Saturday, 23 April 2022 14:51

የትንሳኤ እንግዳ - የፈንዲቃ የባህል ማዕከል መስራች አርቲስት መላኩ በላይ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“ትከሻዬ ነው እዚህ ትልቅ መድረክ ያደረሰኝ”

              ከገጠር የመጡት ትክክኛዎቹ አዝማሪዎቹ ናቸው ትክክለኛውን ሥራ የሚሰሩት
ከተለያዩ የዓለም አገራት በርካታ ሽልማቶችን የተቀበለው የውዝዋዜ  ጠቢቡ፤ በቅርቡ ደግሞ እነ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በተናገሩበት መድረክ ስራውን ለማቅረብ ችሏል።
የ”TEDD Fellwow 2022” እጩ ሆኖ በካናዳ ቫንኮቨር ተገኝቶ ብዙዎች የተደመሙበትን ጥበባዊ ክዋኔ አቅርቦ ተመልሷል። የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛዋ ናፍቆት ዮሴፍ አርቲስቱን የትንሳኤ እንግዳ በማድረግ፤ ይህን ጨምሮ በሙያ ህይወቱ ዙሪያ እንዲህ አውግታዋለች።
አርቲስት መላኩ በላይ ለየት ባለውና ትኩረት በሚሰጠው ባህላዊ ውዝዋዜው   ይታወቃል። ከልጅነት እስከ ዕውቀት በውዝዋዜ ጥበብ ነው የኖረው። የትከሻ ቋንቋ ይለዋል - አርቲስቱ። ለ12 ዓመታት ያለ ደመወዝ በሽልማት ብቻ በፈንዲቃ ባህል ማዕከል መስራቱን የሚያስታውሰው የውዝዋዜ ባለሙያው፤ ያላየው የዓለም ክፍል እንደሌለ ገልጿል።
በ1990ዎቹ በካዛንቺስ አካባቢ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ 17 ገደማ ባህላዊ የአዝማሪ ቤቶች 16ቱ በልማት ፈርሰው፣  አዝማሪዎቹ  የሥራ ዘርፋቸውን ቀይረው አሁን የቀረው አንድ ለእናቱ  የሆነው “ፈንዲቃ” ብቻ እንደሆነ ይናገራል። እሱም ቢሆን ፎቅ መሥራት ካልቻለ ለመፍረስ ጫፍ ላይ መሆኑን ተናግሯል። ከጥበብ የተጣላ አገር ማደግ አይችልም የሚለው አርቲስቱ፤ መንግስት የጥበብ ቤቶችና ቅርሶችን እያደነ ማፍረሱ ግራ የሚያጋባ  እና ሊታሰብበት የሚገባ ነው ብሏል።


            ሀገርህን ወክለህ የተገኘህበት “ቴድ ፌሎው” እጅግ ታላላቅ ዓለም አቀፍ ሰዎች ተገኝተው ንግግር የሚያደርጉበት መድረክ ነውና ይህን እድል እንዴ አገኘህ?
እኔ እንግዲህ ሰው ያውቀኛል፣ ያከብረኛል ብዬ የማልጠብቀውን ያህል፣ ነገሩ ከምጠብቀው ውጪ ሆኖ ነው ያገኘሁት። እና እዚህ በምሰራው  ስራ የሚያደንቀኝና የሚያግዘኝ ሰው  አለ።  ይህ ሰው ሲቪዬን ተጠቅሞ ለቴድ ፌሎው አመለከተልኝ። በዚህ መርሃ ግብር ላይ  ከመላው ዓለም ከ1 ሺህ 700 በላይ ሰዎች አመልክተው ነበር። ከዚህ ሁሉ ሰው ለዋናው የመጨረሻ አቅራቢነት የተመረጥነው 20 ሰዎች ብቻ ነን… አስቢው። እኔ ከዛ በፊት ስለዚህ ተቋም ሰምቼም አላውቅም። እጩ መሆኔ ከተነገረኝ በኋላ ይህን የሰሙ ሰዎች “እንዴ ቴድፌሎው እጩ ሆንክ? ትልቅ መድረክ እኮ ነው” ሲሉ መስማት ጀመርኩ። በኋላ “ኮንግራጁሌሽንስ” የሚል መልዕክት ላኩልኝና፣ “በግል እንንገርህ እኛ ይፋ እስክናደርግ ግን ለማንም እንዳትገልጽ አሉኝ። አካሄዳቸው በጣም ጥብቅና በጥንቃቄ የተሞላ ነው። እኛ ሳንፈቅድ ይህንን ለህዝብ ይፋ ካደረግህ እንሰርዝሃለን” ነው ያሉኝ። ከዚያ እነሱ ሲፈቅዱ እኔም ይህንን ጉዳይ ይፋ አደረግኩኝ። ቀጥሎም ሰው መደቡልኝ።
ምን አይነት ሰው? ማለቴ ምን የሚያደርግልህ?
