡፡ የአንድ ወይም የሁለት ምርቶች እጥረት አይደለም። ገንዘብ ሲረክስ፤ አነሰም በዛ፣ ከሞላ ጎደል በሁሉም ምርት ላይ፣የገበያ ዋጋ ይጋሽባል፡፡
የብዙ አገራት መንግስታት ደግሞ ገንዘብ ከማተም አይቦዝኑም፡፡
ይህ፣ መሰረታዊ ጠቅላላ እውቀት ነው፡፡
የአገራችንን ወቅታዊ ጉዳዮችና መረጃዎች ደግሞ እናክልበት፡፡ ኢትዮጵያ አገራችን፤ አለመረጋጋትና ስጋት ብቻ ሳይሆን፤ ጥቃትና ጥፋት፣ መፈናቀልና መመሳቀል በዝቶባታል። ኢኮኖሚን የሚያደናቅፉ ነባር ችግሮችን ለመቅረፍ፣ የእፎይታ እድሎች ብዙም አልተፈጠሩም፡፡ በዚህ ላይ ነው፤ አገርን የሚያቃውስ ጦርነት የተጫነባት፡፡
የጦርነት መከራ፤ እጥፍ ድርብ ነው። ያወድማል፤ እንደገና አገርን አድክሞ ለሌላ ውድመት ያመቻቻል-ጥላቻንም በማዛመት፡፡
ኢኮኖሚ ላይም፤ የጦርነት ጉዳት በሁለት ወገን ነው፡፡ ኢኮኖሚን ያዳክማል፡፡ የገበሬዎች ምርት ይቀንሳል፤ የፋብሪካዎች ስራ ይቀዘቅዛል፡፡ ብዙ ማሳ፣ ጦም ያድራል፡፡ ብዙ ኢንቨስትመንትና ፋብሪካ ይሰናከላል፡፡
ይህ ብቻ አይደለም፡፡
ጦርነት፣ኪስን ያራቁታል፡፡ ብዙ ገንዘብ ይበላል፡፡ መንግስት ለወትሮም ገንዘብ በቅቶት አያውቅም፡፡ በጀት ይጎድልበታል፡፡ ገንዘብ ሲያጥረው፤ብር ያትማል፡፡ በጦርነት ጊዜ ደግሞ፣ የመንግስት የገንዘብ እጥረት ይብስበታል፡፡ ብር ማተም ግድ ይሆንበታል፡፡
ጦርነት፤ በአንድ በኩል ምርትን ያዳክማል፤ በሌላ በኩል ደግሞ፤ የገንዘብ ሕትመትን የሚያባብስ ሰበብ ይሆናል፡፡
በአጭሩ፣ ጦርነት አዲስ የዋጋ ንረትን ይፈለፍላል፡፡ ነባር  የዋጋ ንረትን ደግሞ እንደጉድ ያግለበልባል፡፡
አሁን አስቡት፡፡ ለጦርነት እልባት የሚሰጥ መፍትሔ ለማበጀት ሳናስብ፤ የዋጋ ንረትን በቁንፅል ማስወገድ የምንችል  ይመስላችኋል? በምን ተዓምር?
የጦርነት መዘዝ፤ ለቁጥር ለስፍር ያስቸግራል። ህይወትን  ማርገፉና አካልን ማጉደሉ ሳያንስ፤ የስነ ምግባር ትንሿንም ቅሪት እየሸረሸረ፤ ጨርሶ ያራቁታል፡፡ የዋጋ ንረትም፤ ልክ እንደዚያው በጦርነት ሳቢያ ከሚባባሱ መዘዞች አንዱ ነው፡፡
ታዲያ፣ ጦርነትን ይዘን፤የዋጋ ንረት ለብቻው ተለይቶ መድሃኒት እንዲያገኝ ብንመኝ ምን  የሚሉት ሞኝነት ይሆናል?
