Friday, 29 April 2022 00:00

ዊሊያም አሳንጄ ለአሜሪካ ተላልፎ እንዲሰጥ ፍ/ቤት ወሰነ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

     175 አመታት በሚደርስ እስር ሊቀጣ ይችላል ተብሏል

               በለንደን በእስር ላይ የሚገኘውና የበርካታ አገራት መንግስታትን፣ ግለሰቦችንና ባለጸጎችን የግል ሚስጥራዊ መረጃዎች እየጎለጎለ በአደባባይ በማስጣት የሚታወቀው የዊኪሊክስ ድረገጽ ባለቤት ዊሊያም አሳንጄ፣ ከ10 አመታት በላይ ስታድነው ለኖረችው አሜሪካ ተላልፎ እንዲሰጥ የእንግሊዝ ፍርድ ቤት ባለፈው ረቡዕ መወሰኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
አሜሪካ ከ10 አመታት በፊት #ወታደራዊና የደህንነት መረጃዬን ዘርፎ አሰራጭቶብኛል፤ ሰልሎኛል; በሚል ስታሳድደው የኖረችውና 18 ክሶችን የመሰረተችበት አሳንጄ፤ ከአሜሪካ መንግስት ለማምለጥ 7 አመታት ለንደን በሚገኘው የኢኳዶር ኤምባሲ ጥገኝነት ጠይቆ መቆየቱንና ካለፉት 3 አመታት ወዲህ በዚያው በለንደን በሚገኝ ቤልማርሽ የተባለ እስር ቤት እንደሚገኝ ያስታወሰው ዘገባው፣ ፍርድ ቤት ባለፈው ረቡዕ አሳንጄ ለአሜሪካ ተላልፎ እንዲሰጥ ቢወስንም ፍርዱ ተፈጻሚ የሚሆነው የእንግሊዝ የሃገር ውስጥ ሚኒስቴር ሲያጸድቀው ብቻ መሆኑን አመልክቷል፡፡
የለንደኑ የዌስትሚኒስቴር ፍርድ ቤት አሳንጄ ለአሜሪካ ተላልፎ እንዲሰጥ ውሳኔ ቢያስተላልፍም፣ የግለሰቡ ጠበቆች ግን ውሳኔውን እንዳያጸድቁ ለእንግሊዝ የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አቤቱታቸውን እንደሚያቀርቡና ውሳኔው የሚጸድቅ ከሆነም አሳንጄ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔውን በመቃወም ይግባኝ የመጠየቅ መብት እንዳለው ዘገባው አመልክቷል፡፡
የዊሊያም አሳንጄ ጠበቆች ግለሰቡ ለአሜሪካ ተላልፎ የሚሰጥና በአሜሪካ ችሎት የሚዳኝ ከሆነ እስከ 175 አመታት እስር የሚደርስ ቅጣት ሊጣልበት እንደሚችል ስጋታቸውን መግለጻቸውንም አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
የ50 አመቱ አውስትራሊያዊ ዊሊያም አሳንጄ ከሶስት ሳምንታት በፊት በእስር ላይ በሚገኝበት የእንግሊዙ ቤልማርሽ እስር ቤት ከረጅም ጊዜ የፍቅር ወዳጁ ስቴላ ሞሪስ ጋር የተሞሸረ ሲሆን፣ በጥንዶቹ የሰርግ ስነስርዓት ላይ የታደሙት 2 አፈራራሚዎችና 2 ጠባቂዎች ብቻ እንደሆኑ መዘገባችን ይታወሳል፡፡


Read 3454 times