መናገር የምፈልገው ነገር ላይ እንድዘጋጅ የሚያግዙኝ ማለት ነው። ያለህ ስምንት ደቂቃ ነው። አራቱ ላንተ ንግግር፣ አራቱ ደግሞ ለተርጓሚህ” አሉኝ።
በእንግሊዝኛ ንግግርህን ማቅረብ ነበረብህ። አንተ ግን በራሴ ቋንቋ በአማርኛ ነው ማቅረብ የምፈልገው ብለህ በመከራከርህ ማለት ነው?
አዎ! ግን ግራ ገባኝ። አራት ደቂቃ ምንድን ናት? ኢትዮጵያን አስቢያት። አድዋ፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ እምነት… የቱን አንስቼ የቱን ልተው ነው… አራት ደቂቃ የሚሉኝ? የሚል ጭንቀት ውስጥ ገባሁ። ከባድ ነው። በአራት ደቂቃ ውስጥ ኢትዮጵያን ከመግለጽ 1 ሺህ መጽሐፍ ማንበብ ይቀላል። እውነቴን ነው። ስለዚህ እኔ ወደ ትከሻ ቋንቋዬ ነው ያዘነበልኩት።
ወደ ውዝዋዜህ ማለት ነው?
አዎ! ለምን ብትይኝ ይሄ ትከሻዬ ነው እዚህ ትልቅ መድረክ ላይ ያደረሰኝ። እናንተም ታሪኬን እንደምታውቁት፣ እዚህ ፈንዲቃ የዛሬ 24 ዓመት የገባሁት በትከሻዬ ነው። ከ24 ዓመት ውስጥ 12ቱን ዓመት እዚህ ቤት ያለደሞዝ በሽልማት ብቻ ሰራሁ። 7 ዓመት ደግሞ ሳር ፍራሽ ላይ እዚሁ ቤት ባንኮኒ ስር ተኛሁ። እናም ይህ ሁሉ ያለፈው በትከሻዬ ነው።አሁን እዚህ ትልቅ መድረክ ላይ ስቀርብ ኢትዮጵያን በአራት ደቂቃ በአንደበቴ ለመግለጽ አልችልም። ኦሮምኛ አልችልም፣ ትግርኛ አልናገርም፣ ወላይተኛም ሆነ ጉራጊኛ የትኛውንም ቋንቋ አልችልም። ትከሻዬ ግን ሁሉንም የኢትዮጵያን ቋንቋዎች አቀላጥፎ ይናገራቸዋል። ስለዚህ ከአንደበቴ ይልቅ ትከሻዬ ነው ኢትዮጵያን የሚወክለው። በብሄር ብሄረሰቦች ዳንስ አብረን ጨፍረን ተግባብተን፣ ምንም አይነት ፖለቲካዊ ጭቅጭቅም ሆነ የዘርና ሌላ ጉዳይ ሳይነሳብን መግባባት ችለናል። ዳንስ ትልቅ የመግባቢያ ቋንቋ ሆኖ አስተሳስሮናል። ከአገር ውጪም ቢሆን ቻይንኛም ባልናገር፣ ፈረንሳይኛም ባልሰማ፣ ጣሊያንኛም ቋንቋ ባልናገር፣ ትከሻዬ ድልድይ ሆኖ ወስዶኛል።
ስለዚህ በትከሻዬ የምጫወታቸውን የኢትዮጵያ ባህላዊ ጭፈራዎች እንዴት ለፍትህ እንደምጠቀምበት፤ ለትግል፣ ለነጻነት፣ ለእኩልነት እንዴት እንደምጠቀምበት  ቋንቋ ሆኖ ትከሻዬ ያወራልኛል። ለምሳሌ የቅርስ ቤቶች ሲፈርሱ፣ ጥበብ ሳይከበርና ሳይጠበቅ ሲቀር፣ ዳንስ እንደ ባህል ሳይቆጠር ሲቀርና ሲናቅ፣ ሰው ከጥበብ ሲጣላና ሲኳረፍ መቅኖ እንደሚያጣና ዓለምም ሆነች ሀገር ያለጥበብ እንደማትድን በዳንስ ውስጥ እንዴት ልግለጸው ብዬ አሰላስዬና አስቤ ዳንስን መርጫለሁ አልኳቸው።
ምን አሉህ ታዲያ?
