Monday, 25 April 2022 00:00

ኪየቭ የሚያደርሰው ምላስ ነው መትረየስ?

Written by  አበራ ሣህሌ
Rate this item
(0 votes)

     ‘አፒዝመንት’
ኔቪል ቻምበርሊን የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ፡፡ ዳግመኛ ጦርነት በአውሮፓ እንዳይነሳ ይፈልጋሉ። ፔኒሲሊን የማይታወቅበት ጊዜ በመሆኑ ትከሻውን ጥይት ሸርፎት ያለፈ ወታደር ሁሉ ቁስሉ እያመረቀዘ የማይድንበት፤ ሰው እንደጉድ የረገፈበት፤ አሰቃቂ የነበረው የአንደኛው ዓለም ጦርነት ትዝታ ከአይምሮአቸው አልጠፋም። ጀርመን ቨርሳይ ውስጥ የፈረመችውን ስምምነት ጥሳ ጦሯን ከማደራጀት ባለፈ ቅርብ ያሉትን መሬቶች ወደ ግዛቷ ስትቀላቅል ግጭት በመፍራት ሲያባብሏት ቆይተዋል።
በመጨረሻም የሙኒክን ስምምነት በመፈረም ሂትለር ሱዴተንላንድ የሚባሉትን የቼኮዝሎቫኪያ መሬቶች ከግዛቱ ጋር እንዲቀላቅል፣ በምትኩ ከዛ በኋላ ወረራ እንዳይፈፅም ተስማምተዋል። ሙሶሊኒም ጦሩን ወደ ኢትዮጵያ ሲያዘምት ያኔ በነበረው የመንግሥታቱ ማህበር(ሊግ ኦፍ ኔሽን) ዓፄ ኃይለሥላሴ ተማፅኖ ቢያቀርቡም፣ በባሪያ ፍንገላ ለሚታማ ለባህር ማዶ ግዛት ሲል ግጭት ውስጥ የሚገባ የአውሮፓ አገር አልነበረም። ሙሶሊኒም ከዛ በላይ ምንም አይፈልግም በሚል ጦርነት ውስጥ ላለመግባት ዝም ተባለ።
ለተቆጣ አንበሳ ቁራጭ ሥጋ በመወርወር ለማባበል የሚደረገው ጥረት ጫፍ የደረሰበት የ1930ዎቹ የፖለቲካ ስልት ‘አፒዝመንት’ በመባል ይታወቃል። ቃሉ በፖለቲካ ሳይንስ ውስጥ ታዋቂ ከሆኑት አንዱ ነው። ሂትለርን ያላስቆመው ያ ስልት፣ የድክመት መገለጫ ሆኗል።
ባለፈው የካቲት ወር ቭላዲሚር ፑቲን ዩክሬይን ላይ ጥቃት እንዲፈፀም ሲያዙ፣ የዛ አይነት ማባበያ ጠብቀው ሊሆን ይችላል። ከዛ ቀደም በ2014 (ሁሉም በአውሮፓ አቆጣጠር) ክራይሚያ የተባለችውን በውሃ የተከበበች መሬት ከዩክሬይን ወስደው ወደ ግዛታቸው ሲቀላቅሉ፣ ከውግዘት ባለፈ ምንም እንቅፋት አልገጠማቸውም። ጦራቸውን ወደ ኪየቭ ሲያዘምቱ ግን ጊዜው መለወጡን አሜሪካና አውሮፓ አስረድተዋቸዋል።
ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ግማሽ ምዕተዓመት በዘለቁበት የፖለቲካ ሕይወት፣ ቭላዲሚር ፑቲንን በደንብ አስተውለዋል። ፍራቻቸው ሩሲያ  በዩክሬይን ብቻ አትመለስም፤ ከዛም ትገፋለች ነው። ፑቲን ግን “ሶቪየት ሕብረትን የማይናፍቅ ልብ የለውም። እሱን ለመመለስ የሚጥር ደግሞ አይምሮ የለውም” በሚል የመስፋፋት ጉጉት እንደሌላቸው በተደጋጋሚ አሳስበዋል። ዓላማቸው ዩክሬይንን “ናዚስት” እያሉ ከሚጠሯቸው ሃይሎች ማፅዳት እንደሆነ አስገንዝበዋል። 
