Saturday, 23 April 2022 15:17

"ስለ ኤርሚያስ አመልጋ እጠይቃለሁ"

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

                        "ስለ ኤርሚያስ አመልጋ እጠይቃለሁ"
                            በአዜብ ወርቁ


              እንደኔ እምነት፤ የአቶ ኤርሚያስ እስከዛሬ የታዩ የንግድ ሃሳቦች አሠራርና አካሄዶች በደንብ ተፈትሸውና ጠርተው በግልፅ ካልወጡ አደጋው እስከዛሬ የአቶ ኤርሚያስን ሃሳብና ቅስቀሳ አምነው ለከሰሩት ብቻ ሳይሆን፣ እሳቸውን እንደ ተምሳሌት ለሚያዩ ለወደፊት የንግድ ሥራ ፈጣሪዎች እንዲሁም ለሌሎችም ጭምር ነው።
ለመሆኑ አቶ ኤርሚያስ ወደ 70 ዓመት እየተጠጋ ባለው እድሜያቸው ተሳካላቸው የሚባለው፣ እሳቸውስ ተሳካልኝ የሚሉት ስራ የቱን ነው?
ወደ ኢትዮጵያ ኢምፖርት እየተደረጉ ይሸጡ እንደነበሩት Evian ያሉ የታሸጉ የመጠጥ ውሃዎችን ሃይላንድ በሚል ስያሜ በሀገር ውስጥ የማምረት ስራ መጀመራቸው? … ግን ሳይቀጥሉበት መቅረታቸው?
የከተማ ውስጥ የመኖሪያ አፓርትመንትና ቤቶች  ከአቶ ኤርሚያስ በፊትም በኋላም  ጀምረው የተሳካላቸውና በታማኝነት ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል አጠናቀው ቤት ያስረከቡም እያስረከቡ ያሉም፤ የከሰሩም፣ ያጭበረበሩም አሉ፡፡ የአቶ ኤርሚያስ አክሰስ ሪልእስቴት፣ ከ13 ዓመት በፊት 1.4 ቢሊዮን ብር በእምነት የሰጧቸው ቁጥራቸው ከ2ሺ በላይ የሆኑ ቤት ገዢዎችን  ይዘው ወድቀዋል፡፡
ከውጭ ሀገራት ዘመናዊ የባንክ አሰራር ሃሳብ አምጥተው የመሰረቱት ዘመን ባንክ ብቻ ተሳክቶ ዘልቋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ብሔራዊ ባንክ፣ የባንክ ሕግና አሰራር ስላለው፣ መቆጣጠር መከታተልና የአቶ ኤርሚያስን  ህገወጥ አካሄድ መጠየቅና ማገድ ስለቻለ ነበር፡፡ ዝርዝር ትግሉን በወቅቱ የነበሩት የቦርድ አባላት ይናገሩት።
አቶ ኤርሚያስ ካቋቋሟቸውና አክሲዮን  በመግዛት ከተቀላቀሏቸው ወደ 16 የሚጠጉ የተለያዩ የንግድ ድርጅቶች ውስጥ ይተገብሩት በነበረው ህግን ያልተከተለ፣ ግልጽነት የጎደለው፣ ለጥቅም ግጭት የተጋለጠ ግድየለሽነትና ድፍረት የሚስተዋልበት አሰራር፣ ድርጅቶቹን ለክስረት እንደዳረጋቸው ማስረጃዎች በግልጽ ይመሰክራሉ፡፡
የትኛው ስኬታቸው ነው አድናቂዎችን ያተረፈላቸው?
ባለ ምጡቅ አይምሮ፣  ያለ ዘመኑ የተፈጠረ፣ በማይመጥነው ሐገር ውስጥ የሚኖር፣ ሕዝቡ ያልተረዳው፣  #እሳቸው ይምሩን፣ ኢኮኖሚ ያማክሩ፣ ኢትዮጵያ ትጠቀምባቸው; ያስባላቸው?
በተምሳሌትነት፣ በአስተማሪነትና የክብር እንግዳነት መድረክና ሚዲያ በስፋት እንዲቆጣጠሩ (ፕሮሞት እንዲደረጉ) ያስቻላቸው  የትኛው ስኬት ይሆን??