ካልክ ይሁን አሉና መጀመሪያ ሰባት ሰው አዘጋጁልኝ። እነዚህ ሰዎች አማካሪዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው ትልልቅ ባለሙያዎች ናቸው። የ”ቴድፌሎው” ቋሚ በጎ ፈቃደኞች ሆነው ያገለግላሉ። እነዚህ ሰዎች በግላቸው፣ በሙያቸው ሲሰሩና ሲያማክሩ በሰዓት እስከ 500 ዶላር የሚያስከፍሉ ናቸው። መጀመሪያ ቃለ-መጠይቅ (ኢንተርቪው) አደረጉልኝ። በአጠቃላይ የኔን ህይወትና አስተሳሰብ በተመለከተ ማለት ነው። የፈንድቃ ሲቪው አላቸው። የእኔን ፍላጎት በድምጼ መስማት ፈለጉና በደንብ አናዘዙኝ ማለቱ ይቀላል። ከዚያ  በኋላ እኔ ዳንሱ ላይ በማተኮር በተሰጠኝ አራት ደቂቃ እንዴት ግብ መምታት እንደምችል የሚረዳኝን ያማክሩኝ ጀመር። በዚህ ሂደት በኦንላይን ለረጃጅም ሰዓት እየተገናኘን ስንሰራ፣ የሚያማክሩኝ ሰዎች ቁጥር 29 ደረሰ። 29ኙም ፕሮፌሽናል ናቸው። ቃለ-ምልልሱ እስከዛሬ የሰራሁት ብቻ ሳይሆን ወደፊትም ያቀድኩትን ኢንቨስትመንት ጭምር የሚያካትት ነበር። ይን ሁሉ አልፌ የ”ቴድ ፌሎው” አባል ስሆን የራሳቸው ባለሃብቶች አሏቸው፣ ለእቅዴ ሁሉ የሚያስፈልገውን ሁሉ ያመቻቻሉ ማለት ነው። ለምሳሌ ፎቅ ልሰራ ነው ፈንዲቃ እንዲህ ባለ መልኩ ከቀጠለ ሊፈርስ ይችላል። ስለዚህ እንዲህ አይነት ፕሮጀክት አለኝ። ይህን ያህል ነገር ወጪ ይፈልጋል ብዬ አመለክታለሁ ማለት ነው። እውነት ለመናገር ፈንድቃ አሁንም አደጋ ላይ ነው፤ ፎቅ ካልገነባሁ መንግስት ያፈርሰዋል። ከዚህም በፊት ታግለን ነው ያዳንነው። ለዚህ ነው ለቴድ መድረክ ዳንስን የመረጥኩት። ዳንስን ለትግል፣ ለነጻነት፣ ለኪነጥበብ ጥበቃ እጠቀምበታለሁ ያልኩት ለዚህ ነው።
ሁሉም እንደሚያውቀው እዚህ ፈንድቃ በሚገኝበት ዙሪያ፣ ከ17 በላይ አዝማሪ ቤቶች  ነበሩ፤16ቱ ለልማት በሚል ፈርሰዋል። 16ቱ ቤቶች ውስጥ ይሰሩ የነበሩ አዝማሪዎች ሥራ ቀይረው የሉም። ስለዚህ ቤት ሳይሆን ሰው ነው የፈረሰው፣ ትውልድ ነው የፈረሰው። ስለዚህ በሙያዬ እንደዚህ አይነት ነገሮችን ነው የምሟገተው። ይህንን ሀሳቤን ነው ያሰፈርኩት። እነዚህ አማካሪዎቼ በዚህ ሂደታችን ሀሳቤን ሲረዱ፤ “አትደንስልንም ወይ?” የሚል ጥያቄ አቀረቡልኝ። እኔ ብቻዬን መደነስ አልፈለኩም። ከእነሙሉ ክብሩ ባንዶች አሉኝ። “ትልቅ ኹነት እንደመሆኑ ዳንሱም በተሟላና ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ ቢደረግ እመርጣለሁ” አልኳቸው። “ሀሳብህ ጥሩ ነበር ግን ወጪው ብዙ ነው፤ ይህ ደግሞ ከእቅዳችን ውጪ ነው አሉ። “እሺ እዛው የጃዝ ባንድ አዘጋጁና እደንሳለሁ” አልኳቸው። “ችግር  የለም” ብለው በጣም ጥሩ የሚባለውን ባንድ አዘጋጁና “ዘፈን እንላክልህ” ሲሉኝ፣ ዘፈንም አትላኩ ሙዚቀኞቹንም ማወቅ አልፈልግም መድረክ ላይ ተገናኝተን ብቻ መደነስ ነው ምፈልገው አልኳቸው። ይህን ያልኩበት ምክንያት ዳንስ እራሱ የዓለም ቋንቋ ሆኖ፣ አንድ ቀን እንዴት ሀይል እንደሚሆን ለማሳየት ነው። “እርግጠኛ ነህ?” አሉኝ አዎ እርግጠኛ ነኝ አልኳቸው። “ይሄ በጣም የሚገርም ነው። እኛ አድርገነው አናውቅም” አሉ። “ግዴላችሁም እዛው መድረክ ላይ እንገናኝ” አልኳቸው።
ከዚያ ሄድኩኝ። ነጭ ልብሴን ለብሼ በባዶ እግሬ፣ ያው ከተፈጥሮ ጋር መገናኘትም ስላለብኝ፣ ብዙ መልዕክት እንዲኖረው አድርጌ ቀረብኩ። ያንን ሀሳቤን እኔ በአማርኛ፣ ተርጓሚዋ በእንግሊዝኛ አቀረብንና ባንዱ ጀመረ። ይዣቸው ሌላ ዓለም ገባሁ። በዚህ ክዋኔ በጣም በአስደናቂ ሁኔታ ነው የታየሁት። በጣም ገርሟቸው እስካሁንም የሚያወሩት እሱን ነው። የኢትዮጵያ መንፈስም አምላክም ከፊት ይመራኛል። ቅዱስ ሚካኤልም እሱ ነው ግርማ ሞገስ የሰጠኝ ፈጣሪዬን አመሰግነዋለሁ።
አየሽ የመጪው የዓለማችን ፖለቲካና የቴክኖሎጂ ሂደት ወሳኝ የሆነ ፕሮግራም ላይ ገብቶ እንቁ መሆን፤ ከእኔ አቅም በላይ ነው።
በ”ቴድ ፌሎው” ፕሮግራም ላይ ታዳሚ ለመሆንና በአካል ለመገኘት 10 ሺህ ዶላር፣ በኦንላይ ለመከታተል ደግሞ 150 ዶላር እንደሚከፈል ተገልጿል። ትልልቅ ሰዎችም ሀገራቸውን ወክለው ቀርበዋል በአጠቃላይ መድረኩ ምን ይመስላል?
እውነት ነው ተቋሙ ትልቅ ነው፣ በአካል ለመታደም 10 ሺህ ዶላር፣  በኦንላይን ለመታደም 150 ዶላር ያስከፍላል። ይህንን ገንዘብ የሚሰበስቡት ለቻሪቲ ስራ ነው። በዚህም ዙር ወደ 900 ሚሊዮን ዶላር መሰብሰባቸውን ሰምቻለሁ። የእኛን የተመረጥነውን የትኬት፣ የሆቴል፣ ምግብና መሰል ወጪዎች ግን  ራሳቸው ናቸው የሸፈኑት። ታዳሚው የሚከፍለውም እነዚህ ከዓለም የተመረጡ ሰዎች እነማን ናቸው ብሎ እኛን ለማየት ነው።
የገንዘብ ሽልማት አለው እንዴ?
የገንዘብ  ሽልማት የለውም። ከመላው ዓለም ካመለከቱ 1 ሺህ 700 ሰዎች ምርጥ 20ዎቹ ውስጥ መግባት፣ ከነዚህም ውስጥ በልዩና በአስደናቂ ሁኔታ መታየት ከገንዘብ በላይ ነው። በምንም የሚለካ ጉዳይ አይደለም። ይህ መድረክ ከዚህ በፊት እንደነ ባራክ ኦባማና ሌሎችም የዓለም ታላላቅ ሰዎች ንግግር ያቀረቡበት መድረክ ነው። እኔ ገና ለዚህ እጩ ስሆን በአሁኑ ወቅት የዓለማችን ቁጥር አንድ ቱጃር የሚባለው ሰው እንዲሁም የአየርላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚቀርቡበት ነው ሲባል እጅግ ነበር የጓጓሁት።