ጥላቻን የሚያባብሱና ለጦርነት የሚማግዱ፣ የብሔር ብሔረሰብና የሃይማኖት ፖለቲካ ቅስቀሳዎችን፤ ጭፍን የብሽሽቅና የውንጀላ ሱሶችን ታቅፈንስ፣ እንዴት ጦርነትን ማስቀረት፤ ወይም ጦርነትን መግታት ይቻለናል?
ይህን ሁሉ እያየን እንዳላየን ስንሆን፤ የዋጋ ንረትን በዋጋ ተመን አማካኝነት ለማስወገድ  ስንሞክር፤ ከንቱ ምኞት አይደለምን? ከከንቱም የከፋ ነው፡፡ፈዋሽ ይሆንልናል ያልነው “መድሀኒት”፤ በተቃራኒው ህመምን ይጨምርብናል፡፡ አዳዲስ በሽታዎችንም ያመጣብናል፡፡ የገበያ ግርግርና የኢኮኖሚ ቀውስ ነው-ትርፉ፡፡
የዋጋ ንረትን ብቻ በነጠላና በቁንፅል እያየን፤ “በቁጥጥር እናክመው” ብንል፤ ከድጡ ወደ ማጡ ያስገባናል፡፡
በነጠላ ነጥብ ነጥቡን ብቻ ሳይሆን፤ በሰፊው ማየትና ተዛማጅ ጉዳዮችን በጥቅል ማገናዘብ ካልቻልን፤ እንደገና ከማጥ ወደ ረመጥ ይጨምረናል፡፡
እንዲህ ሲባል ግን፤ ነጠላ ጉዳዮችና ዝርዝር መረጃዎች ላይ፤ እያንዳንዷን ጠጠርና ጠብታ እያነሳን፤ ነጥብ ነጥቡን መነገር የለብንም ማለት አይደለም፡፡ ማሰብና መነጋገርማ አለብን፡፡

አንዲት መጥፎ ህግ፤ አንድ ክፉ አንቀጽ?
አምና ወይም ካቻምና የወጣ አንድ ሕግ፤ “መጥፎ ሕግ ነው”፤ ብለን ብንናገር አይደንቅም። አስረኛው ወይም ሃያኛው አንቀፅ፣ “በጣም ጎጂ ነው” ብንል አይገርምም። በእርግጥም፤ አንድ ነጠላ አዋጅ፣ አገርን የሚያተራምስ ሊሆን ይችላል።
አንዲት ቅንጣት አንቀፅ፤ ለሚሊዮን ሰዎች ከባድ መከራ የምታመጣበት አጋጣሚም ይኖራል። ወቀሳና ትችት፤ ቅሬታና ምሬት ቢበዛ፤ ነውር የለውም። ወቀሳና ቅሬታ ብቻ ሳይሆን፣ የመፍትሄ ሀሳብና የማስተካከያ ዘዴ ሲጨመርበት፤ ቅንነትና ጥረት ሲታከልበት ግን፤ ከስህተት ያድናል፤ ወደ ብስለት ያሻግራል። የጥበብ መንገድ ፍሬያማ ነው።
ወቀሳና ምሬት ላይ ብቻ መረባረብ ግን፤ ተጨማሪ እሬትን ያበቅላል። መቃቃርን እያበዛ ያራባል። ከመዋቀስ ወደ መቃወስ ይዞ ይሄዳል።
የባሰም አለ። አንድን አዋጅ ለመቃወም ሲያስብ፤ አንዲትን አንቀፅ ለመቃረን ሲፈልግ፣ ያችኑን አንቀጽና ህግ መተቸት አያረካውም። ከዳር እስከዳር፤ ሌሎች ሕጎችንና አንቀፆችንም ሁሉ በጅምላ ጠቅልሎ ማንቋሸሽ ይቀናዋል፤ ይቀልለዋል። እንደሰበብ እንደማመካኛ ይጠቀምባቸዋል።
