Print this page
Saturday, 30 April 2022 12:49

በቁጫ ህዝብ ላይ የሚደርሰው በደል እየከፋ መምጣቱ ተገለፀ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  የቁጫ ህዝብ በደልና መገፋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱንና በዚህም ህዝብ የከፋ እንግልትና ሰቆቃ እየተጋፈጠ መሆኑን የቁጫ ህዝብ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ቁህዴፓ) አስታወቀ። ፓርቲው ከትላንት በስቲያ ከሰዓት በኋላ ቦሌ የሺ ህንፃ ላይ በሚገኘው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር  ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ  በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በቁጫ፣ በቁጫ አልፋና  በቁጫ ሰላም በር ከተማ “ ቁህዴፓን ለምን መረጣችሁ” በሚል ህዝቡ እስራት፣ መሰደድ፣ ከስራና ከንግድ መፈናቀልና ድብደባ እየተፈጸመበት ነው ሲል አማርሯል።
የቁጫ ህዝብ ለውጡ በፈነጠቀው አንጻራዊ ሰላምና ነፃነት ተጠቅሞ ለዘመናት የዘለቀውንና ያጎበጠውን ጭቆና፤ህጋዊ ሰውነት ባለው ፓርቲ ለመታገል ቁህዴፓን መመስረቱን ያስታወሱት የፓርቲው አመራሮች፤ በ6ኛው አገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1 ለክልል ምክር ቤት ተወካዮች ሶስት አባላቱ እንደተመረጡለት አውስተዋል። ይህን ተከትሎ ግን  በቁጫ ወረዳ፣ በቁጫ አልፋና በሰላም በር ከተማ ውስጥ ያሉ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች በአካባቢው የብልጽግና አመራሮች ከስራ ከመታገድ ጀምሮ የእስራት፣ የግርፋት የንግድ ስራ መስተጓጎልና በርካታ ሰቆቃዎች እየደረሱበት መሆኑን የፓርቲው ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ታመነ በሌ በመግለጫው አብራርተዋል።
ያለመከሰስ መብት ያላቸውና ቁጫን ህዝብ ወክለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የገቡት የተከበሩ ገነነ ገዴቦ (ረ/ፕ)፣ ከህዝቡ ጋር ለመወያየት ወደ ቁጫ ባቀኑበት ጊዜም በብልጽግና አመራች የመታገትና የመጉላላት ችግር የደረሰባቸው ከመሆኑንም በላይ  ከህዝብ ጋር እንዲወያዩ ተደርገው መኪናቸውን አዙረው እንዲመለሱ መደረጉንም  በመግለጫው ላይ ተገኝተው ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ከሚሰሩበት ቦታ እየታደኑ ለወራት ለእስርና ለእንግልት መዳረጋቸውንና ያለጥፋት ያለ ማስረጃ ለወራት ታስረው መለቀቃቸውን አቶ ታመነ ጨምረው ተናግረዋል።
የቁጫ ህዝብ በብዙ ጫና ውስጥ ሆኖ የመረጠው የምርጫ ውጤት እንዲታጠፍ በብልጽግና ፓርቲ አመራሮች የተጀመረውን ክስ አጥብቀን እንቃወማለን ያሉት የቁህዴፓ አመራሮች ይህ ህገ-ወጥ ክስ የሚያሳየው የመራጭ ህዝቡን ሉአላዊነት፣ ክብርና መብትን የሚያሳንስ እና ሀገራችን የምታደርገውን የመድብለ ፓርቲ ስርዓት የሚያቀጭጭ መሆኑን ነው ሲሉ ወቅሰዋል።
ፓርቲው ባወጣው ባለ 12 ነጥብ የአቋም መግለጫም በቁጫ፣ ወረዳ፣ በቁጫ አልፋ ወረዳና በቁጫ ሰላም በር ከተማና በመላ አገሪቱ በቁጫ ህዝብና በፓርቲው ቁህዴፓ አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ላይ የሚፈጸመው ሰቆቃ በአስቸኳይ እንዲቆም፣ በጽንፈኝነትና በብሄርተኝነት ስሜት የቁጫ ማህበረሰብ አባላትን ከመንግስት ስራ ማፈናቀል እንዲቆም፣ በምርጫው ፓርቲያችን ቁህዴፓ ማሸነፉን ተከትሎ የብልጽግና አመራሮች ባደረባቸው ብስጭት የቁጫን መራጭ ህዝብ የእልህ መወጣጫ አድርጎ የተከፈቱት የእስር፣ የድብደባና ከፓርቲ አልባነት እንዲወጡ ማስገደድና መሰል በደሎች በአስቸኳይ እንዲቆሙ፣ ቁህዴፓን መርጣችኋል በሚል የፓርቲውን አመራሮች፣ አባላትንና ደጋፊዎቹን ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከየቀበሌው ለበርካታ ወራት እያሰሩ መቅጣት በአስቸኳይ እንዲቆም፣ የገዢው ብልፅግና ፓርቲ የቁጫ ህዝብ የምርጫ ውጤት እንዲታጠፍ የጀመረው ክስ ህጋዊ መሰረት የሌለው በመሆኑ በአስቸኳይ ከዚህ እንቅስቃሴውእንዲቆም፣ ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ የሚዲያ ተቋማትና ጋዜጠኞች በቁጫ ህዝብ ላይ የሚደርሰውን በደልና እንግልት በማጋለጥ ከጭቁኑ የቁጫ ህዝብ ጎን እንዲቆሙና ለዘመናት የዘለቀው የቁጫ ህዝብ የማንነት ጥያቄና ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ጥያቄ እንዲመለስ  ፓርቲው ጥሪ አቅርቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የፓርቲው የድርጅት ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑትን አቶ ባንዲራ በላቸውን፣ ከቁጫ ወረዳ ሰላም በር ከተማ የመጡ ፖሊሶች፣ በዛሬው ዕለት ከልደታ ፍርድ ቤት አስረው እንደወሰዷቸው የቁህዴፓ አመራሮች ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡


Read 11146 times
Administrator

Latest from Administrator