ከዚህ ቀደም ፈረንሳይ አገር፣ ሆላንድ፣ ሞሮኮ ኳታርና የመሳሰሉት አገራት ተሸልመሃል አገር ቤትም እንደነ “በጎ ሰው” ያሉ ሽልማቶችን አግኝተሀል። አለም አቀፍ ሽልማት ላንተ አዲስ አይደለም ማለቴ ነው። ሌላው በፈንድቃ የባህል ማዕከል በጃዝ ምሽትም ሆነ ኢትዮ ከለር  ባንድ ምሽት አልፎ አልፎ ጎራ ስንል የገረመን ከሀበሻው ይልቅ የውጭ ዜጎች አዳራሹን ሞልተውት ማየታችን ነው። እናም ከእኛ ይልቅ የውጪው ዓለም ይበልጥ የተረዳህ ሁሉ ይመስለኛል…።
ትልቅ ነጥብ ነው ያመጣሽው!! የውጪው ዓለም ቀድሞ በደንብ ተረድቶኛል። ሌላው እኔ በፈንድቃ ትልልቅ ስራ እየሰራሁ በዩቲዩብ መልቀቅ ምናምን የሚባል ነገር ውስጥ የለሁበትም ነበር። አንዳንዴ ዩቲዩብ ላይ የሚለቀቁ ስራዎችን ታያለሽ፤ ትታዘቢያለሽ መቼም። ከዚያ ኮቪድ መጣ። የኮቪድ መምጣት ብዙ ችግሮችን በዓለም ደረጃ አስከትሏል። ነገር ግን መጥፎ ነገር ሲመጣ ወደ መልካም አጋጣሚ የምትቀይሪበትን መንግድ መፍጠር ተገቢ ነው። የፈለገ ችግር ቢመጣ Never give up! እኔ ማለቃቀስ አልወድም። በኮቪድ ምክንያት ሁሉም ነገር ተዘጋግቶ ለሰባት ወር ችግር ሲከሰት እኔ ስራዬን በዩቲዩብ  መልቀቅ ጀመርኩ። አርቲስቶችን እየጠራሁ በኦንላይን አሰራ ነበር። ለወቅቱ ችግር ወቅታዊ መፍትሄ አመጣሁ ማለት ነው። ዋይፋይ አስገብቼ በኦንላይን ስራ ስጀምር ትልቅ ሪቮሉሽን አመጣሁ። በመላው አለም ፈንድቃ የበለጠ (ኤክስፖዠር) አገኘ ማለት ነው። የተለያየ ዓለም በስራ ሄጃለሁ። ነገር ግን በዩቲዩብ እኔ ያልሄድኩበት ሁሉ ቦታ ስራዬ ሄደና፣ “ይሄ ሁሉ አቅም  የት ነበር እስከ ዛሬ” የሚል ጥያቄ አስነሳ።
በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያም ህዝብ በጣም እየኮራ መጣ። በተለይ በውጪ የሚኖረው ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ ዲያስፖራ ሁሉ ኩራቱ እየጨመረ፣ ኢትዮጵያ ሄጄ ይህንን ቤት ካላየሁት እስከማለት ደረሰ ማለት ነው።
በተለይ አሁን ደግሞ የ”ቴድፌሎው” እጩ ስሆንና ጉዳዩ ሲወራ ሀገር ቤት ያለው ህዝብ በደስታ ነው የተነቃነቀው። ለኔ የ”ቴድፌሎው”ን ሽልማት በጣም ለየት የሚያደርገው፣ በተለይ በተለይ ያንቺ ወዳጅ ጋዜጠኛ ትዕግስት ታደለ (ቲጂ ዳና) ለፍታ ወዲህ ወዲያ ብላ ቤተሰቤን፣ የፈንድቃን አባላት አስተባብራ፣ አየር መንገድን አስፈቅዳ ልክ ተሸልሜ መጥቼ ከአውሮፕላን ስወርድ የተደረገልኝ አቀባበል ነው። ከእስከዛሬው