ሕጎችን በሙሉ ካላንቋሸሸ፤ የቅሬታውን ክብደት ማሳየት የሚችል አይመስለውም። አንድ ህግ ላይ ብቻ ያነጣጠረ ወቀሳ፣ ምሬቱን አይገልፅለትም። አንድ ሁለት አንቀፆችን ብቻ በነጠላ ከተቸ፤ ጉዳዩ ሰሚ የማያገኝ፣ በቸልታ የሚታለፍ ይመስለዋል።
እናም፤ አንቀፆችን ከመዘርዘር ይልቅ፤ አዋጁን በደፈናው ማብጠልጠል… አንድ ሁለት ህጎችን ከመተቸት ይልቅ፤ ህጎችን ሁሉ በጅምላ ማውገዝ ይጀምራል።
በእርግጥ፣ ከስር መሰረቱ የተበላሸ፤ ስህተቶችና ጎጂ አንቀፆች የበዙበት፤ ከሞላ ጎደል፤ ከጫፍ እስከ ጥግ፣ መጥፎ የሆነ አጥፊ አዋጅ ወይም እቅድ ሊኖር ይችላል። የትምህርት ፍኖተ ካርታ የተሰኘው እቅድ አንድ ምሳሌ ነው። የማህበረሰብ የተፋሰስ ልማት በሚል ስያሜ የወጣው ህግ ደግሞ ሌላ በአጥፊ ሃሳቦች የታጨቀ ህግ ነው።
የትምህርት ፍኖተ ካርታው፤ መሰረታዊ መረጃዎችንና እውቀትን ያንኳስሳል። መረጃና እውቀት በኢንተርኔት ሞልቷል የሚል ምክንያም ያቀርቡለታል። የፈጠራ ችሎታ ላይ ማተኮር  አለበት ትምህርት ይሉለታል። እስቲ የህክምና እውቀት በሌለው ይታከሙና ውጤቱን ይንገሩን።
 የማህበረሰብ የተፋሰስ ልማት የተሰኘው አዋጅ፣ ጥፋት አደጋ ነው። ከተሞች በዙሪያቸው ለሚገኙ የገጠር ማህበሮችና ቀበሌዎች፤ ግብር ወይም ታክስ እንዲከፍሉ ያስገድዳል- አዋጁ። ስንት ዓይነት ውዝግብና ጣጣ እንደሚፈጠር አስቡት።
 በተመሳሳይ ቅኝት የተቀረፁ መጥፎ ህጎች እየተከታተሉ የሚመጡበትና የሚበረክቱበት ጊዜም ይኖራል። በዚያው ልክ፤ በስፋት መውቀስ፤ በርካታ ሕጎችን  በማዕቀፍ ሰብሰብ ጠቅለል አድርገው መተቸት ተገቢ ነው -ለመፍትሄ በሚጠቅም መንገድ።
ከዚህ ውጭ ሲሆንስ? አንዲቷን አንቀፅ ለመንቀፍ፣ አንዲቷን ህግ ለመንቀስ ከጀመረ በኋላ፣ በጭፍን ስሜት፣ ግራ ቀኙን ሁሉ መርገም፤ ዙሪያውን ሁሉ እየተሽከረከረ በጭቃ መመረግ ያመጣል። ለጊዜው፣ የልብ የሚያደርስ ይመስለዋል።
የጭፍን ስሜት ጊዜያሳ “እርካታ” ግን፤ ይባሱኑ እርካታን ያሳጣል። “የዛሬ ህግ ደግሞ ሕግ ነው እንዴ! እዚህ አገር ደግሞ ህግ አለ እንዴ!”…ወደማለት ይሻገራል። ምንም ነገር የማይጥመው ሁሉም ነገር የሚኮመጥጠው ይሆናል።
