Monday, 25 April 2022 06:19

“ሳድግ አነስኩ” አለች ውሻ

Written by  ከነቢይ መኮንን
Rate this item
(4 votes)

 የግጥም ጥግ

              “ሳድግ አነስኩ” አለች ውሻ
                     ከነቢይ መኮንን


አባባዬ ሁሉ ጠፋ፣ ጧት ያሻሸኝ፣ ህይወት
ስሻ፤
የማለዳዬ መነሻ
“ሳድግ አነስኩ” አለች ውሻ!!
ማነው ሲያድግ ያላነሰ ?
ወጣትነቱ ያልሳሳ፣ ትኩስ ወኔው ያልቀነሰ?
ከቶ ማነው ትኩሳቱ፣ ንዝረቱ ዕውን
ያልኮሰሰ?
ማነው ውበቱ ድምቀቱ፣
ሲያድግ ያልላመ ጉልበቱ?
“ሳድግ አነስኩ” አለች ውሻ….
የተነሰነሰው ሁሉ፣ የህይወት ቄጤማ
ሳይደርቅ
ማነው ፍፃሜውን ´ሚያቅ?
ማነው ትጥቁን የሚያጠብቅ?
ማነው ጭንቁን የማይደብቅ?
ማነው ዕድሜን የማይሰንቅ?
ማነው እንደአየለ የሚኖር፣ ማነው
በቀኑ´ማይወድቅ?
“ሳድግ አነስኩ” አለች ውሻ……
ማነው ሲያድግ ያላነሰ?
የዘንድሮው ሳይሆን ሲቀር፣ ያምናን ታሪክ
ያልጠቀሰ?
ማነው?......
አዲስ ጋን በመሾም ጉጉት፣ አሮጌ ጋን
የማያጥን
ማነው …በዛሬው ድካም ጦስ፣
የማይጠቅስ ትላንትናን
መቼም እድሜ መንገድ ነው፣ መዞሪያ-
ኩርባው አይጥፋን
የያዝነውን ሳናጠብቅ፣ ያጠበቅነው
አይላላብን።
ያለምነው ህልምም አይነትን፤
እንዴ ያለፍነው አይቆጨን፣
ያጠለልነው ጠላም አይጉሽ፣
የታቀፍነው ሀሳብ አይሽሽ!
“ሳድግ አነስኩ” አለች ውሻ።
ዕውነቷን ነው!......
ይህን ዕውቀት ይህን ሐቅ፤
በተለይ ንጉስ ያድምጠው!
(ሚያዝያ 2012፤ ለሚሰሙ መሪዎች)

Read 1667 times