ሽልማቴ ልዩ ያደርገዋል። አየር መንገድ ውስጥ ልጆቼ ሮጠው መጥተው ሲያቅፉኝ፣ ቤተሰቤ በድምቀት ሲቀበለኝ ለማመን ተቸግሬያለሁ። ትዕግስት ሰርፕራይዝ አድርጋኛለች፤ በጭራሽ አልጠበቅኩም ነበር። ምክንያቱም እስከዛሬ እየተሸለምኩ ስመጣ “አባከና” ብሎኝ የሚያውቅ የመንግስትም ሆነ ሌላ አካል የለም። ተመልከቺ… በተለያየ ምክንያት ምቹ ሁኔታ ሳይፈጠር ቀርቶ ገና ጣሊያን አገር የምሸለመው ሽልማት አለ፤ ገና ወደፊት የሚሆን ነው። ግን ከዚህ በላይ ምንም ሽልማት ቢመጣ አይደንቀኝም።
የአየር መንገዱ ብቻ እንዳይመስልሽ ከዛ መጥተን ፈንድቃ ገብቼ ነበር ወደ መኖሪያ ቤቴ መሄድ የፈለግኩት። ምክንያቱም የትም ቦታ ሄጄ ስመለስ ፈንድቃን ሳላይ ወደ ቤቴ ሄጄ አላውቅም። የዛን እለት ግን “አይ ቤት አርፈህ ትመለሳለህ”
ብለው ይዘውኝ ሄደው፣ አረፍ ብዬ ወደ ፈንድቃ ስመለስ እንግዳ ተጋብዞ፣ መድረክ ተዘጋጅቶ፣ ባንድ ዝግጁ ሆኖ ባነር ተሰቅሎ ቡፌ ተደርድሮ፣ እነ ሄኖክ  ተመስገን፣ ተፈሪ አሰፋ፣ ታደለ በቀለ፣ ፋንቱ ማንዶዬ፣ ስዩም ጥላሁን፣ አስናቀ ገብረየስ፣ እያዩ ማንያዘዋል… ማን የቀረ አለ ኢትዮ ከለር ባንድ፣ ፈንዲቃዎች፣ አዝማሪዎቹ  ማንም የቀረ የለም። እጅግ ነበር የተደነቅኩት። አየር መንገድ እኮ ጋሞዎቹ ባንዶች አልቀሩም ሲቀበሉሉኝ።  
ተጓዡ ሁሉ እያጨበጨበ ነው የተቀበለኝ እና “ቴድፌሎው” እዛ ካለው የመድረኩ ስፋት (ስታዲየም በይው)፣ ከመድረኩ ትልቅነት፣ ከሽልማቱ ከፍተኛነት ባሻገር እዚህ የተደረገልኝ አቀባበል ለየት ብሎብኛል፤ ኮርቻለሁም። ተመልከች… ይሄ ስዕል ሙዚቃው እየተሰራ እዚሁ መድረክ ላይ ነው ሰዓሊዋ የሳለችው። ኢቨንቱንና እኔን ይወክላል ብላ በትክክል ሀሳቧን ገልጻለች። እኔ ውስጧ ስላለሁ፣ እዚህ ፈንድቃ ውስጥ የምንሰራ ሰዎች የመንፈስ ትስስር ስላለን ሀሳቧን በስዕል  ለመግለጽ አልተቸገረችም። እንግዲህ ፈንድቃ አርት ጋለሪ፣ ቤተ-መጻህፍት፣ የህጻናት ስዕል መሳያና የተለያዩ ቀለማትን ማወቂያ፣ ሙዚቃና ሁሉንም የያዘ አርት የሚተነፈስበት፣ለኢትዮጵያዊያን አንድነትና ጥምረት ትልቅ ማሳያና ምሳሌ የሆነ ቤት ነው። በጃዙ ብትይ በአዝማሪው ሁሉንም አሟልቶ የያዘ ቤት ነው። ይህንን ሁሉ የምንሰራው ተተኪ ጀግኖችን ለማፍራት ነው።
ብዙ ጊዜ አዝማሪ ሲባል ወደ አዕምሯችን የሚመጡት አማርኛ ተናጋሪ አዝማሪዎች ብቻ ናቸው። እውነታው ግን ይህ እንዳልሆነ ለማሳየት በየክፍለሀገሩ እየዞርክ የትግራይ፣ ኦሮሞና ሌሎች አዝማሪዎችን ወደፊት የማምጣት ስራ ስትሰራ ነበር። በዚህ ነው ዩኔስኮ የ50 ሺህ ዶላር ተሸላሚ አድጎርህ የነበረው?
