Monday, 25 April 2022 06:23

የቻርልስ ዳርዊን የተሰረቁ የማስታወሻ ደብተሮች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ከ20 ዓመታት በኋላ ተገኙ
ከእንግሊዙ የካምብሪጅ ዩኒቨርስቲ ቤተ መጻህፍት ተሰርቀው እንደነበር የተነገረላቸው የቻርልስ ዳርዊን ሁለት የማስታወሻ ደብተሮች መገኘታቸው ተገለፀ- ከጠፉ ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ፡፡
ዩኒቨርሲቲው ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ የማስታወሻ ደብተሮቹ በሮዝ የስጦታ ቦርሳ የቤተ መጻህፍቱ ህንጻ ውስጥ ተቀምጠው ነው የተገኙት -ለቤተ መጻህፍት ሠራተኞቹ “እንኳን ለትንሳኤ በዓል አደረሳችሁ” ከሚል ማስታወሻ ጋር፡፡
የ19ኛው ክ/ዘመን ሳይንቲስቱን ዝነኛ የ1837 “Tree of Life” ንድፍ ያካተቱት የማስታወሻ ደብተሮቹ፣በ2001 ለፎቶግራፍ ከቦታቸው ከተነሱ በኋላ ነው ደብዛቸው የጠፋው፡፡ በወቅቱ ግን የቤተ መፃህፍቱ ሰራተኞች ያለ ቦታቸው ተቀምጠው ሊሆን ይችላል ብለው ነበር ያሰቡት፡፡ የቤተ መጻህፍቱ ስብስብ የሆኑት 10 ሚሊዮን መፃህፍት፣ካርታዎችና ረቂቅ ሰነዶች ተበርብረውም ግን የማስታወሻ ደብተሮቹ ሳይገኙ ቀሩ፡፡ ይሄኔ ለፖሊስ ሪፖርት ተደረገ፤ በኦክቶበር 2002 ዓ.ም፡፡
የአገሪቱ ወንጀል መርማሪዎች ወዲያው ጉዳዩን ለዓለማቀፉ የፖሊስ ድርጅት ኢንተርፖል ያሳወቁ ሲሆን ዓለማቀፍ የአደን ዘመቻም ጀመሩ - በሚሊዮን ዶላሮች  የሚተመኑትን የማስታወሻ ደብተሮች ለማግኘት፡፡
ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ ማርች 9 ቀን 2022 ዓ.ም የማስታወሻ ደብተሮቹ ከጠፉበት ድንገት ተገኙ- የደህንነት  ካሜራ በሌለበት የቤተመፃህፍቱ ህንጻ ውስጥ፡፡ የማስታወሻ ደብተሮቹ በሮዝ የስጦታ ቦርሳ ውስጥ ጉዳት ሳይደርስባቸው የተገኙ ሲሆን አባሪ የተደረገው ማስታወሻ፡- “የቤተመፃህፍቱ ሠራተኞች፤ እንኳን ለትንሳኤ በዓል አደረሳችሁ” ይላል፡፡
የዩኒቨርስቲው የቤተመጻህፍት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄሲካ ጋርድነር፣ በማስታወሻ ደብተሮቹ መገኘት የተሰማቸውን የእፎይታ ስሜት፤ “ጥልቅና በበቂ ሁኔታ ለመግለጽ የማይቻል ነው” ብለዋል፡፡
“አሁን የማስታወሻ ደብተሮቹ ከቀሩት የዳርዊን ስብስቦች ጋር የአገሪቱ የባህልና ሳይንሳዊ ቅርሶች እምብርት በሆነው ካምብሪጅ፣ተገቢ ቦታቸውን ሊያገኙ ይችላሉ፤ከሰር አይሳክ ኒውተንና ከፕሮፌሰር ስቲፈን ሃውኪንግ ስብስቦች ጎን ለጎን፡፡; ብለዋል፤ዳይሬክተሯ፡፡
የማስታወሻ ደብተሮቹ ከመጪው ሐምሌ ወር ጀምሮ የዳርዊን ኤግዚቢሽን አካል ሆነው በቤተመጻህፍቱ ለህዝብ ዕይታ እንደሚቀርቡ ተነግሯል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ፣ የካምብሪጅሻየር ፖሊስ በጉዳዩ ላይ ሲያካሂድ የነበረውን  ምርመራ  እንደሚቀጥልበት አስታውቋል፡፡



Read 1570 times