በዩክሬይን ላይ የተሰነዘረውን ጥቃት ተከትሎ ሀገሪቱን ያሽመደምዳሉ የተባሉ የገቢ ወጪ ንግዶች ላይ ማዕቀብ ተጥሏል። በውጭ ባንኮች የተቀመጠ በመቶ ቢሊየን የሚቆጠር ዶላር አይንቀሳቀስም። ትልልቅ የሀገሪቱ ባንኮችም እጅ እግራቸው ታስሯል። ከፑቲን ጋር ቅርበት ያላቸው ባለሀብቶች በሳተላይት ሁሉ እየተፈለጉ፣ ውድ የመዝናኛ ጀልባዎቻቸው መልሕቅ በጣሉበት እንዲረጉ ተደርገዋል። በታላላቅ ከተሞች የገዟቸው ቤቶች እግድ ወጥቶባቸዋል። የእንግሊዙ ቸልሲ ቡድንም ለሽያጭ የቀረበው ባለቤቱ ሮማን አብራሞቪች የፑቲን ወዳጅ ናቸው በሚል ነው። እነዚህ ሁሉ ሀብቶች በካሣ መልክ ለዩክሬይን የሚሰጡበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል።
ምክንያት
ሩሲያ “ልዩ ወታደራዊ ተልዕኮ” የምትለው ጦርነት በአንድ ጀምበር አተካራ የተጀመረ አይደለም። በ1991 ሶቪየት ሕብረት ተበታትና አስራ አምስት ሀገሮች ስትሆን ዩክሬይንና ሩሲያ ከማንም በላይ በባህል፥ በቋንቋና በሃይማኖት ተመሳሳይ ነበሩ። አብዛኛው ዩክሬይናዊ እንደ ሩሲያውያን ሁሉ የኦርቶዶክስ ክርስትና ተከታይ ነው። ጥንታዊቷ ሩሲያ ኪየቭስካያ-ሩስ ነው የምትባለው። ልዩነቱ እየሰፋ የሚሄደው በዩክሬይን ምእራባዊ ክፍል ሲሆን የካቶሊክ ሃይማኖትና የምዕራብ አውሮፓ ስሜት እያየለ ይሄዳል። ወደ ፖላንድ ድንበር ሲኬድ ያለችው ልቮቭ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ናት።
የሶቪየት ሕብረት መከፋፈል ወደ 25 ሚሊየን የሚደርሱ ሩሲያውያንን ወደተለያዩ ሀገሮች ዜግነት ቀይሯል። ከዩክሬይን 43 ሚሊየን ህዝብ ስምንት ሚሊየን የሚጠጋው ሩሲያኛ ተናጋሪ እንደሆነ ይገመታል። እነሱም በብዛት ያሉት ዶንባስ ተብሎ በሚታወቀው በአንፃራዊነት በኢንዱስትሪ በበለፀገው  የምሥራቁ ክፍል ነው። አዲሱ የዩክሬይናውያን ብሔረተኝነት፣ ሩሲያኛ ተናጋሪዎችን የሚገፋ ነገር ነበረበት። እነሱም ቢሆን ዩክሬይን ወደ ምዕራብ አውሮፓ በተለይም የኔቶ እቅፍ ውስጥ መግባቷን አልወደዱትም። እነዛ ለሰላሳ አመታት ያህል የቆዩ ፍትጊያዎች ናቸው የዚህ ጦርነት ምክንያት።
በዚህ አለምአቀፍ ፖለቲካ ውስጥ ዋነኛው ነገር ብሔራዊ ጥቅም ነው። ብሔራዊ ጥቅም ደግሞ ከምክንያታዊነት ጋር ሲላተም ይታያል።  ነገር በምሳሌ፦
ጓሮ ሜዳ
የምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ላይቤሪያ ዋና ከተማ ሞንሮቪያ ይባላል - ላይቤሪያ በተመሰረተችባቸው 1820ዎቹ አመታት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት በነበሩት ጀምስ ሞንሮ ስም። ፕሬዚዳንቱ በጣም የሚታወቁት ግን ‘የሞንሮ ዶክትሪን’ በሚባለው የውጭ ጉዳይ መርህ ነው። ይህ መርህ ምዕራባዊውን የዓለም ንፍቀ ክበብ የአሜሪካ ጓሮ ሜዳ አድርጎ ይመለከታል። መርሁ ላለፉት ሁለት መቶ ዓመታት ሠርቷል። እዛ ሰፈር አሜሪካን የሚፃረሩ አመለካከቶች አልቀናቸውም።
አንድ ጊዜ ቺሊ ውስጥ ሳልቫዶር አየንዴ የሚባል ግራ ዘመም ምሁር በምርጫ አሸንፎ ሥልጣን ቢይዝ፣ በሲአይኤ በታገዘ መፈንቅለ-መንግሥት የሕይወት ዋጋ ከፍሏል። ኒካራጉዋ በሶቪየት ድጋፍ ሶሻሊዝምን ብትሞክርም፥ አሜሪካ ኮንትራስ የሚባሉ አማፂዎችን በማስታጠቅ ሀገሪቱን የሽምቅ ውጊያ ቀጠና አድርጋለች። ከሁሉም ግን የተጎዳችው ኩባ ነች - በማዕቀብ ስትደቆስ ይኸው ስልሳ አመት። በ1959 እነፊደል ካስትሮ የሶሞዛን መንግሥት ገልብጠው ሥልጣን ሲይዙ፣ ግንኙነታቸውን ከሶቪየት ሕብረት ጋር አደረጉ። ቀደም ሲል አሜሪካ ጣሊያንና ቱርክ ውስጥ ለተከለችው ሚሳይል አፀፋ ለመስጠት ከአሜሪካ ድንበር 140 ኪሎሜትር በምትርቀው ኩባ፣ ሶቪየቶች ሚሳይል ተከሉ። ሚሳይሎቹ ይነሱ አይነሱ የሚለው ውዝግብ ሶስተኛውን የዓለም ጦርነት ያጭራል የሚል ስጋት ነበር። ‘የኩባ ሚሳይል ቀውስ’ የሚባለው ፍጥጫ በሚሳይሎቹ መነቀል እልባት አገኘ። ዋናው ጉዳይ እንዴት ደጃፌ ላይ ጦር ይተከልብኛል ነው።
በዚህ ስሌት ካየነው ዩክሬይን የኔቶ አባል ከሆነች ተፃራሪ የጦር ቡድን ደጃፍዋ ላይ መሣሪያውን ሲያነጣጥርባት ሩሲያ ዝም እንድትል አይጠበቅም። ከሶቪየት መፈራረስ በኋላ የቀድሞ ምስራቅ አውሮፓ ሀገሮች የኔቶ አባል ሲሆኑ ሩሲያ አቅም በማጣት ተቃውሞዋን ከማሰማት ውጪ ምንም ማድረግ አልቻለችም። ዩክሬይንና ጆርጂያ አባል መሆን በፈለጉበት ወቅት ግን ቀና ያለችበት ጊዜ ነበር። ጡንቻዋን በግሮዝኒ፥ በሶርያና በክራይሚያ አሳይታለች። በርካታ የዩክሬይን ከተሞችንም ወደ ፍርስራሽነት ቀይራለች።
የሩሲያ ስጋት
