Saturday, 23 April 2022 14:24

ንጉስ የቆረጠው እጅ እንዳለ ይቆጠራል!

Written by 
Rate this item
(3 votes)

አንዳንድ እውነት ሲያረጅ ተረት ይመስላል፡፡
“የዛሬ ዐርባ ዓመት ገደማ የበርበሬ አሻጥር ፈፅመዋል በሚል ነጋዴዎች ተገድለዋል!  ወይም እንደ ጊዜው አባባል አብዮታዊ እርምጃ ተወስዶባቸዋል!” ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ ሲሚንቶ ጤፍ ውስጥ ቀላቅለው የሸጡ አሻጥረኛ ነጋዴዎች ታሰሩ ተባለ፡፡ ውሎ አደረና ለግንባታ የሚያገለግል ሲሚንቶ ካገር ጠፋ ተባለና በየደብሩ ለቤተ- ክርስቲያን መስሪያ በህዝብ መዋጮ የተገዛና የተከማቸ ሲሚንቶ ሳይቀር ተነጠቀ - በመንግስት፡፡ ለምሳሌ፣ ከደብረ ሊባኖስ ገዳም፡፡ ከዛ ቀጥሎ ደግሞ ቅቤ ተወደደ። እንደ ዛሬው ሙዝ በዳቦ ብሉ ባልተባለበት ዘመን፣ ለዩንቨርስቲ ተማሪዎች ምግብ የተገዛው ቅቤ ሙዝ ተቀላቅሎበታል ተብሎ የዕቃ-ግዢ ሠራተኞች ከነጋዴ ተመሳጥራችኋል ተብለው ታሰሩ! ደሞ ዋልን አደርንና፣ የዘይት ነጋዴዎች ታሰሩ፡፡ አንዱ የዘይት ነጋዴ ከምርመራ ክፍል አዛዡ ጋር የተነጋገረውን እንይ፡፡ መቼም እንደ ተረት ነው የምንተርከው፡-
አዛዥ፤ “ሥራህ ምንድን ነው?”
ነጋዴ፤ “ንግድ፡፡”
አዛዥ፤ “ምን ዓይነት ንግድ?”
ነጋዴ፤ “የዘይት ንግድ”
አዛዥ፤ “የት?”
ነጋዴ፤ “እዛው መርካቶ!”
አዛዥ፤ “የት አስቀምጠህ ነው ወደ መርካቶ የምታወጣው?”
ነጋዴ፤ “አሁንማ ምንም የለኝም”
አዛዥ፤ "እሺ ሸጠህ ከመጨረስህ በፊት የምታከማቸው የት ነበር?”
ነጋዴ፤ “እኔማ መጋዘን የለኝም፡፡ ዘመድ ቤት ነበር የማስቀምጠው!;
አዛዥ፤ “ይሄ በዘመድ መስራት አልቀረም ማለት ነው….? በል አሁን በአጃቢ ዘመድህ ቤት ሄደህ ቦታውን ትጠቁማለህ፤ ዘመድህን ይዛችሁ ትመጣላችሁ፡፡” አሉና ትዕዛዝ ሰጡ፡፡
ዘመድ የተባለው ተይዞ መጣና አዛዡ፤ “ዘይቱን የት ነው የምታከማቸው?" ቢሉት “ዘመድ ቤት” አለ፡፡ በዚህ ዓይነት እየታሰሩ የሚመጡት ባለዘይቶች ቁጥር ከሃምሳ (50) በለጠ፡፡ (ይህንን የሚመስል ሁኔታ የዛሬ ሠላሳ ዓመት በቦንዳ ነጋዴዎች፣ በሳሙና ነጋዴዎች፣ “ከኢዲዲሲ በሚወጡ በርካታ ሸቀጣ ሸቀጦች” ዙሪያ ታይቷል፡፡) ከላይ ያነሳነውን  ዘይት ነጋዴ መጨረሻ እንይ፡፡
 አዛዥ፤ “መንግስት፣ የአንተን ጉዳይ በተመለከተ ውሳኔ ወስኗል”
ነጋዴ፤ “ምን ተወሰነልኝ ጌታዬ?”