እኔ ይሄ ፕሮሞሽን ያሰጋኛል። ምክንያቱም እኔ የዛ ተጠቂ ነኝ። ከዛሬ 14 ዓመት በፊት አካባቢ ኢንፎቴይመንት የተሰኘ መፅሔት ከአቶ ኤርሚያስ ጋር ቃለመጠይቅ አድርጎ ነበር። አቶ ኤርሚያስ ያላቸው ስጦታ ተናግሮ ማሳመንና ሰውን የመሳብ ችሎታ ይመስለኛል። ቃለመጠይቃቸውን አንብቤ በጣም ተሳብኩ። አክሰስ ሪልእስቴት ሲጀመር  ተሻምቼ፣ ቦሌ ሜጋ አካባቢ ለሚገነባ  አፓርትመንት ከፈልኩ።   ውል ለመፈረም ያኔ ቢሯቸው ይገኝበት የነበረው ምንትዋብ ሕንፃ፣ ከጓደኛዬ ከሜሊ ተስፋዬ ጋር ሄድን።
 አቶ ኤርሚያስ ቢሮ ውስጥ ወዲያ ወዲህ ሲሉ አገኘናቸው። በአክብሮት ከመቀመጫችን ብድግ ብለን ሰላምታ አቀረብንላቸው፣ አድናቆታችንን ገለፅንላቸው።  አቶ ኤርሚያስ የኪነጥበብ ሰው እንደሆንን ስላወቁ ጥበብን እንዴት እንደሚደግፉ፣ ስላቋቋሙት የሮክ ባንድ አጫወቱን።  በጨዋታችን መጨረሻ ከቢሯቸው ከመውጣታችን በፊት፡-  እኔና ባለቤቴ እዚህ ሀገር ከሪል እስቴት ቤት የመግዛት ፍርሃት እንደነበረብን፣ ከአክሰስ የገዛነው የሳቸውን ቃለ-መጠይቅ ካየሁ ጀምሮ በሳቸው ላይ እምነት ስላደረብኝና ስላመንኳቸው ብቻ መሆኑን ነግሬያቸው ነበር።
የአክሰስ ቤተ ገዢ ገንዘቡ መና እንደቀረ በተረዳበትና አቶ ኤርሚያስ ሀገር ጥለው በወጡበት ሰሞን ከተቋቋሙት የቤት ገዢ ኮሚቴ አባላት መካከል አንዷ ነበርኩ።  በኮሚቴነት በማገለግልበት ወቅት የበርካታ የከሰሩ፣ ጤናቸው የተቃወሰባቸው ፣ ትዳራቸው የፈረሰባቸው እጅግ የሚያሳዝኑ እስከዛሬም የማይረሱኝ የቤት ገዢዎችን  አሳዛኝ ታሪኮች አድምጫለሁ፤ በቅርበት ተከታትያለሁ።
አንዳንዶች አቶ ኤርሚያስ እድል ይሰጣቸው ሲሉም ይደመጣሉ፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ ብዙ እድል ተሰጥቷቸዋል፡፡  ለምሳሌ ሸሽተው ዱባይ በተቀመጡበት ጊዜ የአክሰስን ጉዳይ እሳቸው ቢመጡ ይፈቱታል የሚለው የእሳቸውና  የአድናቂዎቻቸው ሰፊ ቅስቀሳ፣ ብዙ ቤት ገዢዎችንና  የመንግስት አካላትንም ጭምር ስላሳመነ፣ ወደ ሐገር ተመልሰው አክሰስ ሪል ስቴትን ቢመሩና ቤቶቹ እንዲገነቡ ቢያደርጉ፣ ቤት ገዢዎች በሳቸው ላይ  ክስ እንደማያነሱ መንግስትም በቅድመ ሁኔታ ለተገደበ ጊዜ ያለመከሰስ መብት እንዲጠብቅላቸው፣ የደህንነት ጥበቃ እንዲደረግላቸው ስምምነት ላይ ተደርሶ፣ ወደ ሐገር ተመልሰው አክሰስ ሪልእስቴትን ለአንድ ዓመት አካባቢ የመምራት እድል ቢያገኙም፣ ግልጽነት የጎደለውና የብቻ አድራጊ ፈጣሪነት አመራራቸውን በመቀጠላቸው፣ ለመንግስትና ለቤት ገዢዎች  የገቡትን ቃልም ባለመፈጸማቸው ታስረዋል፡፡
እና እጠይቃለሁ… የትኛው፣ ጥረታቸውና ስኬታቸው ነው እነዚህን ሁሉ ሃላፊነት በጎደላቸው አካሄዶችና ግድየለሽነቶች የተፈጸሙ ግፎችን ሸፍኖ መድረክና ሚዲያ እንዲቆጣጠሩ፣ በስፋት ፕሮሞት እንዲደረጉ፣ እንዲደነቁ ያስቻላቸው ? ሌሎች እንደ እኔ በፕሮሞሽናቸው ሰለባ እንዳይሆኑ፣ እንዲጠይቁ ነው ይሄን ሃሳቤን ያካፈልኩት።

Read 923 times