Monday, 25 April 2022 00:00

አሳዳጅ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ  

በእውቀቱ ስዩም

በእውቀቱ ስዩም Archives - Andafta Media

           የኑሮ ውድነት የማያሳስባቸው ነዋሪዎች፥ ደላላ፥ የመሬት ሽያጭ ሰራተኛ፥ ሰባኪ፥ ታዋቂ ዘፋኝና አነቃቂ ንግግር አቅራቢ ናቸው፡፡ ባለፈው አንድ የታወቀ አነቃቂ ነኝ እሚል ሰውዬ፣ ለአስር ደቂቃ አፉን ያለገደብ ወለል አድርጎ ከፍቶ ሲያዛጋ አየሁት፥ ጠጋ አልኩና "በውኑ ከዚህ አፍ መነቃቃት ሊወጣ ይችላልን?" ስለው በስንግ ቃርያ ጥፊ ወለወለኝ! ብታምኑም ባታምኑም የሌለ ነቃሁ! እውነት ለመናገር በንግግር መነቃቃት የሚባል ነገር የለም፥ በንግግር የሚነቃቃ ንግግሩ ሲጠናቀቅ ይተኛል፥ እውነተኛ አነቃቂዎች የሚከተሉት ናቸው፥ የደመወዝ ጭማሪ፥ የኢኮኖሚ እድገት፥ ፍትሀዊ አስተዳደር እና የቶሞካ ቡና፡፡
ባለፈው እኔና ምኡዝ በረንዳ ላይ ቁጭ ብለን ቡና ስንጠጣ፤
“ስማ፤ ዘመኑ ከፍቷል፥ ተጠንቀቅ" አለኝ
“እሞክራለሁ”
“በጊዜ እየገባህ ነው?”
“አዎ! ለምሳ ቤቴ ከገባሁ አልወጣም”
“ይህም በዛ! ተጠንቀቅ እንጂ ተንቦቅቦቅ አልተባልክም”
ድንገት አንድ ጎረምሳ በረንዳው ላይ ዱብ አለና ጠረጴዛው ላይ የነበረውን የምኡዝን ስልክ አፈስ አድርጎ ዘለለ፤ ምኡዝ ተከትሎት ሊሮጥ ሲቃጣ ክንዱን ያዝ አደረኩትና፤ “ቆይ! ትንሽ አቫንስ እንስጠው; አልኩት፥ ካሜሪካ ከመጣሁ ወዲህ ጂም ስላልሰራሁ ሌባው ሮጦ ያሯሩጠኛል ፥ፍሪምባዬ አካባቢ ያለውን ስብ እንዳቀልጥ ያግዘኛል ብዬ ተስፋ አድርጌ ነበር፥ ሌባው ግን ያልተጠበቀ ነገር አደረገ። ባቅራቢያው አቁሞት የነበረው ሞተር ሳይክል ላይ ጉብ ብሎ ኮለኮለው፥ እኔና ምኡዝ ስንከተለው አስፓልቱ ዳር ትራፊክ መብራት የያዘው ሌላ ኮስማና ሞተረኛ አየን፥
“አንተም የሱ ግብረአበር ሳትሆን አትቀርም" አልኩና ኮሌታውን ጨምድጄ ያዝኩት፡፡
“እረ ፖስተኛ ነኝ" አለ ሰውየው፡፡
“ጭራሽ ፖስታም መስረቅ ጀምራችኋል” አልኩና ከነሞተሩ በጠረባ ጣልኩት፥ ከጥቂት ደቂቃ በሁዋላ በማረኩት ሞተር ጓደኛዬን አፈናጥጬ ሌባውን ማሳደድ ቀጠልኩ። ሌባው ሞተሩን አግለበለበው! ጭራሽ የሆነ ጊዜማ እንደ አገው ፈረስ አቆመው፥ አንዱን ሲኖትራክ ዘለለው፤ ቀጥሎ ውሀ ልማትን የሚገምሰውን የባቡሩን ድልድይ እመመመር ብሎ አለፈው፥
በመጨረሻ ምኡዝ እንዲህ ሲል ሰማሁት፥
“ይሄ ልጅ ቀን ጎድሎበት ነው እንጂ ሆሊውድ ወይም ቦሊውድ ውስጥ የአክሽን ፊልም አክተር መሆን እሚችል ሰው ነበር፥ በል አባርረን እንድረስበትና ላፕቶፕ እንሸልመው”

Read 1644 times