አዛዥ፤ “አብዮታዊ እርምጃ  እንዲወሰድብህ ወይም የሰረቅህበት እጅህ እንዲቆረጥ! የቱ ይሻልሃል?" አሉና ጠየቁት
ነጋዴ፤ “እጄ ይቆረጥ!"
አዛዥ፤ "ለምን እሱን መረጥክ? ስራ መስሪያ እጅ  የለህም ማለት ነው እኮ?”
ነጋዴ፤ “ግዴለም ጌታዬ! ንጉስ የቆረጠው እጅ እንዳለ ይቆጠራል!” አለ ይባላል፡፡”
*   *   *
ሀገራችን የአሻጥር (የህገ-ወጥ ሌብነትና ምዝበራ) ደሃ ሆና አታውቅም፡፡ ለሆስፒታል ጥኑ ህሙማን ግሉኮስ ግዙ ሲባል እንኳን የደፈረሰ ውሃ የሚሸጡ ነጋዴዎች ያሉባት አገር ናት፡፡ ይሄ እንግዲህ የኦፕራሲዮን መቀስ እሰው ሆድ ውስጥ የሚረሱትን ዶክተሮች ሳንጨምር ነው! የንግዱ ቅጥት ማጣት፣ የዓለም-አቀፍ ሕግ ለፈረመችው አገር ከጉዳይ የሚጣፍ ነገር አለመሆኑ፣ የስር፣ የመሰረት ነውና አያስገርም ይሆናል፡፡ የትም የማይገኝ መድሐኒት፣ ዶክተሮቻችን ብቻ የሚያውቁት የነጋዴ መጋዘን ተኪዶ የሚገዛ ከሆነ፣ ለህክምና የሚያስፈልጉ ዕቃዎችና መድሀኒቶች የኮንትሮባንድ፣ ንግድ፣ እንዴት “እንደበለፀገ” መነጋገር ቢያንስ ጅልነት ነው!
በመሰረቱ መሪዎች፣ የመምሪያ ሃላፊዎች፣ የአስተዳደር ሃላፊዎች ከነጋዴዎች ጋር መመሳጠራቸው ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡ ፊውዳሊዝምን፣ ኢምፔሪያሊዝምንና ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝምን እንዋጋለን ሲባል ከብሔራዊ ከበርቴው (National Bourgeoisie) እና ከአቀባባዩ ከበርቴ (Compounder Bourgeoisie) ጋር መዋጋት አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜ መኖሩን  ያፀኸይልናል፡፡ መንግስት ንግድን የማረጋጋት ኃላፊነት አለበት ስንል እጁን አስገብቶ ነጋዴ ይሁን ማለት አይደለም፡፡ ለዚያ ለዚያማ ንግድ ሚኒስቴርስ የራሱ አይደል? አንድም፤ ከዕለታት አንድ ቀን እንደተደረገው የመርካቶዎቹን ሱቆች ሁሉ ከርችሞ ማሸግም እንዳየነው ትርፉ ፀፀት ነው! “ይሄን ብሉ፣ ይህን አትብሉ!” ማለትም “የምግብ ሥራ ድርጅትን" ሠርተህ አትብላ እንደማለት ነው! ዋናው ትክክለኛውን ሰው በትክክለኛው ቦታ ማስቀመጥ ነው ብለን ደጋግመን የወተወትነው ለዚህ ነበር፡፡ አሁን ሲታሰብ ግን ለካ ሁለት ዋና ዋና ጥያቄዎችን ያስነሳል፡-
1ኛ/ ትክክለኛ ሰው አለን?
2ኛ/ ትክክለኛ ቦታስ አለ?