“የዚህ ዓለም ህግ፤ ሰው የፃፈው አንቀፅ ሁሉ፤ ጠማማ እሾሃማ ነው” ብሎ ምልዓተ ዓለሙን ባጠቃላይ ይረግማል፤ ሰውን ለዘለዓለም ይኮንናል።
በአንዲት አንቀፅ ሰበብ የተጫረው የጭፍንነት ልክፍት ዙሪያውን እየነካካ ይስፋፋል። ከነአካቴው፤ ሕግንና ስርዓትን በጥቅሉ ሁለመናውን እስከማውገዝ ይደርሳል። ህገወጥነትን እያላመደ ወደ ስርዓት አልበኝነት የሚወስድ ነው - እንዲህ አይነት ጭፍንነት።
ሌላ ተፊካካሪ ጭፍንነትም አለ። ተከታዮቹ ብዙ ናቸው። በጅምላ ከማፅደቅ፣ በደፈናው ከመደገፍ ውጭ፤ ሌላ ነገር አይጥማቸውም። አንድ ሁለት አንቀፆች ላይ ትችት ወይም ወቀሳ ሲቀርብ፤ ይከነክናቸዋል። የሴራ ምልክት የጠላትነት ማረጋገጫ ሆኖ ይታያቸዋል።
ሁለት ሶስት ሕጎች ላይ ቅሬታና ምሬት ከተፈጠረ፤ “የሕገ ወጥነትና የስርዓት አልበኛነት ዘመቻ ነው” ብለው ይፈርጁታል። “አገርን የሚንድ፤ ስርዓትን የሚያፈርስ ነው” በማለት በጅምላና በደፈናው ይወነጅሉታል።
እንዲህ በጭፍን ካልፈረጁና ካልወነጀሉ፤ ደካማ የሆኑ፤ ጥፋተኝነትን ሁሉ ጠቅልለው የተቀበሉና የተናዘዙ ይመስላቸዋል። እንደ ደካማ እንደ ጥፋተኛ እቆጠራለሁ ብለው ይሰጋሉ። ይንቁኛል፤ ይዳፈሩኛል የሚል ፍርሀት ያድርባቸዋል።
“ለቅንጣት ትችት፣ ለአንዲት ወቀሳ መንገድ መክፈት፣ ፊት መስጠት፣ የውድቀትና የሽንፈት መጀመሪያ ነው” ብለው ያምናሉ። ሙሉ በሙሉ፣ በደፈናው፣ በጅምላ፣ ቀሪና ሽራፊ የሌለው፣ ያልተገደበ ድጋፍና ውዳሴ ብቻ ነው የሚጥማቸው።
አንዱ፣ በደፈናው ይቃወማል፤ ያጣጥላል፣ በጅምላ ያወግዛል።
ሌላው፣ የዚያኑ ያህል በደፈናው ይደግፋል፤ በጅምላ ያፀድቃል።
አንዱ ያለገደብ ያላግጣል፤ ያንጓጥጣል፤ ሌላው አለቅጥ ይክባል፤ ያሞካሻል። ይሄ፤ አጥፊ የጭፍንነት መንገድ ነው።
በእርግጥ፤ የሆነ የሚማርክ የሚያባብል ነገር አለው። በደፈናው በጥቅሉ መደገፍና መቃወም፣ ወዲህና ወዲያ አያምታታም። በዚያ ላይ፣ ሃሳብና ሂሳብ አያስፈልገውም። በጣም ቀላል ነው።
“ላይክ”፣ “ላይክ”፣ “ላይክ”… የማለት ያህል ነው - ቀላልነቱ። “ዲስላይክ”፣ “አንላይክ” እያሉ በእሩምታ መልቀቅም አይከብድም።
