Monday, 25 April 2022 06:13

ከሬጌ ሙዚቃ ድግሶች ጀርባ ያለችው ሴታታ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ሬጌ ሙዚቃን ምንም ከኢትዮጵያ  ልንለየው የማንችል ነው። የሬጌ ሙዚቃ ፍቅር፤ እኩልነት፤ ነፃነት፤ ሰላም፤ ደግነት እና የሰው ልጅ አንድ መሆንን የሚዘምር ነው።  ትውልድ ራሱን ፈልጎ የሚያገኝበት ነው።”
ማህሌት (ሐና) ሰለሞን

           የመጀመርያው ዘላን ፌስቲቫል ሚያዚያ 22 ላይ በፋና ፓርክ ይካሄዳል፡፡ ከዚህ ዓለም አቀፍ ደረጃ ካለው ፌስቲቫል በስተጀርባ ያለችው ጠንካራ ሰው ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ማህሌት (ሐና) ሰለሞን ትባላለች፡፡ የሬጌና  አፍሮቢት ሙዚቃና ሙዚቀኞች ቱር ማናጀር፤ የኮንሰርት አዘጋጅና አቅራቢ፤  ሼፍና ዓለም አቀፍ የስነምግብ ባለሙያ፤ naturopathic  እንዲሁም የአምስት ልጆች እናት የሆነችው ማህሌት ለአዲስ አድማስ የሰጠችው ልዩ ቃለምልልስ ከዚህ በታች እንደቀረበው ነው፡፡

   
             ከኢትዮጵያ ወደ ጀርመን  ከዚያም ኦስትሪያ
ማህሌት (ሐና) ሰለሞን ተወልዳ ያደገችው  ቦሌ አካባቢ ልዩ ስሙ ኦሎምፒያ ሰፈር ነው። አዲስ አበባ ላይ ብዙ ትምህርት ቤቶችን አካላልለች፡፡ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርቷን  በመሰረተ ክርስቶስ የቀሰመች ሲሆን ሰባተኛና ስምንተኛ ክፍልን ደግሞ በፈለገ ዮርዳኖስ ተምራለች፡፡ ከቤት የበለጠ ስነምግባርን  በፈለገ ዮርዳኖስ መማሯን በአድናቆት ታስታውሳለች። ሃይስኩልን ደግሞ ለሁለት ዓመት በምስራቅ አጠቃላይ፤ ለሁለት ዓመት ደግሞ በቦሌ ትምህርት ቤቶች ተከታትላ ነው የጨረሰችው፡፡
ከኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ የወጣችው ከመላው ቤተሰቧ ጋር በጀርመን ፍራንክፈርት  ለመኖር ነው፡፡ በወጣትነቷ   መሰደዱን ባትፈልገውም ከዘመድ አዝማድ የነበረውን ግፊት መቀበል ግድ ሆኖባታል፡፡ ጀርመን ውስጥ ቮኬሽናል ትምህርት ቤት በመግባት የሙያ ትምህርት ስትማር ቆይታ ለመጨረስ 1 ዓመት ሲቀራት በትዳሯ ምክንያት ወደ ኦስትሪያ አቀናች። እስካሁንም ከልጆቿና ከቀድሞ ባለቤቷ ቤተሰቦቿ ጋር የምትኖረው በዚያው ነው፡፡ ኦስትሪያን የቤት እመቤት ሆኗ ልጆቿን በስርዓት ያሳደገችበት አገር መሆኗን ትገልፃለች። አምስት ልጆቿን እያሳደገች ቤት ውስጥ ስትቀመጥ  ስለህይወት ብዙ ነው የተማረችው፡፡
