Sunday, 24 April 2022 00:00

የኮሮና ክትባትን “ቢዝነስ” ያደረጉት አዛውንት

Written by 
Rate this item
(0 votes)


             ነዋሪነታቸውን በምስራቅ ጀርመን ከተማዋ ማግድበርግ ያደረጉት የ60 ዓመቱ አዛውንት፣ እስከ 90 የሚደርስ የኮሮና ክትባት መከተባቸው የተረጋገጠው በቅርቡ ነው፡፡ አሶሼትድ ፕሬስ እንደዘገበው፤ አዛውንቱ ይህን ያደረጉት፣ የኮሮና ክትባት መከተብ ለማይሹ ሰዎች ሃሰተኛ የክትባት ማረጋገጫ ካርድ (ፓስፖርት) ለመሸጥ ነው።
በጀርመን የግል ምስጢርን የመጠበቅ ህግ መሰረት፣ስማቸው ያልተጠቀሰው አዛውንቱ፤ በዚህ ወር በፖሊስ እስከተያዙበት ጊዜ ድረስ በምስራቃዊቷ የሳክሶኒ ግዛት ውስጥ ከሚገኙ የክትባት ጣቢያዎች፣ እስከ 90 የሚደርስ የኮሮና ክትባት ወስደዋል ተብሏል፡፡
ተጠርጣሪው በቁጥጥር ሥር ባይውሉም፣ ህገወጥ የክትባት ፓስፖርት በመስጠትና ሃሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት  ወንጀል ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑ  ታውቋል፡፡
አዛውንቱ በሳክሶኒ፣ ኢይልንበርግ የክትባት ጣቢያ፣ የኮሮና ክትባት ለመከተብ ለሁለተኛ ተከታታይ ቀን በመጡበት ጊዜ ነበር የተያዙት፡፡  ፖሊስ በርካታ ባዶ የክትባት ካርዶችን ከሰውየው ላይ የወረሰ ሲሆን የወንጀል ክስ  መጀመሩም ተጠቁሟል፡፡
እስከ 90 የሚደርሱ የተለያዩ ሥሪቶች የሆኑ የኮሮና ክትባቶች፣ በሰውየው የግል ጤና ላይ የሚያደርሱት ተፅዕኖ እስካሁን በግልፅ አልታወቀም፡፡
በጀርመን ኮሮና  መኖሩን የሚክዱና ክትባቱን ለመውሰድ የማይፈቅዱ በርካቶች እንዳሉ ይነገራል፤ ነገር ግን እኒህ ወገኖች የክትባት ካርዱን (ፓስፖርቱን) ይፈልጉታል፤ በምግብ ቤቶች፣ ቴአትር ቤቶች፣ የመዋኛ ሥፍራዎች ወይም የስራ ቦታዎች በቀላሉ መግባት እንዲችሉ፡፡ አዛውንቱ ለእነዚህ መሰል ሰዎች ነው ሃሰተኛ የክትባት ፓስፖርቱን የሚሸጡት!! የሆነስ ሆነና ሰውየው እንዴት የጤናቸው ነገር ሳያሳስባቸው ቀረ? ያውም ዕድሜያቸው እንዲህ ገፍቶ!!


Read 861 times