Wednesday, 27 April 2022 00:00

ምቾት የነሳኝ የጠ/ሚኒስትሩ አገላለጽ

Written by 
Rate this item
(0 votes)


         ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

ሙክታሮቪች ኦስማኖቫ

                ጠቅላይ ሚኒስትራችን  ለብልፅግና አመራር የሰጡትን ስልጠና አየሁት። በበርካታ ጎኖች በመልካምነት የወሰድኩት ሀሳቦች አሉበት።  በስልጠናቸው ንግግሮች ያልተስማማሁባቸው የተወሰኑ ሀሳቦች አሉ። በየፈርጁ ማቅረብ ይፈልጋሉ። ይህች አገላለፃቸው ግን ከሌላው ለየት ስላለችብኝና  ምቾት ስለነሳችኝ ስሜቴን ላጋራ፤
“አንዳንዶች ጠዋት የዩኒቨርሲቲ አስተማሪ ናቸው፤ ከሰዓት አክቲቪስት ናቸው” ብለዋል።
ታዲያ ይህ ምን ችግር አለው? ስራቸውን እስካልበደሉ ድረስ የተማሩ ሰዎች፣ ለሀገራቸው በመቆርቆር፣ ስለ ሀገራቸው መጨነቃቸውና ህዝብን ማንቃታቸው ምን ችግር አለው?
በሚሰሩት የአክቲቪስትነት ስራ ያጠፉ ካሉ በህግ መጠየቅ ነው። በደፈናው በዩኒቨርሲቲ ውስጥ እየሰሩ ለሀገር በማሰብ፣ ሀሳብ የሚያሻግሩና ሀገር የሚያበጣብጡትን አብሮ መጨፍለቅና መፈረጅ አግባብ አይመስለኝም።  ለምሳሌ እኔ አስራአምስት አመት አስተምሬያለሁ። ያስተማርኳቸው በርካታ  የህግ ምሩቃን  ህይወታቸው ተለውጧል። በህግ ከአላባማ ዩኒቨርሲቲ የማስትሬት ድግሪ ከያዝኩ 11 አመት ይሆነኛል። በህግ ትምህርቴ ጠበቃ ብሆን፣ ይሄኔ ሀብታም ነበርኩ። ግን የምርጫ ጉዳይ ነውና መምህር ነኝ።
እዚህ በፌስቡክ የምጨቃጨቀውና የምሰደበው፣ እና ደግሞ ዘልዛላ ተደርጌ የምቆጠረው፣ የኢትዮጵያ ጉዳይ ስለሚያንገበግበኝ ነው። እንደኔ በርካቶች አሉ። ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በትንሽ ደሞዝ እየማቀቁ ያሉ መምህራን፣ ስለ ሀገራቸው ግድ ብሏቸው፣ ሀሳባቸውን መግለፃቸውና ህዝባቸውን ማንቃታቸው ሊወደሱበት እንጂ ሊወቀሱበት አይገባም።  ህቅ እንቅ በሚያደርግ ደሞዝ ውስጥ ሆነው ለሀገራቸው በማሰብ፣ ሀሳባቸውን የሚያጋሩትን ማድመጥ እንጂ መፈረጅ በፍፁም አይገባም
ብልፅግና የራሱን ካድሬና አመራር በመግራት፣ ለህዝብም ለራሱም እንዲበጅ ይስራ። የተጋረጡበትን መሰናክሎች ይቅረፍ። ፍረጃ ለወያኔም አልበጀውም። ስለ ሀገር መቆርቆር ህሊናችን የጣለብን እዳ ስለሆነ ነው እንጂ ተራ ላይክና ኮሜንት ፈልገን አይደለም።
ኢትዮጵያ ነፍስ ስለሆነች ነው።

Read 1557 times