ሩሲያ ከማናቸውም ሀገሮች በበለጠ በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍላለች። በዛን ጊዜዋ ሶቪየት ሕብረት ወደ ሃያ ሰባት ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ  ሕይወቱን እንዳጣ ይታመናል። ጦርነቱ ካለቀ ከሰባ አምስት ዓመት በኋላም አሻራው አልደበዘዘም። ሙሽሮች በደስታቸው ቀን ባልታወቀው ወታደር መታሰቢያ ላይ አበባ ያኖራሉ፤ በየከተማው ባሉ ሀውልቶች ስር የሚንቀለቀሉት እሳቶች ለተሰዉት አርበኞች ዘላለማዊ ክብር ይሰጣሉ፤ ትውልዱ ታላቁ የአርበኝነት ጦርነት እንዳይረሳ፥ አባታዊ ሀገርን(አቴቸስትቫ) ማስከበር እንዳለበት ያሳስባሉ።
በ19ኛው ክፍለዘመንም ቢሆን እንደ”ጦርነትና ሰላም” የመሣሠሉ ሥራዎች የተፃፉባቸው የናፖሌዎንን ወረራዎች መክታለች። ናፖሌዎን አውሮፓን ሊውጥ ተቃርቦ በነበረ ጊዜ ጦሩ የተፈታው ሞስኮ ላይ ነው። ከዛ ማገገም ሳይችል ነው ወደ መጨረሻው የሴንት ሄለና ደሴት ግዞቱ ያመራው። ስለዚህ ሩሲያውያን የጦርነት እንቅስቃሴ ቢያሰጋቸው የሚጠበቅ ነው። ታሪካቸው አስተምሯቸዋል።
ሩሲያ በስፋት በዓለም አንደኛ አገር ነች። የበርካታ ማእድኖች፥ የደን ሀብት፥ የሣይንስ፥ የሥነጥበብ፥ በወታደራዊ አቋሟም እስከ ኒውክሊየር መሣሪያ የታጠቀች ሀገር ነች። እነ ሜንዴሌቭ፥ ፖፖቭ (ሳይንቲስቶች)፥ ቻይኮቭስኪ፥ ስትራቬንስኪ(ሙዚቀኞች)፤ ቶልስቶይ፥ ዶስቶየቭስኪ (የብዕር ሰዎች)፤ ካስፐርስኪ፥ ሰርጌይ ብሪን (የኮምፒውተር ጠበብት)፤ ጋጋሪን፥ ቴሬሽኮቫ (የጠፈር ሰዎች) እንዲሁም አሁን ሕዋ ላይ ያለው ሚር የተባለው ብቸኛው የጠፈር የምርምር ጣቢያን ብናይ እንኳ ሩሲያ ለዘመናዊው ዓለም ያበረከተችው አስተዋፅኦ ቀላል እንዳልሆነ እንረዳለን።
ሞስኮ መላውን ሩሲያን ባትወክልም የሃገሪቱን ሥልጣኔ ታሳያለች። የነጎርኪ ፓርክ ፅዳት፥ የአርባትስካያ ጎዳና ዘመናዊነት፥ የቨደንሃ ቋሚ ርዕይ ግዝፈት፥ የሽንኩርት ቅርፅ ያላቸው የክሬምሊን ጉልላት፥ የመዝናኛ ጀልባዎች የሚንሸራሸሩበት የሞስኮ ወንዝ፥ የምድር ባቡሩ ቅልጥፍና(ካመለጠዎት አይጨነቁ - የሚቀጥለው ሜትሮ በሁለት ደቂቃ ይደርሳል!)፤ የነባልሾይ ቴአትር ኪነ ሕንፃ ሩሲያ የአንደኛው ዓለም ሀገር መሆኗን አስረግጠው ያሳያሉ። በመሃል ሞስኮ የሚገኙት ጉምና ፁም የተባሉት የገበያ አዳራሾች የኔ ብጤው ዓይኑን ሲያንከራትት የሚውልባቸው ናቸው። እነ ቨርሳቺና ፕራዳ እዛ ሰፈር ብርቅ አይደሉም። የመደብሮቹ መኖር የሕዝቡን የመግዛት አቅም ያሳያል።
ቭላዲሚር ቭላዲሚሮቪች