ዩኔስኮ ተሸላሚ ያደረገኝ እኔ ራሴ በፈንድቃ ውስጥ በሰራሁት ስራ ነው። ነገር ግን ያ ገንዘብ ሲመጣ እነዚህን አዝማሪዎች እየፈለግኩ ወደፊት የማምጣቱ ስራ ላይ እንድሰራ እድል ሰጥቶኛል። እንዳልሽው አዝማሪ ሁሌ ከተማው ላይ አማርኛ ተናጋሪ ብቻ እንደሆነ ይታሰባል። እድለኛ ሆኜ የኦሮሞ  አዝማሪ አገኘሁ። የትግሬውንም አመጣሁት። አንድ ላይ የሰራነውን ስራ አልረሳውም። እኔ የምሰራው ምልከታ መስጠት ነው።
ለምሳሌ በቴሌቪዥን የአዝማሪ ውድድር እንደሌላው ጥበብ ቢካሄድና አሸናፊዎች ቢሸለሙ፣ ህይወታቸው ቢቀየር ከስር ያሉት ይበረታታሉ፤ ይወጣሉ፤ ይጠቅሙናልም። አሁን እየጠፉ ነው ያሉት። ለዚህ ነው ዩኔስኮ 50 ሺህ ዶላር ማበረታቻ ሲሸልመኝ ጎንደር፣ ወሎ፣ ሱሉልታና ሌሎችም ቦታዎች እየሄድኩኝ ዓይነተኛ አዝማሪዎቸን እየፈለግኩ እያመጣሁ፣ በአንጋፋዎቹ ስልጠና እንዲሰጣቸው እያደረግሁ ያበቃኋቸው። ከቴአትር ቤት፣ ከያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት የሚወጡት ሽባ ሆነው ነው የሚወጡት። የቅዱስ ያሬድን ስም ይዘው “ያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት” እየተባሉ የሞዛርትንና የቪትሆቨንን ትምህርት ነው የሚያስተምሩት። ማሲንቆና ክራርን´ኮ ማይነር አድርገውታል። በኖታ ምስረታም እኮ ዕዝልና ሀራራይን  ሲሰራ ቅዱስ ያሬድ ይቀድማቸዋል። ይሄ ሁሉ ክብርና እውቅና አላገኘም፤ ይሄ ሁሌም ያበሳጨኛል። ከገጠር የመጡት ትክክለኛዎቹ አዝማሪዎች ናቸው ትክክለኛውን ስራ የሚሰሩት፣ ሲያስጨፍሩን ሲያበሩን የሚገኙት።
መላኩ በጣም የሚደነቅበትና የሚመሰገንበት አንዱ ጉዳይ አብረውት የሚሰሩትን ከመሬት ማንሳትና ማብቃት በመቻሉ ነው ይባላል። ከዌይተርነትና ከጽዳት አንስተህ ፕሮፌሽናል ተወዛዋዥ፣ ድምጻዊና መሳሪያ ተጫዋች ያደረግሃቸው እንዳሉ እሰማለሁ። እስኪ በዚህ ላይ ትንሽ አውጋኝ….
በምሳሌነት መሳይን ብናነሳ ዌይተር ነበር። አሁን የሁሉንም ብሄር ብሄረሰብ ጭፈራ በጣም በሚገርም ሁኔታ ይጨፍራል። የሙዚቃ መሳሪያዎችን ይጫወታል። ሳውንድ ማን ነው፣ ካሜራ ማን ነው። “ጉንጉን” የተሰኘ የራሱን ባንድ አቋቁሟል። እሙቹንም ብትወስጃት ውዝዋዜ ጀመረች አሁን ትዘፍናለች ብቻ ይህን ይህን ማውራት አልፈልግም። ብዙዎቹ ተለውጠዋል እነሱ ቢመሰክሩ ይሻላል።
እኛ አገር አንዳንዶች “እኔኮ አርቲስት ነኝ” በሚል ትንንሽ ስራዎች መስራት አይፈልጉም። ኔእ አርቲስት ነኝ ግን የፈንድቃ መጸዳጃ ቤት ቆሽሾ ካየሁ አጥባለሁ ዝቅ እላለሁ፤ ሀምብል ነኝ። የእነዚህ ልጆች ምሳሌ እኔ ነኝ። እኔ ዝቅ ብዬ እየሰራሁ በየት በኩል አልፈው ትዕቢተኛና ጉረኛ ይሆናሉ?
እኔ እንደሰው ነው የምኖረው፤ ከአንድ እንጀራ በላይ አልበላ፣ ሲደክመኝ የትም ነው የምተኛው። ብቻ አብረውኝ በሚሰሩት ልጆችና በእኔ መካከል፣ የጌታና የሎሌ ግንኙነት የለም። የመደብ መለየት ስራ የለም። ብዙ ሰው እንደ ምክር “ ለሰራተኛ ፊት አትስጥ” የሚለኝ አለ። እኔ ይሄ አባባል እራሱ ይዘገንነኛል። ሌላውና መታወቅ ያለበት፣ እኔ ችዬ በትዕግስት ስለማልፍ እንጂ ከሥርዓት የሚወጣ ስለሌለ አይደለም።
በአንድ ወቅት ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ሄደህ የውዝዋዜ ስልጠና ሰጥተህ ነበር ይባላል። እውነት ነው?
ሀርቫርድ ውስጥ የፒኤችዲ አስተማሪዎች አሉ። ጥናትና ምርምር ሲሰሩ ለእነሱ ግብአት ልሰጥ ነበር የሄድኩት።
ሀበሾች ናቸው?
