Monday, 25 April 2022 06:38

ታሪክ - ስድስት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በጉጉት ስንጠብቀው የነበረው የመጀመሪያ ልጃችን አቢ የተወለደው በ2004 ዓ.ም ነው። ጤናማ ልጅ ለመውለድ በነበረኝ ጉጉትና ልጄ ሆዴ ውስጥ እያለ እንዳይጎዳብኝ በማሰብ የእርግዝና ሂደቴን እከታተል የነበረው በሁለት የተለያዩ ቦታዎችና በሁለት የተለያዩ ሐኪሞች ነበር።
የመውለጃ ጊዜዬ ሲደርስ፤ ልጁ ያለምንም ችግር በጥሩ ጤንነት ተወለደ። የዕድገት ደረጃውን በተመለከተም ጡት ካለመጥባቱ በስተቀር ምንም ዐይነት ችግር አልበረውም። በዐስራ አንድ ወሩ ቆሞ ለመሄድ ችሏል፣ በ6 ወሩ ጥርስ አብቅሏል፤ ደስተኛና ንቁ ሕጻንም ነበር።
አቢ በተወለደ በዓመቱ ነበር፤ የአቢ ታናሽ ወንድም የተወለደው፡፡ ከዕድሜያቸው መቀራረብ የተነሳና የሥራችን ሁኔታም አመቺ ስላልነበረ፣ አቢን አያቶቹ ጋር ክፍለ ሀገር ወሰድነው። ይሁንና በየጊዜው እየተመላለስን እንጠይቀው እንከታተለው ነበር። ልንጠይቀው ስንሄድ፣ በጣም በደስታ ይቦርቃል፣ ይሯሯጣል። ነገር ግን በስም “እማማ”፣ “አባባ” ብሎ አይጠራንም ነበር።
በአረብኛ የሚተላለፉ ፊልሞችን በተመስጦ ቁጭ ብሎ ማየት ይወድ ነበር። ምግብ ሲበላ፤ ቴሌቪዥን እንዲከፈትለት ይፈልጋል። ቴሌቪዥን ሳይከፈት፤ እርሱን ቁጭ አድርጎ ማብላት ፈጽሞ የማይታሰብ ነበር። በሰው እጅ ነበር የሚመገበው። ውሃ ሲፈልግ “ውሃ እሺ” ብቻ ይል ነበር። ሶስት ዓመት ሲሆነው፤ ትምህርት ቤት ለማስገባት ወደ አዲስ አበባ አመጣነው። በወቅቱ “ውሃ እሺ” ከሚለው ቃል ውጪ ሌላ አይናገርም፤ የመናገር ፍላጎትም አልነበረውም፤ ሲፈልግ ትርጉም የሌላቸው ቃላትን አልፎ አልፎ ይናገራል።
እኛም የማያወራው፤ ብቻውን ስላደገ ሊሆን ይችላል ብለን፤ ለአንድ ወር ያህል ከወንድሙ ጋር አብረው እንዲሆኑ  በማድረግ መከታተል ጀመርን። ከወንድ ጋር በጋራ ከመጫወት ይልቅ ብቻውን፣ ጥግ ይዞ ዕቃዎችን ሰብስቦ መጫወት፣ ጆሮውን እያራገበ መሯሯጥ፤ በተጨማሪም ከሚወዳቸው ነገሮች ውጪ ለአካባቢው ምንም አይነት ትኩረት አለመስጠት ይታይበት ነበር።
እኛም ሁኔታውን ከታናሽ ወንድሙ ጋር ስናነጻጽረው፤ ታናሽ ወንድሙ በመናገርም ሆነ በሚያደርጋቸው ተግባራት፤ የተሻለ ሲሆን የእርሱ ድርጊት ግን የተለየና ያልተለመደ ስለሆነብን ወደ ሀኪም ይዘነው ሄድን።
ሀኪሙም የአቢን ሁኔታ ከተመለከተና ከእኛ ጠይቆ በተረዳው መሰረት፣ አንዳንድ ልጆች ላይ የሚታይ ችግር መሆኑን አስረዳን። በመቀጠልም፤ መደበኛ ት/ቤት ከተቀበሉን ብንሞክር ጥሩ እንደሆነ መክሮን ተለያየን።
በተለይ “መደበኛ ትምህርት ቤት ከተቀበሏችሁ ሞክሩ” ያለው ነገር በጣም አስደንጋጭ ቢሆንም፤ በአካባቢያችን አዲስ የተከፈተ መዋእለ ሕጻናት ስለነበረ እዛ አስገባነው።