አስገራሚው ነገር፤ “በጥቅልና በሰፊው አለመናገር”፣ “በቁንፅልና በነጠላ ብቻ ማሰብ”፤ መፍትሄ አይለደም። እንዲያውም፣ ይሄም ሌላ የጭፍንነት ገፅታ ነው።
አዎ፤ ውሃ ለመጠጣት፣ ወደ ጥልቅ ባህር መግባት፤ ለማንም አይበጅም። ይህ ማለት ግን፤ የውሃ ጠብታ ሲቆጥሩ የሚውሉ ሰዎች ብፁዓን ናቸው ማለት አይደለም። “ድፍን ሃሳብ መጥፎ ነው” ማለት፣ “የተንጠባጠበ ሃሳብ ይፈውሰናል፤ የተበጣጠሰ ሃሳብ መፍትሔ ይሆንልናል” ማለት አይደለም።
የተንጠባጠበ ቅንጥብጣቢ ሃሳብ፣ መፍትሄ ቢሆንማ ኖሮ፤ ብዙ “ባለ-መፍትሄ ሰዎች” ይኖሩን ነበር።
የዋጋ ንረትን በቅፅበት ዘርረው የሚያስወግዱ፤ የኑሮ ውድነትን በአንድ ምት ጥለው ልክ የሚያስገቡ፣ “የቁንጽል መፍትሔ ጌቶች” ጥቂት አይደሉም።
የዋጋ ተመን ማውጣት፤ ሁነኛ መፍትሔ እንደሆነ የሚያምኑ ሰዎች ብዙ ናቸው። በቃ፤ አንዲት የዋጋ ተመን አዋጅ በማዘጋጀት፣ አንዲት ገፅ መመሪያ በማውጣት፤ የኑሮ ችግርን ማቃለል! በጣም ቀላል መፍትሔ አይደለም? ውስብስብ ሃሳብ የለውም።
“የዋጋ ንረት” በሚለው ፅሑፍ ምትክ፣ “የዋጋ ተመን” የሚል ፅሑፍ አምጥቶ መተካት ብቻ ነው። እዚህም አይደርስም፣ “ንረት” የምትል ቃል ወርውሮ፣ “ተመን” ብሎ ማስገባት ብቻ! መፍትሔው፤ እንደዚህ ቀላል ይመስላቸዋል፤ ያስመስላሉ።
በዋጋ ተመን ሳቢያ ነገ የሚፈጠሩ መዘዞችን ዛሬውኑ ማሰብ አይፈልጉም። ዛሬንና ነገን፣ ሰበብና መዘዝን፣ ተግባርና ውጤትን አጣምሮ፣ በሰፊው አቅፎ ማሰብ ያስጠላቸዋል።
ዛሬ ያጨበጨብንለት የዋጋ ቁጥጥርና ተመን፤ ነገ ችግር ሲያስከትልስ?
ዛሬ፣ በነጠላና በቁንፅል፣ የዛሬዋ የዋጋ ንረትና ተመን ላይ ብቻ አናስብ? ነገ፤ የገበያ ግርግርና የምርት እጥረት ሲፈጠር፤ ያኔ… ያ ችግር በነጠላ ይታያል። ሌላ ነጠላ መፍትሄ ይመጣለታል። እስከዚያው ግን፣ ዛሬ ላይ ብቻ ማተኮር! እናም፣ የዋጋ ቁጥጥሮችን ማጧጧፍ! ከዚያስ? ገበያ ተረብሾ፣ የሸቀጦች እጥረት ይፈጠራል። የፍተሻ ዘመቻ ይጀመራል።
በእርግጥ፤ የእያንዳንዱን ገበሬ ጓዳ እየበረበሩ፤ ስንዴና ሽንኩርት ለገበያ እንዲያቀርብ ማስገደድ ከባድ ነው።
ስለዚህ፤ የዋጋ ተመኑና ፍተሻው በነጋዴዎች ላይ ብቻ! ያነጣጠረ ይሆናል። ግን ይሄም ያስቸግራል።
