ከትናንት በስቲያ በሒልተን ሆቴል በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተነገረው፣ ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ የተመዘገቡ የበጐ አድራጐት ማህበራትን ፋይል ለማጣራትና ምዝገባ ለማካሄድ የሰነድ ምርመራ በሚደረግበት ጊዜ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ተፈጥሮአዊ ባህሪው የበጐ አድራጐት ሥራ አለመሆኑ መረጋገጡን አቶ አሰፋ ተናግረዋል፡፡
ይህ በሚሆንበት ጊዜም የድርጅቶቹን አመራሮች በስልክ ያነጋገሯቸው መሆኑን ጠቅሰው፣ በጉዳዩ ላይ ከመግባባት ደረጃ መድረሳቸውንና ለማጭበርበር ተግባር ተሰለፈ ስለሚባለው ጉዳይ እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡
የበጐ አድራጐት ማህበራት በተለያዩ ምክንያቶች ሥራቸውን ቢያቆሙ፣ ቢዘጉ ወይንም ቢፈርሱ ሀብታቸው ለተመሳሳይ ዓላማ፣ተቀራራቢ ለሆነ ተግባር ወይም ደግሞ ለልማት ይውላል እንጂ መንግስት ሊዘርፈው አይችልም ያሉት አቶ አሰፋ፤ ሊወረስ ነው የሚባለው ዘገባ የተሳሳተ ነው ብለዋል፡፡
ጉዳዩን አስመልክቶ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ እንደተናገረው፤ ታላቁ ሩጫ አትራፊ ድርጅት ሆኗል መባሉን ተቃውሞ “እኛ አገር በስፖርት ማትረፍ ሃጢያት ነው፡፡ እንዴት በስፖርት ታተርፋላችሁ ይሉናል፡፡
በሌሎች አገራት ስፖርት ትልቅ የገቢ ምንጭ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በደንብ መነጋገርና መወያየት ይኖርብናል” ብሏል፡፡
ታላቁ ሩጫን እናቁም ብንለው እንኳን ልናቆመው አንችልም፡፡ ላረጋግጥላችሁ የምፈልገው ጉዳይ ቢኖር ለሚቀጥሉት 100 ዓመታት ታላቁ ሩጫ እንደሚካሄድ ነው ሲል ተናግሯል - አትሌት ኃይሌ፡፡