Print this page
Sunday, 24 April 2022 00:00

ከ40 ዓመታት በላይ የዘለቀ የጥበብ አበርክቶ - አርቲስት ዘነቡ ገሠሠ (ዜና ዕረፍት)

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ከአባቷ ከ፲ አለቃ ገሠሠ ነጋሽና ከእናቷ ወ/ሮ ስመኝ ዓለሙ፣ በቤጌምድርና ስሜን ጠቅላይ ግዛት፣ ጎርጎራ ከተማ ሚያዝያ 27 ቀን 1956 ዓ.ም. የተወለደችው አርቲስት ዘነቡ ገሠሠ፤ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርቷን በቀዳማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ተከታትላለች፡፡
ባደረባት ሕመም ምክንያት በተወለደች በ57 ዓመቷ፣ ሚያዝያ 16 ቀን 2014 ዓ.ም. ያረፈችው አርቲስት ዘነቡ፣ በነጋታው ሚያዝያ 17  በቦሌ ቡልቡላ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን የቀብር ሥርዓቷ ተፈጽሟል።
ሁለገቧ የጥበብ ባለሙያ አርቲስት ዘነቡ ገሠሠ በተወዛዋዥነት፣ በድምፃዊነትና በተዋናይነት ከአርባ ዓመታት በላይ  ከፖሊስ ሠራዊት ኤርኬስትራ፣ እስከ ራስ ቴአትር አገልግላለች፡፡  
በቀድሞዋ የኤርትራ ክፍለ ሀገር በአስመራ ከተማ በሚገኘው የሰሜን ዕዝ ፖሊስ ኦርኬስትራ፣ ከጥበብ ጋር የተዋወቀችው  በ1970 ዓ.ም. ከተቀጠረች በኋላ ነው። በህይወት ታሪኳ ላይ እንደተገለጸው፣ በአስመራ በነበራት የአራት ዓመታት ቆይታ በተወዛዋዥነት፣ በድምፃዊነትና በአጫጭር ተውኔቶች አገልግላለች፡፡
ከዚያም በራስ ቴአትር በ1976 ዓ.ም. የተቀጠረችው አርቲስት ዘነቡ፤ በተወዛዋዥነትና በመድረክ ሥራዎች ላይ ተሳታፊ ነበረች፡፡ ከተውኔቱ ዓለም ይበልጥ በተዋወቀችበት ራስ ቴአትር ከተወነቻቸው ተውኔቶች መካከል ላጤ፣ የሰው ሰው፣ ዘር አዳኝ፣ አሻራ የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡
አርቲስቷ ከዚህም ባሻገር በሜካፕ፣ በአልባሳትና በቁሳቁስ ባለሙያነት፣ በአዳራሽና በሌሎች ኃላፊነቶችም በትጋት ማገልገሏ በህይወት ታሪኳ ላይ ተከትቧል፡፡
ሁለገብ አርቲስቷ ከተወነችባቸ  የሙሉ ጊዜ ፊልሞችና ሲትኮም ድራማዎች መካከልም "አያስቅም፣ ያለ ሴት፣ አስታራቂ፣ የከበረ ደሃና ሹገር ማሚ" በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡
አርቲስት ዘነቡ ገሠሠ በህይወት ዘመኗ ላበረከተችው ሙያዊ አስተዋጽኦ የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝታለች - ጉማ አዋርድ አንዱ ነው፡፡  
አርቲስት  ዘነቡ የሁለት ሴትና የሁለት ወንድ ልጆች እናት የነበረች ሲሆን፤ የሁለት ሴት ልጆችም አያት ለመሆን በቅታለች፡፡



Read 11375 times
Administrator

Latest from Administrator