ኦስትሪያ እንደገባች ብዙ ፈተና ነው የገጠማት፡፡ ከአዲስ አበባ ከተማ ወጥታ ኦስትሪያ  ውስጥ ገጠር አካባቢ መኖር ስትጀምር ማማረሯ አልቀረም፡፡ ሰላምና ፀጥታ የሰፈነበት ገጠር ውስጥ መቆየት ከተፈጥሮ ጋር ተጣብቆ መኖሩን የምትለምደው አልመሰላትም። ዛሬ ላይ ግን በኦስትሪያ ስላሳለፈችው አስደሳች ህይወት አውርታ አጠግብም፡፡ የልጆቿ አባትና አያቶቻቸው ስለህይወት፤ ስለባህል ብዙ አስተምረዋታል፡፡ በተልዕኮ ትምህርት የተለያዩ ኮርሶችን በመውሰድም ሙያዎቿን አጠናክራለች፡፡ የተፈጥሮ መድሃኒትን  በማጥናት ቤተሰቧንም በእውቀቷ ለመንከባከብ በቅታለች። በአኗኗር ተፈጥሯዊ መሆንን፤ ስፖርት ማዘወተርን፤ በአመጋገብ ጥንቃቄ መውሰድን፤ የመስክ ጉዞና ካምፒንግ ማድረግን በቤት እመቤትነቷ በኦስትሪያ ኑሮዋ የተማረቻቸው ልዩ ዝንባሌዎች መሆናቸውንም ታስረዳለች። ከተፈጥሮ ጋር መዋሃድን፤ ህይወትን አቅልሎ መኖርን፤ ስለውጫዊውው ሳይሆን ስለውስጣዊው ማንነት መጨነቅን፤ ታማኝነትን ስለቀሰምኩባት ኦስትሪያ አውሮፓን እንድወድ ያደረገች አገር ብላ ነው የምታደንቀው፡፡
ወደ ሬጌ ሙዚቃ ኢንዱስትሪው


ለሬጌ ሙዚቃ ያላት ዝንባሌና አድናቆት ገና በወጣትነቷ ኢትዮጵያ ውስጥ የተጠነሰሰ ነበር። ገና በልጅነቷ ሬጌን መስማት እንደጀመረችና ከልቧ እንደወደደችው ስትናገር፤ አገሯን እንድትወድ ህዝቧን እንድታከብር ማድረጉን ጠቅሳለች፡፡ የአጼ ሐይለስላሴን፤ የኢትዮጵያን ታሪክ ወደኋላ ተመልሶ ለማጥናትም አስችሏታል፡፡ “ሬጌ ሙዚቃን ምንም ከኢትዮጵያ  ልንለየው የማንችል ነው። የሬጌ ሙዚቃ ፍቅር፤ እኩልነት፤ ነፃነት፤ ሰላም፤ ደግነት እና የሰው ልጅ አንድ መሆንን የሚዘምር ነው።  ትውልድ ራሱን ፈልጎ የሚያገኝበት ነው።” በማለት አመለካከቷን ትጠቀልለዋለች፡፡
በዚህ የሬጌ አድናቂነቷ ሳቢያ የሙዚቃ ፕሮሞተር ለመሆን፤ ከእውቅ የሬጌ ሙዚቀኞችና ቡድኖች ጋር አገሯ ላይ የመስራት  ህልም ሰንቃለች፡፡  በጀርመን  ውስጥ ስትኖር ሬጌ ቻት ተብሎ በሚዘጋጅ  ኹነት ላይ ቋሚ ተሳታፊ ነበረች፡፡ በተለይ ወደ ታዋቂው የሬጌ መድረክ ሰመርጃም ሄዳ  ለመታደም የነበራትን ፍላጎት ብዙም ሳትቆይ ነው ያሳካችው፡፡  ኦስትሪያዊው የቀድሞ ባለቤቷም ከሙዚቃ ስራዎች ጋር በነበረው ቅርበት ከሬጌ ሙዚቀኞችና ከተለያዩ ፕሮሞተሮች ጋር የምትተዋወቅበትን እድል ፈጥሮላታል፡፡
በሬጌ የሙዚቃ ኢንዱስትሪው ላይ መስራት የጀመረችው  ከመድረክ ጀርባ  ነው፡፡ በአውሮፓ በሚካሄዱ ትልልቅ የሙዚቃ ድግሶች ላይ ከቤተሰቦቿ ጋር የተለያዩ የንግድ ስራዎችን ታከናውን ነበር፡፡ በጀርመንና በኦስትሪያ ብቻ ሳይሆን በሆላንድና በጣሊያን በሚካሄዱ የሬጌ ኮንሰርቶች እየተዟዟረች ተካፍላለች። ከጀብደኝነቷ የተነሳ በአንዳንድ ግዙፍ ፌስቲቫሎች የመኖርያ ፈቃድ ባይኖራትም የምትፈልገውን ሰፊ ልምድ ለማካበት ተንቀሳቅሳለች፡፡ ከታዋቂ የሬጌ ሙዚቀኞች ለመጀመርያ ጊዜ ያገኘችው አልፋ ብሎንዲ ነው፡፡ ይህኑ አጋጣሚ ስታስታውስም  አጠገቧ ሆኖ ሲያወራት በአክብሮት እጆቿ ይንቀጠቀጡ እንደነበር ሁሉ ትዝ ይላታል፡፡  በ1990ዎቹ ወጣትነቷን ያሳለፈች አዲስ አበቤ በመሆኗ ብርቅ ሆኖባታል፡፡ በእሷ ትውልድ ሬጌ ሙዚቃ ለመስማት ብዙ እድል አልነበረም፣፣ ሬጌ ሙዚቀኞችን በአካል ለማግኘት ይቅርና ሲዲያቸውን እንኳን ለማግኘት የማይታሰብ ነበር፡፡