ፈረንጆች ናቸው። ያው እንደምታውቂው አስተምራለሁ። ህጻናትን፣ ዲያስፖራውን አስተምራለሁ። በማስተምርበት ጊዜ እግረ መንገዴን ጥናትም እሰራለሁ። አንድ ጊዜ እስክስታ እንዴት መጣ ብዬ ስጠይቅ እራሱ  እስክስታ ባዩ “ኧረ አላውቅም” ይላል። አንድ ጊዜ አንድ ትልቅ ሰው  በዚህ ዙሪያ የሰጡት ቃለ-ምልልስ ገረመኝ። አንዲት ልጅ ወንዝ ውሃ ልትቀዳ ትሄድና ቀድታ ስትመለስ እባብ ሊነድፋት አንገቱን ቀጥ አድርጎ ይጠብቃታል። “ስ…ስ.. ስ.. “እያለ አንገቱን ሰግግ መለስ እያደረገ (በአንገቱ እስክስታን አሳየኝ) ከዚያ ደንግጣ ቆማ ግን የእባቡን አንገት እንቅስቃሴና  ስ..ስ..ስ… የሚለውን የምላሱን ድምጽ ትይዘዋለች እባቡ የሚለውን እያለች ከእባቡ ተረፈች። ከዚያ ልጅቷ ወደ ቤት ሄዳ ለቤተሰቧ “ እባብ ሊነክሰኝ ነበር” ትላቸዋለች። “እና እንዴት ተረፍሽ?” ሲሏት የእባቡን እንቅስቃሴ እያሳየች፣ እሱ የሚያደርገውን ነገርና እሱ የሚለውን እስክስ…  እስክስ እያልኩኝ ስቆም ጥሎኝ ሄደ አለች። አሁን ይሄ እንደ አፈ ታሪክ እየተቆጠረ፣ እንደ ቀልድ እየታየ አይጠናም፤ ትኩረት አያገኘም እንጂ ቢጠና ይሄ ክስተት የእስክስታ መጀመሪያ ሊሆን ይችላል። አገር በቀል እውቀቱ አልተጠናም፣ ዶክመንት አልተደረገም አልተከበረም። ዳንስ እራሱ እንደ ሙያ ገና አልተቆጠረም። እሱን ለማስከበር በምናደርገው ጥረት፣ አገር ቤት ሳንከበር ዓለም ስራችንን እያየ እያበረታታን ነው።
ሁሌ የሚያሳስበኝ ነገር አለ። አሁንም ቅርስ ማፍረስ፣ ቤት ማፍረስ አልቆመም። በተለይ ከጥበብ መጣላት ለማንም ጥሩ አይደለም። ራስ መኮንን ድልድይ አካባቢ “ ጉራማይሌ አርት ጋለሪ” አለ።
እዛ ቤት ውስጥ ብዙ ሰዓሊዎች አሉ፡፡ የሚገርም የአርት ገዳም ነበር፡፡ እዛ አካባቢ ለሰዓሊያን አንድ መንደር ሊሰጧቸው ሲገባ  በ3 ቀን ውስጥ ልቀቁ ሊፈርስ ነው ብለዋቸዋል፡፡ እንዲህ አይነት ነገር ሰሚ የሚያገኘው መቼ ነው? ማናችንስ ምን ዋስትና አለን? በነገራችን ላይ እንደነ ጋሽ ጥላሁን “የኢትዮጵያ ህዝብ ነው ሀብቴ” አልልም። የኢትዮጵያ ህዝብ ባለ ዕዳ ነው ይክፈል፡፡ አርቲስቱ በደንብ ከፍሏል፡፡ መክፈልና መጠበቅ ባይችል ቢያንስ መረዳት መገንዘብ መቻል አለበት፡፡ ሰይጣን ቤት ተሸንሽኖ ገበያ ሆኗል፤ ያሳዝናል፡፡ ምንድን ነው ነገሩ? ሞራል የሚባል ነገር እኮ አለ። እልህ ነው? አለማወቅ ነው ? አልገባኝም፡፡ አለማወቅ  ከሆነ ምልከታ እንስጥ፡፡ እልህ ከሆነ ከማን ጋር ነው እልሁ? እና ይሄ ነገር ትኩረት ማግኘት አለበት። እኔ በሙያዬ የምጋፈጠው እነዚህን ጉዳዮች ነው፡፡ ሁሉም ትኩረት ሊሰጠው ሊታሰብበት የሚገባው ጉዳይ  ነው እላለሁ፡፡ በመጨረሻ ለሁሉም የክርስትና እምነት ተከታዮች፤ እንኳን ለትንሳኤው በዓል አደረሳችሁ ማለት እፈልጋለሁ።


Read 3877 times