አመራርን በተመለከተ ግን ላለፉት 22 ዓመታት ሩሲያውያን ከፑቲን አልተላቀቁም። በምዕተ ዓመቱ መባቻ ላይ ሥልጣን ከያዙ በኋላ ሁለት ጊዜ በመመረጥ ስምንት አመታት መርተዋል። ገደባቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የራሳቸውን ሰው በቦታው ላይ አስቀምጠው ጠ/ሚኒስትር ሆነዋል። ከአራት አመት በኋላ ተመልሰው አሁን ድረስ በፕሬዚዳንትነት አሉ። ይህ ዘመናዊ ዛር (ንጉስ) ያደርጋቸዋል።
ቭላዲሚር ቭላዲሚሮቪች ፑቲን የሶቪየት የስለላ ተቋም ኬጄቢ ሰራተኛ ነበሩ። ለአምስት አመታትም በቀድሞዋ ምሥራቅ ጀርመን ድሬዝደን ከተማ ተመድበው ሰርተዋል። በዚህ የኬጂቢ ዳራቸው የተነሳ የስልክም ሆነ የድረ ገፅ መረጃ ልውውጥ ምሥጢራዊ ይሆናል ብለው አያስቡም። አሁን ምዕራባውያን በግል ማዕቀብ ሊጥሉባቸው ሀብታቸውንና ገንዘባቸውን ሲፈልጉ ምንም ያላገኙት ዱካ እያጠፉ በመጓዛቸው ነው።
ከሶስት ዓመት በፊት ሞስኮን አይቻታለሁ። በዝርዝር ሳንቲም በተከራየኋት ዕድሜ የጠገበች ክፍል ማታ ማታ ‘ፔርቪይ ካናል’ ላይ የማየው የዜና ዕወጃ፣ በፕሬዚደንቱ ውሎ ላይ የሚቆዝም ነው። ቀንም በየጥጋጥጉ ባሉት ሱቆች የሚታዩት የቀን መቁጠሪያዎች አብዛኞቹ የሳቸው ፎቶዎች ያሉባቸው ናቸው። ፑቲን ከወገብ በላይ ራቁታቸውን ሆነው ፈረስ ሲጋልቡ፥ አሣ ሲያጠምዱ፥ ጥቁር መነፅራቸውን አድርገው ሳይቤሪያ ላይ ደረታቸውን ሲያሰጡ፥ ወይም ለአንጋፋዋ ዘፋኝ አላ ፑጋቾቫ አበባ ሲያበረክቱ - ብቻ ፑቲን የማይታዩበትን ቦታ ማግኘት ያስቸግራል።
ፑቲን ያስተዋወቁን አርበኛ
ጦርነት ጀግኖችን ይፈጥራል። ከሁለት ወር በፊት ምን እንደነበሩ የማይታወቁት የዩክሬይኑ ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ዜሌንስኪ የአይበገሬነት ምልክት ሆነዋል። አንዳንዶች ከእንግሊዙ የሁለተኛው ዓለም ጦርነት መሪ ዊኒስተን ቸርችል ጋር እያመሳሰሏቸው ነው። የሩሲያ ወታደሮች ኪየቭ ሊደርሱ ሲሉ አገሩን ጥለው ይጠፋሉ የተባሉት የቀድሞው አዝናኝ ተዋናይ ዳገቱ ላይ የተገኙ ሰው ናቸው። በዛ አስቸጋሪ ሰዓት እሳቸው ብቻ ሳይሆን የቅርብ አማካሪዎቻቸው ሁሉ እንዳሉ ያሳዩበት የስልክ ምስል ከፍተኛ አክብሮትን አስገኝቶላቸዋል። በከተማቸው መንገዶችና በተለያዩ ስፍራዎች እየተገኙ ሕዝባቸውን አረጋግተዋል። አመራር ሰጥተዋል። ሩሲያ ባላሰበችው መንገድ ለዩክሬናውያን ጀግና ፈጥራለች።
በሰላሙ ጊዜ ሁለቱ ሞክሼዎች ‘ይዚክ ዳቬዲዮት ደ ኪየቫ’ን ይተርቱ ይሆናል። ምላስ ኪየቭ ያደርሳል።  ‘ዘመነ ግርንቢጥ’ ሆነና ዛሬ ኪየቭ የሚያደርሰው ታንክና መትረየስ ነው።

Read 8821 times Last modified on Saturday, 30 April 2022 20:34