በሬጌ ፌስቲቫሎች አውሮፓ ውስጥ እየተዟዛረች ስትሳተፍ ከቤተሰቧ ጋር ‹‹አይዞህ ዶርዜ›› የሚባሉ የባህል ልብሶችና ሌሎች እደ ጥበቦችን ከኢትዮጵያ በማስመጣት ትሸጥ ነበር። ከሬጌ ጋር በተያያዘ ይህን ልምዷን ካሳደገችው በኋላ ወደ ሌላ አዲስ ምዕራፍ ነው የገባችው። ከ400 ሺ በላይ ታዳሚ በሚያገኘው የቤልጅዬሙ ቱሞሮላንድ የሙዚቃ ፌስቲቫል  በሮድ ማናጀርነት ለመጀመርያ ጊዜ ሰራች፡፡ በኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ በሚታወቀው በዚህ ፌስቲቫል አራት ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸውን ዲጄዎችን ያሰራች ሲሆን  ዴቪድ ጉዬታ፤ ዲጀ ስካት እና ዲጄ ላምበርት የተባሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ለዲጄዎቹ  ሮድ ማናጀር በመሆን የምትሰራው የስራ መርሃ ግብሮቻቸውን በማመቻቸትና በቅደም ተከተል የማስኬድ ሃላፊነት ወስዳ ነው። ከዚህ ተመክሮዋ በኋላ በመላው አውሮፓ ያልደረሰችበት እና ያልነካችው የፌስቲቫል አይነት የለም፡፡ አርቲስቶችን ለኮንሰርቶችና ለፌስቲቫሎች ቡክ በማድረግ (ለመድረክ የሙዚቃ ስራ በማብቃት) በሙሉ ፍላጎት ስትሰራ አብዛኛውን ጊዜ በነፃ የምትሰራውና በበጎ ፈቃድ የምታደርገው አስተዋፅኦ ነበር የሚያስደስታት። በአውሮፓ የሚንቀሳቀሱ ታዋቂ ሙዚቀኞች አብረዋት ለመስራት ቢፈልጉም፤ የቤተሰብ ሃላፊነቷን ወደጎን ትታ ጨክና ወደ ስራው አልገባችበትም፡፡ ልጆቿን ከማሳደግ ጋር ጎን ለጎን ሙሉ ሃላፊነቱን ወስዳ ለመስራት ማመንታቷ አልቀረም፡፡ የሙዚቃ ኢንዱስትሪውን  የሙሉ ግዜ ስራዋ ሳታደርገውና ለአገልግሎቷ የሚገባው ክፍያ ሳያስጨንቃት ከተለያዩ ሙዚቀኞች ጋር ተቀራርባ እየሰራች ሰፊ ልምድ እያካበተች ቆየች፡፡ ዓለም አቀፍ ሙዚቀኞችን በትጋት ስታገለግል የሙዚቃ ፌስቲቫሎች፤ ኮንሰርቶች፤ ፌስቲቫሎችና በትልልቅ ከተሞች በሚካሄዱ የክለብ ስራዎች እንዲሳተፉ በማመልከትና እንዲሰሩ ማገዙን ተካነችበት፡፡ በሙዚቃ ኢንዱስትሪው ይህ ሙያዋ ስራው ቀላል የሚባል  አይደለም፡፡ ሙዚቃውን በግዙፍ መድረክ ወይም በክለብ ደረጃ ለመስራት የሚፈልግ ሙዚቀኛና ቡድንን ማስተባበርን ልዩ ብልሃትና ተግስትን ይጠይቃል፡፡ ፕሮሞሽን ከሚሰራለት ሙዚቀኛና ቡድን ጋር 24 ሰዓት ግንኙነት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ስኬታማ የሚባል ሁነት ለማካሄድም 3 እና 4 ወራት ቀድሞ መዘጋጀትም ይጠይቃል፡፡ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መስራትና መደራደር ውል ማሰር ውል ማፍረስን የሚያካትት ነው፡፡ በአንዳንድ ትልቅ እቅድ ምናልባት ከዓመት በላይ በልዩ ስነምግባርና የስራ ቅደም ተከተል  መንቀሳቀስም ግድ ይላል፡፡
በሙዚቃ ኢንዱስትሪው ላይ በማተኮር ሙሉ ሃላፊነት ይዛ ለመስራት ስትነሳ በመጀመርያ በአጋርነት አብራ የሰራችው ከዲጄ ዚጊድ ኢንተርቴይመንት ጋር ነው፡፡ዚጊድ ኢንተርቴይመንት በአፍሮቢት እርሷ ደግሞ በሬጌ ሙዚቀኞች ላይ ለመስራት የስራ ድርሻቸውን በመከፋፈል ተቀናጁ፡፡ በአውሮፓ ውስጥ የክለብና የኮንሰርት ስራዎችን ለሙዚቀኞች ተሳትፎ በማመልከትና በማመቻቸት ከዚህ ተቋም ጋር ብዙ ሰርተዋል፡፡  በአውሮፓ በተለያዩ አገራት በሚካሄዱ የሬጌ ፌስቲቫሎች ታዋቂ ሬጌ ሙዚቀኞችን በማሰራት የያዘችው ልምዷ ዛሬም ድረስ በኢንዱስትሪው ተዓማኒ እና ተፈላጊ አድርጓታል፡፡በ2022 እኤአ ላይ በእጇ ያሉ የሬጌ ሙዚቃ አርቲስቶችም ጥቂት አይደሉም፡፡
ታላላቅ የሬጌ ሙዚቃ ድግሶች በአዲስ አበባ
በአውሮፓ የተለያዩ አገራት ካከበተቻቸው አስደናቂ ልምዶች በኋላ ወደ አገር ቤት ለመመለስ የሚያስፈልገውን ወረቀት አሟልታ ስትመለስ ከዲያስፖራው የቀደማት እንዳልነበረ ነው በልበሙሉነት የምትናገረው፡፡ በሙዚቃ ኢንዱስትሪው የመጀመርያ ስራዋን ለማከናወን  ወደ አዲስ አበባ ለማምጣት ወስና ተግባራዊ ስታደርገው የገጠማት በፍፁም ያልጠበቀችው ነው፡፡ ከምታውቃቸው የሬጌ ሙዚቀኞችና ባንዶች መካከል የተወሰኑትን አስተባብራና አደራጅታ ሙሉ ወጭ በመሸፈን ወደ አዲስ አበባ መጣች፡፡ በሙዚቃ ኹነቱ ላይ አብሯት ሊሰራ የነበረ ግለሰብ ስልኩን አጥፍቶ ተሰወረባት። በዚህ ሙከራዋ  ኪሳራ ቢገጥማትም ተስፋ አልቆረጠችም፡፡ ከዚያን   በኋላ አውሮፓ ውስጥ በሚደረግ ታዋቂው የአፕራይዚንግ ፌስቲቫል ጋር ከሌላ ኢትዮጲያዊት ጋር ተገናኙ። ለ17 ዓመታት በመላው አውሮፓ በዳንስ ሙያዋ ዝነኛ ከነበረችው አሮን ሚቱ ጋር ነበር፡፡ እዛው አውሮፓ  ላይ ተመካክረው ኢትዮጲያ ውስጥ የዳንስ ዎርክሾፕ ለመስራት መጡና ተሳካላቸው።
የዳንስ ዎርክሾፑን በአዲስ አበባ በማዘጋጀት የተገኘው ልምድ ወደ ሌላ አዲስ እቅድ ተሸጋገረ። የሬጌ ሙዚቃ በከፍተኛ ደረጃ ኢትዮጵያ ውስጥ ለማዘጋጀት ነው፡፡ በ2014 እኤአ ላይ በመላው አፍሪካ ተዟዙረው እየሰሩ ከነበሩት የሬጌ ሙዚቃ ግዙፍ ቤተሰብ ሞርጋን ሄሪቴጅ ጋር በፈጠረችው ግንኙነት ወደ አዲስ አበባ መጥተው የክለብ ስራ እንዲሰሩ ጋበዘቻቸው፡፡ ለግራሚ ሽልማት የበቃው ሞርጋን ሄሪቴጅ የሬጌ ሙዚቃ ቡድን ወደ አዲስ አበባ ለመውጣት ሲወስኑ ዋና