"The Right Man at the Right Place" - ለካ ጥሩ መፈክር ወይም መርህ እንጂ የተግባር አጀንዳ ካልሆነ ዋጋ የለውም!  ያለጥርጥር መልካም ምኞት ነው፡፡ መልካም ምቾት ግን አይደለም፡፡
በትምህርት መስክም ሌብነትና የፈተና ሥርቆት መበራከቱን እየሰማን ነው! ፈተና አውጪው፣ ፈታኙ፣ ፈተና አታሚው፣ አራሚው የተሰናሰለ ሌብነት እንዳይፈፅሙ መቆጣጠር ካቃተን፣ እንደ "ሿሿ” የባስና የታክሲ የማይታረም ሌብነት ጉዳይ፣ የብዙ ሰዓት የቴሌቪዥን አየር ጊዜ ከመብላት የተሻለ ረብነት ያለው ድርጊት እየፈፀምን አይደለም፡፡
ብዙ መልካም ተግባራት የሚፈፅሙትን ያህል እስከ መዘጋት የተቃረቡ መስሪያ ቤቶችና ድርጅቶች ከዕለት ሰርክ እየበደኑ ሲሄዱ ይታያሉ፡፡ ቸል ሊባሉ አይገባም፡፡
ይሄ ሁሉ ሆኖ ግን አሁንም የሀገራችን ሰላም ጉዳይ፣ የጎረቤት አገሮች ትንኮሳና ወረራ፣ የሰሜኑና የደቡቡ የሀገራችን ክፍል “መንኳኳት የማይለየው በር” መሆን እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ የተቃዋሚዎችና የአማጺያን እንቅስቃሴ ግንዛቤ ውስጥ መግባት አለበት፡፡ ከሁሉም በላይ ግን መንግስት የሚፈፅማቸው ውሎች፣ ውስጥ ለውስጥ የሚያካሂዳቸው ውይይቶችና ድርድሮች የአገርን ዲፕሎማሲ በማይጎዳ መልኩ ለህዝብ ማሳወቅ አለበት!
የጎረቤት አገሮች ነገር “ሰው እንደቤቱ እንጂ እንደጎረቤቱ አይኖርም” የሚለውን የአባቶች ብሂል በቅጡ ያስታውሰናል፡፡ “የግብፅና የሱዳን ጆሮ ይደፈን” እንጂ እኛስ “ምቀኛ አታሳጣኝ” ማለቱን እናውቅበታለን! ግድ ገንብተን መስኖ ጀምረንም፣ ልማት እናለምልም መሰረተ ልማት  እናበልጽግ ብለንም፤ ነገረ - ዓለሙን “ወይ አፍሪካን ወይ ፋፍሪካን?!” ብለን አልፈነዋል፡፡
እዛም ሄድሽ፣ እዛም ሄድሽ፣ ወዲህም ወዲያም አልሽ
ሰው ታዘበሽ እንጂ፣ ምንም አላፈራሽ!” ያለው ያገሬ ገጣሚ ጨርሶታል፡፡
 ምንጊዜም ቢሆን መሪው መማክርቱ፣ የካቢኔ አባላቱ፤ የየክልሉ የየወረዳውና ቀበሌ ሃላፊዎች ወሳኝ መሆናቸውን ተገንዝበውና ተጠያቂ መሆናቸውንም አውቀው፣ አመራራቸውን ማሳመር ይገባቸዋል፡፡ ያ ካልሆነ ህዝብ አንድ ቀን አራስ ነብር የሆነ እለት፣ እስከዛሬ “ንጉስ የቆረጠው እጅ እንዳለ ይቆጠራል” እያለ ማቀርቀሩን ትቶ ቀና እንደሚል አይዘንጉ!! “ጊዜም የስልጣን እጅ ነው” ይሏልና፡፡ ሌላው  አሳሳቢ ችግር ጦርነትን ትዝታ ለማድረግ አለመቻላችን ነው፡፡ ግጭትን መቀነስ አንድ መላ ነው፡፡ ወቅትን ያልጠበቀ ግጭትን መቀነሰ ግን ከባድ መስዋዕትነትን ቢጠይቅም ታላቅ መላ ነው!

Read 12503 times