Monday, 25 April 2022 00:00

የዩክሬን ተፈናቃዮች ቁጥር ከ12 ሚሊዮን አልፏል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  ሁለት ወራትን ባስቆጠረውና ተባብሶ በቀጠለው የሩስያና የዩክሬን ጦርነት፣ በዩክሬን ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከ12 ሚሊዮን ማለፉንና ከአገሪቱ የተሰደዱ ሰዎችም ከ5 ሚሊዮን በላይ መድረሱን ያስታወቀው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፤ ዩክሬንን ጥለው ከተሰደዱት ሰዎች መካከል ግማሽ ያህሉ ህጻናት መሆናቸውንም ገልጧል፡፡
ተቀማጭነቱን በጄኔቭ ያደረገው የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መረጃ እንዳለው፣ ጦርነቱ 5.03 ሚሊዮን ሰዎችን ከዩክሬን እንዲሰደዱ ያደረገ ሲሆን ይህም ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ በምድረ አውሮፓ የተከሰተው የከፋ የስደት ቀውስ ነው ተብሏል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ የፋሲካን በዓል ምክንያት በማድረግ እስከ ነገ የሚቆይ የ4 ቀናት ተኩስ አቁም እንዲደረግ ባለፈው ማክሰኞ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ የተኩስ አቁሙ እርዳታ ለማድረስና ተጎጂዎችን ካሉበት በሰላም ለማስወጣት የታሰበ ነው ተብሏል፡፡
ሩስያ ካለፈው ሰኞ ጀምሮ በዩክሬን ምስራቃዊ ክፍሎች እንደ አዲስ ጥቃት መክፈቷን ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰንና የካናዳው አቻቸው ጀስቲን ትሩዱ ለዩክሬን ተጨማሪ የጦር መሳሪያ እርዳታ ለመላክ መወሰናቸውን እንዳስታወቁ የዘገበው ዘ ጋርዲያን፤ ኖርዌይ በበኩሏ 100 የሚሳኤል መከላከያዎችን መለገሷን አመልክቷል፡፡
ሩስያ ለዩክሬን ተሰልፈው ሲዋጓት የነበሩ የእንግሊዝ ወታደሮችን ማረክሁ ባለችበት ረቡዕ ዕለት፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ደግሞ ጦርነቱ በሰላማዊ ውይይትና ድርድር እንዲፈታ ለሁለቱ አገራት መንግስታት ጥሪ ማቅረባቸውን በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ መግለጻቸውን ፍራንስ 24 ዘግቧል፡፡

Read 1628 times