ምክንያታቸው ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅና ኢንዱስትሪውን ለማነቃቃት እንደሆነ ነግረዋታል፡፡ ይህ አይነቱን የትልቅ ሬጌ ሙዚቃ ቡድን በአዲስ አበባ ለማስተናገድ አብረዋት ከሰሩ ተቋማት በአድናቆት ያነሳችው ደግሞ በኢዮኤል የሚመራውን ኢኤምኤል ኤቨንትስ ነበር፡፡ የሴክሪዊቲ እና የኢንተርቴይመንት ተቋሙ እርሷ ከነበራት ራዕይ ጋር በብዙ ሃሳብ በመስማማት እና በመተባበር ሊሰሩ በቅተዋል፡፡ ከኢኤምኤል ኤቨንትስ ጋር ከሰራችበት ልምዷ በአዲስ አበባ ከተማ ኮንሰርት ለማዘጋጀት ያለውን ሁኔታ እና ስኬታማ መስተንግዶ ማድረግ የሚቻልበትን አዳዲስ ነገር ለመገንዘብ መብቃቷንም ከምስጋና ጋር ገልፃለች፡፡
ሞርጋን ሄሪቴጅ የሬጌ ሙዚቃ ቤተሰብ አዲስ አበባ መጥተው በክለብ ደረጃ ከሰሩ በኋላ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን ኮንሰርቶች አብዛኛዎቹን ከኢኤምኤል ኢቨንትስ ጋር እንዲሁም ሌሎች ወጣት ፕሮሞተሮችና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ለማካሄድ ተችሏል፡፡ ከኮሮና ወረርሽኝ  በፊትም እውቆቹን የሬጌ ሙዚቀኞች እና ሌሎች ታዋቂ ሙዚቀኞችን ወደ አዲስ አበባ ማስመጣት መደበኛ ስራ ሆኖ ለመለመድ በቅቷል፡፡ ማህሌት (ሐና) ሰለሞን በአዲስ አበባ ከሚንቀሳቀሱ በርካታ የፕሮሞሽን ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ጋር ስትሰራ በተከታታይ ለሙዚቃ ዝግጅት ከመጡት ዓለም አቀፍ ሙዚቀኞች መካከል ክሮኒኪስ፤ ፕሮቶጄ፤ ጄሲ ሮያል፤ ያድ ኮር፤ ጃህ9፤ ሞርጋን ሄሪቴጅ፤ ዴምያን ማርሌይ፤ ጁልያን ማርሌይ ይገኙበታል፡፡
ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ሙዚቀኞች ሲመጡ
እንደ ማህሌት አገላለፅ ታዋቂ ሙዚቀኞች ወደኢትዮጵያ ሲመጡ የተለያዩ ምክንያቶች ይኖራቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ የሙያ ዘመናቸውን ታሪክ ለማሳደግ የሚሰሩ ናቸው፡፡ እንደ ሞርጋን ሄሪቴጅ፤ ጄሲ ሮያል፤ ፕሮቶጄና የማርሌይ ወንድማማቾች ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ መስራት ብቻ ሳይሆን ለመኖር ያላቸውን ፍላጎት የሚገልፁበት ነው፡፡ ብዙዎቹ የሬጌ ኮከቦች ከሙዚቃ ስራው ባሻገር ከኢትዮጵያ ይዘው የሚሄዱትን ባርኮትና ቁምነገር ለመሰነቅ ነው የሚፈልጉት፡፡ በሙዚቃ ዝግጅቶቻቸውም ስለማነነታቸው ብዙ አውቀውና ተምረው ነው ወደመጡበት የሚመለሱት፡፡ አንዳንዶቹ ሙዚቀኞች ኢትዮጵያ ከመጡ በኋላ ተመልሰው ሲሄዱ በጣም ቅር እንደሚሰኙም ከነበራት ልምድ በማስታወስ ትገልፃለች፡፡ ፕሮቶጄና ጄሲ ሮያል ከስራቸው በኋላ ኢትዮጵያን ለቅቀው የሚወጡበትን ውሳኔ ለመቀበል ተቸግረዋል፡፡ እነ ሞርጋን ሄሪቴጅ ኢትዮጵያ ደርሰን ስነመለስ የግራሚ ሽልማት አሸንፈናል በማለት በይፋ እስከመናገርም ደርሰዋል፡፡ ማህሌት በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄዱት ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው የሬጌ ሙዚቃ ድግሶች ብዙ ውጤቶች መገኘታቸውንም በዝርዝር  ትገልፃለች፡፡ ከቦብ ማርሌይ 60ኛ ዓመት የልደት በዓል አፍሪካ ዩናይት በሚል በመስቀል አደባባይ ከተካሄደው ግዙፍ ኮንሰርት በኋላ ታሪክ የማይረሳቸውን ግዙፍ ኮንሰርቶች በአዲስ አበባ ለማዘጋጀት መቻሉ የመጀመርያው ነው፡፡ በኮንሰርቶቹ አማካኝነት አዎንታዊ መልዕክት ያዘለውን ሬጌ ሙዚቃ በመዝናኛነት ለመመልከት ተችሏል፡፡ ወጣቱን ትውልድ ለአገር ያለውን አመለከካት ወደ አዎንታዊ አስተሳሰብ ለመቀየር ጉልህ ሚና መጫወት ተችሏል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ለዓለም አቀፍ ሙዚቀኞች በግዙፍ መድረክ ለመስራት የተፈጠረው እድል በአገር ውስጥ ለሚገኙ ሙዚቀኞች ከፍተኛ እድል በመፍጠር በተሰጥኦዋቸው እንዲፈልቁ ለዩ እገዛ ተፈጥሯል።
ለወደፊቱን ኢትዮጵያን ወደ ላይ ለማውጣት
ማህሌት (ሐና) ሰለሞን አሁን ባለችበት ደረጃ የሬጌና  አፍሮቢት ሙዚቃና ሙዚቀኞች ቱር ማናጀር፤ የኮንሰርት አዘጋጅና አቅራቢ፤  ሼፍና ዓለም አቀፍ የስነምግብ ባለሙያ፤ naturopathic  እንዲሁም የአምስት ልጆች እናት ናት፡፡ በአውሮፓ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ የተለያዩ አገራት በኬንያ፤ በጋምቢያ፤ በኡጋንዳ እና ደቡብ አፍሪካ የረጌ ሙዚቀኞችና ባንዶችን ለፌስቲቫሎች በማስመዝገብ እና ለስራ በማደራደር እየሰራች ነው፡፡ ዋናው ህልሟ ግን ኢትዮጵያን በሬጌ ሙዚቃ ኢንዱስትሪው ዓለም አቀፍ መናሐርያ ማድረግ ነው፡፡ እንደ ማህሌት አመለካከት ሬጌ ዓለም አቀፍ መልዕክት ይዞ ነው የሚንቀሳቀስ በመሆን በአገር ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶት በቁምነገር መሰራት ይኖርበታል፡፡ እንደ ቀልድ መያዝ የለበትም፡፡ በአዲስ አበባ በተደጋጋሚ ካካሄደቻቸው ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው የሬጌ ድግሶች በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህን በከፍተኛ ደረጃ የመቀየር አላማ ነው ያላት፡፡ በሬጌ ሙዚቃ ያለውን አቅም ማህሌት ስትገልፅ የኮንሰርትና የመዝናኛ ኢንዱስትሪው በትክክል ከተሰራበትና