ቃሪያና ሎሚ፣ ቀሚስና ሱሪ ላይ፣ እልፍ የዋጋ ተመኖችን፣ በሰንጠረዥ ማወጅ፣ ከዚያም መቆጣጠርና ሱቆችን መበርበር፣ የት ያደርሳል? ለስንት የቀሚስና የሱሪ አይነት፣ ስንቱ የዋጋ ተመን ተሰልቶ ይዘለቃል? እንደ ሰሜን ኮሪያ፣ ሰዎች ሁሉ “ዩኒፎርም” እንዲለብሱ በአዋጅ ካልተወሰነ በቀር፤ ለልብሶች የዋጋ ተመን አውጆ መቆጣጠር ችግር ነው።
ብዙ ሰው የዋጋ ተመንን ስለሚቃወም አይደለም - ችግሩ። ብዙ ሰው ይደግፋል። ግን፣ ጥቅል ሃሳብና መርህ ስለያዘ አይደለም።
“በብዙ ነገሮች ላይ የዋጋ ተመንን የሚደግፍ” ገበሬ፤ የዋጋ ተመን ይዘው ወደ እህል ገበያ ከመጡበት ይቃወማል። ስንዴና ጤፍ ላይ፣ የዋጋ ተመኖች እንዲታወጁበት አይፈልግም። በገዛ ንብረቱ፣ በገዛ ምርቱ፣ እንደ ሌባ ተቆጥሮ፣ ወደ ጓዳው ወደ ጎተራው አጠገብ ፍተሻ ሲመጣበት አይወድም።
“በገዛ ምርቴ! በገዛ ንብረቴ!” ብሎ በነጠላና በቁንፅል ያስባል፣ ይቃወማል።
“የንብረት ባለቤትነት መብት”፤ “የግለሰብ ነፃነት” የሚሉ መርሆዎች፣ ለሁሉም ሰው፤ በሁሉም ቦታ ተግባራዊ እንዲሆኑ፣ “ሰፊ የመፍትሔ ማዕቀፍ” አያቀርብም። የዋጋ ተመኑ በፋብሪካ ውጤቶች ላይ ብቻ እንዲሆን ይመኛል።
ሌላኛው ደግሞ የልብስ ነጋዴ ስለሆነ፣ “የመንግስት የዋጋ ተመን፤ ዘይትና ሳሙና፤ ስንዴና ጤፍ ላይ” እንዲያተኩር ይፈልጋል።
“መሰረታዊ ሸቀጦች ላይ ማነጣጠር አለብን” ይላል አንዱ። “መሆን የለበትም ብሎ ይከራከራል” - ሌላኛው። “መሰረታዊ ሸቀጥ የሚያመርቱ ዜጎችን ማዳከም የለብንም” ብሎ ይሞግታል።
“የዋጋ ቁጥጥር የሚያስፈልጋቸው፤ መሰረታዊ ያልሆኑ የቅንጦት ሸቀጦች ናቸው” ብሎ ለማሳመን ይጣጣራል።
ሁሉንም፣ በቁጥ ቁጥ ነው የሚያስቡት-ያለ መርህ።
ያው፤ የዋጋ ተመን፣ ከደሞዝ ተመን ጋር ቅንጣት ግንኙነት እንደሌለው ያስባል ብዙ ሰው። አንዳንድ ሰዎች ግን፤ የደሞዝ ተመንም በአዋጅ እንዲወጣ ይፈልጋሉ። ታዲያ፤ ዝቅተኛውን ደሞዝ ለመተመን እንጂ፤ እንደ ሸቀጥ ዋጋ፤ “የደሞዝ ንረትን ለመቆጣጠር” አይደለም። “ከፍተኛውን የደሞዝ መጠን የሚገድብ ተመን” በሃሳባቸው አይመጣላቸውም።
የዋጋ ንረትን ከላይ መድፈቅና ማመቅ፣ የደሞዝ ክፍያን ደግሞ ከታች መቆስቆስና እየጎተቱ መለጠጥ!በቃ?