 ት/ቤት ውስጥ ለየት ያሉ፤ እርሱ ላይ ብቻ ጎልተው የሚታዩ ባህርያት ነበሩት። ክፍል ውስጥ ተረጋግቶ አይቀመጥም ነበር። ነገር ግን በአጋጣሚ ወጣ ገባ እያለ የሚሰማቸውን ፊደላትና  ቁጥሮች ያስታውሳል። የማስታወስ ችሎታው ከፍተኛ ነው። በዚህም መምህራኑ በጣም ይደነቃሉ። በግድ እጁን እየያዝን ጽሁፍ እናለማምደው ነበር። አንድ ነገር ጫን ብለን ደጋግመን ካለማመድነው የመያዝ ችሎታው ጥሩ ነው።
ትምህርት ቤት ውስጥ ሰልፍ አይሰለፍም። ይልቁን በሰልፍ ጊዜ ለብቻው ተነጥሎ የፈለገውን በማድረግ ብቻ ያሳልፋል። መምህራኑም “እርሱ እንደልቡ ነው” በማለት ዝም ይሉት ነበር።
መደበኛ ትምህርት ቤት ሲገባ፤ ብዙ ነገር ይቀየራል ብለን አስበን ነበር። ሆኖም ግን በት/ቤት ውስጥ ያለው ባህሪ እንደሌሎች እኩዮቹ አለመሆኑና ለውጥ አለማሳየቱ እያሳሰበን መጣ። ነገሮችን እቤት ውስጥ እንደሚያደርገው ትምህርት ቤት ውስጥም፤ በራሱ መንገድ ያደርጋል እንጂ ሰው የሚለውን አይሰማም ነበር።
ስለዚህ ችግሩን ተረድቶና ኦቲዝም ያለባቸውን ልጆች አካቶ የሚያስተምር ትምህርት ቤት ስንፈልግ፤ እንደ አጋጣሚ አንድ የስነ-ልቦና ባለሙያ በአንድ ወቅት፣ በዩቲዩብ ስለ ኦቲዝም ባደረገችው ቃለ-ምልልስ ላይ የስልክ አድራሻዋን አገኘን። ሐኪም የሰጠንን ማስረጃና ልጃችንን ይዘን ወደ ባለሙያዋ ሄድን።
ከባለሙያዋ ጋር ባደረግነው ውይይትም፤ ተገቢውን ድጋፍ ካደረግንለት በተለይም ካለው የማስታወስ ችሎታ ጋር ተያይዞ ጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚደርስ ተስፋ አገኘን። ለዚህም ይረዳን ዘንድ ባህሪውን ለማስተካከል የሚያግዝ ስልጠና  ወሰድን። ከባለሙያዋ በተነገረን መሰረትም፤ ለእርሱ ይጠቅማል ያልነውን ሁሉ ማድረግ ጀመርን።
እኔና ባለቤቴ ተቀጣሪ ሰራተኞችና ጠዋት ወጥተን ማታ የምንገባ ስለሆንን፤ ከጠዋት 11 ሰዓት ጀምሮ ስራ ከመሄዳችን በፊትና ባለን ጊዜ ሁሉ ስልጠናውን መስጠት ተያያዝነው። ድካሙ፣ ተስፋው፣ ግራ መጋባቱና ድግግሞሹ የተለያዩ ስሜቶች ቢኖሩትም ለትንሽ ቀናት ካልረዳነው፤ ወደ ኋላ መመለሱ ትዕግስትን የሚፈትንና ብዙ ጽናት የሚጠይቅ ነበር። አሁን ስናስበው በጣም ይገርመናል።
አሁን ከእኩዮቹ ጋር እኩል ይማራል፤ በትምህርቱም ጎበዝ የ2ኛ ክፍል ተማሪም ሆኗል። ከፍተኛ የማስታወስ ችሎታ አለው። መጽሐፍትን ማንበብ በተለይም ግጥም ማንበብ፤ በጣም ይወዳል። ማውራት ችሏል፤ ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ እስኪያልቅ ድረስ በትዕግስት ቆይቶ ያስቀድሳል፣ ከዕድሜ እኩዮቹ ጋርም፤ ትርጉም ያለው ጨዋታ ይጫወታል። ነገር ግን ትንሽ የሂሳብ ትምህርት ስለሚያስቸግረው፤ በቀን ለ2 ሰዓት የአንድ ለአንድ ስልጠና ይሰጠዋል። ደስተኛና ተወዳጅ ልጅ ነው።
ይህንን ሁሉ ለውጥ  ሊያመጣ የቻለው፤ በፍላጎቱ ላይ የተመሰረቱ፤ የተለያዩ ዐይነት ቴራፒዎች /ሕክምናዎች/ በማግኘቱ፤ በአካቶ ትምህርት ቤት በመማሩና እኛም እስከ አሁን ከትምህርት ቤቱ በሚሰጠን መመሪያ መሰረት ድጋፍ ማድረጋችንን ባለማቋረጣችንና ከሁሉ በላይ እግዚአብሔር እኛን በማገዙ ነው።


Read 1500 times