የመንግስትና ባለድርሻ አካላት አቀናጅቶ እየተስፋፋ የሚሄድ ከሆነ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ይኖሩታል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግዙፍ የሙዚቃ መድረኮችን በማዘጋጀት ከመላው ዓለም ብዙ ጎብኝዎችን መፍጠር እንደሚችል፤ በአገር ውስጥ በሚካሄዱ ግዙፍ የሙዚቃ ኹነቶች ለመላው ዓለም አንጡራ ባህልና አቅምን የማሳየት እድል እንደሚፈጥር እንዲሁም ገፅታን እንደሚገነባ ፤ ለሙዚቃ ብሎ የሚመጣን ቱሪስትን በመሳብ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንደሚያስገኝ፤ የአገር ውስጥ ሙዚቀኞችን ወደ ዓለም አቀፍ መድረክ ለማሻገር ከእውቅ ሙዚቀኞች ጋር ተጣምሮ የሚሰሩበትን ሁኔታ እንደሚያመቻች ነው የምታስገነዝበው። ወደፊትም በተመሳሳይ አጀንዳ ላይ የምትሰራበትን ሁኔታ ስታብራራም ዋና ዓለማዋ ኢትዮጵያን እንደአዲስ ለማስተዋወቅ ሳይሆን አየር ላይ ያለችበትን ዝና እና ክብር ወደ ላይ ለማውጣት ነው ብላለች፡፡
 በዓለም አቀፍ ፌስቲቫሎች ያለባት ቁጭት
በሙዚቃ ኢንዱስትሪው ከ18 ዓመታት በላይ ካካበተችው ልምድ በመነሳት በቁጭት የምትገልፀው በአውሮፓ አህጉርና በበመላው ዓለም በሚካሄዱ ፌስቲቫሎች የኢትዮጵያ በተሳትፎ ደካማ መሆኑን ነው፡፡ በትልልቅ ፌስቲቫሎች ላይ የኢትዮያውያን በብዙ ነገሮች ላይ አለመገኘት ያስቆጫታል፡፡ የኢትዮጵያ ኪነጥበብና ባህል በብዙ ዓለም አቀፍ ፌስቲቫሎች በሚያረካ ደረጃ እየተሰራበት አይደለም ነው የምትለው፡፡ እነሱዳን፤ ሞሮኮ፤ ጋምቢያ፤ ናይጄርያ፤ ደቡብ አፍሪካ... ሌሎችም የአፍሪካ አገራት በሚገኙባቸው ዓለምአቀፍ ፌስቲቫሎች ኢትዮጵያ የለችም ብትኖርም የሚደረገው ተሳትፎ በቂ አይደለም፡፡ ለምሳሌ የጠቀሰችው ደግሞ በኦስትሪያ የሚካሄድ ግዙፍ የአፍሪካ ፌስቲቫልን ነው፡፡ የአፍሪካ ቀን ተብሎ ለ15 ቀናት በሚካሄደው  ፌስቲቫል ላይ መላው አፍሪካ በመቶዎች በሚገመቱ ልዑካን እየተንቀሳቀሰ ሲሰራ ለሁልተና ሶስት ሰዓት በፌስቲቫሉ ተገኝተው የሚጠፉ ኢትዮጵያውን ብዛታቸው ከ 10  አይበልጥም፡፡ አስቀድሞ በጣሊያን ከዚያም በኋላ በስፔን በሚካሄደው ታላቁ የሬጌ ፌስቲቫል ሮቶቶም ሰንስፕላሽ ላይም ኢትዮጵያን ወክሎ በመሳተፍ ብዙ አልተሰራም ስትልም ታስረዳለች፡፡ በአውሮፓ በሚካሄዱ ፌስቲቫሎች ላይ ከአፍሪካውያን ጋር መቀላቀል ያቃተን ለምንድነው የሚለውን ጥያቄ  ሁሌም የምታነሳው ነው፡፡ ወደፊት አንዳንድ ሙከራዎችንም በማድረግ ይህን መቀየር ትፈልጋለች፡፡
ኢትዮጵያውያንን ዓለምአቀፍ  ደረጃ ባላቸው ፌስቲቫሎች ላይ በማሳተፍ መስራት እንደሚቻል ባህልና ኪነጥበቡንም በተሻለ ደረጃ እንዲያስተዋውቁ ነው፡Read 1412 times