ነገር ግን፤ “እንዲጎትት” የተፈቀደለትና ስልጣን የተሰጠው መንግስት፤ ወደ ቀኝ ብቻ እንደሚጎትት በቁንፅል ብናስብ፤ ራሳችንን እናታልላለን። ወደ ግራ እንዲገፋን የፈቀድንለት ጊዜ፤ ሽቅብ እንዲወረውረን፤ ቁልቁል እንዲደፍቀንም ፈቅደናል። “መንግስት የዜጎችን ደሞዝ ወይም የሸቀጦችን ዋጋ፣ መጎተት ይችላል “የምትል ቁንፅል አንቀፅ፤ በነጠላ ብቻ ሳይሆን በሰፊው መታየት አለባት ማለት ነው።
እንደ ጤና ባለሞያ፤ እንደ ሀኪም ብንሆን አስቡት።
 በጥቅሉ፣ ስለ ህያው ተፈጥሮ፣ ስለ እንስሳት ምንነት፤ በተለይ ደግሞ፣ ስለ ሰው ተፈጥሮ፣ ሰፊ መሰረታዊ እውቀት ሊኖረው ይገባል። የህይወት ጠቅላላ ስርዓትን፤ የህይወት ተስማሚ ጤናማ ሂደቶችን፣ በጥቅሉ ይማራል፤ ያጠናል። በዘርፍና በአይነት ከፋፍሎ፤ በየደረጃና በዓይነት እርከን አበጅቶ፤ በእውቀት እየሰፋ፣ እየረጀ እየረቀቀ፣ እየተሳለ፣ በሙያ እየተካነ፤ ብቃቱን ይገነባል።
ዝርዝር ጥናትና ጥቅል እውቀት፤ እርስ በርስ እየተደጋገፉ፣ የአንድ ዘርፍ ልህቀትና ሰፊ መሰረታዊ እውቀት እርስ በርስ እየተቀናጁ ያድጋሉ። የህክምና እውቀት እነዚህን ሁሉ ያካትታል።
 የእለት ተእለት ስራው፤ የእድሜ ልክ ሙያውስ?
እዚህ ላይም፤ እንደ እውቀቱ፣ የተግባር ሙያውም፣ ዝርዝርና ጥቅልን፤ ወቅታዊውንና ዘላለማዊውን፤ ነጠላውንና ማዕቀፉን፤ በአግባቡ ያዋሃደ ነው-የሀኪም ጥበብ።
ስለሰው ተፈጥሮ፣ ስለ ሰው ጤንነት፤ ሁሉን አቀፍ እውቀት አለው-ጥቅል እና ዘላለማዊ ግንዛቤዎችን ገንብቷል።
የሀኪም አገልግሎት ግን፤ “ሰውን በጥቅሉ ማከም “አይደለም። የአሪስቶተል አባባል ነው። አበበ ወይም አበበች ወደ ሃኪም ይሄዳሉ እንጂ፤ “ሰው” በደፈናው እግር አውጥቶ ወደ ሃኪም አይመጣም።
በነጠላ የየራሳቸው ህልውና ያላቸው ግለሰቦች፣ ለህክምና ቀጠሮ ያስይዛሉ፤ ወይም ወረፋ ይይዛሉ።
“ሰው” በጥቅሉ፤ የክሊኒክ በር አያንኳኳም። በጥቅሉ “ለሰው”፤ በጥቅሉ የሚቀርብ ህክምናና ክኒን የለም።
በሰው ጤንነት ዙሪያ ሰፊ ጥቅል የህክምና እውቀት ያስፈልጋል። ነገር ግን፤ ለግለሰቦች ነው ህክምናው።
ሃኪሟ፣ ዘላለማዊ እውቀት አላት። ግን የታማሚውን ወቅታዊ ምልክቶችን፤ ትመለከታለች። የጤና ባለሙያዋ ስለሰው ጤንነት፣ ሰፊና ጥቅል እውቀት አላት። ነገር ግን፤ ታካሚውን በነጠላ ተቀብላ፤ ዝርዝር የምርመራ መረጃዎችን ታስተውላለች።
ነጠላ ግለሰብ፤ ወቅታዊ ሁኔታ፤ ዝርዝር መረጃ ከሌለ፤ ህክምና የለም።
ግን ደግሞ፤ ሁሉን አቀፍ ጥቅል የጤና እውቀት ከሌለ፤ ህክምና አይኖርም።
ዘላለማዊ የሰው ተፈጥሯዊ እውነታዎችን በአግባቡ ያላጠና መንገደኛ፤ ዝርዝር የላብራቶሪ መረጃዎችን ማገናዘብና ለግለሰቦች የጤና መፍትሄ መስጠት አይችልም።
በአጭሩ፤ የህክምና ጥበብ፤ የቅርብና የሩቅ፤ ዘላለማዊውን ተፈጥሮና ወቅታዊውን ሁኔታ፤ ጥቅል እውቀትንና ዝርዝር መረጃዎችን ያዋሀደ ጥበብ ነው።

Read 9440 times